ባለፈው ዓመት ከተለያዩ ሀገራት የመጡ 934ሺ ቱሪስቶች በኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታዎችንና የማይዳሰሱ ቅርሶች ቢጎበኙም ከቱሪዝሙ የሚገኘው ገቢ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ያለው አስተዋጽኦ በመረጃ እንደማይታወቅና ዘርፉ እንዳልተሰራበት ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ታደለ ጀማል «በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አንድ ቱሪስት በቀን በአማካይ 230 ዶላር ወጪ ያደርጋል ተብሎ የሚታሰበውን፤እንዲሁም የቆይታ ጊዜውን ወደ 16 ቀናት ከፍ በማድረግ ገቢን ለማሳደግ አንድ ሚሊዮን የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስጎብኘት ቢታቀድም በሀገሪቷ በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችና በተለያዩ ምክንያቶች ማሳካት አልተቻለም፡፡የቱሪስት ፍሰት ዕድገቱም ከዓመት ዓመት አይራራቅም፡፡ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፈው ዓመት 3ነጥብ5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ከመግለፅ ውጪ ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያበረከተ ስላለው አስተዋጽኦ በጥናት የተደገፈ መረጃ የለውም» ብለዋል፡፡
ሃይማኖታዊ ጉዞዎች በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸው ሚና በተለምዶ ከሚነገረው ውጪ እንዳልሆነ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምሪያ ማህበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማዕከል ፀሐፊ አቶ ካሳሁን ኃይሌ ይገልጻሉ፡፡
እርሳቸው እንዳሉት ለትራንስፖርት፣ለምግብ፣ ለወንበር፣ለድንኳን፣ለድምጽ ማጉያ፣ለቀረጻ ለሚሆን ወጪ እያንዳንዱ ተጓዥ 230ብር እንዲከፍል ይደረጋል፡፡በዚህ መልኩ በተለያየ የጉዞ መርሐግብር በዓመት ሁለት ጊዜ በሚከናወነው ጉዞ የሚሳተፈው 18ሺ ያህል ምዕመን በግሉ ከሚያበረክተው እጣንና ጧፍ ውጪ መንፈሳዊ ትምህርት በሚሰጥበት ቦታ ለቤተክርስቲያን ልማት በአንድ ቀን ውስጥ ከሁለት መቶ ሺ እስከ ሰባት መቶ ሺ ብር ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ይሁን እንጂ ለጉዞ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን በበቂ የሚያቀርብ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ በአንድ ጊዜ ከ13ሺ በላይ ምዕመናን እንዳይጓዙ ገደብ በመደረጉ የብዙ ሰው ፍላጎትን ማሟላት አልተቻለም፡፡በከተማዋ ውስጥ በአንድ ጊዜ 10ሺ እንጀራና ዳቦ አቅራቢ የለም፡፡የተለያዩ ግዳጆች ሲኖሩ በአንድጊዜ 60 ሰዎችን የሚይዝ ተሽከርካሪ ማግኘትም እንደሚያስቸግር አቶ ካሳሁን ኃይሌ ያስረዳሉ፡፡
በቅርቡ ዳካር የተሾሙት አምባሳደር ሀሰን ታጁ ከቱሪዝም መዳረሻዎች ጋር በተያያዘ ከአንድ ዓመት በፊት የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ባዘጋጁት ዓውደጥናት ላይ ያቀረቡትን የመነሻ ጽሁፍ መሰረት አድርገው እንዳስረዱት፤ የእምነት አካባቢዎች ከቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
አልነጃሺን ከጎረቤት ሀገሮች ከሴኔጋል ፣ከሱዳን፣ከኬኒያ፣ከኢንዶኔዥያ፣ከፓኪስታን፣ከቱርክና ከህንድ ሳይቀር ለመጎብኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ ፣በኢትዮጵያ አየር መንገድ አቋርጠው ወደሌላ ሀገር የሚሄዱ 22ሺ የሚደርሱ ተጓዦች አልነጃሺን እንዲጎበኙ ሁኔታዎች ቢመቻቹ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ጥናቱ ያስረዳል፡፡
የሃይማኖት ተጓዦች ብዙ ምቾት አይፈልጉም፡፡ ስፍራዎችንም ለማስተዋወቅ ድካም አይጠይቅም፡፡ ስፍራዎቹን ምቹ ማድረግ የሚጠይቀው ወጪ አነስተኛ ነው፡፡አሁን ባለው የእምነቱ ተከታዮች የአካባቢውን ነዋሪዎች ቤት በመከራየት ነው ቆይታ የሚያደርጉት፡፡እርድም በግላቸው በማከናወን ይጠቀማሉ፡፡የእምነት ቦታዎችን ማደራጀት ከተቻለ እንደ አልነጃሺ ካሉ ትላልቅ ቦታዎች በተጨማሪ በእስልምናው በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያና በሌሎችም የሀገሪቷ ክፍሎች ብዙ የቱሪስት መስህብ የሚሆኑ ቦታዎች አሉ፡፡በአልነጃሺ ብቻ በዓመት ሦስት መቶ ሺ ቱሪስቶችን ማምጣት የሚቻልበት ዕድል ቢኖርም፤ ቱሪዝም ከፋይ የሆነ ዘርፍ ሆኖ በኢትዮጵያ በአግባቡ እንዳልተሰራበት ይገልፃሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊና የዘርፉ ባለሙያ አቶ ስለሺ ግርማ እንዳሉት፣ ቱሪዝም ኢኮኖሚን በማመንጨት ድርሻው የጎላ ነው፡፡አንድ ቦታ የሚገኙ 10 ቱሪስቶች ለአንድ ዜጋ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ ሰፊ የቱሪስት ፍሰት ሲኖር ደግሞ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠራል፡፡
የዘርፉ ተዋናይ የሆኑት ሆቴል ቤቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የስጦታ ዕቃ መሸጫ ሱቆችና ሌሎችም ከቱሪዝሙ ከሚያገኙት ገቢ ግብር ሲከፍሉ የመንግሥት ገቢ ያድጋል፡፡ ቱሪስቶች የሚጠ ቀሙት የስጋና የዶሮ ውጤቶች፣አትክልትና ፍራፍሬ አርሶአደሩ አምርቶ የሚያቀርባቸው በመሆኑ በተዘዋዋሪ አርሶአደሩ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ቱሪስቶቹ ለሚያገኙት አገልግሎት ለአስተናጋጆች የሚሰጡት ጉርሻም ዋጋ አለው፡፡በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ላለባት ሀገር ቱሪዝም ለኢኮኖሚው ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡
ለንግድ፣ዘመድ ጥየቃ፣ለስብሰባ፣ለመዝናናት በጥምቀትና በገና በዓላት እንዲሁም ወደሌላ ሀገር ለመሸጋገር የሚመጡ ቱሪስቶች መኖራቸው ቢታወቅም በተለያየ መንገድ የሚገቡ መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ስለሺ የመቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ ቱሪዝም በኢትዮጵያ ለማኑፋክቸሪንግና ለተለያዩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ትኩረት ተሰጥቶ ማበረታቻ አልተደረገለትም፡፡ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ተጠሪ ለሆኑ ተቋማት የሚመደበው ዓመታዊ በጀት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አይደለም፡፡ቱሪዝም እንደማህበራዊ ዘርፍ የሚታይ ነው፡፡ በመንግሥት ቱሪዝምን የማሳደግ ፍላጎት አለ፡፡ ቁርጠኝነቱ ግን የለም፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት በዓመት ሁለት ጊዜ በሚዘጋጅ መንፈሳዊ ጉዞ በአንድ ቀን 13ሺ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እንደሚጓዙ፤በአማራ ክልል ወልዲያ ዳና በተባለ አካባቢ በመውሊድና በአልነጃሺ በአሹራ በዓላት ከአንድ መቶሺ በላይ የሙስሊም እምነት ተከታዮች በስፍራው ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንደሚያካሂዱ መረጃዎች ያመለክ ታሉ፡፡
የቱሪስት መዳረሻዎችን አልምቶ ምቹ ከማድረግ ጀምሮ ቱሪስቱን በማቆየት ላይ አሰራሩ ደካማ ነው፡፡ከሁለት ዓመት በፊት ያሉት መረጃዎች የሚያሳዩት በሀገር ደረጃ 750ሺ ቱሪስት ነው መሳብ የተቻለው፡፡ከኢትዮጵያ ያነሰ የቱሪስት መዳረሻ ካላቸው ሀገሮች ጋር ሲነጻፀር በዘርፉ አልተሰራም፡፡ቱርክ፣ግብጽ፣ደቡብ አፍሪካ፣ናይጄሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን በመሳብ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪዝም መስህብ ሀብት ቢኖራትም መጠቀም የሚገባትን ያህል መጠቀም ባለመቻሏ በዘርፉ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሊታይ አልቻለም፡፡ የቱሪዝሙ መዳከም በዚሁ እንዳይቀጥል የሚመለከታቸው አካላት ካሸለቡበት መንቃት ይኖርባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 10/2011
ለምለም መንግስቱ