በእስልምና እምነት ያሉ አስተምሮዎችን በሚገባ ተምረዋል። ለእምነቱ ተከታዮች የሚሆኑ መጽሐፍትን በመጻፍና በማድረስ፤ ትምህርቶችን በማስተማር ይታወቃሉ።ከወረዳ እስከ ፌዴራል ድረስ በእምነቱ ዙሪያ የተለያዩ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ሰርተዋል።የእምነቱ ተከታዮችም በትምህርትም ሆነ በመብት ጥበቃቸው ላይ የተሻለ አማራጭም እንዲያዩ ያስቻሉ ናቸው።በተለይ ለየት የሚያደርጋቸው ደግሞ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር ያላቸው ቀረቤታ ነው።በሰርጋቸው ዕለት እንኳን ሚዜ ያደረጉት ክርስቲያን ጓደኛቸውን እንደነበረ በወጋችን መካከል አንስተናል።ይህንን ሁሉ ተሞክሯቸውን ያጋሩን ዘንድ የዛሬው ‹‹ የህይወት ገጽታ አምድ›› እንግዳችን አድርገናቸዋል። የፌዴራል ሸርያ ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዚዳንትን ሸህ መሀመድአልሙባረክ መሀመድን።
ልዩነት የሌላው ልጅነት
በደቡብ ትግራይ አሸንጌ ሐይቅ ኦፍላ ከተማ አዲሽላ መንደር ውስጥ በ1966 ዓ.ም መስከረም አንድ ለቤተሰቡ ልጅ የተገኘበት ጊዜ ነበር።በዘመን መለወጫ ዕለት የሸህ መሀመድ አልሙባረክ ቤተሰብ ‹‹ልጃችን እንኳን ደህና መጣህ›› በማለት ተቀብለውታል። ቤቱ ሞቅ ደመቅ ብሎ ከጎረቤት ጋር በደስታ የታለፈበት ቀንም ነበር።ይህ ደግሞ ጊዜውን ጠብቆ ለሚያድገው ህጻን በህብረት መኖርን እያስተማረ ያደገ እንደነበር እንግዳችን ያወሳሉ።በየበዓሉ የሚሰባሰበው ጎረቤት ለብቻ መብላትና መጠጣት እንደማይቻል አስለምዷቸው አድገዋል። ከጎረቤት ዘመድ አዝማድ ጋር አብረው በልተውና ጠጥተው ከልጆች ጋር ተሰባስበው ተጫውተው እንደኖሩም ያስታውሳሉ።
በባህሪያቸው ዝምተኛ የሚባሉ ልጅ እንደነበሩና ምግብ እንኳን ይሰጠኝ ብለው እንደማይጠይቁ ያጫወቱን ሸህ መሀመድ አልሙባረክ፤ ሌሎች ወንድሞቻቸው ስጡት ወይም ታናሽ ወንድማቸው ርቦት ሲያለቅስ ምግብ ይቀርብላቸው እንደነበር አይረሱትም።በዚህም አባታቸው ሸህ መሀመድ አወል ‹‹ለልጁ ትኩረት ስጡት›› ይሉ እንደነበርም ይናገራሉ።
ሸህ መሀመድ አልሙባረክ አባታቸው የሀይማኖት መሪ በመሆናቸው ብዙ ነገሮችን ከእርሳቸው ወርሰዋል። ከእነዚህ መካከልም ስለእምነቱ ጥልቅ እውቀት መፈለግ አንደኛው ነው።እንደውም ከዚህ ጋር ተያይዞ መምህራቸው ብዙ ጊዜ ሲመታቸው ዋና ጉዳያቸው እውቀት መቅሰም በመሆኑ እንደሌሎቹ ተማሪዎች አልማርም ብለው ቀርተው አያውቁም።በዚህም አንድ ቀን ሁኔታቸው ያስገረመው መምህር ‹‹ለምን ስትመታ በዚያው አልቀረህም›› ሲሉ ጠይቀዋቸው እንደነበር አይረሱትም።
እንግዳችን የእስልምና እምነት ተከታይ ቢሆኑም ያደጉበት ቦታ ብዙ ክርስቲያን የሚኖርበት አካባቢ በመሆኑ ብዙውን ነገር ከክርስቲያኑ ወስደዋል።በዚያው ልክ ግን የእስልምናውንም ትምህርት በላቀ ደረጃ እየተረዱ ነው ያደጉት።ክርስቲያን ጓደኞቻቸው ማርያምን እያሉ ሲምሉ እርሳቸውም ‹‹ ማርያምን ››ብለው ይምሉ እንደነበር ይገልጻሉ።ሆኖም ከተማሩ በኋላ የእርሳቸው እምነት የሚፈልገውን ማድረግ መጀመራቸውን ያነሳሉ።
‹‹ሁሉም በአንድነት ተፋቅሮ የሚኖርበት ቦታ ላይ በማደጌ ሁሉንም እንድወድ አድርጎኛል።በዚያ ላይ አባቴ የሀይማኖት መሪ፤ መምህርና የአገር ሽማግሌ በመሆኑ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች አማካኝነት የተለያዩ ልምዶችን እንድቀስም እድል ገጥሞኛል።ለሰዎች ልዩ ክብር መስጠትና መታዘዝ ያለውን ዋጋ እንድረዳም ስላደረገኝ የልጅነት ጊዜዬን እደሰትበታለሁ፣እወደዋለሁም›› ይላሉ።
አባታቸው ከተማሪዎቻቸው ጋር ተካፍለው የሚበሉ፤ ብቻቸውን መመገብ የማይወዱ በመሆናቸውም ለትንሹ ታዳጊም ትልቅ አርአያ እንደነበሩ ያወሳሉ።መስጠትን እንዲለምዱ፤ ከሰዎች ጋር በፍቅር እንዲኖሩ፤ በስነምግባር የተሻሉ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውም ይናገራሉ።እስልምናና ክርስትና እምነት እንጂ ልዩነት አለመሆኑን አሳውቆ አሳድጎናል።ዛሬ በብሄርም ሆነ በሀይማኖት ዙሪያ ስለልዩነት ሲሰሙ ወደውስጣቸው እንዲገባ አይፈልጉም። ከሁሉም ሰው ጋር ተስማምቶ በፍቅር የመኖራቸው ምስጢር ከቤተሰባቸው የወረሱት መሆኑን ያስረዳሉ።
አካባቢያቸው ለራያ ቅርብ በመሆኑ በባህላዊ መንገድ የሚከወኑ ጨዋታዎች የመጫወት ዕድሉ ነበራቸው ። በተለይ ‹‹ጥጉራ›› ወይም ጅራፍ ማጮህ ፤ ሩርና ትግል እንደሚወዱና አዘውትረው የሚጫወቷቸው ጨዋታዎች እንደነበሩ ያወሳሉ።በዚህ ደግሞ ብዙ ጊዜ አሸናፊ እንደነበሩም አይረሱትም።ይህ ደግሞ በብዙ ልጆች ተመራጭ አድርጓቸው እንደነበረም አውግተውናል።
ለእንግዳችን መጻፍ የልጅነት የደስታ ምንጫቸው ነው።በዚህም ዘወትር እግራቸው ላይ በእንጨት የተለያዩ ነገሮችን ይሞነጫጭሩ ነበር።የልጅነት ፍላጎታቸውም የሀይማኖት መምህር መሆን ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ ደራሲና ፀሐፊ መሆንም ነበር።
ቤተሰብ በግብርና የሚተዳደሩ ስለሆነ ታዳጊው ሸህ መሀመድ አልሙባረክ በከብት ጥበቃና በመላላክ ያግዙ እንደነበር ያስታውሳሉ። አባታቸው ግን በትምህርታቸው የላቁ እንዲሆኑ ይፈልጋሉና በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ይገፋፏቸው እንደነበር ይናገራሉ።እርሳቸውም የአባታቸውን ምክር ይቀበሉ ነበር።ይህ ደግሞ ልክ እንደአባታቸው የሀይማኖት መሪና መምህር መሆንን እንዲሹ አድርጓቸዋል።ስለዚህም ይህንን ለማሳካት በሀይማኖት ትምህርቱ ዘልቀው እንደተጓዙ አጫውተውናል።
አያቶቻቸው አንዳንዶቹ ክርስቲያን እንደሆኑ የሚገልጹት ባለታሪኩ፤ ቤተሰብ ቤተሰብ ነው፤ ክርስቲያን ደግሞ ለእኛ ልዩ ቦታ አለው። በዚያ ላይ በአካባቢው የተለመደው ልዩነት ሳይሆን አንድነት ነውና በፍቅር ይኖራል።ሙስሊም ክርስቲያን የሚባል ነገር የለም።ስለዚህም ሁሉም የሁሉንም ልጅ ተንከባክቦና ቆንጥጦ ነው ያሳደገው።ይህ ደግሞ ስናድግም በዚያው ማንነት እንድንገነባ አድርጎናል ይላሉ።
መቻቻል የሚለውን ነገር እንደማይደግፉ የሚናገሩት እንግዳችን፤ ‹‹ማንን ነው የምንችለው›› ብለው ይጠይቃሉ።ሁላችንም የአዳም ዘሮች ከዚያም አለፍ ስንል ኢትዮጵያዊያን ነን።በዚህም በምንም እንለያያለን ብዬ አላምንም።መቻቻል መባል ያለበት ሰው ነብርን አልምዶ ሲኖርና ባህሪውን ይለውጣል ብሎ እየሰጋ ሲኖር ነው።ለሰው ልጆች ግን የሚያስፈልገው መከባበር መሆን አለበት የሚል እምነት አላቸው።
ትምህርት በወላጅ እጅ
የትምህርት ሀሁ አስጀማሪያቸው አባታቸው ሲሆኑ፤ ፊደላትንና የሀይማኖት ትምህርትን ከእርሳቸው ዘንድ ቀስመዋል።ከአባታቸው እግር ስር ቁጭ ብለው በመጀመሪያ የቀሩት ቅዱስ ቁርአንን ነበር።ለዚያውም ከ10 ገጽ የማይበልጥ።ተመላልሰው የተማሯቸው ትምህርቶች እንዳሉ ሆነው።ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ አባታቸው የሚሰጡት ትምህርት ጠንከር የሚል መሆኑ ነው።ስለዚህም ትንሽ ከተማሩ በኋላ ለተማሪዎቻቸው ሰጥተዋቸዋል።
ከአባት ቀጥለው ያስተማሯቸው የቁርአን ልዩ መምህሩ ሸህ ከማል መሀመድአማን ሲሆኑ፤ ሁለተኛ መምህራቸው ናቸው።በዚያው ልክ ደግሞ ለሌሎች ትምህርቶች ያግዛቸው ዘንድ ሸህ ኢብራሂም ከሚባሉት የአባታቸው ተማሪ ዘንድ ለዓመት ያህል አማርኛ ቋንቋን ተምረዋል።
ቁርዓንን በዓመት እድሜ ውስጥ እንዳጠናቀቁ የነገሩን ሸህ መሀመድአልሙባረክ ፤ ‹‹ገባተ›› ወደሚባል መንደር በመሄድ በታላቅ እህታቸው ባለቤት አማካኝነት ‹‹ሽጅአ›› የተባለ የሐይማኖት መፀሐፍ መማር ችለዋል።ከዚያ ዳግም ወደ አባታቸው በመመለስ በዚያው በአሸንጌ ‹‹ባፈድል›› የተባለ ሀይማኖታዊ መጸሐፍን ተማሩ።ቀጥለው ደግሞ ወደ ገንደጭረቻ በመሄድ ከሸህ ሁሴን ዘንድ ‹‹ ኡምዳ›› ፤ ‹‹ሚኒሀጂ›› የሚባሉ መፀሐፍትን ተምረው
የበለጠ ትምህርቱን ለመቅሰም አሁንም ወደአባታቸው ተመልሰዋል።
‹‹ነህዊ›› የተባለውን የአረብኛ ሰዋሰው ትምህርት ቀስመዋል።‹‹ ዳህናን፤ አስማዊ፤ አብናጃ›› የተባሉ የሰዋሰው ትምህርቶችንም በሚገባ እንዳወቁ አጫውተውናል። ከዚያ ጉዧቸው ወደ ወሎ ያደረጉ ሲሆን፤ ሀርድቦ ወይም ሀይቅ በሚባል ስፍራ በሸህ ኢብራሂም ሁሴን አማካኝነት የተለያዩ ስነጽሁፋዊ ትምህርቶችን ተማሩ።ኢዕራብ ወይም አጅሪባ ሙልሃ የተባሉ መጸሐፍንም ጠንቀቀው አወቁ።
ሁልጊዜ የትምህርት ጅማሯቸውን ከአባታቸው ዘንድ የሚያደርጉት እንግዳችን፤ ከላይ የተጠቀሱትን ትምህርቶች ካጠናቀቁ በኋላም ሀዲስን ( የነብዩ መሀመድ አስተምህሮቶችንና ተግባራትን) ለመማር ዳግም አባታቸው ዘንድ እንደሄዱ ይናገራሉ።ለዓመት ያህልም ከእርሳቸው ሳይለዩ ማወቅ ያለባቸውን ትምህርቶች ተምረዋል።ከዚያ በቀጥታ የላቀ ትምህርት ፍለጋ ባህር ማዶ የተሸገሩ ሲሆን፤ ሱዳንም ገቡ።
ሀይማኖታዊ ትምህርትን በተማሩበት ዘመናዊ ትምህርታቸውን ለመቀጠል እንደቻሉ የሚናገሩት ባለታሪኩ፤ ሱዳን እንደገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው የሆነው የሚሰጠውን አጠቃላይ መመዘኛ መፈተን ነበር።በዚህም በተሻለ ውጤት በማለፋቸው 11ኛ ክፍልን ተቀላቅለዋል።የወሰዷቸው ፈተናዎች ሂሳብ፤ ታሪክ፤ ጆግራፊና እንግሊዝኛ ሲሆኑ፤ በሚገባ አልተማሩምና ይህንን አጥንተው ነው የተፈተኑት።
በ‹‹መሀድ ኸርጦም አልዕልሚ›› በሚባል ትምህርትቤት ገብተው መማር እንደጀመሩ የሚናገሩት ሸህ መሀመድአልሙባረክ፤ በትምህርታቸው የተሻሉና የደረጃ ተማሪ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።እንደውም 12ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ ከ500ው ጥያቄዎች 498 በማምጣት በአገሪቱ ተሸላሚ ተማሪ እንደነበሩ አይረሱትም።ግን ከዚህ በኋላ ዘመናዊ ትምህርቱን አልቀጠሉበትም።ምክንያቱም ለእርሳቸው የተሻለው ሀይማኖታዊ ትምህርት ነው።እናም የበለጠ በሚወዱት ትምህርት ለመቀጠል ቀጥታ ጉዟቸውን ወደ መካ አደረጉ።በዚያም የሀዲስ ትምህርትን ለሰባት ዓመታት ያህል ተማሩ።ከዚያው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀሊሞች (የሀይማኖት አዋቂዎች) ጋር ይገናኙ ነበርና ከእነርሱ ዘንድ ትምህርትን ቀስመዋል።ብቃታቸውን የሚያረጋግጠውንም ‹‹ኢጃዛ›› ወይም ሰርተፍኬት ተቀብለዋልም።ከዚያ ወደ አገራቸው ተመልሰው በቆቦ ‹‹ዘቡል›› ተብሎ በሚጠራ ቦታ ሄደው ያልጨረሱትን ‹‹ሸዙር አዘሃብ›› የተባለ የሰዋሰው ትምህርትን አጠናቀቁ።ይህ ሲያልቅ ግን ቀጥታ ወደ ሥራ ነው የገቡት።
ስራ ከመቀሌ እስከ አዲስ አበባ
የሥራ ጅማሮዋቸውን ያደረጉት በትግራይ ሲሆን፤ ‹‹ሀሊድ ኢብኒል ወሊድ›› በመባል በሚታወቀው መስጂድ በአሰጋጅነት ነው።መምህርም ነበሩ።ድርሰቶችንም ይጽፉ ነበር።ከዚህ በፊት የተጻፉ ታሪኮችን በማሳጠር ሰዎች በቀላሉ እንዲያነቡ ያስችሉ እንደነበር አጫውተውናል።
እንግዳችን መጽሀፍም ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል።ይህም ‹‹ ምን ሀቲል ጀዋልድ›› የሚል ሲሆን፤ አሁንም ሁለት መጽሐፍትን ጽፈው ለማሳተም በዝግጅት ላይ ናቸው።እነዚህ መጽሐፍትም ‹‹ አልእዕላም፤ አልቀዳ ቤልአልማዲ ወለሀድር›› ይሰኛሉ።ከዚያ በተጨማሪ በተለያየ ጊዜ አጫጭር ግጥሞችም ጽፈው እንደሚያውቁ ይናገራሉ።
ሸህ መሀመድአልሙባረክ ከመስጅዱ ሥራ በኋላ ወደ ‹‹ጃፈር ኢብኒ አብጣሊ የቁርአን ትምህርት›› የተባለ ድርጅት ውስጥ በዋና ጸሐፊነት ተቀጥረው የሰሩ ሲሆን፤ ሶስት ዓመትም በዚያ አገልግለዋል።ከዚያ በቀጥታ በሹመት ትግራይን ወክለው አዲስ አበባ የፌደራል ሸሪዓ ጠቅላይ ፍርድቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ማገልገላቸውን ቀጠሉ።አምስት ዓመትም በዚህ ሹመት ቆይተው ወደ ፕሬዚዳንትነት ከፍ ብለው ይሰሩ ጀመር። ከ10 ዓመት በላይ በተቋሙ የቆዩት ስራውን ስለሚወዱት መሆኑንም ይናገራሉ።
በዚህ መስሪያቤትም ከሴቶች መብት ማስከበር በተጨማሪ የተለያዩ ህጋዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አካላት መብታቸው እንዲከበር የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።በተለይ ማህበረሰብን ማገልገል ራስን ማገልገል ነው ብለው ስለሚያምኑ ምንም አይነት መድሎ ሳይኖር በተቋሙ የሚመጣ ጉዳት የደረሰበት ሰው በጊዜ ማስተናገድ ግዴታቸው እንደሆ አምነው ይሰራሉ። ይሄም እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ። በተመሳሳይ ተቋሙ በለውጥ ምዕራፍ ውስጥ እንዲጓዝ በማድረግም የተቻላቸውን ማድረጋቸውን ይናገራሉ።እንደውም ተቋሙ የራሱ ህንጻ እንዲኖረው ለማድረግ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ሶስት ሺህ ካሬ ለመረከብ ብዙ ነገሮች እንዳለቁ አጫውተውናል።
‹‹ቀሪያ››
በእስልምና እምነት እንደ ክርስቲያን የቆሎ ተማሪ ሁሉ መንደር ተዘዋውረው የዕለት ጉርሳቸውን በመለመን ትምህርት የሚማሩ ‹‹ቀሪያ›› በመባል የሚታወቁ አሉ። ሸህ መሀመድአልሙባረክ በዚህ ህይወት ካለፉት መካከል አንዱ ናቸው።በዚህ ህይወት በውሻ ተባረው፤ የሰው ፊትም ገርፏቸዋል፡፡ይሄ የትምህርቱ አንዱ ባህሪ ነውና ተወጥተውታል።ብዙ ደስታ ያለበትንም ትዝታዎች አሳልፈዋል።ከእነዚህ መካከል አንዱና በጣም የማይረሱት ከክርስቲያኖች ጋር ያሳለፉት ጊዜ ነው።
እነርሱ ማለትም ቀሪያዎቹ እና የክርስቲያን የቆሎ ተማሪዎቹ በአንድ አካባቢ ይለምናሉ።በዚህም በተለይ ክርስቲያኖቹ አርፍደው ስለሚወጡ ባዶ አቁማዳዎችን ይዘው ነው የሚመለሱት።ምክንያቱም እነ ሸህ መሀመድአልሙባረክ ሁሉንም ቤቶች አዳርሰው ወስደውታል።እናም ይህ ያሳሰባቸው እንግዳችንም አንድ ዘዴ ፈጠሩ።
አንድ ቀን ጓደኞቻቸው አልወጡም ነበር።እርሳቸው ግን በቂ ምግብ አግኝተዋል።ከርቀት መጥተው ስለነበር ደክሟቸዋል።እናም ‹‹በሉ ብሉ›› ብለው አቀረቡላቸው።‹‹አንተስ›› ሲሏቸው ‹‹እናንተ ከበላችሁና ከጠገባችሁ በኋላ እበላለሁ›› ሲሉ መለሱላቸው።ግን እነዚያ ወንድሞች ‹‹ይህማ አይሆንም አብረን መመገብ አለብን›› ሲሉ አስገደዷቸው።እንግዳችንም ‹‹ይህንን የምትሉት ለእኔ ብቻ ነው ወይስ ለሌሎቹም ነው›› ሲሉ ጠየቋቸው።እነርሱም ለሁሉም ሰው መሆኑን ገለጹ።በዚህም ሀሳባቸው መስመር እንደያዘ በማሰብ በቀጥታ ወደፈለጉት ጉዳይ ገቡ።
‹‹ አንድ ነገር ልነግራችሁ እፈልጋለሁ›› አሏቸው።እነርሱም በተመስጦ ያዳምጧቸው ጀመር። ክርስቲያን ወንድሞቻችን እንደኛ ተማሪ ናቸው።ግን እኛ በጠዋት ሁሉንም ቤት አዳርሰን ያለውን ሁሉ በመውሰዳችን እነርሱ ምንም ሳያገኙ ይገባሉ።በዚህም ጦማቸውን እንዲያድሩ ሆነዋል።እናም ለሁሉም ሰው የሚገደን ከሆነ አንድ ነገር ማድረግ አለብን።ይኸውም በአካባቢያችን 44 ቤት ስላለ ለእነርሱ የሚቀርባቸውን 22 ቤት መውሰድ አለባቸው።እኛ ደግሞ በእኛ በኩል ያለውን 22 ቤት እናዳርስና በቂያችንን እናገኛለን›› አሏቸው፡፡ይህ ሀሳባቸው በጓደኞቻቸው ተቀባይነትም አግኝቶ ወደ ትግበራው እንደተገባ ይናገራሉ።
ሸህ መሀመድአልሙባረክ ለቆሎ ተማሪዎቹ ለማስረዳት ሲሄዱ መጀመሪያ አልፈለጓቸውም ነበር።ግን ሀሳባቸውን ሲነግሯቸው እንደተደነቁ አይረሱትም።እንደውም የእነርሱ መምህር ድረስ ወስደዋቸውም ምርቃት እንደተቀበሉ አጫውተውናል።
ሌላው ከክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር የነበራቸው ቁርኝት ሚስት ሲያገቡ የነበረው ሲሆን፤ ሚዜዎቻቸውን አንዱን ሙስሊም አንዱን ክርስቲያን አድርገዋል።በእምነቱ ሚዜ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል።በዚህም እርሳቸውም ይህንን አድርገውታል።እንደውም አንዱን ከአንዱ ለይተው እንደማያዩም ይናገራሉ።ሁለቱንም ‹‹ዓይኔ›› እያሉ እንደሚጠሯቸውም ይገልጻሉ።ለዚህም ምክንያታቸው አይን ከሌለ ብዙ ነገሮች መስራት ስለማይቻል ከሁሉም አካላችን ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ።
መሀመድ አሚን የሚባለው ሙስሊሙ ሲሆን፤ አባቱ የአባታቸው ሚዜ ነበሩ።አያቱም የአያታቸው ሚዜ እንደነበሩ ከአባታቸው ሰምተዋል።ግን ሀፍቱ መሰለ የተባለው ጓደኛቸው በምንም አይገናኙም።ይሁንና የሚወዱት የልብ ጓደኛቸው በመሆኑ ሚዜ አድርገውታል።ለእርሱም ልዩ ክብር አላቸው።
በእስከዛሬው ልምድም ሆነ በአደኩበት አካባቢ ያየሁት አንዱ ለሌላው ከለላ ሲሆን ነው።ችግር ውስጥ መግባት ካለበትም ራሱን አሳልፎ ይሰጣል እንጂ ማንንም አያስነካም።ዛሬ ግን ይህ ተሸርሽሯል።ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ ማህበረሰቡ ሳይሆን ከላይ ለመኖር ብሎ የሚሰራው ለአገሩ ክብር የሌለው ነው።ስለዚህም ማህበረሰብን የሚወክል ሰው መሆን ይጠበቅበታል።የብዙሃንን ሰው ውክልና ያላቸው ሰዎች ስለ አገርም ሆነ ስለህዝብ ያስባሉ።አሁን ያለው አመራርም ያንን መሆን አለበት ይላሉ።
ህግ ሲባል ሰዎች ወደህጉ መጥተው የሚመዘኑበት እንጂ ሰው ወደህጉ ሄዶ የሚታይበት አይደለም።ሀይማኖትም ሰዎች የሚታዩበት እንደሆነ የሚያነሱት ባለታሪኩ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አማኝ ነው። በዚህም ለእምነት ቅርብ የሆነ አካል ዕምነቱ ከሚያዘው ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ ይቅርታ ማንነት ወጥቶ ጎኑ ያለውን ወንድሙን አያጠቃም።እናም አባቶቻችን ያለፉበት እርከን እኛም ማድረግ ግዴታችን ነው ባይ ናቸው።
ሙስሊም ልማት፤ ሙስሊም ፍቅር፤ ሙስሊም ከምላስና ከእጁ የተጠበቀ ነው፤ ሰዎችን የማያስቀይም ነው።ስለሆነም ይህ ነው ዛሬ ላይ መተግበር ያለበት የሚሉት ሸህ መሀመድአልሙባረክ፤ ልጆቻችን ከእኛ
የተሻለ አገር፣ ዕድገትና መልካም ነገር ማግኘት አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ያንን ሁኔታ ማመቻቸት ያለብን ዛሬ በህይወት ያለው ሰው መሆኑን ይገልጻሉ።
ህልውናው የተበላሸ፣ ስነ ምግባሩ የወደቀ፣ ከሰዋዊ ስሜት የወጣ አማኝ እንዳይፈጠር ደግሞ እያንዳንዱ ድርሻ አለውና ሁሉም በቀደመ ማንነት፤ ቂምና በቀል በሌለበት ፤ ፍቅር በበዛበት ማንነት ልጆቹን መቅረፅ አለበት ይላሉ።
ሸሪያ ፍርድቤትና ሴቶች
የሸሪያ ፍርድቤት በዋናነት ስራው መብቶች እንዳይጣሱ ማድረግ ነው። ቀደም ሲል ሸሪያ ሳይቋቋም ግን በተለምዶ ትዳር ሲፈርስ ሴት ልጅ ትንሽ ብር ተሰጥቷት ትሰናበታለች።ነገር ግን በቁርዓን ላይ እንደተቀመጠው ሴት ልጅ የግራ ጎን ፣ የራስ ክፋይ ነች።ስለዚህም ማንኛውም ሰው የሚያደርገውን ነገር ማድረግ ትችላለች።ሙፍቲ እስከመሆንም እድል ይሰጣታል።በመሆኑም በሸሪያ ፍርድቤትም ይህ ተግባራዊ መሆን ይገባዋል።በአሁኑ ወቅት ሴቶች በትግራይ፤ በአፋርና በሱማሌ ትልልቅ ቦታዎች ላይ ደርሰዋል።
የነብዩ መሀመድ ባለቤት እናታችን አይሻ ብዙ ነገር ከነብያችን ወስዳለች።ለእርሳቸውም ቢሆን የእውቀታቸው ምንጭ እንደነበረች ይገለጻል።ከእርሷ ብዙ ነገር ውሰዱ ማለታቸውም እሙን ነው።ስለዚህም ሴቶች በእምነቱ ልዩ ቦታ የሚሰጣቸውና መብታቸው የተከበረ መሆኑን ያረጋግጣል።በዚህም ፍርድቤቱም የተለያየ ስራ እየተሰራ መሆኑን አጫውተውናል።
ረመዳን እና ኮሮና
ረመዳን በሙስሊሙ ህብረተሰብ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ትልቅ ጊዜ ነው። ቁርአን የወረደበት፣ ፈጣሪ ለምህረት ባሪያዎቹን ዕድል የሚሰጥበት ትልቅ የእርቅና የምህረት ጊዜ ነው።በይቅርታ፣ ከሰዎች ጋርም ሆነ ከፈጣሪ ጋር ባለ ግንኙነት ውዴታ የምንከጅልበት ትልቅ ጊዜ ነው።በተለይም የመጨረሻዎቹ 10 ቀናቶች የተለዩ ጊዜያቶች ናቸው።በውስጡ ‹‹ለይለት አልቀድር›› የሚባለውን የያዘ ከአንድ ሺ ወራቶች በላይ የሆነች አንዲት ሌሊት አለች ትባላለች።ያቺ ቁርአን የወረደባት ዕለት ናት።በእዛ ቀን የሚሰራ በጎ ስራ ከ 83 ዕድሜ በላይ እንደሰራ ይቆጠራል ይባላል።እናም በጣም ዕጥፍ ድርብ ምንዳ፣ ዋጋ የሚሰጥበት ጊዜ ነውና ይህንን ለማግኘት ሁሉም ይረባረባል። እናም ይህ ወቅት ለእምነቱ ተከታዮች ትልቅ በረከት የምናፍስበት ነው ይላሉ።
በጾም የሚገኝ በረከት የሚታይና ከሰው መልስ የሚጠበቅበት አይደለም።በመስጠት የበለጠ የሚገኝበት ነው።ሳይታይ አላህን እየፈራና እርሱ በረከቱን ያበዛልኛል ብሎ ማድረግ ያለበት ነው።ስለዚህም የኮሮና መምጣት ብዙዎችን ረድተን የበረከቱ ተካፋይ እንዲሆን የሚያስችለን ነው ።
ረመዳን ለኮሮና መፍትሄ ሰጪ ይሆናል።ምክንያቱም በረመዳን ወቅት የሚደረግ ምጽዋት ልዩ በረከት አለው።እንደራሱ አድርጎ ሌሎችን ማገዝ ያለበት በመሆኑ ባደረገው ልክ ይደረግለታል ተብሎ ስለሚታመን ይህንን ሁሉም ያደርጋል። ብቻውን የሚያፈጥር አንድም ሰው አይኖርም ። ስለዚህ ይህንን ጾም ችግረኛ ሳይሰማው በደስታ ይጾመዋል።ይሁንና ይሄ ወቅት የረመዳንን አብሮነት ቀይሮታል።
በጋራ ማፍጠር አይቻልም።ግን ብዙ አማራጮች አሉና እነርሱን በመጠቀም ሰዎችን ማገዝና የበተረከቱ
ተሳታፊ መሆን እንደሚገባ የሚያወሱት ባለታሪኩ፤ በባንክ አካውንታቸው ለማፍጠሪያ የሚሆን ገንዘብ በማስገባት፤ ያም ካልተቻለ ካለ ላይ ቀንሶ በማድረስ ማገዝ ይቻላል።መስጠት በሽታን ማምጣት ስላልሆነ ይህንን በማድረግ ጊዜውን መዋጀት እንደሚገባ ይመክራሉ።
ጊዜው መረዳዳትን ይበልጥ የሚፈልግበት ነው።ከዚህ ቀደም ሰው ተሯሩጦ የቀን ጉርሱን ይሞላል፤ ሳይበላ አያድርም።አሁን ግን በልቶ የማያድረው ብዙ ነው።ለመስራት የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯልና።በሽታውን በመፍራት ረሀብ ከሚገለኝ በልቼ ልሙት በሚል ስሜት እየፈራ የሚሰራው ብዙ ነው።በተለይ ተላልኮና ተሸክሞ ኑሮውን የሚያሸንፍን ሰው በዚህ በሽታ ክፉኛ እየተጎዳ በመሆኑ ችግረኞችን ማገዝ የእኛ የረመዳን ጾም ባለቤቶች ትልቅ ሀላፊነት ነው ይላሉ።
ሁሉም ሰው ንክኪ እንዳይኖር ስለሚፈልግ በራሱ ማድረግ ጀምሯል።እናም ረመዳን ለዚህ ሁሉ መፍትሄ ሰጪ መሆን ይችላልና ዛሬን እንዲሻገሩ ማገዝ አለብን።
ስለበሽታው ሁለት ነገሮችን ማንሳት እፈልጋለሁ የሚሉት እንግዳችን፤ እንዲህ አይነት መቅሰፍቶች አንድም ለትምህርት ሌላውም ለመቅሰፍት ይመጣሉ።በዚህም መጀመሪያ ራሳችንን ቆም ብለን እንድናይ ያስፈልጋል። ከመጥፎ ስራችን መታረም አለብን።በይቅርታ ሁላችንም መታጠብ ይጠበቅብናል።ሌላው በቤት እንድንቀመጥ የሚያደርግ በመሆኑ ተተኪው ትውልድ በስነምግባር እንዲያድግና ቤተሰቡን በተለያየ መንገድ ማገዝ እንዲቻልም በር ይከፍታል።እንዲሁም በቤት ውስጥ ለመቆየት ጊዜ ስላገኘን ይሄንኑ ጊዜ ለመልካም ነገር መጠቀም ይገባል ይላሉ።
‹‹ጥሩ ነገር መስራት እድሜን ያረዝማል፤ ከመጥፎ ውድቀትም ይታደጋል፤ ነብያችንን በተግባራቸው እንድንከተል ያደርገናል።እኔም በዚህ የበረከት ጾም ካለኝ ላይ ለተቸገሩ በማካፈልና እንዲያፈጥሩ በማድረግ እያገዝኩ ነኝ።ከዚያ ባሻገር ልጆቼንና የአካባቢውን ልጆች በመምከር እያሳለፍኩ ነው›› ብለውናል።
መልዕክተ መሀመድ
‹‹ጀግንነት ያለፈ ታሪክን በማውራትና በማወደስ ብቻ አይሆንም። የአባቶቻችንን ታሪክ ማንሳቱ ብቻ አይጠቅምም። የአሁኑ ትውልድ ታሪክ መስራት ይጠበቅበታል።ይህንን ደግሞ እውን ለማድረግ በጋራ መጣር ያስፈልጋል።›› የሚሉት እንግዳችን፤ ወቅቱ ሌሎችን የምናስብበት፣የሌሎችን ችግር የምንካፈልበት፣ለተራቡ የምንደርስበት፣ለታረዙ የምናለብስበት ጊዜ ነው። እናም በጾማችን በረከቱን ለማግኘት የተራቡትን ማብላት፣ የታረዙትን ማልበስና የተቸገሩትን ከደረሰባቸው መከራ ማውጣት ይገባናል ።
በኢትዮጵያ ነጃሺን የተቀበሉት እስላም ክርስቲያን ሳይሉ ነው።አዲስ ሀይማኖት ይዘው መጥተው አትግቡ አልተባሉም።እንዳውም ደስ ያለህን አድርግ ነው የተባሉት።ግን እስላሙን እስላም ቢቀበለው ምንም የሚደንቅ ነገር አይኖርም።
የአባቶቻችንን እንከተል ሲባል ሰውን በሰውነቱ ተቀብለን እናስተናግድ ነውና ይህንን ማድረግ ይገባናል። አንተ ከዚህ ከዚያ መባባል ለማንም አይበጅም።ይህ ደግሞ በአላህ ዘንድ ትልቅ ዋጋ አለውና ይህንን ሀይማኖታዊ ትምህርት ማስቀጠል ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አጋርተዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው