ክፍል አንድ
ለግንዛቤ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቴሌግራም እና በፌስቡክ ገጾች ላይ የጫማ፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች፣ የመድሃኒቶችና ሌሎችንም ምርትና አገልግሎቶችን የተመለከቱ ማስታወቂያዎች መበራከታቸውን ሳናስተውል አልቀረንም። የአውቶበስ ቲኬት መቁርጥና ሌሎችም ግብይቶች እንዲሁ በእጅ ስልካችን መከናወን ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
በእነዚህ ማስታወቂያዎች ታዲያ ማንነታቸውን በአካል የማናውቃቸው ሻጮች ወይም አምራቾች ስለምርትና አገልግሎታቸው ዝርዝር ማብራሪያ ከዋጋና ከዕቃዎቹ ምስል ጋር በድረ-ገጾች ላይ ይለጥፋሉ። በዚህም ጥቂት የማይባሉ ግብይቶች ናቸው የሚከናወኑት።
ይሁንና ግዥው ከተከናወነ በኋላ ከሻጮቹ ማንነት አለመታወቅ፤ ከምርትና አገልግሎቶቹ ጉድለት እንዲሁም ከክፍያው ሂደት አስተማማኝነት ጋር በተያያዘ በርካቶች እክል ገጥሟቸው ሲያጉረመርሙ ይደመጣሉ።
ይህችን ቀላል ማሳያ አቀረብኩ እንጂ አሁን ባለንበት ዘመነ-ቴክኖሎጂ እንዲህ ያለው የዲጂታል ግብይት በአገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል። ትልልቅ ኩባንያዎችና ከፍተኛ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ ግለሰቦችም በዚሁ የንግድ ልውውጥ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እየሆኑ ነው።
የመንግሥት ተቋማትም ቢሆኑ አንዳንድ አገልግሎታቸውን (የሥራ ቅጥር ምዝገባ፣ የንግድ ምዘገባና የግብር አከፋፈል የመሳሰሉትን) በዚሁ የኤሌክትሮኒክ መንገድ በመጠቀም ለተገልጋዮች በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
የዚህ ዓይነቱ የግብይትና የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን ነው የሚባለው። ይህም ተንቀሳቃሽ ስልክንና ሌሎች መሰል መሣሪያዎችን ጨምሮ በኮምፒውተር በታገዘ የኢንፎርሜሽን መረብ ሥራን ማከናወን ነው። ይህም የኤሌክትሮኒክ ንግድንና የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎትን ይጨምራል።
ከአካላዊ መቀራረብና ከንክኪ መቆጠብ የግድ በሆነበት በአሁኑ ”የኮሮና ወቅት” ይህ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን የቱን ያክል የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ለመገመት አያዳግትም።
እጃችን ላይ ባለው ስልክ አልያም ጠረጴዛችን ላይ ባለው ኮምፒውተር አማካኝነት ግብይት መፈፀም እና የመንግሥት አገልግሎት ማግኘት እንድንችል የሚያደርግ በመሆኑ ምነው ቀደም ብለን የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን ሥርዓትን ጀምረነው በነበር ያሰኛል።
የሆነው ሆኖ ይህ የግብይት ሂደትም ሆነ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ በአገራችን የሕግ ድጋፍ የሌለውና ሥርዓትም ያልተበጀለት በመሆኑ ከችግሮች አላመለጠም።
የውል፣ የሽያጭ፣ የኩባንያ፣ የባንክና የኢንሹራንስ እንዲሁም እንደገንዘብ የሚያገለግሉት የተላላፊ ሰነዶችን የተመለከቱ ሕጎቻችን በ1950ዎቹ የወጡ በመሆናቸው ከሰነድ ግበያ ባለፈ ከኤሌክትሮኒክ ግብይቶች ጋር የማይተዋወቁ ናቸው።
እናም በተለይ ከውል አቀራረብና አቀባበል፤ ከፊርማ፣ ከማህተም፣ ከክፍያ ሂደት፣ አለመግባባቶች ከመፍታትና ከመሰል ጉዳዮች አንፃር ግብይቱና አገልግሎት አሰጣጡ የሕግ ድጋፍ የሌለው በመሆኑ የሚፈጠሩት ችግሮች ቀላል አይደሉም።
በዚሁ መነሻ መንግሥት የኤሌክትሮኒክ ንግድንና አገልግሎትን የተመለከተ አዋጅ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።
ስለ ረቂቅ አዋጁ
ረቂቅ አዋጁ “የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሸን አዋጅ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በውስጡም የኤሌክትሮኒክ ንግድ (Electronic Commerce) እና የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎት (Electronic Government) የተባሉ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን አካቷል።
ወረቀትን ማዕከል ባደረገው የንግድና የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓት ውስጥ ውሎች ሕጋዊ ውጤት እንዲ ኖራቸው መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በኤሌክትሮኒክ ንግድና በኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎቶች ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ተመሳሳይ ናቸው።
ይሁንና አንዳንድ አገራት ለንግድና ለመንግሥት አገልግሎት ሁለት የተለያዩ አዋጆች ያወጣሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት አዋጁን ለማዘጋጀት ባደረገው ጥናት በአገራቱ የወጡት ሁለቱ የተለያዩ ሕጎች ፍፁም የሚባል የይዘት መመሳሰል እንዳላቸው አረጋግጧል።
እንዲህ ከሆነ ደግሞ ለሁለቱ ጉዳዮች ሁለት የተለያዩ ሕጎችን ከማውጣት ይልቅ ምሉዕ የሆነ ሁሉን አቀፍ አንድ ሕግ ማውጣቱ ተመራጭ እንደሚሆን እሙን ነው።
በርካታ አገራትም የኤሌክትሮኒክ ንግድ አዋጅን እና የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎቶች አዋጅን በአንድ በማጣመር የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን የሚል ስያሜ በመስጠትና አዋጅ በማውጣት ወደ ሥራ ገብተዋል።
በዚሁ መነሻ ረቂቅ አዋጁ ወረቀትን ማዕከል ያደረጉ ሰነዶችን፣ ኢንፎርሜሽኖችን እንዲሁም ኮምፒውተርን ማዕከል ያደረጉ ሰነዶችንና ኢንፎርሜሽኖችን የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በእኩል እንዲስተናገዱ የማድረግ ዓላማን ሰንቋል።
ከዚህም ሌላ የኤሌክትሮኒክ ንግድ በራሱ የገበያ አማራጮችን የሚያሰፋ መሆኑን መነሻ በማድረግና ዜጎችን በኢኮኖሚው ውስጥ በማካተት ኢትዮጵያ የዲጂታል ዘመንን እንድትቀላቀል የማስቻል ዓላማም አለው።
ከኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ አንፃር ደግሞ የመንግሥት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ መስጠት ቢጀምሩ በየደረጃው ውጤታማና ተጠያቂ መንግሥታዊ ተቋሞችን መገንባት እንደሚያስችል አዋጁ ታሳቢ ያደርጋል። በዚህም መልካም አስተዳደር እንደሚሰፍን በማመን።
አዋጁ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ሁኔታዎች
ረቂቅ አዋጁ በኤሌክትሮኒክ ንግድ፣ በኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎቶች፣ በኤሌክትሮኒክ መልዕክቶች፣ ለአገር ወይም ለድርጅት ተለይቶ በሚሰጥ የኤሌክትሮኒክ መለያ (ዶሜይን ስም) አስተዳደር፣ ማኔጅመንትና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል።
የኤሌክትሮኒክ ንግድ እና የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት አገልግሎቶችን በተመለከተ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባ መሠረታዊ ነጥብ ሰዎች ግብይት ለመፈፀምም ሆነ ከመንግሥት ተቋማት አገልግሎቶችን ለመቀበል የኤሌክትሮኒክ መልዕክቶችን እንዲጠቀሙ ማስገደድ እንደማይቻል በአዋጁ መደንገጉን ነው። እናም ግለሰቦች በዚህ ረገድ ፈቃዳቸውን ሊሰጡ ይገባል።
አዋጁ ጋብቻና ፍቺ እንዲሁም የኑዛዜ አሰጣጥ አይሸፈንም። በተጨማሪም የፍርድ ቤት ትዕዛዞች፣ በማይንቀሳቀሱ ንብረት ዙሪያ የሚደረጉ ግብይቶችና የውክልና አሰጣጥ ሥርዓቶች ቀድሞ እንደነበረው ወረቀትን ማዕከል በማድረግ የሚፈፅሙ እንጂ ኮምፒውተርን ማዕከል በማድረግ እንደማይፈፀሙም ተደንግጓል።
በመሆኑም እነዚህ ጉዳዮች በኤሌክትሮኒክ ቢፈፀሙ በሕግ ፊት አይፀኑም። በሕግ ፊት የፀኑ እንዲሆኑ የጉዳዩ ባለቤቶች በሕግ ሥልጣን በተሰጠው አካል ፊት መቅረብና ፈቃዳቸውን ግልጽ በሆነ መንገድ መስጠት ይገባቸዋል።
የኤሌክትሮኒክ መልዕክቶችና ሕጋዊ ውጤታቸው
በረቂቅ አዋጁ በተሰጠው ትርጓሜ መሰረት የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ማለት በኤሌክትሮኒክ መንገድ ወይም በሌሎች ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት የመነጨ፣ የተላከ፣ የደረሰ ወይም የተከማቸ ኢንፎርሜሽን ነው።
በንግዱ ተዋንያን እንዲሁም በመንግሥት አገልግሎት ሰጪዎችና ተገልጋዮች መካከል የሚደረገው የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ልውውጥ ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ አዋጁ መስፈርቶችን አስቀምጧል።
ሕጋዊ ዕውቅና መስጠትን በተመለከተ አዋጁ ”ኢንፎርሜሽን በኤሌክትሮኒክ መልዕክት ይዘት መቅረቡ ሕጋዊ ውጤት እንዳይኖረው አያደርግም” የሚል መርህ አስቀምጧል። ይህም የኤሌክትሮኒክ መልዕክቶች በወረቀት ላይ ከሰፈሩ መልዕክቶች እኩል ሕጋዊ ዕውቅና የሚሰጥ መርህ ነው።
መልዕክት በሁለት መንገድ ሊቀረፅ ይችላል። አንደኛው ወረቀትንና ኮምፒውተርን ማዕከል ባደረገ መንገድ ነው። አሁን በሥራ ላይ ባለው ሥርዓት ደግሞ ወረቀትን ማዕከል ያደረገ ኢንፎርሜሽን በሕግ ፊት ተቀባይ እንደሆነ በተለያዩ ሕጎች ተደንግጎ እናገኛለን።
በመሆኑም የአሁኑ ሕግ ኢንፎርሜሽን ሕጋዊ ዋጋ እንዳይኖረው የቀረበበት መንገድ ከልካይ ምክንያት እንዳይሆን አድርጓል። ከዚህ በኋላም በኤሌክትሮኒክ መልክ የቀረበ ኢንፎርሜሽን በወረቀት ላይ ከቀረበ እኩል ዋጋ ይኖረዋል ማለት ነው።
በተጨማሪም አንድ ኢንፎርሜሽን በኤሌክትሮኒክ መልዕክት ውስጥ ተካቶ አለመቅረቡና ነገር ግን ይህ ኢንፎርሜሽን በዚህ መልዕክት ውስጥ መጠቀሱ ሕጋዊ ውጤት እንዳይኖረው እንደማያደርግም አዋጁ ያስቀምጣል።
መንግሥት ለፓርላማው ባቀረበው ማብራሪያ እንደገለፀው ይህ መርህ የሚመለከተው በኤሌክትሮኒክ መልዕክት ውስጥ በቀጥታ ያልተካተቱ ነገር ግን በተዘዋዋሪ በዚህ መልዕክት የተካተቱ ኢንፎርሜሽኖችን ናቸው።
ለምሳሌ በወረቀት ሥርዓት ውስጥ አባሪ (attachment) በማያያዝ ሌሎች ኢንፎርሜሽኖችን ለማጣቀስ የሚቻልበት አግባብ አለ። በተመሳሳይ በኮምፒውተር ሥርዓት ተጨማሪ ኢንፎርሜሽን አባሪ ከማድረግ ባሻገር በዋናው መልዕክት ውስጥ ሊንክ በማስቀመጥ ተጨማሪ ኢንፎርሜሽን ማድረስ የሚቻልበት ሥርዓት አለ።
ይህ መርህ የሚመለከተው ታዲያ እንዲህ ዓይነት የዋናው መልዕክት ተቀጥያ ኢንፎርሜሽኖችን ነው። በዚሁ መሠረት እንደነዚህ ዓይነት ኢንፎርሜሽኖች በዋናው የኤሌክትሮኒክ መልዕክት ተካተው አለመቅረባቸው ሕጋዊ ውጤት እንዳይኖራቸው አያደርግም።
ሕጉ በመርህ ደረጃ ይህንን ካስቀመጠ በኋላ አንድ ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታንም አስከትሏል። ይህም እነዚህ ኢንፎርሜሽኖች ለተላከለት ሰው ተደራሽ የመሆናቸው ጉዳይ ነው።
እናም እንደነዚህ ዓይነት ኢንፎርሜሽኖች ለተላከለት ሰው ተደራሽ እስከሆኑ ድረስ የተላኩበት አግባብ በኤሌክትሮኒክ መሆኑ ሕጋዊ ውጤት እንዳይኖራቸው አያደርግም።
ከሕጋዊነት ጋር ተያይዞ ሌላው የሚነሳው ጉዳይ የኤሌክ ትሮኒክ መልዕክቶች የማስረጃነት አቅም ነው። በአገራችን ራሱን የቻለና የተጠቃለለ የማስረጃ ሕግ ባለመኖሩ የሰነድም ሆነ የትኞቹንም ዓይነት ማስረጃዎች አግባብነትና ተቀባይነት ላይ በፍርድ ቤቶች ብርቱ ክርክር ይደረጋል።
ረቂቅ አዋጁ ታዲያ የኤሌክትሮኒክ መልዕክቶች በፍርድ ክርክርም ሆነ በማንኛውም የሕግ ሂደት ተቀባይነት እንዳላቸውና እንደ ማስረጃ ሊቀርቡ እንደሚችሉ በመደንገጉ ሙግቱን ከወዲሁ ይቀጨዋል።
የጽሑፍ ነገር በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን
በአገራችን ብሒል “’ምንና’ ወረቀት የያዘውን አይለቅም” ይባላል። ወረቀትን ማዕከል ባደረገ ሥርዓት ኢንፎርሜሽን በጽሑፍ እንዲቀርብ ከሚፈለግባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ወረቀት የያዘውን ስለማይለቅ ነው።
ለምሳሌ ከውል አንፃር ውል በጽሑፍ እንዲቀመጥ የሚፈለገው ተዋዋይ ወገኖች ውል በፈፀሙ ጊዜ የነበራቸው ፍላጎት ምን እንደሆነ ለማየት የተሻለው መንገድ ስለሆነ ነው።
ውል በጽሑፍ መቀመጡ ተዋዋይ ወገኖች የገቡት ውል ሕጋዊ ውጤቱ ምን እንደሆነ በቀላሉ እንዲያውቁት ያደርጋል። ከዚህም ሌላ በወረቀት ላይ የሰፈረ ኢንፎርሜሽን በጊዜ ብዛት የማይቀየር በመሆኑ ለማስረጃነት ያገለግላል። በተለይ በወረቀቱ ላይ የሰፈረው ኢንፎርሜሽን በፊርማና በማኅተም የተረጋገጠ ከሆነ ጉልበቱ ከፍተኛ ነው።
የኤሌክትሮኒክ መልዕክት በዚህ ልክ ጠቀሜታ እንዲኖረው ለማድረግ አዋጁ እውቅና የሚያገኝበትን አግባብ አስቀምጧል። በዚሁ መሠረት ማንኛውም ኢንፎርሜሽን በጽሑፍ እንዲቀርብ በሕግ ግዴታ የሚጣለው ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው።
የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ ኢንፎርሜሽኑ ተቀባይነት እንዲያገኝ በኤሌክትሮኒክ መልክ የቀረበ ወይም የተቀመጠ መሆኑ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ከቴክኖሎጂ አንፃር የኤሌክትሪክ፣ የማግኔታዊ፣ የኦፕቲካል ወይም ሌላ ተመሳሳይ አቅም ያለው የመጠቀሚያ መንገድ ማለት እንደሆነ ትርጓሜ ተቀምጧል።
ስለዚህ ኢንፎርሜሽኑ በኤሌክትሮኒክ መልክ ቀረበ ወይም ተቀመጠ ማለት በኮምፒውተር ውስጥ ወይም በሌሎች መሣሪያዎች ማለትም በሲዲ፣ በፍላሽ ዲስክ፣ ወዘተ ቀርቧል ወይም ተቀምጧል ማለት ነው።
ሁለተኛው መስፈርት ተደራሽ ከመሆን ጋር የተያያዘ ነው። በኤሌክትሮኒክ መልክ የቀረበው ወይም የተቀመጠው መልዕክት ተደራሽ መሆን መቻል አለበት።
ይህ ማለት ኢንፎርሜሽኑ ሊነበብ የሚችል ወይም በሌላ አገላለጽ ዜሮንና አንድን መሠረት ካደረገው ከኮምፒውተር ቋንቋ ወጥቶ ሌሎች ሊረዱትና ሊያነቡት በሚችሉት ቋንቋዎች ሊቀርብና ተደራሽ ሊሆን የሚችል መሆን ነው።
ሦስተኛው መስፈርት ኢንፎርሜሽኑ በቀጣይ ለማመሣከሪያነት ሊውል የሚችል ሊሆን የሚገባው ሲሆን ይህም በኤሌክትሮኒክ የቀረበው ወይም የተቀመጠው ኢንፎርሜሽን በጊዜ ብዛት ያልተቀየረ መሆኑን ለማረጋገጥ እንጂ፤ ኢንፎርሜሽኑ ሦስተኛ ወገኖች በክፉ ልቦና የማይቀይሩት እንዲሆን ተደርጎ መዘጋጀት አለበት የሚል ግዴታ ለመጣል እንዳልሆነ ለፓርላማው ከቀረበው ማብራሪያ መረዳት ይቻላል።
እናም ኢንፎርሜሽን ለውጥ የተደረገበት መሆኑን ከሰነዱ ማየት እስከተቻለ ድረስ ለውጥ የተደረገበት መሆኑ ኢንፎርሜሽኑ በጽሑፍ እንዲቀርብ የተጣለውን የሕግ ቅድመ ሁኔታን አልተሟላም የሚል መደምደሚያ እንድንይዝ አያደርግም።
ፊርማና የኤሌክሮኒክ ትራንዛክሽን
ፊርማ በወረቀት ሥርዓት ውስጥ የፈረመውን ሰው ማንነት ለማወቅ ይረዳል። ይህም በቅድሚያ ፊርማን በማኖር ሂደት ውስጥ ግለሰቡ በቀጥታ ተሳታፊ የነበረ መሆኑን ለማረጋገጥ ያገለግላል።
በመቀጠል ፈራሚው በፊርማው ካረጋገጠው ሃሳብ ወይም በሰነዱ ላይ ካረፈው ይዘት ጋር ያለውን ተያያዥነት ለማረጋገጥ ይረዳል።
በንግድና በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ነገር የሆነውን የፊርማን ጉዳይ ታዲያ በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን ውስጥ የሚኖረውን ሥፍራ አዋጁ በግልጽ አስቀምጧል።
በዚሁ መሠረት ማንኛውም ሰነድ ፊርማ እንዲያርፍበት ሕግ ግዴታ ከጣለና የትኛው ፊርማ ተቀባይነት እንዳለው ሕጉ ካልገለፀ በሕግ የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ እንደተሟላ የሚቆጠረው ልክ እንደ ጽሁፍ ሁሉ ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው።
የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ በኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ ውስጥ ፊርማውን ያኖረውን ግለሰብ ማንነት ለማወቅ የሚያስችል ዘዴ መኖሩ ነው።
ሁለተኛው በኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ ውስጥ የተካተተው ኢንፎርሜሽን በግለሰቡ የፀደቀ መሆኑን የሚያመላክት ዘዴ ጥቅም ላይ የዋለ መሆኑ የሚሉ ናቸው።
ሦስተኛው ቅድመ ሁኔታ የፈራሚውን ማንነትንም ሆነ ፈራሚው የመልዕክቱን ይዘት ያረጋገጠ መሆኑን የሚያሳየው ዘዴ የኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ ለመነጨበት እና ኮሙኒኬት ለተደረገበት ዓላማ አስተማማኝና ተስማሚ ሆኖ የቀረበ መሆኑን የተመለከተው ሁኔታ ነው። ይህ ዘዴም በተዋዋይ ወገኖች በስምምነት ሊወሰን የሚችል ነው።
እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች የሚያሟላ ፊርማ ታዲያ በረቂቅ አዋጁ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ በመባል ይጠራል።
የኤሌክትሮኒክ ፊርማ የሚለውን ሲተረጉመውም ከኤሌክትሮኒክ መልዕክት ጋር በተያያዘ ፈራሚውን ለመለየትና በኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ ውስጥ የተካተተው ኢንፎርሜሽን በፈራሚው የፀደቀ ወይም ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ለማመልከት ጥቅም ላይ የሚውል በኤሌክትሮኒክ መልዕክት ውስጥ ያለ፣ በኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ ላይ የተለጠፈ ወይም ከኤሌክትሮኒክ መልዕክቱ ጋር ምክንያታዊ በሆነ አኳኋን የተቆራኘ በኤሌክትሮኒክ መልክ ያለ ኢንፎርሜሽን ነው በማለት ደንግጓል።
በዚህ ትርጓሜ መሠረት የኤሌክትሮኒክ ፊርማ በራሱ ኢንፎርሜሽን ነው። ይህን ኢንፎርሜሽን በተመለከተ በምን አግባብ እንደሚመነጭ፣ ከመልዕክት ጋር እንዴት እንደሚቆራኝ፣ በምን አግባብና በማን እንደሚዘጋጅ እንዲሁም ሕጋዊ ውጤት እንዴት ሊኖረው እንደሚችል ራሱን የቻለ ዝርዝር አዋጅ በቅርቡ ወጥቶለታል።
ይህም የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ቀጥር 1072/2010 በመባል ይታወቃል። የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን ረቂቅ አዋጅም ይህን የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ እንዳለ ተቀብሎታል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2012
ከገብረክርስቶስ