
አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ ግብጽ የዓባይ ግድብን ግንባታ ወጪ 50 በመቶ እንድትሸፍን በዲፕሎማሲ ሥራዋ ውስጥ አካታ መሥራት ይኖርባታል ሲሉ የውሃ ጉዳዮች ተመራማሪ ኢንጅነር ጥላሁን ኤርዳኖ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢንጅነር ጥላሁን ኤርዳኖ (ዶ/ር) ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ በግብጽ የሚገኘው አስዋን ግድብ የሚይዘው የውሃ መጠን እንዳይቀንስ የዓባይ ግድብ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። በእዚህና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ግብጽ ለዓባይ ግድብ ግንባታ ወጪን 50 በመቶ መሸፈን ነበረባት። አሁንም ይህንን ጉዳይ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲዋ ውስጥ አካታ መሥራት ይጠበቅባታል ብለዋል።
ግድቡ የዓባይ ወንዝ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ይደርስ የነበረውን የጎርፍ አደጋን ያስቀራል ያሉት ኢንጅነር ጥላሁን (ዶ/ር)፤ ከዚህም ባለፈ አስዋን ግድብ በክረምትም በበጋም የማይቋረጥ ውሃን ማግኘት እንዲችል ያደርጋል ነው ያሉት። ከዚህ መነሻነትም የዓባይ ግድብ ግንባታ ወጪን 50 በመቶ መክፈል ይኖርባታል ነው ያሉት።
ዓባይ ወንዝ ከፍተኛ የሆነ የውሃ መጠን እንዳለው ጠቁመው፤ ኢትዮጵያም የዚህ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለመሆን ዓባይ ግድብን ገንብታለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውሃውን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ከተጠቀመች በኋላ ውሃውን ስለምትለቅ ወደ ግብጽ የሚሄደው ውሃ ላይ የጎላ ተጽዕኖ እንደማያሳድር ጠቁመው፤ ይህም አስዋን ግድብ በክረምትም በበጋም የማይቋረጥ ውሃን ማግኘት እንዲችል ያደርጋል ነው ያሉት።
አስዋን የተገነባበት ቦታ ለውሃ ብክነት የሚዳርግ በመሆኑ በወቅቱ የእንግሊዝና የአሜሪካ ምሁራን ጭምር ተቃውመውት እንደነበር አውስተው፤ የግብጽ የውሃ አጠቃቀም አባካኝ ነው፣ ከዚህ መውጣትም አይፈልጉም ሲሉ ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ 60 በመቶ ያህል የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደማያገኝ ገልጸው፤ የዓባይ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የህልውና፣ የዕድገትና የልማት ጥያቄ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል
የኢትዮጵያ ወንዞች ላይ ከግብጽ ባለፈ ሌሎች ሀገራት ፍላጎት ነበራቸው። ይህንንም ለማሳካት ለጠላት ሀገራት የገንዘብና የመሣሪያ ድጋፍ ያደርጉ ነበር ያሉት ኢንጅነር ጥላሁን (ዶ/ር)፤አንድ ሀገር በግዛቱ ውስጥ ያለውን ሀብት ሙሉ ለሙሉ የመጠቀም መብት አለው ። ግብጽም ግድቡ ስለሚጠቅማት ልትከፍለን ይገባል ያሉት።
አንድ ስኒ ውሃ የማታመርት ሀገር 85 ከመቶ ውሃ የምታመርተውን ሀገር መቆጣጠር አትችል ም ብለዋል።
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ያለው ዓለም አቀፍ ሕግ ፍትሐዊና እኩል ተጠቃሚነት መርህ ያደረገ ነው። ይህም የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ተጠቃሚ ሀገራት ለውሃ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ላይ መሠረት ያደረገ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ነገር ግን ግብጽ ለወንዙ የምታበረክተው አስተዋጽኦ ሳይኖር ለዘመናት ተጠቃሚ ሆናለች። የሀገር ውስጥ ፖለቲካ መበላሸትም ለግብጽ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ያሉት ኢንጅነር ጥላሁን (ዶ/ር)፤ አንድ ስኒ ውሃ የማታበረክት ሀገር 85 ከመቶ ውሃ የምታበረክተውን ሀገር መቆጣጠር አትችልም ብለዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም