ያሳረፈ መርዶ
(ክፍል ሁለት)
ባልና ሚስት በሀሳብ በመናወዝ ላይ ሳሉ ነበር ልጃቸው በመሀል ገብታ ያነቀቻቸው። እራት በልተው ሮዛ ልጇን ወደ መኝታ አስገብታ ካስተኛቻት በኋላ ከኤሊያስ ጋር ተያይዘው ወደ መኝታ ቤት ገቡ።ድርጊታቸው አንድ ይሁን እንጂ በመሀላቸው ምንም አይነት የሀሳብ ልውውጥ የለም። ሁለቱም በሀሳብ ጭልጥ ብለው ወደ መኝታቸው አምርተው በሀሳብ የዛለ ሰውነታቸውን ብርድ ልብስ ውስጥ ተሸጎጡ። ሁኔታቸውን ላየ እነዚያ በፍቅር ልዩ ደስታን አንዳቸው ላንዳቸው የሚፈጥሩ ምርጥ ባልና ሚስት ፈፅሞ አይመስሉም።አንዳች ነገር ከመሀላቸው ገብቶ ትልቅ ጸብ ውስጥ የገቡ እንጂ ውስጣቸው ባለ የሀሳብ ነውጥ አንደበታቸው መቆለፉን ማንስ ሊገባው ይችላል።
ኤሊያስ፡-“ውዴ” በሚል የዘወትር ጥሪው ዝምታውን ሰበረው። ሮዛን በስምዋ ጠርቷት አያውቅም።
ሮዛ፡- “ወዬ” ከነበረችበት አንዱ የአልጋው ጫፍ ወደ ኤሊያስ ተጠግታ ደረቱ ላይ ልጥፍ ብላ በስስት አይን አይኑን እያየች ለጥሪው ምላሽ ሰጠች።
ኤሊያስ፡- “ዛሬ በላይን አውርቼዋለው ምን አልባትም በዚህ ሳምንት መጨረሻ የህክምናውን ለመሸፈን የሚያስችል ብር ሊሰጠኝ እንደሚችል ቃል ገብቶልኛል። ፈጣሪ ከረዳን ልጃችን ድኖ ደስታችን ይመለስ ይሆናል።”
ሮዛ፡- “ለምን የኔ ፍቅር እንዲህ አይነት ጥሩ ወሬ እያለ ያልነገርከኝ…ጥሩ ዜና እኮ ነው የኔ ጌታ…..” አንገትዋን ቀና አድርጋ በንቃት የኤሊያስን አይን አይን ማየት ጀመረች።
ኤሊያስ፡- “ ሰውየው ብር ላይ ያለውን አቋም ታውቂ የለ። እርግጠኛ መሆን እኮ ይቸግራል። ፈጣሪ ያራራልኝ
እንጂ …እንጃ እውነት መሆኑ… ሰውየው እንደሆን ብር ደም ስሩ ነው”
ሮዛ፡- “ እባክህ መልካም እንመኝ”
ኤሊያስ፡- “እሺ ውዴ እሺ..” ከዚህ በኋላ ቃል
አልተለዋወጡም። ለሳምንት ያህል በቁም አይንን ከመክደን በቀር እረፍት የማያውቀው አካላቸው ለማሳረፍ ነው ዛሬ ሰራተኛቸውና የሮዛ እህት ሆስፒታል አሳድረው ነው እቤት የመጡት። የኤሊያስ አይን ጣራው ላይ የሮዛ አይኖች ደረቱን ተንተርሳ ግድግዳው ላይ ተተክልው ሌላ ብዙ ትካዜ ሌላ ብዙ ሀሳብ ውስጥ ወደ መዘፈቅ ገብተዋል።
ሮዛ፤ በላይ ለልጃቸው ብር ለመስጠት ማቀዱ ሀሳብ ለውጦ ልብ ገዝቶ ይሆናል የሚል ተስፋ በልብዋ አድሯል። በመጠኑም ቢሆን ጭንቀትዋ ቀሎላታል። አሁን ጸሎት ላይ
ናት። ሁሉም ነገር ተሳክቶ ልጅዋ ታክሞ ድኖ በግሩ ሲሮጥ እንዲያሳያት አምላክዋን በብርቱ መማጸን ጀምራለች፤ በልብዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ለምታመልከው ተማጽኖዋን እያቀረበች ነው።
ኤሊያስ የራሱን የሀሳብ ድር ያደራል ልጁን ሊያድንለት የሚችል ገንዘብ ከበላይ ካላገኘ ሌላ ማግኛ መንገድ ይቀምራል፤ ምንም ውል ባይልለትም። በላይን አያምነውም ምክንያቱም ብር አብዝቶ እንደሚወድ ያውቃል። ኤሊያስ በላይን እጅግ ይወደዋል ከገንዘብ ፍቅሩ ውጪ ሁሉ ነገሩን ይወድለታል። በላይ እሱን ለመርዳት የተፈጠረ ሰው መሆኑን ነው የሚያውቀው።
በላይ እሱንና ቤተሰቡን የሚንከባከብ ጻዲቅ፤ገመና ከታቹ እንጂ ቤተሰቡ የሚያፈርስ ሰይጣን መሆኑ የሚያጠራጥር ምንም ነገር አስተውሎበት አያውቅም። አሊያስ በላይ ለብር ያለው ፍቅር ያህል ባይሆንም እሱና ቤተሰቡን እንደሚወድለት ነው የሚያውቀው። ብቻ በጥርጥር ውስጥም ሆኖ ብሩን ሊሰጠው እንደሚችል ተስፋ አድርጓል።
አማራጭ ላጣ ሰው ተስፋው ቃል ነውና አምኗል።ተስፈኛው አምላኩ እንድያሳካለት በተስፋ ተሞልቶ መሻቱ እንዲሳካ ከልቡ ተማጽኖ ከማድረግ በቀር። በተስፋ የተባለውን ከመጠበቅ በቀር። መብራቱን በእጁ አጥፍቶ ጨለማው ላይ አፍጦ ተክዟል። ሮዛም በሌላ አቅጣጫ ተመሳሳይ ጭለማ ላይ አፍጣ ታስባለች።
አዲስ አበባ መልከ ብዙ አይደለች፤ እዚያ ሲጨልም በር ሲዘጋ እዚህ ደግሞ በር ተከፍቶ መብራቶች ይፈካሉ። አንዱ ክፍልዋ በእግዜር ውሀ ጥማት ሰዎችዋን አድክማ በሌላ ክፍልዋ ውስኪ የምታራጭ ተዓምረኛ ከተማ። እዚያና እዚህ የተለያየ ሁለት መልክ።
እዚህ መሸታ ቤት ውስጥ መደማመጥ የለም። የጆሮን ታንቡር የሚበጥስ የሙዚቃ ጩኸት በአንድ ክፍል በተሰቀሉ በአራት ትልልቅ ድምጽ ማጉያዎች ቤቱ ይንቀጠቀጣል።ገና ከውጭ ሲገባ ሲኦል ውስጥ የገቡ ያህል በሰው አስትንፋስ የነደደው አየር በር ላይ ይጋረፋል። ሰዎች ጤና እንዳጡ ሁሉ ስልቱ ባልታወቀ እንቅስቃሴ የተለያየ ክብ ሰርተው እጃቸው በማወራጨት ያለ ስልት ይወዛወዛሉ፤ ይዘላሉ፤አንዳንዴም ይደንሳሉ።
እዚህ በመጠጡ ብቻ ሳይሆን ተደበላልቆ አየሩን በተሞላው የመጠጥ ሽታ እና ታምቡር በሚበጥሰው ሙዚቃ ይሰከራል። ክፍሉ ውስጥ የሰከሩ ሰዎች መወላገድን አይቶ
ስልት የሌለው ጭፈራ ይሁን እስክስታ ተመልክቶ ያልጠጣም ተጋብቶበት ይወላገዳል።
በላይ አንዱ ጥግ ብላክ ሌብል ውስኪ በብርጭቆ እየቀዳ አንዳንዴም እያስቀዳ እግሩን አነባብሮ አጠገቡ ከተቀመጠች እንዲሁ ለበስኩ ለማለት ብቻ ሁለት የልብስ ቅዳጆች የሰውነት ክፍልዋ ላይ ጣል ካደረገች ሴት ጋር በማያስቅ ሳቅ ይንከተከታሉ።
በላይ በአንዱ ጥግ ብላክ ሌብል ውስኪ በብርጭቆ እየቀዳ አንዳንዴም እያስቀዳ እግሩን አነባብሮ አጠገቡ ከተቀመጠች እንዲሁ ለበስኩ ለማለት ብቻ ሁለት የልብስ ቅዳጆች የሰውነት ክፍልዋ ላይ ጣል ካደረገች ልጅ ጋር በማያስቅ ሳቅ ይንከተከታሉ። ስልኩ ደጋግሞ ይጠራል። እሱም ደግሞ ጥሪውን በመዝጋት ወደ ኪሱ ይመልሳል።
ልጅትዋ “ለምን አታነሳውም? ማን ነው?” ሁኔታውን ሲደጋግም ተመልክታ ጠየቀቸው።
በላይ “አሮጊቷ ናት ትጨቃጨቃለች…የት ሄድክ ? ለምን አትመጣም? መሽቷል? የሚሉ ጥያቄና ንትርክ ሰልችቶኝ መሰለኝ እዚህ የተገኘሁት። አንችን ከመሰለች ጽጌሬዳ አበባ ጋር ሆኜ የአሮጊት ንትርክ ልስማ? ሀይይ ሰለቸኝ አቦ ዝም ብለሽ ቅጂ፤አንቺም ጠጪ ሃሃሃሃሃሃሃሃ…ቂቂቂቂቂቂቀ” ሳቅ ተቀባበሉ። ልጅትዋ የስካር ጅማሮ ላይ ብትሆንም በላይ ሞቅታ ላይ ደርሷል።
ልጅቷ፡ “ከሰለቸችህ ለምን አትፈታትም ? እኔን ታገባኛለህ ቂቂቂቂቂቂቂ”
በላይ “መፍታት.. ኖኖ ልጆቼን ታሳድግ አልፈታም በእርግጥ አልወዳትም። ሳልወዳትም ነው ያገባዋት።የወደድኳት ልጅ ጓደኛዬ ቀማኝ የምመኛት ሚስቴን ላደርጋት ሳስብ ላፍ አደረገብኝ። እኔ ደግሞ እልኸኛ ነኝ።ያደረጉኝን ሳላደርግ ማለፍ አልወድም። ፍቅሬን እንዳሳጠኝ ቤቱን አሳጣዋለሁ። አሁን አጋጣሚው እየቀናልኝ ነው። ባይሆን ሮዛን ከኤሊያስ ቀምቼ የኔ ካደረኩ ሚስቴን እፈታለሁ።
ልጅትዋ ድንገት ብድግ ብላ “እኔ ቂመኛ ሰው አልወድም ቻው…..” ብላው የመጠጥ ቤቱን መተላፊያ አቋርጣ ሄደች።በላይ ብርጭቆውን አንስቶ ከበፊቱ በተለየ ሁኔታ አፉን ሞልቶ ተጎነጨ። ፍቅሬን ነጠቀኝ ካለው እሱ ወዳጄ ብሎ ከሚጠራው ኤልያስ ከዚህ በፊት ከነጠቀው ማንነቱ ባለፈ አሁን ክፉ ማንነቱን ለመንጠቅ የወጠነው ውጥን በስካር መንፈስ ማሰቡን ቀጥላል።…
(ይቀጥላል)
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2012
ተገኝ ብሩ