አውሮፓውያኑ ኮሮና ቫይረስ ገና ወደ አፍሪካ እየገባ ነውና ከዚህ በኋላ አደጋው ይከፋል እያሉ ነው። በእነሱም ዘንድ ገና አላባራም። የዓለም ሳይንቲስቶች ክትባትም ሆነ መድኃኒት ፍለጋ እየባዘኑ ነው። ለሙከራ እያዘጋጇቸውም እንዳሉ ይነገራል። ስለፈውሱ እርግጠኛ መሆኑም ላይ ገና ውዝግብ አለ። የገበያ ጦርነትም ገና ይጠብቃቸዋል። እኛ እያለን እንዴት የድሀ ሀገራት ሐኪሞች ለበሽታው መድኃኒት ያገኛሉ የሚለው የዘረኝነት ልክፍትና የሴራ ፖለቲካም ገና ዓለምን ብዙ ዋጋ ያስከፍላታል።
በሽታውንም ሆነ መድኃኒቱን እነማን እንደሚፈጥሩት ዛሬ ዓለም ስላወቀ እርስ በርስ እየተወነጃጀሉበት ነው። ውሎ አድሮ ገና ብዙ ነገር እናያለን። በመላ ዓለም የሚረግፈው ሕዝብ ከረገፈ በኋላ መድኃኒቱ ወይንም ክትባቱ ተገኝቷል ብለው ብቅ ይላሉ። በቅርቡ የአሜሪካ ሳይንቲስቶችን ጨምሮ መድኃኒቱን ለማግኘት ቢያንስ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ይጠይቃል በሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል። የሚገባን ከሆነ በዚህን ጊዜ ምን ያህል የዓለም ሕዝብ ያልቃል ብለን መገመት ነው። አዎ በስልጣኔና በቴክኖሎጂ የመጠቁ እንዲሁም የረቀቁና የራቁ ቢሆኑም ይህ ሁሉ ከፈጣሪ ውጭ ባዶ እና ከንቱ በመሆኑ ራሳቸውን እንኳን ለመከላከል አላስቻላቸውም።
ኤች.አይ.ቪ ኤድስ፣ ኤቦላ፣ ሳርስና አሁን ደግሞ ኮሮና ቫይረስን ፈጣሪ ሕዝብን ለመቅጣት የላካቸው መቅሰፍቶች አይደሉም። ይልቁኑም በምስጢራዊ ፋብሪካዎች የተመረቱ ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ሆነው የሚያገለግሉ በሽታዎች ናቸው ይባላል። ሰው በፋብሪካ የሠራቸው፤ ሕዝብን ለመፍጀት የተፈጠሩ በሽታዎች እንደሆኑም ነው ብዙዎች የሚናገሩት። ፈጣሪም የራሱን ፍርድ ሲሰጥ እያየን ነው። ለድሀው ዓለምና ሕዝብ ፈጣሪ አለ ብቻ ብለን የምንተወው ጉዳይ ግን አይደለም። ያሻቸውን በሽታ እየፈጠሩ የሚያልቀው ካለቀ በኋላ ባሻቸው ጊዜ መድኃኒት ተገኘ ሲሉን ተመስገን ብለን የምንቀበል ቅንና የዋህ ሕዝቦች ነን።
አውሮፓውያን በዚህ ወረርሽኝ በአፍሪካ ብቻ 10 ሚሊዮን ሕዝብ ሊያልቅ ይችላል ብለዋል። ለእኛም ሀገር ግምታቸውን አስቀምጠዋል። በድህነት ውስጥ የምትገኝ በቂ የህክምና ተቋማት የሌላት ሀገር ስለሆነች አደጋው ሊከፋ ይችላል የሚል ነው። አዎን ድሆች ነን። ከመጠንቀቅ ውጭ ሌላ የምናደርገው ነገር የለም። ይሄን ግምታቸውን መናቅ አይቻልም። አሁንም መንግሥትና የጤና ሚኒስቴር የሚሰጠውን መመሪያ በጥብቅ እስካላከበርን ድረስ በእኛ ኑሮና ማሕበራዊ መስተጋብር የሚነገረንንም ስለማንሰማ ከፊታችን ያሉት ቀናትና ወራት ከባድ እንደሚሆኑ ልንጠራጠር አይገባም።እስካአሁን ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት መቀነስ የሚረዳው ብቸኛው መንገድ ርቀትን መጠበቅና ንጽህና መጠበቅ ብቻ እንደሆነ ዋነኛ መተላለፊያ መንገዱም ሳልና ማስነጠስ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት በተደጋጋሚ እየገለጸ ነው።
በሀገራችን ክረምት እየገባ ነው። ብርዱና ዝናቡ ምን ያህል ሳልና ጉንፋን ሊቀሰቅስና ማስነጠስ ሊያመጣ እንደሚችል ከወዲሁ ተዘጋጀቶ መጠበቅ የግድ ይላል፤ ቤት ውስጥ በመቆየትም ከሌሎች ጋር ያለንን ንክኪና ግንኙነት መቆጠብን ይጠይቃል። መንግሥት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው። የሚታየውን ነገር በመዘርዘር ጊዜ ማባከን አይገባም። ኮሮና እኛን አይነካንም፤ ምንም አንሆንም የሚለው ባዶ እብሪትና ግብዝነት ብዙ ወገንና ቤተሰብ እንዳያሳጣን ያሰጋል። ራስን፣ ቤተሰብን፣ ሰፈርና አካባቢንም መጠበቅ ነው። በውጭ ሀገራት ያየነው ዘግናኝና ሰቅጣጭ መዓት በሀገራችን እንዳይከሰት ለማድረግ ሁሉም ሰው ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አለበት። ሀገር ያለ ሰው ባዶ መሬት ነች። ውበትና ድምቀት የላትም። ብዙ ሀገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን በኮሮና ቫይረስ ተነጥቀዋል።
እያንዳንዱ ሰው ከጀርባው ስንት ቤተሰብ እንዳለው ሲታሰብ አደጋውን የከፋ ያደርገዋል። ቤተሰብ ፈረሰ፤ ተበተነ አለቀ ማለት ነው። እንዲህ ሆኖ አይተናል። አሁን ግን ለቀብር ያስቸገረ ሁኔታ ነው የተፈጠረው።
የመንግሥታትን አቅም በእጅጉ የፈተነ፤ ብሔራዊ ኢኮኖሚያቸውን ያንኮታኮተ፤ በታላላቅ ሀገራት ብዙ ሚሊዮን ዜጎችን ከሥራ ያፈናቀለ ፤ ንግዶችን እንዲዘጉ ያስገደደ፤ የዓለምን ኢኮኖሚና ፖለቲካ ከስረ መሰረቱ የለወጠ፤ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ አደጋ ነው – ኮሮና ቫይረስ።
ቫይረሱ መልኩን እየቀያየረ ነው የሚከሰተው። በአንዱ ሀገር የታየው በሌላው ሀገር ላይከሰት ይችላል። በአፍሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደቀን እያሻቀበ ነው። በተለይ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ፣ በግብጽ፣ በአልጄሪያና በሌሎችም የሟቾች ቁጥር ከፍ እያለ ነው። በኢትዮጵያ አገራችንም በኮሮና ቫይረስ የተያዙት ሰዎች ቁጥር በየቀኑ እያሻቀበ ነው። ቁጥሩም ከ330 በላይ አልፏል። ምንም እንኳ ብዙዎቹ ቢያገግሙም አምስት ሰው ደግሞ ሞቷል።
በሀገራችን ስርጭቱን ለመግታት ታላቅ ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም፤ ግዴለሽነትና የጥንቃቄ ጉድለት በስፋት ይታያል። ገና ብዙ መስራትን ይጠይቃል። ከቅን ዜጎች ብዙ መዋጮ እየተሰበሰበ ነው። የእኛ ሕይወት በድህነትና በትግል የተሞላ በመሆኑ የእለት ጉርስ ለማግኘት የሚሮጠው ህዝብ ብዙ ነው። በዚህ ምክንያት ጥንቃቄን ተግባራዊ ማድረግ እንጂ አትንቀሳቀስ ለማለት አይቻልም።
የምግብ ችግርን ለመፍታት መንግሥት የሚችለውን እያደረገና አማራጮችን እየፈለገ ይገኛል፤ እንዲሁም ችግረኞችንና ረዳት የሌላቸውን አቅመ ደካሞችን ለመርዳት ሰፊ ሥራም እየሰራ ነው። ሥራ ተቀዛቅዟል። በቅርብ ዓመታት አዲስ አበባ ከተማ መሸከም ከምትችለው በላይ በሕዝብ ተጨናንቃለች። ሥራ ፍለጋ ወደከተማዋ የገባው እልፍ ነው። ትንፋሽ ለትንፋሽ እየተማማገ፤ እየተገፋፋ፤ እየተተራመሰ ነው የሚሄደው። እንግዲህ ከበሽታው ባሕሪ አንጻር ስንነሳ ወዴት እየሄድን ነው የሚለው በእጅጉ ያሳስባል፤ ያስፈራል። ያስጨንቃልም። መጠንቀቅ እንጂ ተያይዞ ማለቁ መፍትሄ አይሆንም። መዘናጋቱና ምንም አይመጣብንም የሚለው ንቀት ገዝፎ ይታያል። በዚህ ከቀጠለ ትልቁ ተጠቂ የምትሆነው አዲስ አበባ ከተማ ነች።
አሜሪካ 88 ሺህ ዜጎቿን በኮሮና ቫይስ አጥታለች። በሚሊዮኖች ተይዘዋል። በእንግሊዝ በኮረና ቫይረስ የሞቱተ ሰዎች በአውሮፓ የአንደኛነቱን ደረጃ ይዟል። ሁሉም ሰው ከሰዎች ስብስብ እራሱን ያርቅ። ባንወደውም ገለልተኝነትን መልመድና ራቅ ማለት ለጊዜው መፍትሄ ነው። ራስንና ሕዝብን ከአደጋ የመከላከልና የመጠበቅን መመሪያ ተግባራዊ እናድርግ። የእኛነታችን መገለጫ የሆነው በሀዘኑ፣ በሰርጉ፣ በልደቱ፣ በምርቃቱ፣ በመርዶው፣ በእድሩ በቡና ጠጡም ሆነ በሽምግልናው የመሰባሰቡ ነገር ለጊዜው ይቅርብን። የገጠመን በሽታ በትንፋሽ የሚተላለፍ በመሆኑ አደጋው እጅግ የከፋ ነው። እልቂት ያመጣል። ከመጠንቀቅ ውጭ ለጊዜው መድኃኒት የለም። አሁንም ነገም እንጠንቀቅ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2012
ወንድወሰን መኮንን