
አዲስ አበባ፡– መንግሥት የጤና ባለሙያውን ዘላቂ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የጤና ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
የጤና ሚንስቴር ከትናንት በስቲያ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ሚንስቴሩ፤ ለማኅበረሰባችን ጥራቱን የጠበቀ እና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጤና ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በመቅረጽ የኅብረተሰቡን ባለቤትነት ባረጋገጠ መልኩ ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑ የአደባባይ ሐቅ ነው። ምክንያቱም መቼምና በምንም ሁኔታ መቋረጥ ከሌለባቸው ማኅበራዊ አገልግሎቶች አንዱ የጤና አገልግሎት በመሆኑ፤ ስለዚህም ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ቀናት በመላ ሀገራችን በሚገኙ የጤና ተቋማት እንደ ወትሮው ሁሉ መደበኛ የጤና አገልግሎቶች ለማኅበረሰባችን ያለምንም መቆራረጥና መስተጓጎል እየተሰጡ ይገኛሉ ብሏል፡፡
ይሄንን የተረዳው የጤና ባለሙያ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚሠራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ጫና ሳይገፋ የገባውን የሙያ ቃል ኪዳን እና መሃላ ጠብቆ ማኅበረሰቡን እያገለገለ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል ያለው መግለጫው፤ ይሁን እንጂ በጥቂት የማስተማሪያ የጤና ኮሌጆች/ተቋማት በመደበኛ የሥራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ የተወሰኑ ባለሙያዎች እንዳሉ መረጃዎች ደርሰውናል ነው ያለው፡፡
ከእነዚህ የጤና ባለሙያዎች መካከል ብዙዎቹ በሐሰተኛ መረጃ የተወናበዱ ሲሆኑ ጥቂቶቹ ደግሞ ጥፋትን ዓላማቸው ያደረጉ ናቸው ያለው መግለጫው፤ ድርጊቱ የራስን ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ወገን እና መላውን ማኅበረሰብ ከመጉዳት ባለፈ ከሙያ ሥነ ምግባር፣ ከሠብዓዊነት አኳያ ተቀባይነት የሌለው ተግባር እንደሆነ ገልጿል።
ከሕግ አኳያም የጤና ሙያ የሥራ ማቆም አድማ ከማይደረጉባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል ያለው የጤና ሚንስቴር መግለጫ፤ የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ እንኳን ቢኖራቸው በሥራ ገበታቸው ተገኝተው መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ ጉዳያቸውን ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ የጤና ባለሙያዎች ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው ማኅበረሰባቸውን እንዲያገለግሉ በየተቋማቸው ጥሪ ተደርጓል ብሏል።
መንግሥት የጤና ባለሙያውን ዘላቂ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመስጠት ቀደም ብሎ የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ 1362 /2017 አጸድቆ ደንብና መመሪያዎችን በማውጣት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ መግለጫው ጠቁሞ፤ በጎ ኅሊና ያላቸው የጤና ባለሙያዎች ይህንን በመገንዘብ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የሚንስቴር መሥሪያ ቤታችን በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ ያቀርባል ሲል አመልክቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኅብረተሰቡ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚሠራጩ የሐሰት መረጃዎች ሳይረበሽ የሚፈልገውን የጤና አገልግሎት በተለመደው መልኩ በጤና ተቋማት ማግኘት እንደሚችል እናሳውቃለን ያለው መግለጫው፤
መንግሥት በሆደ ሰፊነት ችግሩን ለመፍታት ያሳየውን ትዕግሥት ወደጎን በመተው በሥራ ገበታቸው ላይ ባልተገኙ እንዲሁም በጤና ተቋሙም ሆነ ከጤና ተቋሙ ውጭ ሆነው ሁከትና ብጥብጥ በሚፈጥሩት ላይ አስፈላጊ የሆነ ሕጋዊ ርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ቀድመን እናሳውቃለን ሲል የጤና ሚንስቴር መግለጫ አሳስቧል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም