ዋልታዊነት ወይም ዋልታ ረገጥነት (polarization) ዕለት ዕለት ኑሯችን ከፖለቲከኞች፣ ከሚዲያዎች፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከሁሉም አንደበት የሚሰማ “የጊዜው” ቃል ነው። በዕርግጥ ቃሉ በአሁናዊ አለም ዓቀፍና ብሔራዊ የፖለቲካዊ ተዋስኦ (ዲስኮርስ) ላይ ገኖ የወጣ ቢሆንም በመኖር ደረጃ የሃሳብ ልዩነቶች ከጀመሩበት ቅጽበት አንስቶ፤ በፖለቲካ ሃሳብ ደረጃ ደግሞ የፓርቲ ፖለቲካ በአለማችን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያለና የነበረ መሆኑን በርካታ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ይስማሙበታል።
ዋልታዊነት በአጭሩ የሃሳብ ልዩነቶች በተቃራኒ አቅጣጫ ያለልክ መለጠጣቸውን ለመግለጽ ፖለቲካ ከተፈጥሮ ሳይንስ የተዋሰው ሃሳብ ነው። ግለሰቦች በተፈጥሮ የተለያየ ፖለቲካዊ፣ ኢኮሚያዊና፣ ማህበራዊ አቋም ከመያዛቸው አንጻር፤ ተመሳሳይ ሃሳብ ያላቸው ግለሰቦች የራሳቸውን የጋራ የፖለቲካ ድርጅት ከማቋቋማቸው ጋር ተቆርኝቶ የሃሳብ ልዩነት መከሰቱ መቼስ አይቀሬ ነው። ታዲያ እርግማኑ የሃሳብ ልዩነት መኖሩ ጋር ሳይሆን ልዩነቶች ከቁጥጥር ውጪ ሆነው የሁሉኑም ህልውና ጥያቄ ውስጥ ሲከቱ ነው።
ከቀዝቀዛው ጦርነት በኋላ የመጣው የአዲሱ አለም ስርዓት ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ዋልታዊነት ስር እየሰደደ የመጣበት እንደሆነ በርካታ ጸሃፊዎች ያነሳሉ። በተለይም የቀዝቃዛው ጦርነት ሃገራት በኅብረ ስምምነትና በቃልኪዳን ተሰልፈው የሚያደረጉትን ጦርነቶች በማስቆሙ ህዝቦች የጋራ ጠላት ላይ አተኩረው በውስጣቸው ያለውን መከፋፋል እንዳይረሱት አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪም የማንነትና የቡድን ፖለቲካ በአራቱም የአለማችን ማዕዘናት እየተስፋፋ መምጣት በፖለቲካዊና በኢኮሚያዊ ርዕዮተ አለም ላይ በነበረው የሃሳብ ልዩነት ላይ አዲስ ወርድና ስፋት ጨምሮ መካረሩን እንዳጠናከረው የብዙዎች እምነት ነው።
ሳሙኤል ሃንቲንግተን የተባለ አሜሪካዊ የፖለቲካ ሊቅ “The Clash of Civilizations And the remaking of World Order” በተባለው መጽሐፉ አለም በቀጣይ የምታስተናግዳቸው ታላላቅ ግጭቶች በዋናነት በባህል ወይም በስልጣኔዎች ተቃርኖ ምክንያት የሚከሰቱ ይሆናሉ ሲል ትንታኔውን አስቀምጧል። እውነትም እንደተባለው በሺዎች የሚቆጠሩ ግጭቶች በሃገርና በሃገር፣ በቡድኖችና በቡድኖች፣ በቡድኖችና በሃገር እንዲሁም በቡድኖች ውስጥ ባሉ አነስተኛ አንጃዎች መካከል አይለው የተመለከትንበት ጊዜ ቢኖር ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ያለው ጊዜ ላይ ነው።
የቴክኖሎጂ ምጥቀት፣ የኒኩለር ስጋት፣ ሉላዊ ሙቀትና የአየር ንብረት መዛባት በዘመናችን በአብዛኛው አንድነትን ለማምጣት በሃገር ወዳዶች ወደፊት ቢወጡም ለበጎ አላማ የተፈጠሩ ማህበራዊ የመገናኛ መረቦች ለከፋፋዮችና ከሰላም ለማይጠቀሙ ዋነኛ መሳሪያ በመሆን አለም በዚህ ክንፍና በዚያ ክንፍ፣ በእኛና በእነርሱ፣ በግራና በቀኝ በተራማጅና ወግ አጥባቂ ጎራ እየተጎተተች መናጧን ቀጠለች። ይህም ህዝቦች ተስፋ እንዲቆርጡና አለማችንን በጋራ የሚያጠቃ አንድ ልዩ ክስተት ካልተፈጠረ በቀር ዋልታዊነት በምንም ሚረግብ አይመስልም ወደ ሚል ክፉ ምኞት ሁሉ ሳይመራ አልቀርም። በእንዲህ አይነት ውጥረት መካከል ነው ታዲያ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) በሽታ፣ ሞትና የኢኮኖሚ ድቀትን አስከትሎ አለማችንን ማቅ ያለበሰው።
የኮሮና ቫይረስ ገዳይነት፣ የሚሰራጭበት ፍጥነት፣ በማህበራዊ ህይወትና ምጣኔ ሃብት ላይ የደቀነው ግዙፍ ስጋት በመጨረሻም ሊበጠስ የደረሰውን የፖለቲካ መካረር ፋታ ይሰጠዋል የሚለው የሁሉም እምነት ነበር። በዕርግጥም ወደ መጀመሪያ አካባቢ በመላው አለም ያሉ መንግስታትን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች ህዝቡ ንጽህናውን እንዲጠብቅ፣ አካላዊ ርቀቱን እንዲጠብቅ እንዲሁም ሌሎች ጥንቃቄዎች እንዲያደርግ በአንድ ድምጽ ምሳሌያዊ የሆኑ ተግባራትን አከናውነዋል። ይህም በፖለቲካ ሰበቃ ምክንያት ስጋት ውስጥ ለወደቁት ትልቅ እፎይታ ያመጣ ጉዳይ ነበር። ነገር ግን ፖለቲከኞቹ ለሌላ መልሶ ማጥቃት እያደባ ከኳስ ጀርባ እንደሚከላከል ቡድን ትንሽ ጊዜ ከወሰዱ በኋላ ኮረናንም እንደ መሳሪያ በመጠቀም አዲስ እና አስደንጋጭ ጥቃት አንዱ በአንዱ ላይ ሲፈጽሙ እየተመለከትን ነው።
በሃገረ አሜሪካ ለወትሮውኑም በሪፐብሊካን እና በዲሞክራቶቹ መካከል ያለው መቃቃር በኮረና ምክንያት እንደገና ደርቶ የፖለቲካ ዋልታዊነት በሙላት እየተመለከትን ነው። በጣሊያን አለምን ያስደነገጠ ሞት መመዝገቡ ከአውሮፓ ህብረት ጥለን እንውጣና በህብረቱ ስር እንቀጥል በሚሉ የሃገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል ያለውን ውጥረት ሊያሰክን አልቻለም። በስፔን ኮሮና ቫይረስ እንደ ካታሎኒያ ባሉ ተገንጣይ ሃይሎችና በመንግስተ መካካል ያለውን ውጥረት ከተገመተው በላይ ሊለጥጠው ችሏል። ኮረና ቫይረስ በህንድ የሂንዱ እምነት ተከታዮችን በብዛት ባቀፉና የእስልምና አማኞችን በብዛት ባቀፉ ሃይሎች መካከል ያስከተለው ፍትጊያ ብዙ ሰላም ወዳድ ዜጎችን ስጋት ውስጥ ከትቷል። በአፍሪካና በላቲን የሚገኙ በርካታ ሃገራትም በመንግስት በኩል “ኮሮናን በሚገባ ተቆጣጠርኩ የመሪነት ብቃቴን ተመልከቱልኝ” የማለት በተቃዋሚዎች በኩል ደግሞ “የህዝቡ ጤንነት አደጋ ውስጥ ገብቷል፤ እኔ መሪ ብሆን ይሄ ሁሉ አደጋ አይደርስም ነበር” የሚል አንድምታ ያላቸውና ኮረና ቫይረስን ድጋፍ የማግኛ አይነተኛ መንገድ አድርጎ የመጠቀም ዋልታ ረገጥ የሆኑ አዝማሚያዎች ተበራክትዋል። ሃገራችን ኢትዮጵያስ?
ሃገራችን ኢትዮጵያም የአለማችንን የፖለቲካ ዝንባሌ በመከተል ካለፉት አርባና ሃምሳ አመታት ጀምሮ ወደ ፖለቲካ ዋልታዊነትና የእርስበርስ መራራቅ እያመራች መሆኗ ያፈጠጠ ሃቅ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው ዋልታዊነት በተለይ ከፓርቲ ፖለቲካ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በሃገራችን የአጼዎች አገዛዝ መውደቂያው አካባቢን ተከትሎ የተመሰረቱ ፓርቲዎች “የኔ ህልውና በአንተ አለመኖር ላይ የተመሰረተ ነው” በሚል ትርክታቸው ወደፊት መውጣት ችለዋል። የወቅቱ የፖለቲካ ተዋናዮች ህዝቡን እንደ ስልጣን ክፍፍል፣ መሬትና ዳቦ በመሳሰሉ አንኳር ጉዳዮች ላይ በቡድን ማሰለፍ ቢችሉም ልዩነቶች በአግባቡ ካልተያዙ ኢትዮጵያ ካላት የዘር፣ ቀለም፣ ዕምነትና የሃሳብ ህብር በመነሳት ለያስከትሉት የሚችሉትን መዘዝ በመረዳት ለዛሬ ትውልድ ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ የተውት ቅርስ የለም።
ታዲያም የሃሳብ ልዩነቶች ካለልክ በመለጠጥና ጥላቻና ፍርሃት በመፍጠር አባዜ የተለከፈው ፖለቲካችን ዛሬም ወሳኝ አጀንዳዎች በጠረጴዛ ላይ ሳሉ ከሃቀኛ ውይይት ይልቅ ከመጋረጃ ጀርባ የሚደረግ ስውር ጨዋታ፣ ዱለታ፣ ሴራ፣ ቧልት፣ ስላቅ፣ ነገር ጥምዘዛና ወይ “አጠፋሃለሁ ወይ ታጠፋኛለህ” በሚለው አደገኛ አካሄዱ ቀጥሏል። የኛ ሃገር ዋልታዊነት የሚከፋው በብሔራዊ ዕርቅ ያልተዘጉና ቅራኔ የሚያሳድሩ ታሪኮችን ከሽኖ “ክፉውን ፈጣሪ፣ በጎውን ቀባሪ” በሆኑ የውሸት የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመታገዝ የሚከናወን በመሆኑ ነው። እንግዲህ ትውልዱ በህገ-መንግስቱ፣ በመንግስት አወቃቀር፣ በታሪክ፣ በባንዲራ፣ በከተሞች ስያሜ…ወዘተ… እያለ ህልቆ መሳፍርት በሌላቸው ነገሮች ላይ ሚያንጸባርቀውን የሃሳብ ልዩነቶችን ለራስ እንዲመች ብቻ እያረጉ ውጥረት በመልቀቅ ጊዜያዊ ጥቅም ማጋበስ ነው።
የዛሬ የሃገራችን ፖለቲካዊ ዋልታዊነት “ክሌአዊ/ ሁለታዊ” አሊያም ነጮቹ ‘binary’ ወይም ‘either/ or thinking’ እያሉ የሚጠሩት ነገሮችን በሁለት ሳጥን ውስጥ በመወሰን አስተሳሰብ ዙሪያ ያጠነጠነ ነው። ታዲያ የክሌአዊ/ ሁለታዊ አስተሳሰብ በውስጡ አንድ መርዝ ተደብቆ ይገኛል። ይህም ‘የኔ ወገን ሁሌም ትክክል ያኛው ወገን ደግሞ ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ’ የሚል ፍጹማዊ አስተሳስብ ነው። በዚህ አስተሳሰብ መሰረት ከአንዱ ወገን ፍጹም ስህተት እንደማይፈጠር ከሌላው ወገን ደግሞ ፍጹም መልካም ነገር እንደማይወጣ ብይን ተሰጥቷል።
በሁለንታዊ አስተሳሰብ የሚመራ የፖለቲካ ማህበረሰብ ‘በአጠይቆታዊ አመክንዮ’ (deductive reasoning) እስራት ውስጥ የሚወድቅ ነው። በዚህም መሰረት በጉዳዮች አቋም የሚያዘው በየአውዳቸው በዝርዝር ተመርምረው ሳይሆን ተቀናቃኞቹ መጀመሪያውኑ ከሚቀበሉት የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው። ስለዚህ በአንድ ክስተት ዙሪያ ያለው አውነት ሳይሆን ወደ ድምዳሜ የሚያደርሰው፤ ተቀናቃኞች አስቀድሞ የሚመሩበት ፖለቲካዊ ድምዳሜ ነው ስለ ክስተቱ እውነት የሚሆነው ማለት ነው። ከዚህ ውጭ ከማህበር ጋጋታ ነጠል ብሎ ጥያቄ ለማንሳት መሞከር እና በየነጠላ ጉዳዩ የራስን ምርምር ማድረግ እንደ ደካማና አቋመ ቢስ ማስቆጠሩ የማይቀር ነው።
በእንዲህ አይነት የፖለቲካ ዋልታዊነት አንዴ ከዚህኛው ጥግ አንዴ ከሌላኛው ጥግ እየተላተምን ደክመን ሳለ ነው እንግዲህ ኮሮና ጥፋቶቹን አስከትሎ ከሃገራችን የደረሰው። ኢትዮጵያውን በታሪክ የውስጥ ለውስጥ ቅሬታን ወደ ጎን በማለት የውጭን ጠላት ሲመክት እንደመኖሩ አሁንም ቫይረሱን እንደ ወራሪ በመቁጠር ሁሉም በአንድ ይቆማል የሚል እምነት ነበር። ነገር ግን ቫይረሱ በሌሎች አለማት እንደታየው መናቅን፣ መረሳትንና ጣል ጣል መደረግን በመምረጥ ፖለቲከኞቻችን በመሸወድ ወደ ተለመደው የፖለቲካ ዋልታዊነት እንዲመለሱ አድርጓል። ተቀዋሚው መንግስት ቫይረሱን አሳቦ አገዛዙን ለማራዘም ይሞክራል ሲል መንግስት ደግሞ ተቃዋሚዎች አጋጣሚውን ተጠቅሞ ለስልጣን እየተሻሙ ነው በማለት ሲከስ ኮሮና ከተናቀ ቦታው ሆኖ የሚያደባይ መሳሪያውን በመልቀቅ ጥፋቱን እየጨመረው ነው።
በአጠቃላይ ዋልታዊነት ከላይ እንደተገለጸው ሀገራችን ኢትዮጵያን በሁለት እግሯ እንድትቆም፣ የህዝቧ ሰላም አንዲበዛና ዲሞክራሲና ልማት የተረጋገጠባት የሁሉም ሃገር ለመሆን የምታደርገውን ጥረት የሚያደናቅፍ መሰናክል ነው። የዳበረ ዲሞክራሲና ኢኮኖሚን የሚመሩ ምዕራባውያን ሃገራት በመካከላቸው ያለው የመናናቅና የማጥላላት ፖለቲካ ኮሮና ቫይረስ ላደረሰባቸው ትልቅ ጉዳት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ብዙዎች በሚከራከሩበት በዚህ ወቅት እኛም ቫይረሱ ክፍተቶችን ተጠቅሞ ብዙ ጉዳት ያደርስ ዘንድ ልንፈቅድለት አይገባም። ፖለቲከኞቻችን ከየራሳችን አጥር አንወጣም፤ ህልውናው አደጋ ውስጥ ለወደቀው ህዝብ ቅድሚያ ሰጥተን አንሰራም ካላችሁ በታሪክ ስለሚሰጣችሁ የትውልዶች ወቀሳ መዘጋጀት ይኖርባችኋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2012
በመጋቢ ዘሪሁን ደጉ