በኦሮሚያ ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፡– በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የኦሮሚያ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡ 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ክልሉን መጎብኘታቸው ተጠቁሟል፡፡

በክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ፋንታሁን ታደሰ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በክልሉ 600 የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች መኖራቸውን ቢሮው በጥናቱ አረጋግጧል፡፡ እስከ አሁን ድረስ በእነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች በተሠሩ የልማት ሥራዎች ከቱሪዝም ዘርፉ 35 ቢሊዮን ብር ወደ ኢኮኖሚ ውስጥ ተንቀሳቅሷል፡፡ ከለውጡ በኋላ የቱሪዝም ዘርፉ እንደ አንድ ክፍለ ኢኮኖሚ ተለይቶ ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸው እንዲጨምር መደረጉን አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ባሌ ተራሮች ፓርክ፣ ሶፍ ኡመር ዋሻ፣ በምስራቅ ኦሮሚያ ሁለቱ ሐረርጌ ዋሻዎች እና ታሪካዊ ቦታዎች ፣ በመካከለኛ ምስራቅ ሸዋ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች ቢሾፍቱ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚገኙባቸው ቦታዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ትላልቅ የቱሪስት መዳረሻዎች ሶፍ ኡመር ዋሻ፣ ሼህ ሁሴን፣ አዋሽና ባሌ ተራሮች ፓርክ እና ወንጪ ሐይቅ በፈዴራል መንግሥት ተሳትፎ መልማታቸውን አመልክተዋል፡፡

ያለውን የቱሪስት ሀብት እሴት ጨምሮ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የመሠረተ ልማት እና የማረፊያ ቦታዎችን ከመገንባት አንጻር በግሉ ዘርፍ እና በመንግሥት ተሳትፎ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ሳምቤ ታሪካዊ ቦታ እና ዳት ወለል ፓርክ በምዕራብ ኦሮሚያ ከሚገኙ የቱሪስት መስህቦች ውስጥ የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተው፤ ሳምቤ ከታሪካዊ ቦታነቱም ባሻገር ከህብረብሄራዊ አንድነትና ሀገር ግንባታ አንጻር ያለውን አስተዋፅኦ ለማስተዋወቅና የጥናትና ምርምር ማዕከል ለማድረግ ቢሮው ከኢሉአባቦር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን የተለያዩ ስብሰባዎች እና ሁነቶች በቦታው እንዲካሄዱበት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የክልሉን የቱሪስት ፍሰት መጠን 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ባህላዊ እና ሃይማታዊ በዓላት፣ የገዳ ሥርዓት ሥልጣን ርክክብ እና ኢሬቻ በዓል በክልሉ ለቱሪስት ፍሰት እንቅስቃሴ ዋነኛዎቹ ምክንያቶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ከቱሪዝም ዘርፍ ገቢ አንጻር 37 ቢሊዮን ብር ወደ ኢኮኖሚው እንዲንቀሳቀስ ታቀዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 35 ቢሊዮን ብር በኢኮኖሚ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ መደረጉን ገልጸው፤ ክልሉ ያለውን የቱሪስት መዳረሻ በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ማዕከል ለመሆን ብዙ ሥራዎች የሚቀሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘው ዳት ወለል ፓርክ በአካባቢው ካለው የፀጥታ ችግር የተነሳ መሠረተ ልማት ማሟላት እንዳልተቻለ ጠቁመው፤ እንደ ቢሮም የፓርኩን ወቅታዊ መረጃዎች ለማግኘት አዳጋች ቢሆንም ወደፊት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሮቹን ለመቅረፍ ይሠራል ብለዋል፡፡

ገመቹ ከድር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You