* በወር 3 ሚሊዮን ብር እያስገቡ 85 ሺህ ብር
ኪራይ ሲጠየቁ የምን ያዙኝ ልቀቁኝ…!?
* ዜጋውን በ200 ብር የወር ደመወዝ በባርነት
የሚገዛስ የመብት ጥያቄ የማንሳት ሞራል ልዕልና አለውን ?
በዚያ ሰሞን በመዲናችን አቧራ ያስነሳው ፣ በሚዲያዎችም የተራገበው አብይ ጉዳይ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የንግድ ኪራይ ቤቶች ላይ ያደረገው መጠነኛ ወርሃዊ የኪራይ ማሻሻያ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃንም በተለይ ፋናና በርካታ የግል ጋዜጦች ምንም ማጣራትና ምርመራ ሳያደርጉ የተከራዮቹን ቅሬታ እንደወረደ እንደገደል ማሚቶ አስተጋብተዋል፡፡ ከዚህ አልፈውም ከተከራዮች ጋር አብረው ጉዳዩን ፖለቲካዊ አንድምታ ሊያላብሱት ቃጥተዋል፡፡በዘመናት መካከል ሊጀግን የቃጣውን የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲንም ለማሳጣት፣ ለማሸማቀቅ ብዙ ርቀት ሄደዋል፡፡
ዳሩ ግን እነዚህ ሚዲያዎች የተከራዮችን ቅሬታ ከወቅቱ የግል ንግድ ቤት ኪራይ ዋጋ ጋር በማነፃፀር ለመመርመር ወይም ለማጣራት ምንም ጥረት ሳያደርጉ የቅሬታ አቅራቢዎችን አቤቱታና መፈክር እንደወረደ አስመልክተውናል፡፡ የጋዜጠኝነትን ስነ ምግባር ጥሰውም ለእውነት ሳይሆን ለተከራዮች ጩኸት ወግነው ፤ ኤጀንሲው ማሻሻያ እንዲያደርግ አስገድደዋል፡፡ እጅ ጠምዝዘዋል፡፡ ዘገባቸው ገለልተኛና በምርመራና በማጣራት ላይ የተመሰረተ ቢሆን ኖሮ ግን ሀቁ ሌላ ይሆን ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ሚዲያውን ከጎናቸው ያሰለፉ የተከራዮቹ ተወካዮች የልብ ልብ ስለተሰማቸው ማሻሻያው ገና ይቀረዋል እያሉ ነው ፡፡
ተከራዮች ወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ኪራይ ለመጨመር አይፈቅድም በማለት ማሻሻያውን ፖለቲካዊ አንድምታ ለመስጠት ያደረጉትን ጥረት ሚዲያዎች ተቀብለው ማስተጋባታቸውና በቀላሉ መዘወራቸው እንደ ጋዜጠኛ አሳዝኖኛል፡፡ እነዚህ ተከራዮች ላለፉት 40 እና ከዚያ በላይ ዓመታት እንደ ውርስ እየተቀባበሉ በረከሰ አይደለም እጅግ እጅግ ዝቅተኛ ኪራይ፣ ፒያሳ ፣ አራት ኪሎ ፣ መርካቶ ፣ ካዛንችስ ፣ ወዘተ… ካሉ የግል የንግድ ኪራይ ቤቶች ፤ በእነዚህ ሰፈሮች ካሉ የግል መኖሪያ ቤቶች ኪራይ ጋር እንዲያውም ወጣ ካሉት ፈረንሳይ ፣ ኮተቤ ፣ አስኮ ፣ አቃቂ ቃሊቲ ፣ ድል በር ወዘተ…. የግል መኖሪያ ቤቶች ኪራይ ጋር እንኳ ቢነፃፀሩ የእነርሱ ወርሃዊ ኪራይ ብዙም ልዩነት በሌለውና በረከሰ ኪራይ በመጠቀም ሰፊ ሀብት አካብተዋል፡፡
ሲሆን ሲሆን ኃላፊነት የሚሰማ ቸው ዜጎች ቢሆኑ ኖሮ የምንከፍለው ኪራይ እጅግ ዝቅተኛ ስለሆነ እናሻሽል ብለው ቢነሱ በተገባ ነበር፡፡ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ሀብት ያካበቱበት የሕዝብ፣ የመንግሥት የንግድ ኪራይ ላይ ማሻሻያ ሲደረግ አቧራ ማስነሳት ፣ ሰልፍ መውጣት፣ መፈክር ማስተጋባት ባላስፈለገ ነበር፡፡
ቅሬታ አቅራቢ ደባሎች (ከሚከ ፍሉት እጅግ ዝቅተኛ ኪራይና ከሚያስገቡት ከፍተኛ ገቢ አንፃር ተከራይ ሳይሆኑ የመንግሥት ደባል መሆናቸውን ለመግለፅ ነው) ለማደናገሪያነት የተጠቀሙት የኪራይ ማሻሻያውን በመቶኛ ማስላትን ነው፡፡ ሲከፍሉት የነበረው ኪራይ እጅግ ዝቅተኛና ወቅታዊ ገበያውን ያገናዘበ ስላልነበር የተደረገው ማሻሻያ በመቶኛ ተሰልቶ ላይ ላዩ ሲታይ ከፍተኛ ይምሰል እንጂ አሁንም ከግል ህንፃ አከራዮች የኪራይ ዋጋ እና ከሚያስገቡት ገቢ አንፃር ሲነፃፀር እጅግ እርካሽ ነው፡፡
እነዚህ የመንግሥት የንግድ ቤቶች ተከራዮች የሕዝብ ቤት ነው የያዝነውና ማህበራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ ፤ አገልግሎታችንን በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ እናቅረብ እንኳ የማይሉ ይሉኝታ ቢሶችና የግል ህንፃ ተከራይተው ከሚነግዱ ቀድመው በረባ ባልረባው ደንበኞቻቸው ላይ ዋጋ የሚጨምሩ መሆናቸው ነው፡፡
በፒያሳ ያሉ በናሙናነት የወሰድኳቸው ሆቴሎች ቀጥረው ለሚያሰሯቸው ሠራተኞች እንኳ የግል ቤት ተከራይተው የሚነግዱ ለሠራተኞቻቸው ከሚከፈላቸው ምንዳ (ደመወዝ ለማለት የማይመጥን ስለሆነ ነው) እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ ይህንን ለመግለፅ እኔን እንደ ዜጋ አሳፍሮኛል፤ አሳዝኖኛልም ፡፡ አዎ ጉርሻ ወይም ቲፕ ስለምታገኙ በሚል በወር ለአስተናጋጆች 200 ብር ብቻ ነው የሚወረወሩላቸው ፤ በቀን ከ6 ብር ከ70 ሳንቲም ያነሰ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ራስ ወዳዶችና ለዜጋቸው ምንም ደንታ የሌላቸው ናቸው፡፡ እንግዲህ ኪራይ ተጨመረብን ብለው አደባባይ ለተቃውሞ የወጡትና ያዙኝ ልቀቁኝ ያሉት፡፡
ዘላለም በድሀ ጉልበት በሕዝብ ቤት ያልተገባ ጥቅም ማጋበስን እንደ መብት ቆጥረው ዓይናቸውን በጥሬ ጨው ታጥበው ሰልፍ መውጣታቸው ሳያንስ ፖለቲካዊ ትርጉም ለመስጠት መሞከራቸው ደግሞ ያማል ፡፡ የኪራይ ማሻሻያው ላይ ያለኝን አስተያየት እዚህ ላይ ገታ ላድርገውና ተከራዮች የቤቶች ኤጀንሲን ግልፅና ምክንያታዊ የኪራይ ማሻሻያ ፖለቲካዊ ትርጉም ለመስጠት የሄዱበትን እርቀት አንድ በአንድ በስሱ እንመልከት ፤
1ኛ. ተከራዮች «የኪራይ ማሻሻያው ነጋዴዎችን ከአዲስ አበባ ለማፈናቀል ሆን ተብሎ የተደረገ ስውር ሴራ ነው» እያሉን ነው፡፡ አሁን ማን ይሙት በ40 ዓመት ኪራይ መጨመር ከአዲስ አበባ ማፈናቀል የሚሆነው በምን ምክንያት ነው? በየ6ወሩ ኪራይ በተጨመረበት ቁጥር የግል ተከራይ ቢፈናቀል አዲስ አበባ ወደ ነዋሪ አልባ ባድማነት ተቀየረች ማለት ነው፡፡
«የማይሆን ነገር ለሚስትህ አትንገር» ነው ያሉት አበውና እመው? ይቺ የማፈናቀል የፖለቲካ ጨዋታ አፈናቃዩ ማነው ? ተፈናቃዩስ ? የሚል ጥያቄ ከማስነሳቱ ባሻገር በማር የተለወሰች መርዝ ናት፤
2ኛ ተከራዮች በዚህ አያቆሙም፡፡ «የአዲሱን የኪራይ ጭማሪ ያልሰሙ ነጋዴዎች አሉ፡፡ …» ይሉናል፡፡ የኪራይ ጭማሬውንም ሆነ በኋላ የተደረገውን ማሻሻያ የቤቶች ኤጀንሲ በአደባባይ አውጆት እያለ ፤ ያልሰሙት እንማን ናቸው? በእነዚህ ተከራዮች ክፉ መንገድ መሄድ ስለማልፈልግ ትቼው እንጂ ይህቺ አባባልም እንደ ጥሬ ጥጥ ብትፈለቀቅ ክፉ ሃሳብ አላት፡፡
3ኛ « መንግሥት በአሁኑ ስዓት 1000 በመቶ መጨመር ቀርቶ 10 በመቶ ለመጨመር ጊዜው አይደለም፡፡ …» ይህን ቅሬታ ሳያጣራ፣ ሳይመረምር እንደወረደ የዘገበው «ኢትዮጲስ » እነዚህን ተከራዮች ፤ «ታዲያ ኪራይ የመጨመሪያው ትክክለኛ ጊዜው መቼ ነው ? የሚለውን ጥያቄ ጨምሮ ተከራዮች ከላይ ላነሷቸው አቅጣጫ ማስቀየሻ ሰበቦችን ቢመረምር የጋዜጠኝነት ወጉ ነበር ፤ ይሁንና የፋናንና የሌሎች ሚዲያዎች ስህተት ደግሞታል፡፡
ተከራዮች በማሻሻያው ላይ ፖለቲካዊ ትርጉም ለመስጠት ስለተጓዙበት አደገኛ መንገድ ይሄን ያህል ካልኩ ወደተነሳሁበት አብይ ጉዳይ ልመለስ ፤እነዚህ የመንግሥት የንግድ ቤቶች እኮ የአያት የቅደመ አያቶቻቸው ውርስ ፣ እርስት አይደሉም፡፡ ሌላው ዜጋም በገበያ ዋጋ ተጫርቶ ፣ ተወዳድሮ በተራው፣ በፍትሐዊነት ተጠቃሚ መሆን የሚችልባቸው የህዝብ አንጡራ ሀብቶች እንጂ፡፡
በእርግጥ ኪራዩ ከተወደደባቸውና መክፈል የማይችሉ ከሆነ ማን አስገደዳቸው? ለምን መክፈል ለሚችል አይለቁም ? ስንት የግል አከራይ ያማረረው ተከራይ አለ እኮ! የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲም እንዲህ ከሚቸገር ለምን በግልፅ ጨረታ በገበያ ዋጋ እንዲተላለፉ ለምን አላደረገም ? በቀጣይም ሁሉም ዜጋ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ፤ ሕገ ወጥ የቁልፍ ሽያጭን ለመከላከል ግልፅ ጨረታ ሊወጣባቸው ይገባል እላለሁ፡፡
የተደረገው የኪራይ ማሻሻያ ተከራዮች እንዳራገቡት አለመሆኑን ለማሳየት በፒያሳ የሚገኙ አራት የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የንግድ ሆቴሎችን የኪራይ ማሻሻያና አማካኝ የቀን ገቢ ቅርበት ካላቸው ምንጮቼ ካገኘሁት መረጃ አንጻር ስመዝን ጭማሪው እዚህ ግባ ሊባል የሚችል እንዳልሆነና ከገቢያቸው አንጻር ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል መሆኑን ያሳያል፡፡
የሚያሳዝነው የእነዚህ ሆቴሎች የምግብ ፣ የመጠጥ ፣ የሻይ ቡና እንዲሁም የአልጋ ዋጋ ከግለሰብ በውድ ዋጋ ተከራይተው ከሚሰሩ ሆቴሎች ቢወደድ ወይም ቢጨምር እንጂ ቅናሽ አይደለም። ተከራዮቹ ስለፈጠሩት የሥራ ዕድል በየአደባባዩና በየሚዲያው ቢመፃደቁም «የሚከፍሉትን ደመወዝ!» ስሰማ ግን ማመን አቅቶኛል፡፡አስደንግጦኛልም፡፡
ለመስተንግዶ ሠራተኞች « የሚከፍሉት» ምንዳ በወር 200 ( ሁለት መቶ ብር ) ብቻ ነው፡፡ እደግመዋለሁ ሁለት መቶ ብር ወይም በቀን 6 ብር ከ70 ሳንቲም አካባቢ ማለት ነው ፡፡ በአረብ ሀገራትም ሆነ በሀገራችን ቢሆን የውጭ ባለሀብቶች ባልተወለደ አንጀታቸው በፋብሪካዎች፣ በአበባ እርሻዎችና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተቀጥረው በሚሰሩ ዜጎቻችን ላይ የጉልበት ብዝበዛ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፅማሉ እያልን ስንንገበገብና ስንብሰከሰክ ፤ መሀል ፒያሳ ቲፕ ስለምታገኙ ፣ ማደሪያና ቁራሽ ስለምንጥልላችሁ በወር 200 ብር ይበቃችኋል የሚሉ የምድር ጉዶች መኖራቸውን መስማት ይዘገንናል፤ ያማል፡፡ ሚዲያውም ከእነዚህ ዓይነት ሰዎች ጎን መቆሙ ያሳፍራል፡፡
ስለሆነም በእኔ እምነት ለወገናቸውና ለዜጋቸው ቅንጣት ታክል ርህራሄ የሌላቸው እነዚህ ተከራዮች ለሀገርም ይበጃሉ ተብሎ ስለማይጠበቅ፤ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በያዙት ቤት ላይ ግልፅ ጨረታ ሊያወጣ ይገባል፡፡ በእነዚህ የመስተንግዶ ሠራተኞች ላይ ለዓመታት የተፈፀመ ግፍና በደል ሁላችንን እንደዜጋ ሊሰማን፣ ሊያመን ይገባል ፡፡ በወንድምና በእህት ላይ የሚፈፀም ግፍ በሀገርና በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፀም ግፍ ነውና ፡፡
የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ፣ ሚዲያዎች፣ ለሠራተኛ መብት ቆመናል የምትሉ በተለይ የሕግ ባለሙያዎች የእነዚህ ወገኖቻችንን በደል በችሎት ሞግታችሁ እንድታስከብሩ ፤ እንባቸውን እንድታብሱም በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ «ዓሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል» ይሉሃል እንግዲህ ይህ ነው !
አዲስ ዘመን ጥር 10/2011
በቁምላቸው አበበ (ሞሼዲያን)