ወሬና ማስጠንቀቂያው በየመገናኛ ብዙኃኑ ዘወትር ይነገራል። አምስት ሰው በወረርሽኙ መሞቱንም ቢሆን ሰምተነዋል። ግን በምን መልኩ እንደሆነ ባልረዳም የለም፤ ጠፋ የሚሉት ነገሮች ሳይነገሩ እንዳልቀሩ እገምታለሁ። ምክንያቱም እነዚህ ወሬኞች ዝም ብለው ከመለፍለፍ ውጭ ሥራ የላቸውም የሚለው ብዙ ነው። እንደውም አንዳንዱማ ወረርሽኙ ለመገናኛ ብዙኃኑ ወሬ ማድመቂያ መጥቷል ሲል ይደመጣል።
ሠርጉ ላይ ያለው ሰው፤ ሀዘን ቦታ ላይ ያለው ለቀስተኛ ኮሮና እንዳለ ልብም አላለም። እናም ይህንን ሳይ ለምን እና ለማን ይሆን ይህንን ያህል የምንለፈልፈው እላለሁ። ጎበዝ ታዲያ ጠፍቷል ያልተባለ ይመስላችኋል? እንደኔ ሳየው ግን ተብሏል። ምክንያቱም በየሰፈሩ ተዘዋውረው ሲመለከቱ ኮሮና የገባ ጊዜ አይንዎ ማረፊያ እስኪያጣ ድረስ የእጅ መታጠቢያዎችን በትንንሽ ርቀት ላይ ይመለከታሉ። ዛሬ ግን በጣም ርቀው ከተጓዙ በኋላ ነው እነዚህን የሚያዩት። ይህም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብቻ ነው።
እዚህ ላይ ደግሞ ሌላ ጉድ እናያለን። የእጅ መታጠቢያዎች ለይስሙላ መቀመጣቸውን። ውሃ ወይም ሳሙና ሳይኖራቸው ‹‹ታጠቡ›› ልትባሉ ትችላላችሁ። ‹‹በምኑ›› ስትል ደግሞ አልቆ ነው፤ ሄዶ ነው ወዘተ የሚሉ ምክንያቶች ይቀርቡልሃል። ከዚያ ሻገር ስንትል ደግሞ ከተቋማቱ በተጨማሪ ሰፈርተኛው ሁሉ የተከላቸው መታጠቢያዎች ተነቃቅለው ትመለከታለህ። ታዲያ ምኑ ይሆን መጀመሪያ እንደዚያ ያሯሯጠን ዛሬ ላይ ያዘናጋን።
በየሰፈሩ የተተከሉት የክፍለ ከተሞች ድንኳኖች ሳይቀሩ ዛሬ ላይ ተነቃቅለው አገልግሎት መስጠታቸውን ትተዋል። ታዲያ ይህንን ዜና አልሰሙም ትላላችሁ? መጀመሪያ አካባቢ ለህዝቡ ግንዛቤ ለመፍጠር በየቀኑ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ሰፊ ነበር። በዚያ ላይ በራሪ ወረቀቶች ከእጃችን እስኪተርፍ ድረስ ይሰጡን ነበር። ግን ዛሬ የት እንደገቡ ባላውቅም ኮሮና ጠፍቷል የሚለውን ሰምተው ጠፍተዋል እንድል ያሰገድደኛል።
የሚገርመው ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ጉዳይ ሲሆን፤ የሃይማኖቱ አባቶች ‹‹ ሁላችንም በአንድ ላይ አንለቅ እናንተ ዳኑና እኛ እንሙትላችሁ። እናንተ ካልመጣችሁ ደግሞ እኛ የምንያዝበትን መንገድ ስለሌለ ቀን እስኪያልፍ እባካችሁ ተጠንቀቁልን›› ሲሉም ተማፀኑ። ግን ማንም ሊሰማቸው አልወደደም። እንደውም ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› በማለትም ወደ ቤተ እምነቱ መጉረፉን ተያይዞታል።
ቀደም ሲል የነበረው ሽርጉድ ወረርሽኙን በአንድ ጊዜ አስቁሞት ይሆን ህዝቡ ዳግም ወደነበረበት ሁኔታ የተመለሰው የሚያስብሉ በርካታ ጉዳዮችም አስተውያለሁ። የዜሮ ሪፖርትና ያገገመ ሰው ብዛት ሲነገረንም በቃ ጠፍቷል ማለትና ጥንቃቄን መተውም ጨምሯል። ግን አሁንም መንግሥት ካልተጠነቀቅን በርካታ ሰው እናጣለን ራሳችሁን ጠብቁ ማለቱን አልተወም። ሰሚ ላይ ነው ችግሩ እንጂ።
አባቶች ሲተርቱ ‹‹ ጆሮ ያለው ይስማ›› ይላሉ። መስማት ማለት ደግሞ ከላይ ከላይ ያለውን ሳይሆን አገናዝበን የምናደርገውን ነው። ስለሆነም መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ከልብ ሰምተን ብንተገብረው ለነብሳችን ድህነት ለስጋችን ደግሞ ደህንነት እናገኛለን። ካልሰማን ደግሞ ቤተሰባችንን ብቻ ሳይሆን አገራችንንም ችግር ውስጥ እንከታለን።
መንግሥት መሰራት ያለባቸው በርካታ የአገር ለውጥ የሚያመጡ ተግባራት አሉት። ግን ከህይወት አይበልጥምና በቤታችሁ ሁኑ፤ ዳኑልኝ አለ። ሥራ ገብቶ ለሠራተኛውም ሆነ ለራሱ ችግር ሊያመጣ ይችላል የተባለው ሰው እረፍት ይውሰድና ጊዜው ይለፍልን ሲልም ፈቀደ። ሆኖም እረፍት የጠማው ይመስል በአደባባዩ የሚታየው ሠራተኛ ቀላል አይደለም። እንደ ሥራ አጥ አትሰብሰብ ተብሎ ሕግ በመጣስ ተሰብስቦ ቢራ ሲጋተር የሚውለውም ብዙ ነው። አንዳንዱ መኪናውስጥ ተሰብስቦ ከመጠጥ ቤቱ ፊት ለፊት ይጠጣል። አንዳንዱ ደግሞ ኪስ በምትመስል በር ተደብቆ እየገባ ቤቱ ግን ዝግ በመምሰል አታድርግ የተባለውን ሲያደርግ ይውላል።
አዋጁን እንዲያስፈጽሙ የተላኩትስ ወዴት ናቸው። በተለይም የፖሊስ ሃይሎች ካላችሁ ደግሞ እነርሱም እንደህዝቡ ሰው ናቸውና የሚያደርጉት የተሳሳተ ነገር ይኖርባቸዋል። እያዩ ዝም የሚሉትም
በርካታ ነገሮች አሉ። ግን ስንቱን ደብድበውና መክረው ይችሉታል። ህሊና የሚገዛው ከሌለ። ፖሊሶችም ብትሆኑ የተባላችሁትን ተባሉ እንጂ ኮሮና ይሉኝታ አያውቅምና ለአገራችሁ ሰላምና ለህዝባችሁ ጤንነት ሃላፊነታችሁን ተወጡ።
በሰዎች ላይ ከደረሰ ቸግር መማር ዋጋ አልተሰጠውም። በራስ ላይ ግድ መድረስ እንዳለበት ብዙዎች አምነው ይንቀሳቀሳሉ። ይህ ደግሞ ግለሰብን ብቻ ሳይሆን አገርን ዋጋ እንደሚያስከፍል ማመን ያስፈልጋል። ‹‹እኔ ከሌለሁ ሰርዶ አይብቀል›› ለጣሊያኖችም አልበጀም። እናም ከሌላ መማር ልምዳችን እናድርግና በባለሙያ የሚመከረንን እንስማ።
‹‹ለእኛ አልመጣም፤ እኛን አልያዘንም የያዛቸው ከውጭ የመጡትን ነው›› የሚለው ምክንያት ብዙም እንደማያስኬድ የሦስት ቀን ጉዟችን ያስተማረን ይመስለኛል። ምክንያቱም ብዛቱ ብቻ ሳይሆን ምንም አይነት የጉዞ ታሪክ የሌላቸው፤ ከማንም ጋር ያልተነካኩት ሰዎች ተይዘዋልና።
ሁሉም በሚባል ደረጃ የቀደመ ኑሮውን እያከናወነ መቀጠሉ ለባሰ ችግር መዳረግ እንደሚችል ከዚህ በመማር ጠንቀቅ ለነገ መቆየት ይበጃልና ይታሰብ። የፊት ጭንብል ብቻ ያድናል ብሎ ማሰብም አይገባም። ከዚህ ቀደም ግንዛቤ መስጠቱና ማህበረሰቡን ማገልገል የጀመራችሁ ሁሉ አሁንም ዳይ ወደሥራ ያንን ልምዳችሁን ቀጥሉ። የነገ ተረካቢን እንዳናጣም ሥሩ።
ለማሳረጊያ የመንግሥት ተቋማት ተገልጋይን ሲያገለግሉ ጥንቃቄዎችን በተመለከተ የታዘብኩትን ላጋራችሁ። ፒያሳ እናት ህንፃ ለመግባት የተሰለፈውን ሰው ይመለከታል። መታጠብ፤ ማስክ ማድረግ እንዳሉ ናቸው። ግን ትዝዝሉ በምንም አይነት አልተቀነሰም። ሰውነት ከሰውነት ጋር ፍትጊያ ገጥመዋል።
ለራሱ እንኳን ብሎ ራቅ ያለ ሰው አላየሁም። ስለዚህም መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማድረግ ያለባቸውን አልሰሙም እንዴ ብያለሁ? ወይም ደግሞ ጠፍቷል የሚለውን ሰምተዋል? እንጃ ግራ ተጋብቼ ነበር ወደ እንግዳዬ ጋር የገባሁት። ስለሆነም ለመንግሥትም ቢሆን ይህ ጉዳይ ይታሰብበት ሳልል ማለፍ አልፈልግም። ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው