
ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት በትኩረት እየሰራች ትገኛለች። ለእዚህም የአምስት አመት ስትራቴጂ ነድፋ በመተግበር በርካታ ለውጦችን ማስመዝገብ ችላለች። በዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ፣ አገልግሎት ማስፋፋትና ማዘመን የሚታዩ ለውጦች ይህን ተከትለው የመጡ ናቸው።
በሀገሪቱ የኦንላይ አገልግሎቶች ተስፋፍተዋል። ክፍያና ግብይት በጥሬ ገንዝብ የሚደረጉ ክፍያዎችና ግብይቶችም በዲጂታል መከናወነ ከጀመሩ ቆይተዋል። ከፍተኛ ሀብት በዲጂታል ሥርዓቱ እየተዘዋወረ ይገኛል።
በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በዲጂታል የተከናወነ ግብይት በአጠቃላይ 12 ነጥብ 51 ትሪሊየን ብር መድረሱም የዲጂታል ዘርፉ በግብይቱ እያበረከተ ያለው ሚና ምን ያህል እንደደረሰ ያሳያል። አምና በተመሳሳይ ወቅት ስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊየን ብር ግብይት ነበር የተካሄደው።
የአንድ ማእከል አገልግሎት እውን ተደርጓል፤ በዚህም ተገልጋዮች የተለያዩ አገልግሎቶችን ፍለጋ መዞር አይጠበቅባቸውም፤ በአንድ ሥፍራ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በበርካታ ከተሞች የመሬት አስተዳደርና የመሳሰሉት አገልግሎቶችም በእነዚህ ሥርዓት መከናወን ጀምረዋል፤ ሌሎችም ወደዚሁ ሥርዓት ለመግባት እየሠሩ ናቸው፤ አሁን የዲጂታል አገልግሎቶችን ከፍ ማድረግ ይበልጥ ማዘመን ላይ ትኩረት ተደርጓል። የዲጂታል ቴክኖሎጂው ያልገባበት ዘርፍ የለም፡፡
የዲጂታል ዘርፉ ሰፋፊ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ እየተደረገም ይገኛል። ሰሞኑን ኢትዮ ቴሌኮም እና ከትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ያደረጉት ስምምነት ይህንኑ ያመለክታል። ተቋማቱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክሱን ዘርፍ በሚያዘምኑ ሶስት ጉዳዮች ላይ ስምምነት ፈጽመዋል።
በስምምነቱ ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬ ሕይወት ታምሩ፣ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስትር አቶ አለሙ ስሜ፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደዚሁም ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬ ሕይወት ታምሩ ኢትዮጵያን ለማዘመን እየተሠሩ ካሉ ወሳኝ ሥራዎች መካከል አንዱ የኮሚኒኬሽን ሥራ ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ ለዚህም ኢትዮቴሌኮም የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ በማስተዋወቅ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ዘመኑ የሚፈቅደውን የቴክኖሎጂ ሽግግር እውን ማድረግን እንደተልዕኮ በመውሰድ በዘርፉ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ከመቼውም በበለጠ እየሥራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ኢትዮቴሌኮም ኢትዮጵያን በማገልገል እና በኮሚኒኬሽን ዘርፍ የተሰጠውን ተልእኮ ሲወጣ 130 ዓመታትን አስቆጥሯል። እንደ ሀገር የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ የዲጅታል ሶሉሽን ሕይወት አቅላይ የአገልግሎት ዘርፎችን እያስተዋወቀ ይገኛል።
ተቋሙ በዘርፉ ዓለም የደረሰችበት ደረጃ ለመድረስ በተለያዩ አሠራሮች ወደ ሕዝብ ለመድረስ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ እጅግ ዘመናዊ በሚባሉ የአገልግሎት ዘርፎቹ ብዙዎች በመጠቀም ሕይወታቸውን ከማቅለል ባለፈ ጊዜና ጉልበታቸውን ማዳን እንደቻሉም አስታውቀዋል።
‹‹መጪው ጊዜ በቴክኖሎጂ ረገድ የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ነው›› ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ለዚህ እውን መሆን ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ እና በዲጂታላይዜሽን ሲስተም ከማስተሳሰር አኳያ የኢትዮቴሌኮም ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረው፣ ከትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ጋር ያደረገው ስምምነት የዚህ አንዱ አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንዳስታወቁት፤ በእለቱ በሶስት ወሳኝ የዲጅታል ሶሉሽኖች ማለትም በሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ (cross country public transport)፣ በሀገር አቀፍ የትራፊክ የቅጣት ሕጎች (national traffic point based penalty management system) እንዲሁም የተቀናደ የነዳጅ ክፍያ (enabling all payment platforms for fuel payment) ሥርዓትን ከማዘመን አኳያ ሁለቱ ተቋማት ስምምነት አድርገዋል። ሁለቱ መሥሪያ ቤቶች ይህም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለጀመረችው የዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ መሠረት እንደሚሆንም ተመላክቷል።
የትራንስፖርት ዘርፉ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት መሠረት ነው ያሉት ወይዘሪት ፍሬህይወት፣ በዘርፉ ላይ የሚደረጉ ለውጦች፣ ማሻሻያዎች፣ ሶሉሽኖች ወቅቱ የሚፈልጋቸው ከመሆናቸውም ባለፈ አሁን ላለንበት ዘመናዊ ዓለም እጅግ ወሳኝ የሚባሉ ናቸው ብለዋል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ትራንስፖርት የማይገባበት ሥፍራ የለም። ስልጣኔ ያለዘመናዊ የትራንስፖርት ሥርዓት ትርጉም የለውም። ሕዝብን በማገልገል፣ ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት፣ ሀገራዊ ለውጡን በማፋጠን እንደዚሁም በመሰል ዘርፈ ብዙ ግልጋሎቱ አይነተኛ ሚና አለው።
የዘርፉ መዘመን የቆዩ ችግሮችን ከመቅረፍ እስከ መዘመን እንደሚያደርስ አመላክተዋል። በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎች ብዙ መሆናቸውን ጠቅው፣ ከክፍያ ሥርዓት፣ እስከ ተገልጋይ፤ ከአገልግሎት አሰጣጥ እስከ ስምሪት ሥርዓቱ ክፍተት እንዳለ ገልጸዋል።
‹‹በቀጣይ እነዚህ ተግዳሮቶች ተቀርፈው ሀገራችን ጊዜው በሚፈቅደው የትራንስፖርቴሽን ሲስተም ውስጥ ትገባለች›› ሲሉም አስታውቀዋል። የወረቀት አሠራሩን በማዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ አሠራር በመዘርጋት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የአገልግሎቱ መዘመን የፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱን ለማሳጠርም፣ ባልተሟሉ ወይም ደግሞ ትክክል ባልሆኑ ሰነዶች ምክንያት የሚባክን ጊዜን ለማስቀረት፣ የሽያጭ እና የገቢ ግልጸኝነትን ለማስፈን፣ የመረጃ አያያዝን ለማዘመን ስርቆቶችን ለማስቀረት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
ዲጅታል ሶሉሽኑ የትራንስፖርት ስምሪት አሠራር የፍቃድ እና የምዝገባ ሥርዓት፣ የአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ምዝገባና ስምሪትን እንዲሁም የማኑዋል ቲኬት ህትመት ክፍያዎችን ዲጅታል ማድረግ የተቋማት ወጪን ለመቀነስ እንደሚያስችል ተጠቁሟል። ለባለድርሻ አካላት ክትትል፣ የአሠራር ቁጥጥር እና ሪፖርት፣ ለጉዞ መስመር ዝርጋታ እና የጊዜ ሰሌዳ ዝግጅት፣ ለመናኸሪያ አስተዳደር መስተካከል ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል።
በዘርፉ የሚታዩ የቆዩ እና አዳዲስ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ መሥሪያ ቤታችን ባለፉት ሰባት ዓመታት ፖሊሲዎችን በማውጣት፣ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ፣ እቅድና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መሥራቱን አመላክተዋል።
ካለትራንስፖርት ዘመናዊነት እንደማይታሰብ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ የዕድገት እና የዘመናዊነት መሠረት የሆነውን የትራንስፖርት ዘርፍ ለማሳደግ ከኢትዮቴሌኮም ጋር ተቀናጅ መሥራት መጀመሩን እንደ ትልቅ እርምጃ ጠቅሰውታል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ላይ እንደችግር ከሚነሱት መካከል የመንገድ ደህንነት ጉዳይ አንዱ ነው። በርካታ አደጋዎችም ከመንገድ ጋር ተያይዞ እንደሚከሰቱ ይገለጻል።
ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በሀገሪቱ የተሻሉ የትራንስፖርት ሥርዓቶች እየታዩ መሆናቸው አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፣ ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ መደገፉ ብዙ ችግሮችን እንደሚያስቀር ገልጸዋል፡፡
ከትራፊክ ህግ ጋር በተገናኘ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተናበበ የትራፊክ ቅጣት ሥርዓት እንዲኖር፣ የትራፊክ ሕግ ጥሰቶችን በዲጂታል መንገድ ለመቆጣጠር፣ አሽከርካሪዎች ቅጣት በመክፈል ሂደት የሚደርስባቸውን የጊዜና የጉልበት ብክነት ለመቅረፍ ሥርዓቱ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። አጥፊዎች አንድ ቦታ ስህተት ሠርተው በሌላ ቦታ ጥሩ መስለው የሚታዩበትን ሁኔታ ለመቆጣጠር እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የትራፊክ ሕጎች በአግባቡ እንዲተገበሩ፣ በማዕከል ደረጃ ዳታ የሚመዘገብበት እና በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የትራፊክ አስተዳደር ሥርዓት ለማስፈን ያስችላል፤ የትራፊክ ቅጣት ነጥብ አያያዝ፣ ቅጣቱን ለመፈጸም ያለው ምቹነት፣ ዳታን በመተንተን የመረጃ ውስንነትን እና ውጤታማ ያልሆነ የሀብት አጠቃቀምን ለማስቀረት፣ አዋጪ ፖሊሲዎችን ለማውጣት፣ የመረጃ እጥረትን በመቅረፍ ረገድ አይነተኛ ሚና አለው፡፡
የአሽከርካሪዎችን ሙሉ መረጃ ከመመዝገብ፣ ጤናማ የትራፊክ ፍሰትን በመፍጠር አደጋን ከመቀነስ አኳያ እንደዚሁም የክልል ትራንስፖርት ቢሮዎች ተጨማሪ ኢንቨስትመንትና ወጪ ሳያስፈልጋቸው በቴሌክላውድ ታግዘው እንዲሰሩ ምቹ አሠራር በመፍጠር ለትራንስፖርት ዘርፉ ጠቀሜታ እንዳለው ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የነዳጅ የግብይት ሥርዓትን በተመለከተም ስምምነቱ ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል። በተለይ ከገንዘብ ጋር በተገናኘ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ፣ አሠራርን በማዘመን ለዘርፉ የተሻለ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ዘልማዳዊ አሠራሮችን በማስቀረት፣ ሁሉንም የፋይናንስ ተቋማት (ባንኮች፣ ዋሌቶች፣ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን) ከዋናው የነዳጅ ሲስተም ጋር ለማገናኘት ላቅ ያለ ሚና ይኖረዋል። የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር እና የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አፋጣኝ መረጃዎችን እንዲለዋወጡ፣ የሀገር አቀፍ የነዳጅ ክምችት ሥርጭትንና ሽያጭን በቅርበት ለመከታተል እንደዚሁም በመረጃ ላይ የተደገፈ ተጠያቂነትን ለማስፈን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
ባለፉት ዓመታት መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶችን በመገንባት፣ ዘመናዊ መኪናዎችን በማስገባት ተስፋ ሰጪነቱ እንደታየ ጠቅሰው፣ ስምምነቱ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ከማስቀረት፣ ዘርፉን ከእጅ ንክኪ በጸዳ መንገድ በቴክኖሎጂ በተደገፈ አሠራር ለመመራት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ባለፉት ዘመናት ኢትዮ ቴሌኮም በሀገር የዘመናዊነት ግንባታ ላይ የራሱን አሻራ ማሳረፉን ጠቅሰው፣ በቀጣይ እቅዶች ላይም ተባብሮ በመሥራት የኢትዮጵያን ዘመናዊነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም ባለሙያዎች በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደተጠቆመው፤ የትኛውም ተገልጋይ ቀላል፣ ምቹ እና ጊዜ ቆጣቢ በሆነ መንገድ አገልግሎቱን በስልኩ መጠቀም ይችላል።
እስካሁን በነበረው የሀገር አቋራጭ የትራንስፖርት አሠራር አዲስ አበባን ማዕከል አድርገው ወደተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚሄዱ ሁለት መቶ ሃምሳ አምስት የሚደርሱ አውቶብሶች እንዳሉ የተጠቆመ ሲሆን፣ በዚህም ሂደት በቀን ውስጥ ከአርባ ስምንት ሺህ በላይ ዜጎች ይስተናገዳሉ። ከወጪ እና ከገቢ አኳያ ሲታይም 325 ሚሊየን ብር ገደማ ጥሬ ገንዘብ ይዘዋወራል። ይሄ ሂደት ከእጅ ንክኪ ወደተሻለ የዲጅታል ማርኬት ሥርዓት መግባቱ ብዙ ነገሮችን ያቀላል፡፡
ተገልጋይ ትኬት ከመቁረጥ ጀምሮ አስፈላጊ የሚላቸውን ሁሉንም አገልግሎቶች በማግኘት ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ የሚስተናገድበት ሥርዓት እንደሆነ ጠቁመው፣ ተገልጋዮች የሞባይል ስልኮቻቸውን በመጠቀም እንግሊዝኛን ጨምሮ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የሀገር አቋራጭ የአውቶቢስ ትኬቶችን በማንኛውም ጊዜና ቦታ ቴሌ ብርን ጨምሮ በተለያዩ የክፍያ አማራጮች በመቁረጥ፣ ቦታ መያዝ እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡
በነዳጅ ግብይት እና የትራፊክ ሕጎችን በተመለከተም ተመሳሳይ የአገልግሎት አሠራር እንዳለ የተጠቆመ ሲሆን፣ ተግባራዊ የተደረጉት ሶሉሽኖች ከግል ሶፍት ዌር አልሚ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የለሙ መሆናቸው ተመላክቷል። ይህም ኢትዮ ቴሌኮም የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት እያደረገ ያለውን ጥረት አመላካች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ማዘመን ከተልዕኮው አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ የትራንስፖርት ዘርፉ በዲጂታል ሲስተም ውስጥ መግባቱ፣ ሌብነት እና ማጭበርበሮችን በመግታት፣ የታሪፍ ጭማሪን በማስቀረት መሰል ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በመቆጣጠር ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ እንደተጠቆመው፤ በሀገር የኮሚኒኬሽንም ሆነ የዘመናዊነት ሂደት ላይ የኢትዮ ቴሌኮም ሚና ላቅ ያለ ነው። ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ እንደሀገር ከብዙምቹ ቀልጣፋ ሕይወት አቅላይ አገልግሎቶቹ ጋር ኢትዮጵያውያንን አገናኝቷል፤ ወደፊትም በአዲስ እና በተሻሉ የአገልግሎቶቹ ሕዝቡን ያገለግላል።
በቀላል፣ ምቹ እና አስተማማኝ አገልግሎቱ የሚታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም ለቀልጣፋ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ከትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ጋር ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሱም እንደ ሀገር የተያዘውን የዲጅታል እቅድ ከማሳካት ባለፈ ከኋላቀር አሠራር ጋር ተይይዞ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ በዘርፉ የተሻለ እምርታ ለማስመዝገብ ያስችላል፡፡
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም