ሴቷ ‹‹ከጀበራው ወዲያ ጀበራው ጋርዶታል፤
ጎፈሬው ታሞበት በሻሽ ደግፎታል›› ስትል በነገር ነካ ታድርገዋለች፡፡ ወንዱ ‹‹ከጀበራ በታች ሀገራችን ነው፡፡
እራሴ ቢመለጥ ልቤ ደህና ነው›› ብሎ ይመልሳል፡፡
ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ሴቲቱ ሰውየውን ፈቅዳው ነው በመላጣው አስመስላ እንደወደደችው ስሜቷን የገለጸችለት፡፡ እርሱስ መች የዋዛ ሆነና ‹‹ልቤ ደህና ነው›› ብሎ ፍቃደኝነቱን አረጋገጠላት፡፡ እንዲህ ያሉ ባህላዊ ለዛ ያላቸው ውስጠ ቀይራ ግጥሞች በጥምቀት የበዓል አከባበር ላይ የተለመዱ ናቸው፡፡ አቶ ደሳለኝ አበራ የተባሉ ሰው ናቸው በአንድ የጥምቀት በዓል ላይ አንዲት አጎታቸውን የፈቀደች ሴት ስሜቷን የገለጸችበትን መንገድ ያጫወቱኝ፡፡
አቶ ደሳለኝ በተወለዱበት አካባቢ ሰሜን ወሎ ራያቆቦ በፍቅር የተፈላለጉ ሴትና ወንድ በጥምቀት በዓል ፍላጎታቸውን ገሀድ እንደሚያወጡት ይናገራሉ፡፡ የትዳር ህይወት የቀመሱት መፈላለጋቸውን እንዲህ በግጥም ይገልፃሉ፡፡ ገና ትዳር ውስጥ ያልገቡ ወጣቶች ደግሞ ይተጫጫሉ፡፡ ወንዱ በጎፈሬው መሃል ሚዶውን ሰክቶ ጉራይማሌ የተነቀሰውን ጥርሱን በረጅም መፋቂያ እያፀዳ ኩሏን ተኩላና አደስዋን አድርጋ አምራና ደምቃ ከጭፈራው መካከል ያያትንና ልቡ የፈቀዳትን ከ‹‹ጎቢሶው›› ወይም ከግልድሙ ሎሚውን አውጥቶ ይወረውርላታል፡፡
በአካባቢው የሚታወቀው ጎቢሶ ወንዱ እስከ ደረቱ ድረስ የሚጠመጠመው እንደሆነና ጥቃት ቢደርስበት እንኳን ጥይት እንደማይበሳው ነው የነገሩኝ፡፡ በተለይ የአለመግባባት ችግር ሲፈጠርና አካባቢያዊ ስጋቶች ሲያጋጥሙ እራስን ለመከላከል ይረዳል፡፡
በጎቢሶው ውስጥ የያዘውን ሎሚ አውጥቶ ደፋር ከሆነ በያዘው ቀጭን በትር ጫፍ ላይ ሎሚውን ሰክቶ በቀጥታ እንዲደርሳት ያደርጋል፡፡ አብዛኛው ስለሚያፍርና ሰው እንዳያየው የሚፈልግ በመሆኑም የሚፈልጋት ላይ መወርወሩን ይመርጣል፡፡
ሎሚው ሲወረወር ያለቦታው ሊደርስ ይችላልና እንዲህ ያለው ነገር ቢያጋጥም እንዴት ይሆናል? አልኳቸው አቶ ደሳለኝን፡፡ ያገባች ሴት ከሆነች ልታነሳው ቀርቶ ዞር ብላም አታየውም፡፡ ተጠራጥራ ያነሳች ልጃገረድም ብትሆን የተወረወረበትን አቅጣጫ ማየቷ ስለማይቀር ወርዋሪው እንድታ ስተላልፍለት ምልክት ስለሚሰጣት ሎሚው ከታሰበችው ዘንድ ይደርሳል፡፡
‹‹ሎሚ ብወረውር ደረቱን መታሁት፤ አወይ ኩላሊቱን ልቡን ባገኘሁት…›› ብላ ያቀነቀነችው ዘፋኝ የግጥሟ መነሻ በጥምቀት በዓል ላይ የሚወረወረው ሎሚ ሳይሆን ይቀራል ብላችሁ ነው?
በድንገት ያገኘኋቸው አቶ ደሳለኝ ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› የሚለውንም እንዲህ ነበር ፍችውን የነገሩኝ፡፡ በጥምቀት ሁሉም የክት ልብሱን ለብሶ የሚወጣበት ቀን መሆኑ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ሌላው ፍች፤ አንዲት ሴት በጥምቀት በዓል ሎሚ ተወርውሮላት የሚቀርብላትን የፍቅር ጥያቄ ማሳለፍ የለባትም፡፡ የተወረወረላትን ሎሚ ካልተቀበለች ዓመት ልትጠብቅ ነው፡፡
የጥር ወር በገጠሩ ምቹ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የእርሻ ስራው ያበቃበትና እህል ከጎተራው የሞላበት ወቅት በመሆኑ፤ ሴቷም የማጀቱ ስራ እንደሌሎቹ በዓላት ስለማይ በዛባት ሰርጉም፣ መተጫጨቱም፣ መጫወቱም የጥር ወር ከጥምቀት በዓል ጋር ይደምቃል፡፡ ከፊሉ ታቦታቱን አጅቦ በዝማሬ ሲያወድስ፤ ከፊሉ ደግሞ በባህል ጭፈራ በእስክስታ ‹‹አሸነፋት፣ አሸነፈች›› እያሉ በመጫወት ይደሰታሉ፡፡ ውሃ አጣጭን የሚያገናኘው የጥምቀት በዓል እያለ ‹‹ትራስ አቅፌ እያደርኩ›› ነው የሚሉ አንዳንድ ከተሜዎች አይሞኙ ፡፡
ለነገሩ ባህልና ወጉ ከተማ ላይ ሲደርስ ይሸራረፋል፡፡ ከባህሉ ይልቅ ፌዙ ይበዛል፡፡ ሎሚ ወርውረህ አቻህን ፈልግ ቢባል ሎሚ ኪሎው 80 ብር መግባቱን ሊነግርዎት ይችላል፡፡ የክትፎና ቁርጥ ወጭ ነው የሚታሰበው፡፡ ጨዋታውም ቢሆን ወደ ዘመናዊው ያደላ በመሆኑ ወጣቱ ወደ ዳንስ ይሳባል፡፡የከተማውን ለየት የሚያደርገው፤ ከአለባበስ ጀምሮ ትንሽዋን ኢትዮጵያ ያያሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ታቦታት በአብዛኛው የሚያድሩት በጃንሜዳ በመሆኑ በስፍራው በሺዎች የሚቆጠር ምዕመን ይታደማል፡፡
ታዳሚው በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አልባሳት ተውቦ ስለሚወጣ ኢትዮጵያን ያያሉ፡፡ጨዋታውም እንዲሁ በተለያዩ ቋንቋዎች እየተዘፈነ ይጨፈራል፡፡ ሁሉም እንደየስሜቱ በመንፈሳዊና በተለያዩ ጨዋታዎች ይሳተፋል፡፡ ከምዕመኑ በተጨማሪ ጥንግ ድርብ የለበሱ ቀሳውስትና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በጽናጽልና በከበሮ በጥዑም ዝማሬ ታቦታቱን አጅበው በዝግታ ሲጓዙ፣ በጥምቀተ ባህሩ ለመጠመቅ ያለው መሽቀዳደም የሚሰጠውን መንፈሳዊ እርካታ ማየት ልዩ ድባብ አለው፡፡
ሃይማኖታዊና ማህበራዊ ክንዋኔዎችን በአንድ የያዘ በዓል ለመታደም ሀገር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የሚጎርፉት የውጭ ዜጎችም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዚህ ወቅት ቁጥራቸው ይጨምራል፡፡በዓሉ በየዓመቱ ቢከበርም ሁሌም አዲስና የሚናፈቅ ነው፡፡ ከኦርቶዶክስ ሃይማኖታዊ በዓላት የጥምቀት በዓልን ለየት የሚያደርገው እንዲህ ማህበራዊ ክንዋኔዎች ስላሉት ጭምር ነው፡፡ የአደባባይ በዓል መሆኑ ደግሞ ከእምነቱ ተከታዮች ውጭ የሆኑትም እንዲሳተፉ ዕድል ይሰጣል፡፡
እንግዲህ ውሃ አጣጫችሁን ፈላጊዎችም ይቅናችሁ፡፡ የእምነቱ ተከታዮችም በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የደስታ ይሁንላችሁ፡፡ የከርሞ ሰው ይበለን፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 10/2011
ለምለም መንግሥቱ