ኢትዮጵያ በዓለም ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና እየተሳተፈች ነው

የዓለም ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና ለ58ኛ ጊዜ በኳታር ዶሃ ትናንት ተጀምሯል። የዓለም ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን አባል ሀገራትን ለአንድ ሳምንት በሚያፎካክረው ቻምፒዮና የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን ተሳታፊ ሲሆን፣ ከትናንት በስቲያም ወደ ኳታር ሽኝት ተደርጎለታል።

ኢትዮጵያ ከ45 ዓመት በኋላ በምትሳተፍበት ዓለም አቀፍ ውድድር በአራት ሴት እና አንድ ወንድ ትወከላለች። ቻምፒዮና የሚሳተፈው ብሔራዊ ቡድን በተሸኘበት ወቅት የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛኔ እንደገለፁት፣ ብሔራዊ ቡድኑ ከባለፉት ጊዜያት የተሻለ ዝግጅት አድርጓል። በቻምፒዮናው የሀገርን ክብርና ዝና ከፍ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት የበላይነት በመጠቀም በኳታር በሚካሄደው የዓለም ቻምፒዮና ከተሳትፎም በላይ ለውጤት በመትጋት ልምድ የሚወሰድበት ጭምር አንዲሆን ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ አባላትም ብሔራዊ ቡድኑ በድል እንዲመለስ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል። ከሽኝቱ ጎን ለጎን ፌዴሬሽኑ በአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና ውጤት ላስመዘገቡ እና ለተሳተፉ የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርተኞች፣ አሠልጣኞችና አባላት የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል።

የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከጥቅምት 2-8/2017ዓ.ም መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህም ፌዴሬሽኑ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡና የተሻለ ተሳትፎ ላደረጉ የቡድኑ አባላት ከ 10ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 50ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይም በምስራቅ አፍሪካ የበላይነቱን የሚያጠናክርበትን ቻምፒዮና በማዳጋስካር ያካሂዳል። ብሔራዊ ቡድኑ በዚህ ውድድር በአምስት ሴት እና በአምስት ወንድ የሚወከል ሲሆን ሰኔ 3/2017ዓ.ም እንደሚካሄድም ታውቋል። በሐምሌ ወር 2017ዓ.ም ደግሞ በናይጀሪያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ የታዳጊዎች ቻምፒዮና ይሳተፋል።

ብዙ ትኩረት እየተሰጣቸው ከማይገኙ ስፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ በአፍሪካና ሌሎች ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች አበረታች እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በዚህም ዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን በዚህ ዓመት በፈረንጆቹ ሜይ ወር ባወጣው የዓለም ሀገራት የጠረጴዛ ቴኒስ ደረጃ መሠረት ኢትዮጵያ በወንዶች የቡድን ከዓለም አርባ ሁለተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ስድስተኛ ላይ ትገኛለች። በተመሳሳይ በሴቶች የቡድን ደረጃ ከዓለም ሃምሳኛ ከአፍሪካ ደግሞ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ዶሃ ከሃያ አንድ ዓመት በኋላ የምታስተናግደው ቻምፒዮና ትናንት በድምቀት የተጀመረ ሲሆን፣ በርካታ ሀገራት ጠንካራ ፉክክር የሚያደርጉበት ነው። የዓለም ጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት ኮከቦችም በግልና በቡድን የበላይነታቸውን በማሳየት የሀገራቸውን ክብርና ሰንደቅ ከፍ አድርገው ለማውለብለብ ይፋለማሉ።

ኦሊምፒክን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮች በግልም ይሁን በቡድን ስኬት ቀዳሚ የሆኑት የቻይና ተጫዋቾች በዶሃው ቻምፒዮናም ትልቅ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷቸዋል። የቻይና ተጫዋቾች በወንዶች ነጠላ ፉክክር ካለፉት 15 ቻምፒዮናዎች በ13 በማሸነፍ ቀዳሚ ናቸው። በሴቶች ደግሞ ከ23 ቻምፒዮናዎች በ22 በማሸነፍ ፍፁም የበላይነት አላቸው።

በተመሳሳይ በቡድን ወንዶች ከ16 ቻምፒዮናዎች በ14 ድል ያደረጉት ቻይናውያን ሲሆኑ፣ በሴቶች የቡድን ውድድርም ከ23 ቻምፒዮናዎች 22ቱን ድል በማድረግ ተቆጣጥረውታል። በድብልቅ ፆታ ውድድርም ቻይናውያን የተለየ ታሪክ የላቸውም፣ ከ23ቱ በ19ኙ አሸናፊዎች በመሆን የጠረጴዛ ቴኒስ ባህላዊ ስፖርታቸው እስኪመስል ተቆጣጥረውታል።

ቻይናውያን ከሁለት ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ደርባን ላይ በተካሄደው ተመሳሳይ ቻምፒዮና በአምስቱንም ካታጎሪዎች የሚካሄዱ ውድድሮችን ሲያሸንፉ፣ በሁለቱም ፆታ የነጠላ ውድድርም ቻምፒዮኖች ነበሩ። ይህ የበላይነታቸውም እኤአ ከ2005 የጀመረ ሲሆን ዘንድሮ ከሃያ ዓመት በኋላ ዶሃ ላይ ይቀጥላል? የጠረጴዛ ቴኒስ ስፖርት አፍቃሪዎች በጉጉት የሚጠብቁት መልስ ነው።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You