ባሳለፍነው ሳምንት የኪነ ጥበብ አምዳችን ላይ ቲያትር ቤቶች በወቅታዊው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት እያጋጠማቸው ስላለ ፈተና አንስተን ዳሰሳ መስራታችን ይታወሳል። ከተፅዕኖው ባሻገር የደረሰባቸውን ጉዳት በተለያዩ አስረጂ ሁኔታዎች ላይ ተመርኩዘን እውነታዎቹን ወደ አንባቢዎቻችን አድርሰናል።
ከችግሮቹ ባሻገር እነዚህ የጥበብ ስፍራዎች በችግሮች ጊዜ ምን አይነት መውጫ ቀዳዳ ሊያበጁ ይገባል ስለሚለው ጉዳይም ከጋበዝናቸው እንግዶች አስተያየቶችን በመቀበል ለማመላከት ሞክረናን። በዛሬው ርእሰ ጉዳያችን በዚሁ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ላይ በተለየ መልኩ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የስነ ፅሁፍ፣ የግጥም፣ የዲስኩርና ሌሎች መሰል ምሽቶች እየደረሰባቸው ያለውን ተፅዕኖና ተመሳሳይ የማገገሚያ ስልት መፍትሄዎች ላይ በተመሳሳይ አተኩረን አንዳንድ ሃሳቦችን ወደእናንተ ለማቀበል ወደናል።
ጥቂት መነሻ
የሰውን ልጅ የስልጣኔና የዘመናዊነት ግስጋሴ በየጊዜው ለመገደብ የሚሞክሩ አጋጣሚዎች በተለያዩ ጊዜያቶች ይከሰታሉ። ከእነዚህ መካከል የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ረሃብ፣ የተፈጥሮ አደጋ (ጎርፍ፣የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ድርቅ)፣ ጦርነት ጨምሮ ሌሎችም በምሳሌነት ይነሳሉ። ከሁሉም በከፋ ሁኔታ ግን እንደ ተዛማች በሽታ የዚህን ሰብአዊ ፍጡር ህልውና እየተፈታተነ የሚገኝ አይመስልም። ዓለም አቀፍ ወረርሽኝና ቫይረስ የመኖር ህልውናውን በተደጋጋሚ ፈትኖታል።
ህልውናው ላይ ጥፋት የሚቃጡ ቫይረሶችን በተሰጠው ጥበብ ተመራምሮ መድሃኒት ከማግኘት ጀምሮ ክፉውን ዘመን አጎንብሶ ስነ ልቦናውን አደድሮ የሚያልፍበት መላ ከመዘየድ ወደ ኋላ አላለም። ይህ ጥረቱ እዚህ ቢያደርሰውም ተፈጥሮ ደግሞ ተመሳሳይ ፈተናዎችን ከማምጣት አትቦዝንም። ለዚህም ይመስላል አሁንም ዓለምን በአንድ ከረጢት ውስጥ ከትቶ ከወዲህ ወዲያ የሚያላጋ አዲስ ፈተና የገጠመን።
የስነ ፅሁፍ ምሽቶቹ ፋይዳና ወቅታዊ ፈተና
በትንሹ ላለፉት አስር ዓመታት ያህል በመላው ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ የስነ ፅሁፍ ምሽቶች እንደ አማራጭ በስፋት ሲቀርቡ አስተውለናል። በቲያትር ቤቶች፣ ታዋቂ አዳራሾች፣ በምቹ የመዝናኛ ስፍራዎችና በመገናኛ ብዙሃን አማራጮች ለጥበብ ቤተሰቡ በስፋት ሲቀርቡ ቆይተዋል።
ስነ ፅሁፍ፤ በተለይ ደግሞ ግጥም፣ መነባነብ፣ የተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዲስኩር እንዲሁም በአንድ ሰው የሚሰሩ ቲያትሮች ይቀርባሉ። እነዚህ ስራዎች እንደየ አዘጋጆቹ በተለያየ ስልት ከሙዚቃ ጋር በማዋሃድ የሚቀርቡና የጥበብ አፍቃሪውን ጥም እንዲቆርጡ በጥንቃቄ ተቀምመው የሚዘጋጁ ናቸው። ግጥምን በጃዝ፣ በክራር አዋህደው የተለየ ስልትና የሚፈጥሩና ተከታዮቻቸውን ያበዙ በርካታ ምሽቶች በዋና ከተማዋ አዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች ላይ ይካሄዳሉ።
በእነዚህ መድረኮች ላይ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዘርፈ ብዙ ርእሰ ጉዳዮች ያለምንም ገደብና ስስት በጥበብ ተለውሰው፣ አምረውና ተከሽነው ወደየሰዉ አይንና ጆሮ እንዲደርሱ ይደረጋል። ታዲያ በእነዚህ ስፍራዎች በአካል በርካታ ታዳሚያን ተገኝተው ስራዎቹን ኮምኩመው የልባቸው ደርሶ ሲመለሱ ይስተዋላል። በጠባብ አዳራሽ ውስጥ በአካል ተገኝተው ስራዎቹን ከሚታደሙት አፍቃሪያን ባሻገር በመገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ ድረ ገፆች አማራጭ የሚወዱትን መርጠው የሚከታተሉም ሚሊየኖች ተፈጥረዋል።
አሁን ላይ የከተሞችን ምሽት በተለየ የመዝናኛና የቁምነገር ምሽቶች የሚያደምቁ ዝግጅቶች እንደሌሎቹ በርካታ ዘርፎች ወቅታዊ ፈተና ተደቅኖባቸዋል። በመገናኛ ብዙሃን አማራጭ ከሚቀርቡት ባሻገር በአዳራሾች ውስጥ በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚያን የሚገኙባቸው መድረኮች ሙሉ ለሙሉ ተቋርጠዋል። ለዓለም ህዝብ ድንገት መከራን የደቀነው ማእበል የስነ ፅሁፍ ምሽት ቤቶችን ደጃፍ እንዲዘጉ አስገድዷል። ቀድሞውንም
በፖለቲካዊ ጫና ከእይታ እንዲርቁ ሲገደዱ የነበሩ በቋፍ ላይ የነበሩ መድረኮች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ጠንካራ ክንዱን ሰንዝሮባቸዋል። ከእይታም ተሸሽገዋል።
ጥበባዊ ስራዎችና የስነ ፅሁፍ ምሽቶች ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው በተግባር ተፈትነው አረጋግጠዋል። በተለይ ይህን መሰል ማህበራዊ ቀውስ ሲከሰት የሚከሰተውን ስነልቦናዊ ጫና ለመቋቋም አስፈላጊ መሆናቸውም ይታመናል። ነገር ግን እነዚህን ምሽቶች የሚያስተናግዱ አዘጋጆች ጉዳዩ በድንገት ከመከሰቱ አኳያ የተለየ አማራጭ የመውጫ ቀዳዳዎችን ያዘጋጁ አይመስሉም። አስፈላጊነታቸው በበረታበት ወቅት ከእይታ ተሰውረዋል። ይሄ አጋጣሚ ቀድሞውንም በጠንካራ መሰረት ላይ ላለመጣላቸው ማሳያው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ደግሞ የሰው መሰባሰብ የሚጠላው ወረርሽኝ ሲከሰት አዲስ ስልት ነድፈው ወደማህበረሰቡ አይንና ጆሮ የሚደርሱበትን አማራጭ አለማበጀታቸው ነው።
ለመሆኑ እነዚህ በምሽት በተለያዩ አዳራሾች ይካሄዱ የነበሩ የስነ ፅሁፍ፣ የግጥም እንዲሁም የዲስኩር ምሽቶች ለምን ወቅታዊውን ወረርሽኝ መቋቋም አቃታቸው? በምን አይነት አቋምና የስነ ልቦና ዝግጅት ላይ ይገኛሉ? በቅርብ ጊዜ ውስጥ አማራጭ ስልቶችን ነድፈው የመመለስ እድላቸውስ ምን ይመስላል? እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን ለመመለስ የዝግጅት ክፍላችን በአዲስ አበባ ከተማ ታላላቅ አዳራሾች ውስጥ የሚሰናዱና ተወዳጅ የነበሩትን የኢትዮ ግጥምን በጃዝና ብራና የስነ ጽሑፍ ምሽትን መርጦ ከአዘጋጆቹ ጋር ለመወያየት ችሏል። እነርሱም ወቅታዊው ፈተና ያደረሰባቸውን ችግሮችና በቅርቡ ወደ ማህበረሰቡ ለመድረስ ያሰቡበትን አማራጭ ስልቶች ከዚህ እንደሚከተለው ለማስቀመጥ ሞክረዋል።
ግጥምን በጃዝ
ወደ መድረክ ከመጣ ስምንት ዓመታትን አስቆጥሯል። እስካሁን ሳይቆራረጥ በወር አንድ ጊዜ የሚቀርብ ተወዳጅ የስነ ጽሑፍ ምሽት ነው። ግጥም፣ ዲስኩርና ለየት ያሉ አጫጭር የመድረክ ላይ ቲያትሮችን በማቅረብ ይታወቃል ጦቢያ ግጥም በጃዝ።
ገጣሚና ደራሲ ምስራቅ ተረፈ የመሰናዶው አዘጋጅና ባለቤት ነች። ይህ የስነ ጽሑፍ ምሽት ያደረገው ‹‹ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማድመቅ›› በሚል መርህ ተመስርቶ መሆኑን ትናገራለች። በሂደቱ በርካታ ገጣሚያንና የስነ ጽሑፍ ተሰጦ ያላቸው ወጣቶች የሚፈሩበትና ስራዎቻቸው ታትሞ ለአንባቢያን እንዲደርስ በር የሚከፈትበት መሆኑንም ታነሳለች። አሁን ለተፈጠረው የስነ ጽሑፍ መነቃቃት ድርሻው ላቅ ያለ እንደሆነም ትገልፃለች።
ገጣሚ ምስራቅ አሁን ላይ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ተከትሉ በመድረክ የሚቀርቡ ዝግጅቶች ሙሉ ለሙሉ መቋረጣቸውን ትናገራለች። ይህ ደግሞ የጎላ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል። ዝግጅቶቹ በስፖንሰር አድራጊዎችና ከተመልካች በሚገኝ ገቢ የሚታገዙ ነበሩ። ይህ ገቢ ሙሉ ለሙሉ በመቋረጡ የተነሳ ለገጣሚዎች፣ደራሲዎችና መሰል አስፈላጊ ጉዳዮች የሚፈፀም ክፍያ ላይ እንቅፋት መፍጠሩንም ታነሳለች።
‹‹አሁን አብዛኛው ሰው ቤቱ ተቀምጦ ነው ያለው። በዚህ ሰዓት ደግሞ የኪነ ጥበብ ዘርፉ ትልቅ ስራ መስራት ይጠበቅበታል›› የምትለው ገጣሚ ምስራቅ ፤ በተለይ በማህበረሰቡ ውስጥ በወረርሽኙ ምክንያት የሚፈጠርን የስነ ልቦና ጫና ለመቀነስ ጥበብ ድርሻው ከፍ ያለ መሆኑን ታነሳለች። በባዶ አዳራሽና በመገናኛ ብዙሃን አማራጭ በአዲስ መልክ ተቀርፆ ለማህበረሰቡ የቀደሙትን አይነት ስራዎች መቅረብ መውጫ መፍትሄ መሆኑንም ታነሳለች። ይህን ለማድረግ ግን የሚመለከታቸው አካላት የስነ ጽሑፍ ምሽት አቅራቢዎች ጋር በጋራ መስራት እንደሚኖርባቸው ትጠቁማለች። ችግሩ የጋራ በመሆኑ በጋራ መፍትሄ ማምጣት ደግሞ ብቸኛው አማራጭ መሆኑንም ታነሳለች።
‹‹በእስከዛሬው ልምድ የጥበቡ ዓለም ተነጥሎ እንዳለ ይሰማኛል›› የምትለው ገጣሚ ምስራቅ፤ በመንግስትም ሆነ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ
መሆኑን ትናገራለች። እንኳን አሁን በጋራ ‹‹ችግራችንን እንወጣ አብረን እንስራ›› ተብሎ በጎ ምላሽ ለማግኘት ይቅርና ከዚህ ቀደም በጥበቡ ዘርፍ ለፈጠሩት ከፍተኛ መነቃቃት አይዟችሁ የሚል ማበረታቻ ከመንግስት እንዳላገኙም ታነሳለች። ይህ ከወቅታዊው ጉዳይ ጋር ተደምሮ ተፅዕኖውን እንደሚያበረታው ትገልፃለች። የተሳሳተ አመለካከት በመሆኑም መቅረት ይገባዋል ትላለች። ጥበብን መደገፍ ከተቻለ ማንኛውንም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ወቅታዊ ምስቅልቅል ማሸነፍ ይቻላል የሚል እምነት አላት።
ጥበብ ካልታከለበት ማህበረሰብን ሐኪም ቤት ገንብቶ ብቻ ማከም ለውጥ አያመጣም የምትለው ገጣሚ ምስራቅ፤ በጥበብ የተሸፈነ ማህበረሰብ የጠንካራ ስነልቦና ባለቤት፣ጤናውን የሚጠብቅና ለትውልድ የሚያስብ፣ አገሩን የሚወድና የሚጠብቅ ባለ ራዕይ መሆኑን ታነሳለች። ይህ እንዲሆን መሰል ዝግጅቶችና መድረኮች መደገፍ እንዳለበት በጠንካራ አመክንዮ አስደግፋ ጥሪ ታቀርባለች።
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያኖች ብዙ ፈተናና መከራዎችን አሸንፈናል›› በማለትም አሁን የተከሰተውን ችግርም በጋራ ማሸነፍ የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ ታነሳለች። ዓለም በሽታውን ለማጥፋት ብቻ ሲረባረብ ኢትዮጵያኖች ደግሞ ድርብ ፈተና አለብን ትላለች። አባይን ገድቦ በረከቱን እንበላ ዘንድ እራሳችንን ከወቅታዊው ወረርሽኝ መጠበቅ አልብን ስትል በጠንካራ መልክት ሃሳቧን ትቋጫለች።
ብራና የኪነጥበብ ምሽት
ላለፉት ሁለት ዓመታት በወር አንድ ጊዜ በብሄራዊ ቲያትር የሚዘጋጅ መርሃ ግብር ነው። በዚህ መርሃ ግብር ላይ ዲስኩሮች ወጎች እንዲሁም ሌሎች የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ይቀርቡበታል። የዚህ ዝግጅት መሰናዶን የሚመራው ጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ ይባላል።
ጋዜጠኛ በፍቃዱ እንደሚለው በእያንዳንዱ ዝግጅት ላይ አነሰ ሲባል 600 መቶ ሰው ሲገኝ ከፍተኛው ደግሞ እስከ 1 ሺህ 200 ሰው ይደርሳል። አሁን ላይ በወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ዝግጅቶቹን ለጥበብ አፍቃሪው ማህበረሰብ ማቅረብ እንዳልተቻለ ይናገራል።
‹‹በአሁኑ ወቅት በኪነጥበብ ምሽቶች ላይ የተፈጠረውን ተፅዕኖ በሁለት መልኩ ነው የማየው›› የሚለው የብራና ኪነጥበብ ምሽት አዘጋጅ ጋዜጠኛ በፍቃዱ የመጀመሪያው የስነልቦና ጉዳት ነው፤ ማህበረሰቡ ከጥበብ የሚያገኘውን የአዕምሮ ምግብ እንዲያጣ ተደርጓል ይላል። አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ይቅርታን የሚሰብኩ፣ የሚያዝናኑና ቁምነገር ያዘሉ ጥበባዊ ስራዎችን በጋራ ማህበረሰቡ እንዳይታደም
እንቅፋት መፍጠሩን ይናገራል።
ሁለተኛው ተፅእኖ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ መሆኑን አንስቶ ስራዬ ብለው በነዚህ ዝግጅቶች ላይ እቅድ በማውጣት ስራቸውን የሚያከናውኑ የበርካታ ቡድኖችና ግለሰቦች የገቢ ምንጭ መድረቁን ይናገራል። ከዚህ በተጨማሪ የጥበብ ዘርፉን ለማበረታታት ድጋፋቸውን የሚያደርጉ ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች ወቅቱ ይዞት የመጣውን ማእበል ተከትሎ ድጋፋቸውን ማቆማቸው ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ማስከተሉን ይናገራል።
‹‹የኪነ ጥበብ ምሽት መድረኮቹ ጠንካራ ማህበራዊ ግንኙነት የሚመሰረትባቸው ነበሩ›› የሚለው የብራና ኪነጥበብ ምሽት አዘጋጅ፤ የአልኮል መጠጥን ጨምሮ ሌሎች የመዝናኛ አማራጮች በተለየ መንገድ በርካታ የጥበብ ቤተሰቦች ከፍተኛ ማህበራዊ ትስስር ይፈጥሩበት እንደነበር ይናገራል። አሁን ላይ የኮሮና ወረርሽኝ ይሄን ድልድይ እንደሰበረው በመናገርም ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ መፍጠሩን ይናገራል።
‹‹የበሽታው ትልቁ ጠላቱ የሰዎች መሰብሰብ፤ የሰዎች በጋራ መሆን ነው›› የሚለው ጋዜጠኛ በፍቃዱ፤ ይህ ክፉ ጊዜ እስኪያልፍ ለማህበረሰቡ የአእምሮ ምግብ የሆነውም የጥበብ ስራዎች በተሻለ አማራጭ ለማቅረብ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን ይናገራል። በዚህም የዲጂታል መልቲ ሚዲያ (ማህበራዊ ሚዲያውን) በመጠቀም በከተማና ከተማ ቀመስ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ለመድረስ ስልት ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው። ከቀናቶች በፊት አንድ ሙከራ በማድረግም ከአንዳፍታና ሶደሬ ቲዩብ ጋር በመቀናጀት ጥንቃቄ የተሞላበት የዲስኩር መሰናዶ አዘጋጅተው እንደነበር አንስቷል። በቅርቡም በተጠናከረ መልኩ በዲጂታል አማራጮች ጥበባዊ ስራዎችን እንደሚያቀርብ በማንሳት ሃሳቡን ቋጭቷል።
ሲጠቃለል
ጊዜው ከየትኛውም ወቅት በተለየ መተባበር፣ መደጋገፍ፣ መተሳሰብ በጥቅሉ አንድነትን የሚጠይቅ ነው። ምንም እንኳን የመዝናኛና የኪነ ጥበብ ዘርፉ በተመሳሳይ የዚህ ተፅዕኖ ዳፋ ቀማሽ ቢሆንም በበጎነትና ትብብር ለመስበክ እና አደጋውን ለመመከት ድርሻው ላቅ ያለ ነው። በመሆኑም የደረሰበትን ጠንካራ ቡጢ በመቋቋም ከችግሩ ለመውጣት የሚደረገውን ርብርብ በሙሉ ልብ መቀላቀል ይኖርበታል።
ቀደም ባሉ ጊዜያት በተግባር ያየነውም ይሄንኑ ነው። በመሆኑም የኪነ ጥበብ ምሽት አዘጋጆች ችግራቸውን ዋጥ አድርገው፣ ትከሻቸውን አደድረው ፈተናውን መዋጋት፤ እራሳቸውንም ሆነ ማህበረሰባቸውን ከማቅ ውስጥ ለማውጣት በወኔ መስራት ይኖርባቸዋል መልዕክታችን ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2012
ዳግም ከበደ
የስነ ጽሁፍ ምሽቶችና መውጫ ቀዳዳ