‹‹ሠርግና ሞት አንድ ነው›› የሚል ተረት እናውቃለን። እውነት ነው ሠርግም ሀዘንም የሰዎችን ስብስብ፣ መተጋገዝ እና መረዳዳትን ይጠይቃሉ። በሠርግም ሆነ በሀዘን ወቅት መሰባሰብና መረዳዳት አለ። በሠርግ ደስታን መጋራት እንዲሁም ሀዘንተኛን ማስተዛዘኑ፤ በጋራ እንግዳን መሸኘቱ የባህላችን መገለጫ ነው። በእነዚህ ወቅት ወዳጅ የሚታይበት ተደርጎ ይቆጠራል። ማን ነበር ከጎኔ የቆመ ተብሎም ወዳጅን ከሌላው ለመለየትም ይሞከራል።
ሁለቱም ተግባራት ሲከወኑ ብዙ ወጪን አስወጥተው በማህበራዊ ትስስር እስከመጨረሻው የሚዘልቁ ናቸው። ይህ ደግሞ በማህበረሰቡ እምነት መሰባሰብን ፈጥሮ ግንኙነትን ያጠናክራል። አሁን አሁን ግን ይህን ማድረግ አዳጋች ሆኗል። ምክንያቱም ዓለምን እያስጨነቀ ያለ ማህበራዊ ግንኙነትን የሚገድብ በሽታ ኮሮና ተከስቷል። ዘመነ ኮሮና ብዙዎችን ለችግር ተጋላጭ ያደርጋል። እናም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ፍቅርና መተሳሰብ ቀጣይነት እንዲኖረው ዛሬን ረገብ አድርጎ ለነገ መሰነቅ ይገባል።
በእርግጥ ማህበረሰባችን ‹‹ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል›› የሚል ብሂል አለው። በዚህም የተነሳ ማንኛውንም ነገር በተናጠል ማድረግን አይሻም። ለዚህ ነው ሠርጉንም ሆነ ሃዘኑን በጋራ የሚፈፅመው። የሠርግ ሥነ ሥርዓት ሲፈፀም ለብቻ መብላት፣ ለብቻ መደገስ፣ ለብቻ መጨፈርና ለሽምግልና መሄድ አይቻልም። ዘመድ አዝማድ ጎረቤት ተጠራርቶ የቻለውን ሁሉ አዋጥቶ ደስታውን በባህላዊ ጭፈራ አድምቆ ሥርዓቱን ያሳልፋል።
በተመሳሳይ በለቅሶ ሥርዓቱም እንዲሁ አስከሬን ተሸክሞ ከመሄድ ጀምሮ መተጋገዝና መሰባሰብን ይጠይቃል። እንግዲህ እነዚህና ሌሎችም እንደየ አካበቢውና ባህሉ የሚካሄዱ የደስታና የሀዘን ወቅቶች ዛሬ በገጠመን የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ ጎን እያልናቸው ነው። ምክንያቱም ባህል አለን የምንለው የነበረንን ዛሬም ያለንን ብቻ ሳይሆን ለነገ የሚተርፈውን ጭምር ነውና ነገ ላይ ለመድረስ ዛሬ ባህላዊ ክዋኔዎቻችንን በጋራ ከማድረግ መቆጠብ የግድ ይሆናል።
በዛሬው የባህል አምዳችን ላይ በነዚህ ባህላዊ ይዘት ያላቸው ክንውኖች ላይ ማተኮር ወደናል። ሥርዓቱን፣ ወጉንም ሆነ ልማዱን የግዴታ መከወን ካለብን ደግሞ በዘመነ ኮሮና እንዴት ይከወን? ስንል በባህል ዙሪያ እየሠሩ ያሉ አካላትን አነጋግረናል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል እሴት ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ እስከዳር ግሩም፤ ኮሮና ካላወቅንበትና እያሰብን ካልተራመድን ለሁሉም ባህላዊ ክዋኔዎች መቁረጫ ምሣር ሊሆንብን ይችላል ይላሉ። አሁን እንኳን በጥቂቱ ብናይ የባህል ኢንዱስትሪውን ክፉኛ ጎቶታል። ለዓለም ተምሳሌ የምንሆንበትን የአንድነትና የብዝሃነት እሴታችን ላይ ነው አደጋ የጋረጠው። ለዚህ ደግሞ ተጠንቅቆ መራመድን ይጠይቃል። በመሆኑም ‹‹ቀን እስኪያልፍ የአባቴ ባሪያ ይግዛኝ›› ነውና ነገሩ ችግሩ እስኪያልፍ ሁነቶችን መግታት ይገባል።
‹‹በአካል ተራርቆ በሀሳብ መተጋገዛችንን፣ መተባበርና መተሳሰባችን ግን ማጠንከር ይኖርብናል›› የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ ይህንን ባህላችንን መልሰን ለማምጣት ያግዘናልና ይላሉ፤ መተጋገዛችን በርቀት ይጠበቅ የሚል መልክትም ያስተላልፋሉ። ሠርግ፣ መልስ፤ ቅልቅል እያለን እናሳልፍ የነበረው ደስታ ነገ እንዲሰፋና እንዲጠብቀን ዛሬ እንጠብቀው። በባህላችን አብሮነት የሚጀምረው ጎረቤትን ቡና ጠጡ ከማለት ነው። ይህንን መከልከል ደግሞ ሥነ ልቦናዊ ጫና ብቻ ሳይሆን ብቸኝነትንም ያመጣል። ግን ጊዜ እስኪያልፍ የግዴታ መፈፀም አለበት ይላሉ።
ምርጫው መሞት ወይም መዳን ለሆነ ጉዳይ ቅሬታና ቅያሜ አያዋጣም የሚሉት ወይዘሮ እስከዳር፤ ለቅሶ አለመድረስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያቀያይማል ብቻም ሳይሆን ያቆራርጣል። አሁን ግን እንዲህ የምንባባልበት ወቅት ላይ አይደለንም። ይሄንን ሁሉም ሰው የሚረዳው በመሆኑ በሰለጠነ አስተሳሰብ ሀዘንን በስልክ ልንደርስ ይገባል። የቅርብ ሰዎች ደግሞ ቀብሩን ለቀብር አስፈፃሚው ሁኔታዎችን በማመቻቸት የቤተሰብ አባላት ብቻ ጥንቃቄ አድርገው እንዲሸኙ ማስቻል ያስፈልጋል የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ።
‹‹ጊዜ እስኪያልፍ ያለፋል›› እንዲሉ አበው ይህ የከፋ ጊዜ በቃ እስኪለን ድረስ ብዙዎችን ለማትረፍ ቅሬታ
ይቅር። ስለሚወዱን እንጂ ስለሚጠሉን አራቁንምና እንውደዳቸው›› የሚሉት ወይዘሮ እስከዳር፤ ችግሩ እንዳይሰፋ እንደባህልና ቱሪዝም የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ ይናገራሉ። ለአብነት በቅርቡ ከአዲስ አበባ እድር ዳኞች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ያነሳሉ። በዚህም ሰዎች ቅያሜን አንስተው በሠርጉም ሆነ በሀዘኑ ወረርሽኙን እንዲቀንሱ የሚደረግበትን መንገድ ቀይሰዋል። ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይም የተቻላቸውን እንደሚያደርጉም ተግባብተዋል። ችግሩ የደረሰበት ሰው ሌሎች በህይወት እንዲኖሩ የማድረጉ ሃላፊነት ከፍተኛ ነውና የእድር ዳኞች ይህንን እንዲያደርጉም በማስተማር መግባባት ላይ መድረሳቸውን አጫውተውናል።
‹‹አሁን በባህላዊ መንገድ ነገሮችን እንዲያገናዝቡ መርዳት ግዴታ ነው። በዚህም ባህላዊ የማሳመኛ መንገዶችን ለመጠቀም አንዳንድ ጅማሮዎች አሉ›› በማለት የሚገልፁት ወይዘሮ እስከዳር፤ በዳጉና መሰል ባህላዊ ክዋኔዎች መረጃው እንዲተላለፍ እየተደረገ መሆኑን ያነሳሉ። በጡሩንባም ቢሆን ሀዘናቸውን በሚጋሩበት ልክ እንዲሰሙት የማድረግ ሥራም ተጀምሯል። ለዚህ ሥራ ተፈፃሚነት ክልሎች ወሳኝ በመሆናቸው ከእነርሱ ጋር እየተወያዩ መሆናቸውን አንስተዋል። በተለያዩ ቋንቋዎች እየተተረጎሙ መረጃዎች የሚደርሱበት ሁኔታም እየተሠራበት መሆኑን ይናገራሉ።
መሰባሰቡና በአንድነት ባህላዊ ሥርዓቶችን መከወኑ መልካም ቢሆንም ከጊዜው ጋር አብሮ መሄድና ራስን ከዘመኑ ጋር መዋጀት ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ የሚያነሱት ዳይሬክተሯ፤ ማህበረሰቡ ካለው ባህል አንፃር ማንኛውንም ነገር ብቻህን አድርግ ቢባልም አይዋጥለትም። የነበረበትን ባህልና ልምድ መተውም ይጨንቀዋል። ነገን ለመኖር ግን ዛሬን ማሰብ ያስፈልጋልና ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ።
‹‹ዛሬ ሳንጨባበጥ ብንቀር ነገ እንሳሳማለን፤ ዛሬ ሠርጋችንን ብንተወው ነገ ስላለን ልጃችንን ሻማ ያዢ አድርገን ፍቅራችንን እንገልፃለን። እናም የዛሬ መኖራችን ላይ መሥራት አለብን። ሠርጎች የተባረኩ የሚሆኑት በበጎ ተግባር ሲከወኑ በመሆኑም ግድ ማድረግ አለብን የሚሉ ደግሞ ለድግሳችሁ ያከማቹትን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች በመስጠት አብሮነታቸው ይግለፁበትና ይመረቁ›› ይላሉ።
በመኖራችን ዋጋ የምንጨምር ሰዎች የምንሆነው ራሳችንን ጠብቀን ነገን የሚያዩ ሰዎችን ስናበረክት ነው። ባህላችን ዘመን ተሸጋሪ በመሆኑ ብዙዎችን ይፈልጋቸዋል። በመሆኑም በአግባቡ ለዘመናት እንዲደርስ ትውልዱን፤ ተረካቢውን ዛሬ ልንጠብቀው ይገባል። ለሌሎች ፈተና ከመሆንም ራሳችንን መጠበቅና ተስፋ መስጠትም ይኖርብናል። ለዚህ ደግሞ ዋና መሣሪያችን መሆን ያለበት በጎነትና ለሌሎች መድረስ ስለሆነ ይህንን እናድርግም መልዕክታቸው ነው።
‹‹ኮሮና የመጣው የወል ባህልን በአንድ በኩል ሊያጠፋ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሊታደገው መሆኑን አስበን መረዳዳታችን ከልባችን መሆኑን ማሳየት አለብን›› የሚሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥናት ከፍተኛ ባለሙያው መምህር መክብብ ገብረማርያም ናቸው። እርሳቸው እንደሚያነሱት፤ ደስታ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ዝግጅቱም ልዩ ነው። በተለይም በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል በብዙ ነገሮች ማገዝ ግዴታም ውዴታም ነው። በመሆኑም ጋብቻ ሲመሰረት ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት ገና ሁለቱ አካላት ሲተሳሰቡ ጀምሮ መተጋገዝ ይጀመራል። ከብር መለዋወጡ በተጨማሪ እህልና መሰል ነገሮችም ጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ያዋጣል። በእያንዳንዱ ሁነት ሰብሰብ ብሎም ድግሱን ይደግሳል። ይህ ደግሞ መሰብሰብ ጠል ለሆነው ኮሮና ጥሩ ጊዜ መስጪያ ነው። ብዙዎችን በአንዴ በቫይረሱ የሚጠቁበትን ዕድል ያመቻቻል። ስለዚህ ይህንን ዘመኑ በሚፈቅደው ልክ ማየት ካልቻልን ቅርስ የሆነውን ሥርዓተ ጋብቻችንን ልናጣው እንደምንችልም ይናገራሉ።
ሠርግ ብሔር፤ እምነት፣ ቋንቋ አይገድበውም። ለአንዱ እምነት ተከታይ ሌላው ሚዜ የሚሆንበትን ዕድል የሚሰጥ ጭምር ነው። እናም በዚህ ግንኙነት ደግሞ ማህበራዊ ትስስርን ይበልጥ ያጠናክራል። በኮሮና መምጣት የተነሳ ብዙዎችን ክንዋኔዎች ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው ይላሉ።
ሠርግ ሲደገስ ብዙ ጊዜ ከማን አንሼ በሚል ነው። እናም ኮሮና ይህንን ነገር ለመሸፈን ጥሩ መፍትሄም ነው። ለድግስ የሚያውሉትን ገንዘብ የጎደለውን ለመሙላት ይጠቀሙበታል። የቀጣይ ህይወታቸውንም የተሻለ ለማድረግም ያስችላቸዋል። ከዚያ አለፍ ሲል ደግሞ በደንብ ደግሰው ይዳሩ ነበር በሚልም የሰውን ሽሙጥ ማለፍ ይችሉበታል። ከመቀያየምም ቢሆን ይተርፋሉ። ስለዚህ ችግሩ ለበጎም መጥቷል ብሎ ማሰብ እንደሚገባም ያስረዳሉ።
ለቅሶም ቢሆን እንዲሁ ከመርዶ ነገራው ጀምሮ ብዙ ንክኪ የሚፈጠርበት ክዋኔ ነው። በእድር አማካኝነት ብዙዎች ተሰባስበው በአንድነት የሚያስተዛዝኑበት፤ ችግርና ሀዘንን የሚጋሩበት ነው። ሁሉንም ብቻዬን ላድርገው ቢባል የማይቻልበት ነው። ሀዘን አብሰልሳይ ያደርጋል። አስከሬን ተሸክሞ ቤተ እምነቱ ማድረስ እንኳን የማይሆን ነው። እናም ለሰው መድሃኒቱ ሰው ነው እንዲሉ ዳግም ሌላ ሰው በዚህ አደገኛ በሽታ እንዳናጣ ነገሮችን በጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ።
የሽማግሌዎች ምክረ ሀሳብን፤ የእድር ዳኞችንና የሀዘንተኞችን አስተሳሰብ በመቀየርና የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ እንደነዚህ አይነት ክስተቶችን ያለችግር መወጣት እንደሚያስፈልግ የሚገልፁት መምህር መክብብ፤ አይመለከተኝም እኔ ጋር ብቻ አይምጣ እንጂ ማለት ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራሉ። የአንዱ መጎዳትና የታዘዘውን አለማድረግ ለሁላችንም ይተርፋልና ይታሰብበትም ይላሉ።
‹‹ህይወት የምትኖረውና የምትለመልመው ተስፋ ሲኖራት ነው። ይህ ተስፋ ደግሞ ከጥንቃቄ ይመጣል›› የሚሉት መምህር መክብብ፤ ለሌላ መኖር መጀመር እራስን ማቆየት እንደሆነ ይናገራሉ። ዛሬ ተለይተነው ያዘንበትን ነገ ይባሰ እንዳናዝን ዛሬን በዛሬ መነፀር ማየት ተገቢ ነው። ነገን የሚኖርበት ተስፋን ዛሬ መስጠትም ያስፈልጋል በማለት ይገልፃሉ። ባህላችን ቶሎ መርሳትን ባያስችለንም ‹‹እሺ ይበልጣል ከሺ›› ነውና በእሺታ አድርጉ የተባልነውን ማድረግ ነገን ለመመለስ ያስችለናልና እናድርገው የሚል መልዕክትም ያስተላልፋሉ። በማህበረሰቡ ዘንድ እጁ ያላረፈበት ነገር አያረካም። የራቀም ይመስለዋል። በዚህም በትንሹም ቢሆን ሠርግ ሲደገስ መሳተፍን ይፈልጋል። ግን ዛሬ ተው ማለት ያስፈልጋል። ስብሰባው ነገን ይቀማናልና እንታገስን ቅድሚያ ገንዘብ ማድረግ ይገባል።
በዘመነ ኮሮና ሙሽሮች ለተጋባዦቻቸው ተጋባዦች ደግሞ ለሙሽሮቹ አሳቢ መሆንም ይጠበቅባቸዋል። እደሰታለሁ ብሎ ማዘን እንዳይመጣም ቀድሞ መጠንቀቁ ተገቢ ነው። በችግሩም በደስታውም አብሮ ለመቆየት ዛሬ ይለፍ። ለዚህ ደግሞ ጥንቃቄውን ከልብ ማስተማርንና ማስረዳትን ይጠይቃል። አውቃለሁ በሚል ስሜት ሳይሆን አንተ ልክነህ ግን ይህ ቢሆን የተሻለ ነው በማለት የለመደውንና እንቢ የሚልበትን ተግባር ለጊዜው መግታት እንደሚያስፈልግም ነግረውናል።
አፋዊ ነገራችን ጠፍቶ የልብ መተሳሰብን ኮሮና ሰጥቶናል። ልቦች ከመጠን በላይ ሲቀራረቡ አጠገብ የሌለን ሰው ይበልጥ እንድናስበው ያደርገናል። ስለዚህም የልብ መቀራረብን ማጥበቅና በእገዛችን የሌሎችን ደስታ ልንሸምት ያስፈልጋል። በእኛ መኖር ሌሎች ተስፋ እንዲኖራቸውም ልናደርግ ይገባል። ደጋሽ መሆን ሌሎችን ለሞት መጥራት አይደለምና ይህንን እናስብበት መልዕክታቸው ነው።
እኛም ደስታን አብሮ መደሰት እንጂ አብሮ መጥፋት አይደለምና እውቅናውን ለነገ ማስቀመጥ ወይም ዛሬ ላይ በጥቂቶች ማድረግ ይገባል። መነካካትና ደስታን መገላለጽ በሌለበት እስክስታ ሀዘንን መግዛት የለበትምና ‹‹ጠንቀቅ ለነገ ህይወት›› በማለት ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው