ኢትዮጵያ ባህል የበረከተባት፣ የተዋበ ማንነት ያነፃት ውድ ምድር ናት።ኢትጵያዊነት የባህል ድርብርብነት፤ የመከባበር ተምሳሌት፤ የውህደት፤ የአብሮ መኖር ውጤትነትም ነው።ማህበረሰባዊ እሴቶቻችንን ደግሞ የእርስ በእርስ መከባበራችንን የሚያጎሉ የአብሮ መኖር ትስስራችንን የሚያደምቁ ትልቅ ሀብቶቻችን ናቸው፡፡
አንድ ህብተሰብ ራሱን የሚያስተዳድርበት ባህላዊ ስርዓቶችና ደንቦች ቀርጾ በእነዚህ በቀረጻቸው መተዳደሪያ ደንቦች መመራት እና መገልገል ሲጀመር ባህሉንና ቋንቋውን ተረድቷል፤ አውቆታል የሚለውን ያመለክታል።በተጨማሪም ህብረተሰቡ እየተጠቀመባቸው ያሉት ባህሎችና ቋንቋዎች የመጠበቅ ማህበራዊ ግዴታ እንዳለበትም ያስገነዝበዋል።
እንዲህ ያሉ የባህል ባለቤቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ጊዜውን ባገናዘበ መልኩም ማለፍ የሚችሉት ለባህሉ ሲሳሱና ሲንከባከቡት መሆኑ እሙን ነው።እንዴት እንዲህ ያሉ ወርቃማ እሴቶቻችንን እንጠብቃለን፣ እንከውናለን ከተባለ መልሱ ቀላል ነው።ዘመኑን የዋጀ ሰው መሆን ሲቻል ይህን ማድረግ ይቻላል።አስተዋይ ሰው ሲሆንም ይህ እውን ይሆናል።አስተዋይ ሰው ማለት ትክክለኛን ጊዜ ያወቀ፤ በጊዜው ላይ አስፈላጊ ሰው የሆነ ነው።እናም እንደዚህ በሆነ መተሳሰር እና መቀራረብ ውስጥ የሚኖር ማህበረሰብ እንደቀድሞ እንዳይሆን፤ ማህበራዊ ትስስሩን አጠናክሮ እንዳይቀጥል የሚያስገድድ ችግር ገጥሞታል፤ ኮሮና ! ይህ ወረርሽኝ አካላዊ ርቀት የሚጠይቅና በማህበር የሚከወኑ ተግባራትን መፈጸም የማይቻልበት ነው።
በጎ የሆኑ ባህሎች በተመሳሳይ እና በለመድነው መንገድ የምንተገብረው እና ጊዜውን ያላገናዘቡ ከሆነ ራስን፤ ቤተሰብን አገርን ለኪሳራ እና ለሞት ይዳርጋል።ስለዚህ ትክክለኛ ጊዜን በማወቅ ተገቢውን ተግባር መፈጸም ራስን፣ቤተሰብንና አገርን ማትረፍ ያስችላልና ንክኪ የሌለባቸውን አንዳንድ በጎ ስራ የምንከውንባቸው ባህሎቻችንን በመተግበር ዛሬን መሻገር ይገባል፡፡
ከእነዚህ ውብ ባህሎች መካከል ደግሞ በተለያዩ ብሔረሰቦች ውስጥ ያሉት ክፉን ማምለጫዎቹ የመረዳዳት ባህሎቻችን ናቸው።በእነዚህ ባህሎች ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የእርስ በእርስ ጦርነቶች ሲገጥማት፤ ርሃብ ሲያስቸግራት፤ የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲደርስባት የገጠማትን ችግር ታልፍባቸዋለች፡፡
አሁን ጊዜው እንደሚታወቀው በአለማችን ብሎም በኢትዮጵያ ከባድ የፈተና ወቅት ነው፤ በአለም አቀፍ በተከሰተው ኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በሽታው ታማሚውንም ሆነ ጤነኛውን አሽመድምዶ ከሀኪም ቤት እና ከመኖሪያ ቤት ካዋለ ቆየ፤ታዲያ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ወረርሽኙን ፍራቻ ቤት በተቀመጠው እና የዕለት ጉሩሱን በሚፈልግ መካከል ችግር መፈጠሩ የማይቀር ነውና እነዚህ መልካም የመረዳዳት ባህሎቻችን ዳግም መምጣታቸው ግድ ይሆናል።ምክንያቱም ለችግር ፍቱን መድሃኒት ናቸው።አቅም የሌላቸው ቤተሰቦች ከበሽታው ባልተናነሰ የእለት ጉርስን ያጣሉና መድረስ ያስፈልጋል።እናም መረዳጃዎቻችን ለችግረኞች ይድረሱ ማለታችን አልቀረም።
ይህ ወቅት በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጠው ሃይማኖታዊ ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የረመዳን ጾም ነውና ብዙዎችን ከችግራቸው እንታደጋለን ፤በጻሙ ምክንያት ወሩ እንኳን ቅዱስ ወር ተብሎ ይጠራል።ስለዚህም ቅድስናን ለማምጣት ደግሞ በጎ ማድረግ ሀይማኖታዊ ግዴታ ነውና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ይህ ይተገበራል።
ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆነባቸው ሰዎች በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት የዕለት ጉርሻን እንኳን ሟሟላት ተስኗቸዋል።ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ጾሙን በአግባቡ መከወን እጅግ አዳጋች ነው።ግን
‹‹ሳይደግስ አይጣላም›› ይባላልና ባህላችን ለዚህ መልስ ይሰጣል።ለምሳሌ አብነት አካባቢ የሚኖሩ በጎ አድራጊ ወጣቶች በራሳቸው ፍላጎት በመሰባሰብ እንደዚህ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመርዳት እየሰሩ ናቸው፡፡እኛም የዚህ ቅዱስ ሃሳብ ተዋናይ ከሆኑት መካከል ከተወሱኑት ጋር ቆይታ አደረግን።
ሀሳቡ እንዴት ተጠነሰሰ
ኢብራሂም አስራር ይባላል።ከበጎ ፈቃደኞቹ አንዱ ነው።የሀሳቡን መጸነስም እንዲህ ያስረዳል።ኢብራሂም እንደሚለው፤ እሱና እና ሌሎች በጎ ፍቃደኞች ወጣቶች ለወትሮ የተለያዩ ጨዋታ የሚጫወቱባት በወጣቱ አገላለጽ “ድድ ማስጫ” የሚሏት ስፍራ አለች።በዚያች ቦታ ላይ ጓደኛሟች ተሰብስበው ይመካከራሉ፤ ይወያያሉ እንዲሁም የተለያዩ ጨዋታዎችን ይጫወታሉ።ታዲያ በአንዱ ቀን እንደወትሮ የዘወትር ጨዋታቸውን ለመከወን በተገኙበት ነው ከየት እና ከማን እንደተነሳ በማያውቁበት ሁኔታ አንድ ሀሳብ ወደ ተሰበሰበው ወጣት መሃል ዱብ ያለው።ሀሳቡ ረመዳን ሊገባ ሳምንት መቅረቱንና በኮሮና ምክንያት ቤት የተቀመጡ ወገኖች ይህንን ጊዜ የሚያሳልፉበት መላ መፈልግ ነበር ፡፡
ወጣቱ አሁንም ይናገራል።እንደሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ መከሰቱ በተለይ የዕለት ገቢያቸውን በቀን
በሚያገኙት ላይ የበረታ ነው።ስለዚህም ይህ ሀሳብ እውን እንዲሆን መስራት መጀመራቸውን ያነሳል።በበጎ ፍቃድ ሥራውም እየተሳተፉ ያሉት ሙስሊም ወጣቶች ብቻ አደሉም። የእምነት ልዩነት ሳይደረግ ሁሉም ለሁሉም በሚያስብ መልኩ መሆኑን ያስረዳል።
‹‹በጎነት ሙስሊም ክርስቲያን አይልም››› የሚለውና የበጎ ተግባሩ ተሳታፊ የሆነው ወጣት ዘካሪያስ አለማየሁ በበኩሉ ስለ በጎ ተግባር ምስረታ እንዲህ ይላል።ወረርሽኙ ዘር ቀለም ሃይማኖት የማይመርጥ ነው።ስለዚህ እኛም እንደዚህ ካሉ ልዩነት ወጥተን ልንተጋገዝ ይጋባል በሚል ተሰባስበናል።እርሱ በተወለደበት አካባቢ በህብረት መኖር ፍቅር እና መረዳዳት ልዩ መለያው እንደሆነ ያስታውሳል፤ በየሰፈሩ ባልተጻፈ ህግ የሚኖር ህዝብ ቀላል አይደለም። ይሄ የመተሳሰብ ህግ በአንድ ሰው አቅም የማይከናወኑ ሥራዎችን ተጋግዞ መስራት፣ መተባባር ላይ ትኩረት ያደረገ ባህል ነው።በዚህ ወቅት ይህንን ማድረግ በወረርሽኙ ላለመጎዳት ያግዛል ብሏል።በስራ የታገዘውም ግለሰብ የሥራ ተሳታፊዎቹን ይመርቃል። ያበላል፤ ያጠጣል።
ወጣቱ ዘካሪያስ እንደሚያስረዳው፤ የአካባቢው ነዋሪ በባህላዊ መንገድ መረዳዳት፣ በችግር ጊዜ የሚፈለገውን በማዋጣት የተለያዩ ችግሮችን ለማቃለል በገንዘብ፣ በጉልበትና በምክር ድጋፎች ማድረግን ያጠቃልላል።በዚህም ለረመዳን ያደረጉት ድጋፍ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነና ነገም እንደሚቀጥልበት አጫውቶናል።
ከዚህ በፊት በአካባቢው እጅግ ደሃ ወይም አቅመ ደካማ የሆኑ ግለሰቦችን መልሶ ለማቋቋም በገንዘብና በዓይነት ድጎማ ማድረጋቸውን የሚያነሳው ዘካርያስ፣ በሰርግ ወቅትም ቢሆን ለጋብቻ የሚዘጋጀው ሰው ለሚገጥመው ችግር የአካበቢው ወጣት ገንዘብ በማዋጣት ችግሩን ይፈታለት እንደነበር ያስታውሳል።ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሃይማኖት ሳይገድበው ለረመዳን ጾም ለሚጾሙ ወገኖቹ የተቻለውን እያደረገ ያለውም ያደገበት፤ የኖረበት ጥልቅ እና በፍቅር የተሳሰረው ያልተጻፈው ህግ አስገድዶት መሆኑንም ይገልጻል።
ድጋፉ እንዴት ተከናወነ
ሁሉም በጎ ፍቃደኛ በሃሳቡ ከተስማማ በኋላ ቀጣይ ስራው ምን እንደሆነ እና በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለበት እንደተወያየ የሚናገረው ወጣት ኢብራሂም በውይይታቸው መጀመሪያ ከተነሱት መካከል አንድ የረመዳንን ጾም የሚጾም ግለሰቦች ጾሙ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በወር ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ ያስፈልጋል የሚል ነበር።ከዚያ የወር ማፍጠሪያ ገንዘቡ ምን ያህል እንደሆነም በእኛ አቅም አሰላንና የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸውን ሰዎች ጠይቅን ተባበሩን።በዚህም ለአንድ ግለሰብ በወር አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሀምሳ ብር እንዲደርስ ሆነ።
የገቢው አሰባሰብ ሁሉም በጎ ፍቃደኛ ወጣት መንገድ ዳር ካርቶን በማንጠፍ ሰው የተቻለውን እንዲያደርግና እጁን እንዲዘረጋ በማገዝ እንደሆነ የሚያነሳው ኢብራሂም፤ በተለይ ቤት ለቤት ለድጋፍ በምንሄድበት ወቅት የአካባቢው ነዋሪ ሃይማኖት ሳይገድበው ለሙስሊም ወንድሞቹ የሚያደርገው ነገር ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ይናገራል።ይህ ደግሞ ለእርሱና መሰሎቹ የኢትዮጵያዊነትን ሌላ ጎን እንዲያዩ እንዳስቻላቸውም ያስረዳል።የጠፋ የሚመስለው የመረዳዳት እና የመደጋጋፍ ባህል ተዳፈኖ ነበር እንጂ አልጠፋም የሚለውን ሀሳብ እንዳየበትም ይገልጻል።
በዓይነትም፣ በገንዘብም ሁሉም በሚባል ደረጃ የአካባቢው ነዋሪ የተቻለውን ድጋፍ እንዳደረገ የገለጸው ወጣት ኢብራሂም፤ በመቀጠል ደግሞ በአካባቢው የሚኖሩ አቅመ ደካሞችና የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ቤተሰቦችና ግለሰቦች የምንደርስ ይሆናል፤ ለዚህም ልየታ እያደረጉ መሆኑን ገልጿል።እስካሁን በተሰበሰበው ገንዘብ እና ቁሳቁስ ለሃምሳ ቤተሰቦች ድጋፍ መደረጉን አንስቷል፡፡
ከዚህ በፊት ይላል ወጣቱ ማፍጠር ያልቻለን ግለሰብንም ሆነ ቤተሰብ አቅም ያለው ቤተሰብ ቤቱ ወስዶ ማስፈጠር ሃይማታዊ ግዴታ እንዳለበት እና ይህንን ማከናወኑ በሃይማኖቱ ጽድቅ እንደሚያስገኝ ይታመናልና ያደርገዋል፤ አሁን ግን በወረርሽኙ ምክንያት መሰብሰብ ስለማይቻል ችግሩ ስለሚበዛ ነው ለምግብና ለመሳሰሉት ወጪ ገንዘብ ማሰባሰብ የተጀመረው ብሏል፡፡
የወደፊት ራዕይ
ወጣቶቹ ዛሬ ላይ የደረሱት በልቦና ህግና በፍቅር ብቻ እንጂ ስርዓት ባለው መንገድ ተደረጅተው መደበኛ መንገድ ተከትለው አይደለም።ስለሆነም ይህንን የመረዳዳት ባህላችንን ዘር ፣ሃይማኖት፣ ቀለም ሳንለይ ማስቀጠል አለብን ብለን እየተንቀሳቀስን ነው፤፤ ለሁሉም የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ልምድ ለማድረግ እያለሙ እንዳሉ ተናግረዋል።በተለይም ህብረታቸውን መደበኛ በማድረግ እና የሚረዱበትን ዓላማ እና ስልት ነድፈው በመንቀሳቀስ እስከዛሬ ከአደረጉት ድጋፍ ላቅ ባለ ሁኔታ ለመስራት እንዳሰቡም አጫውተውናል።
ወጣት ኢብራሂም በመጨረሻ እንዳለው፤ ክርስቲያን ወንድሞችን የሙስሊሙ ጉዳይ ጉዳያቸው አድርገው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ስለተባበሩን እና ከእኛ እኩል ደፋ ቀና ስላሉ እናመሰግናቸዋለን።እነርሱም ወንድሞቻቸው በሚፈልጓቸው የትኛውም ጉዳይ ላይ ያለምንም የሃይማኖት አጥር ሄደው የሚፈልጉትን እንደሚያግዙ ቃል ገብተዋል።
በዘንድሮ ረመዳን አምስቱን ስግደቶች ከመስኪድ ውጭ በሆነ መልኩ መስገዱ፤ በህብረት ሆኖ ማፍጠር ባለመቻሉ፣ መካ ሄዶ ሃጅ ማድረግ አለመቻሉ … በተለያዩ ምክንያቶች ታሪካዊ እንደሆነ እና በግል ደግሞ የእሳቸውን ልብ እንደሰበረው በኢቢኤስ የመዝናኛ ፕሮግራም ቀርበው የተናገሩት ደግሞ ሁዝታስ አቡበከር ናቸው ።
እንደ ሁዝታስ አቡበከር ገለጻ ከችግር ይልቅ የተሻለውን ዕድል በማየት ይህንን ክፉ ጊዜ ማሳለፍ ያስፈልጋል፤ አሁን ያለንበት ሁኔታ እያንዳንዱ ምዕመን የማይገናኝበት፣ በህብረት የማይሰገድበት፣ … ብቻ ሁሉም ቤቱ የተከተተበት ሰዓት እንደሆነ የጠቀሱት ሁስታዝ አቡበከር በዚህ ወቅት ሌሎች ወንድሞቻቸውን ማሰብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ይህ ክፉ ጊዜ አልፎ ቀጣይ ብዙ ዓመታትን ሃጃጅ ለማድረግ፣ በጋራ ለመጸለይ፣ ለመረዳዳት በጋራ ለማፍጠር፣ሰብሰብ ብሎ በህብረት ዱአ ለማድረግ … አሁን ላይ በኪነጥበብ ባለሙያዎች በሃይማኖት አባቶች እንዲሁም በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር መስማት እና ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
መሰናበቻ
አገራችን አያሌ ትውፊታዊና ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ናት።እነዚህ እሴቶች ደግሞ የማንነት አሻራ ዋነኛ መደላድል ናቸው። ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ወዲህ ብቻ ዘመናችንን ስናሰላ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ሸኝተናል። በቅድመ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘመኑን ስናይ ደግሞ የንግሥተ ሣባን ድንቅ የአክሱም የስልጣኔ ዘመን ስናክል የትውፊትና የባህል አለባውያኖቻችን መጠን የትየለሌ ይሆናል።
ታዲያ ጥንታዊትና የትናንት ሁነቶች ስናይ አገሪቱ የታሪክ እመቤት የሚያደርጋት ብዙ መለያዎች ይኖሯታል።የራሷ መገለጫ፣ መታወቂያና ፣መለያ ገጽታ አላት። ነባሩ ባህሏ፣ ማህበራዊ ልማዶቿ፣ ሥርዓተ አምልኮዎቿ ባህላዊ ሙዚቃና ኪነቶቿ፣ ሥነ ቃሎቿ ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ባህሎችና ትውፊቶቿ ወዘተ… ሁሉ የሷነቷ ማሳያ መስተዋቶች ናቸው።
ታዲያ እንዲህ ያሉ የበለጸጉ እና የደረጀ ባህል ያላት ይህች አገር እንዲህ ያሉ ባህላዊ መረዳዳቶችን በመጠቀም በወረርሽኙ ምክንያት የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን ለማይችሉ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ እና በተገቢው መንገድ በመድረስ ብሎም ጥንቃቄንም በማድረግ አገሪቱ ያላትን የመቻቻል፣የሰላም እና የፍቅር እሴቶች መጠቀም ይገባናል ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2012
አብርሃም ተወልደ