አዲስ አበባ፡– በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት አሥር ወራት ለ 2 ሺህ 537 ባለሀብቶች አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስት መንት ኮሚሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ መሠረት ወልደማርያም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ በ2017 በጀት ዓመት አስር ወራት ለ 2 ሺህ 537 ባለሀብቶች አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ ከዚህም ውስጥ ለ334 የለውጥ ወይም ማሻሻያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እና ለ99 ምትክ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል።ለ 115 የውጭ ዜጎች ተቀጣሪ ፈቃድ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡ ለ2 ሺህ 760 ባለሀብቶችም የኢንቨስትመንት ፈቃድ እድሳት አድርጓል፡፡
ዳይሬክተሯ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በ2017 በጀት ዓመት አስር ወራትም በዋና ዋና ሥራዎች ላይ ኢንቨስትመንትን በማጥናትና በማስተዋወቅ በኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠት፤ በፕሮጀክት ድጋፍና ክትትል በማድረግ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ማስፋፊያ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ለወሰዱ 245 ባለሀብቶችም ፈቃድ መስጠቱን ጠቁመው፤ ለ818 ተቋማት የካፒታል እቃዎች ፤ ለ106 የግንባታ እቃዎች ፤ ለ14 ተሽከርካሪዎች ፤ ለ32 መለዋወጫ እቃ፤ 93 የገቢ ግብር እፎይታ ፤ ለ51 ተቋማት ጥሬ እቃዎችን ማበረታቻ እቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መደረጉን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ጥንካሬዎችን በመውሰድና ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት መሠረታዊ ቁልፍ ችግሮች የሆኑትን በመለየት ስለመሥራቱም ወይዘሮ መሠረት አንስተዋል፡፡
ከመሠረተ ልማት፤ ከመሥሪያ ቦታ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያሉትን ሥራ በቀጣይም አጠናክሮ በመሥራት ባለሀብቱ ላይ የሚፈጠሩ ጫናዎችን የመቀነስ ሥራዎች ይከወናሉ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በተያዘው የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ሚያዚያ ወር ብቻም ለ399 ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሰጥቷል፡፡
አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከተጣቸው ባለሀብቶች በተጨማሪም ፤ ለ 22 ባለሀብቶች ማስፋፊያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ፤ ለ44 ባለሀብቶች ለውጥ/ማሻሻያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ፤ ለ5 ባለሀብቶች ምትክ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ፤ መስጠቱ ነው የተመላከተው፡፡
መዲናዋ በበጀት ዓመቱ በተሠራ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት አንጻር ሲታይ በኢንቨስትመንት ፍሰትም ሆነ የፕሮጀክቶች ወደ ተግበራ መሸጋገር በተሻለ አፈጻጸም ላይ መሆኑንም ነው በዳይሬክተሯ የተመላከተው፡፡
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም