በጥምቀት ህጻን አዋቂው አዲስ ልብስ ይለብሳል፡፡ አዲስ ልብስ መግዛት ያልቻለም ያለውን አጥቦ ለብሶ በዓሉን ለማክበር ይዘጋጃል። ኮበሌ ሽመልና ከዘራውን ወልውሎ ለጭፈራ ሲወጣ የዘመኑ አራዳም ሰልፊ ስቲኩን ይዞ ለፎቶ ይወጣል፡፡ ሰልፊ መነሳት የፊት ካሜራ ያላቸው ስልኮች ብቅ ካሉበት ወቅት ጀምሮ መዘውተር የጀመረ ልማድ ነው፡፡ ብሉቱዝ ካለው ከየትኛውም ሞባይል ጋር ተገናኝቶ አስገራሚ ምስሎችን ማንሳት የሚያስችል ሰልፊ ስቲክ በገበያው ሞልቷል፡፡
ለሰልፊ አፍቃሪዎች ትልቁ ሀብታቸው ስማርት ስልካቸው ነው፡፡ እጅግ ጠቃሚ የአካል ክፍሎቻቸው ደግሞ ጣቶቻቸው ናቸው፡፡ የሰልፊ ወዳጆች ስልክ ይዞ መግባት የሚከለከልባቸው ቦታዎች ላይ የመገኘት ፎቢያ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ሁሉን ነገር በሰልፊ ማስቀረት ይፈልጋሉ፡፡ ለቅሶ መድረሳቸውን ለማሳወቅ እንኳን ለቀስተኛና አስክሬን ፊት ቆመው ሰልፊ ተነስተው ፖስት ያደርጋሉ፡፡ በጥምቀትም ምንጣፍ ተሸክመው ከሚሯሯጡት እኩል ሰልፊ ለመነሳት የሚራወጡ፤ ቄጤማ ከሚጎዘጉዙት እኩል ሰልፊ ለመነሳት የሚጎዘጎዙ ወጣቶች ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡
በስልካቸው ሰልፊ ሲነሱ የሚያሳይ ፎቶግራፍ መነሳት ሙሽሮች ለሠርጋቸው ከሚነሷቸው ፎቶዎች አንዱ ሆኗል፡፡ ወንጀል እየፈጸሙ ሰልፊ ተነስተው ጀብዱ የፈጸሙ ያህል በኩራት ለጓደኞቻቸው የሚያሳዩ ሰዎችም አሉ፡፡ ከወራት በፊት በቡራዩ ጥቃት ያደረሱ ወጣቶች ጥቃት የደረሰበት ቦታ ላይ ሆነው ዱላ እንደያዙ ሰልፊ የተነሱት ፎቶ በወቅቱ በማህበራዊ ድረገጾች መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡
ከተሜ ሰልፊ የማይነሳበት ቦታ የለም፡፡ ሰልፊ ለመነሳት ብዙ መሰዋዕትነት ይከፈላል፡፡ አንዳንድ የሃይስኩል ተማሪዎች በእግራቸው እየሄዱ ለታክሲ የሚሰጣቸውን ገንዘብ አጠራቅመው የከተማው ተጠቃሽ ሬስቱራንት ውስጥ በርግር እየገመጡ ሰልፊ ተነስተው በርገሩን ሳይጨርሱ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ይለጥፉታል፡፡ ስንት ቀን ያጠራቀሙትን ገንዘብ ለአንድ በርገር ክፍያ ማዋላቸው የሚፈጥርባቸውን ብስጭትም በሚጎርፍላቸው የአድናቆት ኮሜንት ያክሙታል፡፡
የትም ቦታ ቢሆን በአጋጣሚ ያገኙትን ታዋቂ ሰው ለምኖ አንገቱን አንቆ ሰልፊ መነሳት ፋሽን ሆኗል፡፡ ቀደም ሲል ሰልፊ መነሳት የሚቻለው ከድምጻውያን፣ ከተዋንያን፣ ከስፖርተኞች፣ ከደራሲያን፣ ከቴሌቪዥን ቶክ ሾው አዘጋጆችና ከሞዴል አርሶ አደሮች ጋር ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከፖለቲከኞች ጋር ሰልፊ መነሳት ተጀምሯል፡፡ በተለይ ከተቋዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር ውጭ ሀገር ካልሆነ በቀር አይደለም ሰልፊ መነሳት ባሉበት አካባቢ መገኘት አስፈሪ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ነገሮች ተቀይርው የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን አቅፎ ሰልፊ የመነሳት ፉክክር ተጧጡፏል፡፡ በሥልጣን ላይ ካሉ የገዢው ፓርቲ ፖለቲከኞች ጋር ሰልፊ መነሳትማ ህልም ነበር፡፡ ምክንያቱም በቴሌቪዥን ካልሆነ በአካል ባለስልጣናቱን የማየት ዕድል እንኳን አልነበረም፡፡ ለዚህ እኮ ነው ‹‹እስኪ ና ዝቅ በል ውረድ ወደመሬት›› ተብሎ የተዘፈነው፡፡ ዛሬ ግን ከዶክተር አብይ ጋር ሰልፊ የተነሱ ወጣቶችን ፎቶ በተለያየ ጊዜ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ እያየን ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ምን ያህል ሊደሰቱና ኩራት ሊሰማቸው እንደሚችል ገምቱ፡፡
በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ጥምቀት ዋነኛ የመተጫጫ መድረክ እንደሆነ ይነገራል።
ለጥምቀት በዓል ያልዘፈነች ቆንጆ፣
ቆማ ትቀራለች እንደዘላን ጎጆ ፡፡ እየተባለም ይዘፈናል፡፡
አሁን አሁን በጥምቀት በሎሚ ውርወራ ተፈቃቅደው የተጋቡ ጥንዶች በዓመቱ ድንጋይ ተወራውረው ሲፋቱ እያየን ነው፡፡ ጥምቀት በገጠሩ ክፍል ብቻ ሳይሆን እንደ አዲስ አበባ አይነት ከተሞች ላይም የመተያያ መድረክ ነው፡፡ የተለያየ አካባቢዎች ባህላዊ አልባሳትንና በጥለት የደመቀ የሀገር ልብስን የለበሱ ቆነጃጅቶች ያንጸባርቁበታል፡፡ የደረሱ ወጣት ወንዶችም በእጃቸው ፕሪም ይዘው (የአዲስ አበባ ልጅ ፕሪም ነው የሚወረውረው) አይናቸው ሲንቀለቀል ይውላል፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያ አይን ተወርውሮ ለልብ መልዕክት ሲልክ ነው እጅ ሎሚ አሊያም ፕሪም የሚወረውረው፡፡ በለስ ቀንቷቸው ቀልባቸው አንዷ ላይ አርፎ ከተግባቧትም ፕሪም ይጋብዟታል፡፡ ከዛ በጥምቀተ ባህር ውስጥ እየተዘዋወሩ አብረዋት የተለያዩ ጨዋታዎች ላይ እየተሳተፉ ሰልፊ ስቲካቸውን እየመዘዙ ፎቶ ይነሳሉ፡፡
የስነልቦና ባለሙያዎች ሰልፊ መነሳትን ያለቅጥ ማዘውተር የስነልቦና ችግር አንድ ምልክት እንደሆነ ይነገራሉ፡፡ የበታችነት የሚሰማው ሰው ብቻ ነው ከፍ ያለ ቦታ ባየ ቁጥር ላዩ ላይ ቁጢጥ እያለ ሰልፊ ለመነሳት የሚዳደው፡፡ እንደ እኔ የበታችነት የሚሰማው ሰው ሰልፊ ከመነሳት ይልቅ አፓርታማ ላይ የመጨረሻውን ወለል ተከራይቶ (ገዝቶ) ቢኖር ይሻለዋል፡፡ ምክንያቱም ሰባተኛ አሊያም አስራ ሁለተኛ ፎቅ ሲኖር ህዝቡን እንደፈጣሪ ቁልቁል እያየ ከሚሰማው የበታችነት ስሜት ማምለጥ ይችላል፡፡ ደግሞም ወደሰማይ በቀረበ ቁጥር ጸሎቱ ቶሎ ተሰምቶለት ቤቱ በበረከት ይሞላል፡፡ በርግጥ ሀጢያቱም በቅርብ ታይቶ መርገምት ሊወርድብትም ይችላል፡፡
ሰልፊ መነሳት ሱስ ያስይዛል፡፡ ወደ ቅብጠትም ይመራል፡፡ ቅብጠት ደግሞ ጣጣ አለው፡፡ ‹‹የቀበጡ ዕለት ሞት አይገኝም›› ለሰልፊ አይሰራም፡፡ ሰልፊ ለመነሳት የቀበጡ ዕለት ሞት በሽ ነው፡፡ ሊያውም በሴኮንዶች ዕድሜ ያለስቃይ ነዋ፡፡ በኛ ሀገር መረጃ የመያዝ ባህል ባለመዳበሩ እንጂ ሰልፊ ለመነሳት ሲሞክሩ ህይወታቸውን ያጡ አሊያም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ‹‹ኦል ኢንዲያ ኢንሰቱቲዩት ኦፍ ሜዲካል ሳይንስ›› የተባለ ህንድ ውስጥ የሚገኝ የህክምና ባለሞያዎች ስብስብን የያዘ ተቋም በቅርቡ ይፋ ያደረገው አንድ ጥናት እንዳመላከተው እ.አ.አ. ከ 2012 እስከ 2018 መባቻ በዓለም ዙሪያ ሁለት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ሰዎች ሰልፊ ለመነሳት ሲሞክሩ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ምናልባት ለሀገራችን ሰልፊ አፍቃሪያን ትምህርት ሊሰጥ ይችላልና እስኪ ከሟቾቹ መካከል የጥቂቶቹን አሟሟት እንመልከት፡፡
ከኮርማ በሬ ለማምለጥ የሚደረግ ሩጫ ሰፔን ውስጥ እንደ ባህል የሚቆጠር ነው፡፡ በዚህ ባህላዊ ሩጫ የተሳተፈ አንድ ጎልማሳ ከሚያባርረው ግዙፍ ኮርማ በሬ ጋር ሰልፊ ለመነሳት ሲሞክር በሬው በቀንዱ አንስቶት ሩጫውን ጨርሷል፡፡ በምስራቃዊ የቻይና ክፍል ቺን የተባለ ሰው ቁልቁል በሚምዘገዘግ ረጅም ፏፏቴ ጫፍ ላይ በሰልፊ ስቲክ ፎቶ ለመነሳት ሲሞክር ወድቆ ፤ ፏፏቴው ስር ከእጅ ስልኩና ከሰልፊ ስቲክ ጋር ሞቶ ተገኝቷል፡፡ የአስራ ሰባት ዓመቱ ሮማኒያዊ ወጣት እየተጓዘ ባለ ባቡር ጣሪያ ላይ ሆኖ ሰልፊ ለመነሳት ሲሞክር ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የኤሌክትሪክ መስመር ነክቶ የህይወቱ መስመር ተቋጭቷል፡፡
ብራዚል ውስጥ አንድ ወጣት ሽጉጥ ራሱ ላይ ደቅኖ ሰልፊ ለመነሳት ሲሞክር ካሜራውን ተጫንኩ ብሎ ምላጩን ስቦ ራሱን ገድሏል፡፡ አሜሪካን ኮሎራዶ ግዛት ውስጥ የ29 ዓመቱ አብራሪ ፕሌኑን እያበረረ በሰልፊ ስቲክ ፎቶ ለመነሳት ሲሞክር የራሱን እና የተጓዦቹን ህይወት ቀጥፏል፡፡ ህንድ ውስጥ ሶስት የኮሌጅ ተማሪዎች በፍጥነት እየተጓዘ ያለ ባቡር ሲቃረብ ሃዲዱን በመዝለል ደፋር የሚያሰኝ ሰልፊ ለመነሳት ሲሞክሩ በባቡሩ ተገጭተው ወደኮሌጅ ሳይመለሱ ቀርተዋል፡፡
ሰልፊ መነሳት ተገቢ አይደለም እያልኩ አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር ልክ አለው ለማለት ነው፡፡ በጥምቀት በዓል ሰልፊ ለመነሳት ያቀዳችሁ ራሳችሁን ከአደጋ ጠብቁ ፡፡ በበዓሉ ለመታደም በጥምቀተ ባህር ከሚገኙ ዝነኞች ጋር ሰልፊ ለመነሳት ሰልፍ ሊኖር ስለሚችል በጊዜ ተገኝታችሁ ለጥምቀት ያልሆነ ሰልፊ ስቲክ ይሰባበር በሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011
የትናየት ፈሩ