ጉለሌ ክፍለ ከተማ በከተማ ደረጃ የሚካሄደውን 7ኛውን የተማሪዎች የስፖርት ውድድር ለማስተናገድ ሽር ጉድ እያለ ነው፡፡ ለመላው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪዎች የስፖርት ውድድር ጉለሌ ክፍለ ከተማን ወክለው የሚወዳደሩ ተማሪዎች የሚያደርጉትን የውስጥ ውድድር ምን እንደሚመስል እና ክፍለ ከተማው በከተማ ደረጃ የሚያካሂደውን የተማሪዎች የስፖርት ውድድር ቅድመ ዝግጅት በምን አይነት ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን፤ የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ማህበራት ማደራጀት ተሳትፎና የሥልጠና ውድድር ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ተክለማሪያም ሊጋባ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል።
አቶ ተክለማርያም በ2010 ዓ.ም በተካሄደው የመላ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪዎች የስፖርት ውድድሮች ጉለሌ ክፍለ ከተማ አጠቃላይ የውድድሩ አሸናፊ ሆኖ በማጠናቀቁ፤ ዘንድሮ የሚካሄደውን 7ኛውን የመላ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪዎች የስፖርት ውድድር ክፍለ ከተማው እንዲያዘጋጅ እድል የተሰጠው መሆኑን ይናገራሉ።
ለ7ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች የስፖርት ውድድር ክፍለ ከተማችንን ወክለው የሚወዳደሩ እስፖርተኞችን ለመመልመል የውስጥ ውድድሩ በሶስት ምድብ ተከፍሎ እየተካሄደ መሆኑን በማስረዳት፤ ከ5 እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ በቀኑ የትምህርት መርሀ ግብር የሚማሩ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በውድድሩ እንደሚሳተፉና በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በስድስት የስፖርት አይነቶች ማለትም በእግር ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በእጅ ኳስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስ እና በአትሌቲክስ የውድድር ዓይነቶች በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም በአትሌቲክስ፣ በጠረጴዛ ቴኒስና በዳርት በነዚህ በሶስቱ የስፖርት አይነቶች አካል ጉዳተኛ የሆኑ ተማሪዎች የውስጥ ውድድራቸውን እያካሄዱ እንደሆነ ባለሙያው ገልጸዋል።
በሶስተኛው ምድብ የሚካሄደው የውስጥ ውድድር እንደ ቦክስ፣ ጂምናስቲክስ፣ ማርሻል አርት፣ ክብደት ማንሳትና መሰል ስፖርቶችን የሚይዝ ሲሆን፤ በነዚህ ስፖርቶች ውድድር ለማካሄድ በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀው፤ በተለያዩ በክፍለ ከተማው በሚገኙ የስልጠና ጣቢያዎች ስፖርተኞችን እርስ በእርስ በማወዳደር፤ ባለሙያዎችንና ቴክኒክ ኮሚቴዎችም በቦታው ተገኝተው ውድድሩን እየተከታተሉ ክፍለ ከተማውን የሚወክሉ ስፖርተኞችን በመመልመል ላይ እንደሆኑ ገልጸውልናል። በአጠቃላይ በከተማ ደረጃ የተማሪዎች የስፖርት ውድድሩ የሚካሄደው በ17 የስፖርት አይነቶች መሆኑን ያስረዳሉ።
ባለፈው ዓመት አድርገነው ከነበረው ቅድመ ዝግጅት አንጻር ዘንድሮ የተሻለ ልምድ አለ ለማለት አያስደፍርም። ነገር ግን ካምናው በተሻለ በውስጥ ውድድራችን የሴት ስፖርተኞች ተሳትፎና ተነሳሽነት ጨምሯል። በተለይም ሴት ተወዳዳሪዎች አትሌቲክስና እግር ኳስ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው የተሻለ ተሞክሮ ነው። በዚህም በቀጣይ ክፍለ ከተማውን የሚወከሉ ሴት ተተኪ ስፖርተኞችን ያፈራንበት ውድድር ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የውስጥ ውድድራቸው ወረዳቸውን ወክለው ስለሆነ እያካሄዱ ያሉት በጣም በተጠናከረ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል። በተጠናከረ ሁኔታ ባለሙያዎቹም በየውድድር ሜዳው ተመድበው ሁሉንም ጨዋታዎች ትኩረት ሰጥተው በመከታተል ክፍለ ከተማውን የሚወከሉ እስፖርተኞችን በመመልመል ላይ መሆናቸው ከአምናው የተሻለ ጥሩ ተሞክሮ ነው ብለዋል አቶ ተክለማሪያም።
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል የሚካሄደው የተማሪዎች የውስጥ ስፖርት ውድድር በበጀት እጥረትና ርዕሳነ መምህራን ቁርጠኛ አቋም ወስደው ባለመስራታቸው ምክንያት የውስጥ ውድድሩ እየተካሄደ እንዳልሆነ አቶ ተክለማሪያም ጠቁመዋል።
አቶ ተክለማርያም በክፍለ ከተማው ስር ከሚገኙ 16 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተወዳዳሪ እስፖርተኞችን ስም ዝርዝር የላኩልን ሶስት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው ብለዋል። ሌሎቹ 13 ትምህርት ቤቶች በቶሎ የተወዳዳሪዎችን ስም ዝርዝርና የውስጥ ውድድሩን በያዝነው ሳምንት እንዲጀምሩ ቁርጠኛ አቋም ወስደን ወደታች ወርደን በመስራት ውድድሩን እንዲጀምሩ እናደርጋለን ፤ የበጀት ችግሩንም ከርዕሳነ መምህራን ጋር ውይይት በማድረግ ለመቅረፍ እየሰራን ነው ብለዋል።
ተማሪዎች ለባህል ስፖርቱ ፍላጎት አለማሳ የትና በውድድሩም ለመሳተፍ ፍቃደኛ አለመሆን ይታያል። በዚህ ምክንያት የባህል ስፖርቱን በውስጥ ውድድራችን ለማካሄድ ሁሌም ስለምንቸገር ጎን ለጎን ሌሎች የተመልካችን ቀልብ የሚስቡ ስፖርቶችን በማካሄድ ባህላዊ ስፖርት ውድድሮቹን በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄዱ እያደረግን ነው በማለት የውስጥ ውድድሩን ሲያካሂዱ የገጠማቸውን ችግርና ችግሩን ለመፍታት የወሰዱትን የመፍትሄ ሀሳብ አቶ ተክለማሪያም ገልጸውልናል።
ከጥንት ጀምሮ ታዋቂና ዝነኛ እስፖርተኞች የትነው መነሻቸውና መፍለቂያቸው ከተባለ ትምህርት ቤት ነው። ነገ ላይም ተተኪ እስፖርተኞች የሚገኙት ከታች ከሰራን ብቻ ነው። ከታች ባለመስራታችን አሁን ላይ ሀገራችን በምትታወቅበት በአትሌቲክስ ስፖርት እንኳን የውጤት ቀውስ ውስጥ እየገባች ነው። ደግሞም ሁሉም ተማሪዎች ዶክተር፣ መሀንዲስ፣ ኢንጂነር፣ መምህር ወ.ዘ.ተ ከመሆን ባለፈ ነገ ሀገራቸውን በዓለም መድረክ እንደ ብርቅየ አትሌቶቻችን ባንዲራዋን ከፍ የሚያደርጉ ተተኪ እስፖርተኞችን ልናገኝ እንችላለን። ባጠቃላይ ተማሪዎች እራሳቸውን ካልባሌ ቦታና ከሱስ የሚያርቁበት፣ ጤናቸውን የሚጠብቁበትና የሚዝናኑበት፣ ከሌሎች ተማሪዎች ልምድ የሚወስዱበትና የእርስበርስ ግንኙነታቸውን የሚያጠነክሩበት ነው። እንዲሁም እኛ ክፍለ ከተማውን ወክለው የሚወዳደሩ ብቃት ያላቸው እስፖርተኞችን የምናገኝበት ውድድር ነው በማለት የውስጥ ውድድሩን ማካሄዳቸው የሚሰጠውን ፋይዳ አቶ ተክለማሪያም ነግረውናል።
ጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም የሚጀመረውን የመላ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪዎች የስፖርት ውድድር ለማካሄድ ክፍለ ከተማው እያደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅት እንዲህ ሲሉ አቶ ተክለማሪያም ያብራራሉ፤ መጀመሪያ ውድድሩን አስተዳደሩ በኃላፊነት እንዲቀበለው ግንዛቤ የመፍጠር ሰራ እየተሰራ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ለውድድሩ የሚያስፈልገውን በጀት እንዲያዝ አድርገናል። በሶሰተኛ ደረጃ ውድድሩ የተሳካ እንዲሆን የሚያስተባብሩ አበይት ኮሚቴዎችን የማቋቋም ሰራና በክፍለ ከተማው ያሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ኃላፊነታቸውን ቆጥሮ የማስረከብ ስራ ነው የሰራነው። በአራተኛ ደረጃ በክፍለ ከተማው አዘጋጅነት የሚካሄደው የከተማ አቀፉ የስፖርት ውድድር የተሳካ እንዲሆን ከአስሩ ክፍለ ከተማ ባለሙያዎች ጋር በከተማ አስተዳደሩ የውድድር መመሪያዎቹ ላይ ለሶስት ጊዜ ያክል ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
በከተማውና በክፍለ ከተማው ያሉትን የማዘውተሪያ ሥፍራዎችና የስፖርት ሜዳዎችን ለውድድሩ ያለምንም ችግር ለመጠቀም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጋራ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛለን ብለዋል አቶ ተክለማሪያም።
እንደ አቶ ተክለማርያም ማብራሪያ ከተማ የተማሪዎች የስፖርት ውድድሩ ሲካሄድ የዳኞችንና የአስተባባሪዎችን የውሎ አበል ክፍያ፣ የዋንጫ ግዢዎች፣ ሽልማቶች እና አስፈላጊ ተያያዢ ቁሳቁሶችንና ወጪችን ከተማ አስተዳደሩ እንደሚያዘጋጅና እንደሚሸፍን ጠቁመዋል።
በቀስት፣ በኩርቦና ገበጣ ባለ16ና ባለ12 በሶስቱ የባህል እስፖርቶች ብቻ የውስጥ ውድድሮች እየተካሄዱ እንደሆነ፤ በከተማ ደረጃና 3ተኛው ሀገር አቀፍ የተማሪዎች ስፖርት ውድድር በመጭው መጋቢት ወር በመቀሌ ከተማም ሲካሄድ በነዚሁ የስፖርት አይነቶች ብቻ እንደሚካሄድ፤ የባህል እስፖርት ውድድር የሚካሄድባቸውን የመጫዎቻ ቁሶችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን እንደሚያቀርብላቸው አቶ ተክለማሪያም ገልጸውልናል።
በአጠቃላይ አዘጋጅ እንደመሆኑ አመራሩ፣ የስፖርት ባለሙያውና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ልዩ ትኩረት ሰጥተው በጋራ እየሰራ እንዳሉ፤ ከከተማው ስልጠናና ውድድር ዳይሬክቶሬት ጋራ በቅርበትና በቅንጅት እየሰራ መሆኑ ክፍለ ከተማውም የተሰጠውን ኃላፊነት በሚገባ እየተወጣ እንዳለ፤ ውድድሩንም በተሳካ ሁኔታ እንደሚያካሂድ ያላቸውን ከፍተኛ ግምት አቶ ተክለማርያም ይገልፃሉ።
ከባለሙያዎች ጋር በቅርበትና በሰፊው በመስራታቸው ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010ዓ.ም በተካሄደው የመላው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ተማሪዎች የስፖርት ውድድር ጉለሌ ክፍለ ከተማ ለተከታታይ አምስትና ከዚያ በላይ ዓመታት ውድድሩን በአንደኛ ደረጃ እንዳጠናቀቀ አውስተው፤ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ስራ ከተሰራ ውጤታማ የማይሆንበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ከአሁን በፊት የነበራቸውን ምርጥ ተሞክሮ በመጥቀስ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 10/2011
ሰለሞን በየነ