የአካዳሚው ፍሬዎች ተስፋ ያሳዩበት ቻምፒዮና

ከእድሜ ተገቢነት ጋር በተያያዘ ብዙ ወቀሳዎችን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ትናንት ፍፃሜ አግኝቷል። ለሰባት ተከታታይ ቀናት በድሬዳዋ በተካሄደው የወጣቶች ቻምፒዮና 8 ክልሎች ፣ 2 ከተማ አስተዳደሮች፣ 35 ክለቦች፣ ማሠልጠኛ ማዕከላትና የተለያዩ ተቋማት ተሳትፈዋል።

ከ20 ዓመት በታች በተካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ 248 ነጥብ በሁለቱም ፆታ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። መቻል በ215 ነጥብ ሁለተኛ እና ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በ189 ነጥብ ሦስተኛ ሆነው ፈፅመዋል። ከ18 ዓመት በታች በተካሄዱ ውድድሮች ደግሞ ኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በሁለቱም ፆታ በ279 ነጥብ አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን፤ ጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ እና ኦሮሚያ ክልል 2ኛ እና 3ኛ ሆነው ውድድሩን ጨርሰዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሠረት ደፋር እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ለአሸናፊዎቹ ተዘጋጀውን የሜዳሊያ እና የገንዘብ ሽልማት አበርክተዋል። በቻምፒዮናው በናይጄሪያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ18 እና 20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች እንደሚመረጡ ይጠበቃል።

ከእድሜ ጋር በተያያዘ የታየው ትልቅ ችግር በተለይም ከ20 ዓመት በታች በተካሄዱ ውድድሮች ጎልቶ ታይቷል። በ18 ዓመት በታች ውድድሮችም ከችግሩ ነፃ ባይሆኑም በአንፃራዊነት የተሻለ እንደነበር በተለያዩ ርቀቶች በተደረጉ ፉክክሮች የታዩ ወጣቶች ማሳያ ነበሩ። በመሰናክል፣ ረጅም ርቀቶች እንዲሁም በሜዳ ተግባራት ፉክክሮች ይህ የእድሜ ችግር ጎልቶ የታየበት ሲሆን፣ በአጭርና መካከለኛ ርቀት ውድድሮች በአንፃራዊነት በርከት ያሉ ወጣቶች ታይተዋል።

ከእድሜ ጋር ላለው ችግር ክለቦች፣ ክልሎችና ተቋማት በተለያዩ ፉክክሮች ያሰለፏቸው አትሌቶች ግንባር ቀደም ሆነው ተገኝተዋል። በአንፃሩ አካዳሚዎች ተተኪ ወጣቶችን ማፍራት የተቋቋሙበት ዓላማና ግብ ቢሆንም በተሻለ ሁኔታ በርካታ ወጣቶችን ይዘው ተገኝተዋል። ይህ ማለት ግን ከችግሩ ሙሉ በሙሉ ነፃ ናቸው ማለት አይደለም። ያምሆኖ የጎላ ችግር በተነሳበት የወጣቶች ቻምፒዮና የአካዳሚ ፍሬ የሆኑ አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው በበርካታ ውድድሮች ያሳዩትን ተስፋ ማናናቅ የሚቻል አይደለም።

ክለቦች ላይ የእድሜ ተገቢነት ጥያቄው እንዳለ ሆኖ የአካዳሚና የማሠልጠኛ ተቋማት አትሌቶችን በማስኮብለል ውጤታቸው እስከ መሰረዝ የደረሰ ውዝግብ በታየበት ቻምፒዮና፤ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እንዲሁም የዚሁ አካዳሚ አንድ አካል የሆነውና አሰላ የሚገኘው ጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ በተለይም ከ18 ዓመት በታች ውድድሮች ላይ የተሻሉ ሆነው ከመታየታቸው ባሻገር ያስመዘገቡት አጠቃላይ ውጤት ተስፋ ሰጪ ነው።

አካዳሚው በቻምፒዮናው ከ18 ዓመት በታች ውድድሮች 33 ወንድ፣ 27 ሴት በድምሩ 60 አትሌቶችን አሳትፏል። ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች ላይ ደግሞ 27 ወንድና 27 ሴት በድምሩ 54 አትሌቶች አሰልፏል። በአጠቃላይ በሁለቱም ምድብ 54 ሴትና 60 ወንድ በድምሩ 114 የአትሌቲክስ ሠልጣኞቹን በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በረጅም ርቀቶች ሩጫ እና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ማሳተፍ ችሏል። በዚህም 10 ወርቅ፣ 11 ብር እና 8 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከ18 ዓመት በታች የተካሄዱ ውድድሮችን በአጠቃላይ ድምር ውጤት 1 ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ የቻለው።

በመንግሥት በጀት የሚንቀሳቀሱ በርካታ ክለቦችና ክልሎች እንዲሁም ተቋማት ከታዳጊዎች ጀምሮ ተተኪዎችን ኮትኩተው በማሳደግ ለስፖርቱ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባቸው እሙን ነው። በዚህ ረገድ ኮስተር ብለው እየሠሩ እንዳልሆነ የወጣቶቹ ቻምፒዮና ምስክር ነው። እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ አሠልጣኞች ለሚያስመዘግቡት ውጤትና ለጊዜያዊ የግል ጥቅም እንጂ ዛሬም ለተተኪዎች ጉዳይ እየተጨነቁ እንደማይገኙም ቻምፒዮናው በቂ ማሳያ ነው። በወጣቶች አምኖና ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ከተቻለ ግን ውጤት ማስመዝገብም ሆነ ስፖርቱን በዘላቂነት ሊጠቅም የሚችል ዐሻራ ማኖር እንደሚቻል የአካዳሚዎች ጥረት ለክለቦችም ሆነ ለክልሎች ትምህርት የሰጠ ሆኖ የድሬዳዋው የወጣቶች ቻምፒዮና ተቋጭቷል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You