
አዲስ አበባ፡- በቢሾፍቱ ከተማ የሚካሄደው የመጀመሪያው ምራፍ የኮሪዶር ልማት 75 ከመቶ መድረሱን የከተማዋ ከንቲባ ጽፈት ቤት አስታወቀ።
የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፤ በቢሾፍቱ ከተማ የኮሪዶር ልማት በሶስት ምራፎች እየተገነባ ይገኛል ፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ 75 ከመቶ ደርሷል።
የኮሌዶር ልማቱን ተከትሎ የከተማዋ የአስፓልት መንገዱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በአዲስ መልክ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው ፤ የመንገድ ግንባታው አጠቃላይ እርዝመት 16 ኪሎ ሜትር ፤የመንገድ ስፋቱ ደግሞ 10 ነጥብ 5 ሜትር እንደሆነ አስታውቀዋል።
የመንገድ ሥራው 50 ሄክታር ያህል የሚሸፍን አረንጓዴ ልማት፤ አምስት ሜትር የእግረኛ መንገድ እና ሶስት ሜትር የብስክሌት መንገድ የሚሸፍን ፤ እንደ አጠቃላይ ሲታይ የፌዴራል መንግሥት ያወጣውን መስፈርት ሙሉ በሙሉ የሚያሟላ ነው ብለዋል።
የመንገድ ግንባታው አሁን ያለበት 75 ከመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ሰኔ ወር ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
ምክትል ከንቲባው እንዳስታወቁት ፤ በሁለተኛው ምዕራፍ የሚለማው የኮሪዶር ልማት 11 ኪሎ ሜትር እርዝመት እና 31 ሜትር ስፋት ይኖረዋል። የአስፓልት ሥራው በተመሳሳይ መልኩ አንደ አዲስ የሚሠራ ፤ የመጀመሪያው ኮሪዶር ልማት ያካተታቸውን ነገሮች ያካተተ ነው።
የሁለተኛው ምዕራፍ ከተጀመረ አምስት ወራት አስቆጥሯል ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ አሁን ላይ የግንባታ ሥራው 55 ከመቶ ደርሷል። አጠቃላይ የግንባታ ሥራውን በዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሶስተኛው ምዕራፍ 29 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ፤ የአስፓልት ሥራው ከዚህ በፊት የነበረን የመጠናከር ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ፤ ሥራው በሁለት ተቋራጮች እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል። ከመንገድ ሥራው ጎን ለጎን አረንጓዴ ቦታዎችን ጨምሮ የተለያዩ የመንገድ ዳር ካፌዎች እና የህጻናት መጫወቻ አካባቢዎች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። ለሥራው በአጠቃላይ የ 10 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡንም ጠቁመዋል።
በቢሾፍቱ ከተማ ከዚህ በፊት የነበረው አስፓልት 60 ዓመት ያስቆጠረና ጠባብ መሆኑን አመልክተው በዚህ የተነሳም የትራፊክ መጨናነቅ ይፈጠር እንደነበር አስታውቀዋል። የኮሊዶር ልማቱ ይህንን ችግር በመቅረፍ የተሻለ የትራፊክ ፍሰት እንደሚፈጥር አመልክተዋል ። ፕሮጀክቱን በተቀመጠለት ጊዜ በማጠናቀቅ ለሌሎች ተሞክሮ እንዲሆን በርብርብ እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል ።
መንገድ በመሠራቱ ብቻ ሁሉም ነገር ይቀየራል ማለት አይደለም የሚሉት አቶ ገዛኸኝ፤ አሁን የተጀመሩ የመንገድ ልማት ሥራዎች ሲተናቀቁ፤ ከነዋሪዎች ጋር በመወያየት በመንገድ አካካቢ የሚገኙ የመኖሪያ ቤቶችን ወደ ንግድ የመቀየር፤ የሚቀቡ ቀለሞች አይነት የመለየት ፤ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች አጥር በወጣ መስፈርት መሠረት የሚታደስበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።
ቢሾፍቱን ተመራጭ ከተማ ለማድረግ ሀይቆችን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠቀም በስፋት እየተሠራ ነው ፤ ከዚህ አንጻር በከተማው መሥራት የሚፈልጉ አልሚዎች ከወዲሁ መጥተው ከተማዋን ተመራጭ በማድረግ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም