ከሰላሳ አምስት በላይ ነጫጭ ድንኳኖች የደመቀው ጃንሜዳ ትናንት ከቀትር በኋላ ክብ ክብ ሰርተው ዝማሬ በሚያሰሙ ምዕመናንና የተለያዩ ጨዋታዎችን በሚጫወቱ ወጣቶች ተሞልቷል። ፀሐይ ማዘቅዘቅ ስትጀምር ደግሞ ስፍር ቁጥር የሌለው ህዝበ ክርስቲያን በአምስቱ በሮች እየተመመ ገብቶ ግቢውን አጥለቀለቀው።
ቀስ በቀስም ከሩቅ ይሰማ የነበረው በከበሮ የታጀበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአገልጋዮች ዝማሬ ለጆሮ እየቀረበ መጣ።ጥንግ ድርብ የለበሱ ካህናት፣ ነጫጭ ልብስ የለበሱ በገና የሚደረድሩ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ዩኒፎርም የለበሱ ዘማሪያን ልብን በሚያርድ ዝማሬያቸው አሥራ አንዱን ታቦታት አጅበው በመግባት የተዘጋጀ ላቸውን የክብር ቦታ ያዙ። ትናንት ከተራ በጃንሜዳ ሲከበር ድባቡ የተለየ ነበር።ከአብዛኛው ምዕመናን ፊት ላይ የሚነበበው ደስታ ልዩ ነበር።በተለያየ ቋንቋ ምስጋና እና ዝማሬ የሚያሰሙ ምዕመናን እዚህም እዚያም ይደመጣሉ።ወጣቶች አርሞኒካ እየነፉ ይደንሳሉ።በእዚያው ልክ ደግሞ ሸንኮራ አገዳ ፣ፕሬም በጋሪ እየገፉ ፣ከረሜላ፣ ማስቲካ፣ ብስኩትና ሌላም በደረታቸው ተሸክመው ንግድ ላይ የተሰማሩትም ወጣቶች የበዓሉ አድማቂዎች ሆነው አምሽተዋል።
«የዘንድሮው በዓል እስከዛሬ ሲከበር ከነበረው በሦስት ነገር ይለያል» ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊና የጥምቀት በዓል አከባበር አብይ ኮሚቴ አባል መምህር እንቁባህሪ ተከስተ ናቸው። እንደ መምህር እንቁባህሪ የመጀመሪያው ጥምቀት በባህሪው በየዓመቱ አዲስ መሆኑ ፤ ሁለተኛው ደግሞ በዓሉን እንደ መስቀል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የተጀመረው ሥራ ፈር እየያዘ በመምጣቱ ነው።
በዩኔስኮ የማስመዝገቡ ጥያቄ ከቀረበ አንድ ዓመት የሆነው ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ህዳርና ታህሳስ ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። የበዓሉ በዩኔስኮ መመዝገብ ደግሞ ድርብ ድርብር ፋይዳ አለው ያሉት መምህር እንቁባህሪ በቅድሚያ ዓለም የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የህዝቦቿን አንድነትና እንግዳ ተቀባይነት እንዲረዳ የሚያደርግ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ከተለያዩ ሀገራት ጎብኚዎች እንዲመጡ በማስቻል የሀገሪቱን ኢኮኖሚው የሚደግፍ ይሆናል።
የዘንድሮውን በዓል በሦስተኛ ደረጃ ልዩ የሚያደርገው ምእመናኑንና መላውን ኢትዮጵያዊ ሲያሳዝን የነበረው ለበርካታ ዓመታት ለሁለት ተከፍሎ የነበረው የቤተክ ርስቲያኒቱ ሲኖዶስ እርቀ ሰላም አውርዶ አንድ መሆኑ በመሆኑ ነው። በሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የእምነቱ ተከታዮች እንዳሉ በመግለፅም በዓሉ አንድነት፣ ህብረትና ፍቅር የታየበት እንደሆነ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ምክትል ጸሐፊ የሆኑት መጋቤ ሃይማኖት አብርሃም ገረመው በበኩላቸው በዓሉ ከኤርትራ ጋር ሰላም ወርዶ በአንድነትና በፍቅር ያከበርንበት ጊዜ በመሆኑ ከሌላው ጊዜ የተለየ ያደርገዋል ይላሉ። መጋቤ ሃይማኖት እንደሚሉት ዛሬ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የወረደው ሰላምና የተጀ መረው ግንኙነት በሀገር ውስጥ ላለነውም ትልቅ ትምህርት የሚሰጠን ነው። በከተራ ዋዜማ ጥምቀተ ባህሩ የሚያድርበትን ቦታ ሲያጸዱና ሲያዘጋጁ የነበሩት የእስልምና እምነትና የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ድርጊትም ብዙ የሚያ ስተምር ነው። በመሆኑም በመላው ሀገሪቱ የሚገኝ ህዝበ ክርስቲያን በዓለ ጥምቀቱንም ሲያከብርም ሆነ ከዛ በኋላ ስለ ፍቅር በመስበክ ፣በተግባርም ይህንን በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ