‹‹ፖለቲካ ከሸፍጥ፣ ከእልህ፣ ከማጭበርበር፣ ከሴራና ከተንኮል ነጻ ወጥቶ ከእውነተኛ ትግል ጋር የሚታረቀው በእኔና በእናንተ ትውልድ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ንግግር እጅግ ቁልፍ ነው፡፡ ካልተነጋገርን አንተዋወቅም፤ ቃል ካልተለዋወጥን አንግባባም፤ አለመግባባት ጥላቻን ይወልዳል፤ ከጥላቻ ምንም ትርፍ እንደሌለ ተተርኮልን ሳይሆን አይተነው ተረድተናል፡፡ ሁላችንም የምንወዳት ሀገራችን ከእንቅልፏ በመንቃት ላይ ትገኛለች፡፡ ከፍ ብላ ለመብረር እንደተዘጋጀች እርግብ ሆና ትታየኛለች፡፡ ክንፎቿ ስለመጠንከራቸው ግን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል፤ የሀገራችን ክንፎችም እኛ ወጣቶች ነን፡፡››
ይህ መልዕክት የወጣት ሰላሃዲን እሸቱ ነው፡፡ መድረኩ ደግሞ በማህበራዊ ፍትህ፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሰሩት ኢምፓወር አፍሪካና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት የተባሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ‹‹የወጣቶች ሚና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ›› በሚል ርዕስ ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም በጋራ ያዘጋጁት ነበር፡፡ የውይይቱ ዋና ዓላማም የኢትዮጵያ ወጣቶች አሁን ባለው ሀገራዊ ለውጥ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው እና ችግሮችን በመነጋገርና በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ፖለቲካዊ ተሰሚነታቸውንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ መጪዋን ኢትዮጵያ በመፍጠር ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻል ነው፡፡ በውይይቱ ላይ ወጣት ፖለቲከኞች ፣የህግ ባለሙያዎች፣ አክቲቪስቶች፣ ምሁራን ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
የኢምፓወር አፍሪካ ተወካዩ ወጣት ሰላሃዲን እሸቱ ይህ መድረክ ቀደም ሲል ‹‹በሀገራችን ብሄራዊ መግባባት ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?›› እና ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለምን ምክንያታዊነትን አጡ?›› በሚሉ ርዕሶች የተደረጉ ውይይቶች አካል እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ የዕለቱ መድረክም የወጣቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎና ሚና መሰረት በማድረግ ወጣቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲመክሩ፣ ሀሳብን በሀሳብ እንዲሞግቱና ቁጭ ብሎ በመነጋገር ልዩነቶችን መፍታት ይቻላል የሚለውን ባህል እንዲያዳብሩ ማስቻል ነው ብሏል፡፡
የሀገራችን ትልልቅ ህልሞች ሊሳኩ የሚችሉት በትውልዶቿ ጠንካራ ሰብዕና እና ጥረት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ያለችበት ታሪካዊ ምዕራፍ ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል ተብሎ እንደሚገለጸው ዓይነት ነው፡፡ እዚህም እዛም የምናስተውላቸው ትዕግስትን የሚፈታተኑ ክስተቶች የድንግዝግዙ መገለጫዎች ናቸው ያለው ሰላዲን ሀገራችን ወደ ቀደመ ክብሯ እንድትመለስ ወጣቱ መጠንከር እንዳለበት ገልጿል፡፡
‹‹የሀገሬ ፖለቲካ ሌላኛው ነቀርሳ እንደትውልድ ልንታገለው የሚገባን ጉዳይ የእኔ ተራ ነው የሚለው እሳቤ ነው ›› ያለው ወጣት ሰላዲን፤ ዛሬ የእኔ ተራ ነውና ከሌላው በተለየ እኔ መጠቀም አለብኝ በሚል እራሳችንን ማታለል እንደሌለብን አስረድቷል፡፡ በመጨረሻም ኢትዮጵያ በተራ የምናልባት ላም ሳትሆን በጋራ የምንንከባከባት እናታችን መሆኗን ማስታወስ እንዳለብን መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ሌላዋ የዚህ መድረክ አወያይና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆነችው ወጣት ሶሊያና ሽመልስ የመድረኩን አስፈላጊነት ስታስረዳ እርስ በርስ የሚነጋገሩ በውይይት የሚያምኑና ምክንያታዊ የሆኑ ወጣቶችን ቁጥር ማብዛት ነው ብላለች፡፡ ወጣቶች በተለያዩ ጊዜያት ለውጦችን በመምራት ግንባር ቀደም እንደነበሩ በመጥቀስ ለውጡን ለማስቀጠልና ተጠቃሚነታቸ ውንም ለማረጋገጥ መቀራረብና መነጋገር እንዳለባቸው አስረድታለች፡፡
የእለቱን ቁልፍ የመወያያ ሃሳብ ያቀረበችው ወጣት ብሌን ሳህሉ ስትሆን መነሻ ያደረገችው ‹‹የአንድን ሀገር የፍትህ ሥርዓት ለማወቅ መጀመሪያ ስልጣን ላይ ያሉትን አካላት ሳይሆን ከለላ ያልተሰጣቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ጠይቁ›› የሚለውን የምሁራን ሃሳብ ነበር፡፡ ወጣቶች እስከ ዛሬ ባለው የሀገራችን ታሪክ በፖለቲካ ለውጦች ላይ ጫና የመፍጠር ሚና እንደነበራቸው የገለጸችው ወጣት ብሌን ከለውጥ በኋላ ያላቸው ሚና ግን አናሳ እንደሆነ አስረድታለች፡፡
በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት እስከ መቶ አምስት ሚሊዮን እንደሚገመትና የዚህን ቁጥር ከስልሳ እስከ ሰባ በመቶ የሚይዘው ደግሞ ወጣት እንደሆነ የገለጸችው ወጣት ብሌን፤ ይሄ ሁሉ ወጣት ካልተደራጀ ፣ ካልተማረና መረጃ ከሌለው የቁጥሩ መጨመር አዎንታዊ እንደማይሆን አስረድታለች፡፡
የወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ሁለት ጽንፎች አሉት የምትለው ወጣቷ አንደኛው በፍርሀት በመሸበብና እራስን ከፖለቲካ ለማራቅ መሞከር ሲሆን ሌላው ጫፍ ደግሞ እስከ ህይወት መስዋትነት በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ እንደሆኑ አስረድታለች፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፊ በመሆኑ በአካልም ሆነ በህይወት ላይ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ሁኔታ እንደሌለ በመጥቀስ ወጣቱ በዚህ አጋጣሚ ፖለቲካዊ ተሳትፎው ሊጨምር ይገባል ስትል ተናግራለች፡፡ ፖለቲካ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሁሉንም ሰው ህይወት ይዳስሳል ያለችው ወጣት ብሌን ወጣቶች በመርህ ላይ የተመሰረተ መደራጀትና የረጅም ጊዜ ዕቅድና እይታ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስባለች፡፡
በለንደን ኪል ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት ዶክተር አወል ቃሲም በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በላይ ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማድረግ ከፍተኛ መስዋትነትን እንደከፈሉ በመናገር ደርግ በወጣቶቹ ትግል ተመርቶ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ እንደገና አፈሙዙን በተማሪዎች ላይ በማዞሩ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ወደ ትጥቅ ትግል መሸጋገሩን አስረድተዋል፡፡ ደርግን ከስልጣን ያስወገደው የኢህአዴግ መንግሥትም በገባው ቃል መሰረት ህዝቡን ማስተዳደር ባለመቻሉ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለተነሳው የወጣቶች ተቃውሞ ምክንያት ሆኗል፡፡
አሁንም የመጣው ለውጥ በወጣቶች የተመራ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በሀገራችን ታሪክ ወጣቱ በፖለቲካዊ ሽግግር ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው፣ ወጣቱ በለውጡ ሂደት ያደረገው አስተዋጽኦ አዎንታዊ ነው ቢባልም በአንዳንድ ቦታዎች ተገቢ ያልሆኑ፣ ህግን የሚጻረሩና ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ላይ በመሳተፍ አሉታዊ ተግባሮች መፈጸሙ ተገቢ አልነበረም ብለዋል፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ ቦታዎች ከለውጡ ዓላማ ጋር አብረው የማይሄዱ ጸያፍ ተግባራት ሲከሰቱ ታይቷል ያሉት ዶክተር አወል ይህ ግን ሽግግሩን ያደናቅፋል ብዬ አላምንም ብለዋል፡፡
ለውጡ የወጣቶችን ችግር በተለይም የሥራ አጥነትን ችግር የሚቀርፍ አይደለም የሚሉ አካላት አሉ እርስዎ ምን ይላሉ ለተባሉትም፤ዶክተር አወል ሲመልሱ ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው፡፡ በእነዚህ በስምንትና ዘጠኝ ወራት ውስጥ የወጣቶች ሁለንተናዊ ችግር ይፈታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በመጪዎቹ ዓመታት ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን መያዝ ይቻል ይሆናል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ተማሪ የሆነው ወጣት አስቻለው ሰርሞሎ አሁን ለመጣው ለውጥ ወጣቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው በመግለጽ በቀጣይም ለውጡን ለማስቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ወጣቱ ከመንግሥት ጎን መቆም እንደሚገባው ተናግሯል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ብሄርን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች መፈጠራቸው ዩኒቨርሲቲዎች የልቀት ማዕከል ሆነው የማህበረሰቡን ችግር የመፍታት ተልዕኳቸውን ከመፈጸም ይልቅ ችግር በመፍጠር የሰላም ስግታ ሊሆኑ አይገባም ብሏል ፡፡
በአመዛኙ የለውጡ ባለቤት የነበረው ወጣቱ እንደነበር አይካድም ያለው ተማሪ አስቻለው በተቃራኒው ለውጡን ወደ ኋላ መጎተት ለሚፈልጉ ኃይሎች መጠቀሚያ የሆኑ ወጣቶች መኖራቸውንም ገልጿል፡፡ በመጨረሻም እንዲህ ዓይነት መድረኮችን በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም በማዘጋጀት ወጣቶች በመነጋገር ችግሮችን የሚፈቱባቸውን ልምዶች እንዲያጎለብቱ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል፡፡
በሀገራችን የለውጥ ሂደት ውስጥ የወጣቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዴት ይገለጻል በሚል በመድረኩ ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ ወጣቶች ከ1960ዎቹ ዓ.ም ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን በሀገራችን ለውጦች እንዲመጡ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋቸውን ብዙዎች ቢስማሙም አንዳንዶች ግን የወጣቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከዛም በፊት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች በ1930ዎቹ መጀመሪያ አካባቢም የሀገራችንን በፋሽስቶች መወረር አስመልክተው በወቅቱ በነበሩ ጋዜጦች ላይ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች በማስተላለፍ ህዝቡን ለማነቃቃት ይሞክሩ እንደነበር ተወስቷል፡፡ ከዚያም ወዲህ በ1960ዎቹ በይበልጥም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ‹‹መሬት ላራሹ›› የሚል መርህ በመያዝ የዘውድ ሥርዓቱን ለመገርሰስ የሚያስችል መሰረት ጥለዋል፡፡
‹‹በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ›› እንዲሉ ደርግ ተማሪዎች ያንገጫገጩትን የንጉሱን ወንበር ተቆጣጥሮ ዳግም ግፍና መከራ በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ሲያደርስ ኖሯል፡፡ ሥርዓቱን በመቃወማቸውም በርካታ ወጣቶች በግፍ ተገድለዋል፡፡ ይህን የተቃወሙ ወጣቶችም የትጥቅ ትግል በማድረግ የደርግን ሥርዓት እንዳስወገዱት ተወስቷል፡፡ በዚህም ከ1970ዎቹ እስከ 1980ዎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች መንግሥትን የመሞገት አቅማቸው የተዳከመ እንደነበር ተነስቷል፡፡
ኢህአዴግ አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ በተለይም በ1997 ዓ.ም ምርጫ አካባቢ የወጣቱ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደ አዲስ ብቅ ማለት ችሏል፡፡ ከዛም ወዲህ ወጣቱ ባገኘው መድረክ ለምሳሌ በስፖርት ሜዳዎች፣ በዩኒቨርሲቲዎችና በሚሰባሰብባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ቅሬታውን ይገልጽ እንደነበር ተሳታፊዎቹ አስታውሰዋል፡፡
በመጨረሻም ከአራት ዓመታት ወዲህ የተቀሰቀሰው የወጣቶች ተቃውሞ እየበረታ መጥቶ የአሁኑን ነጻነት መጎናጸፍ እንደተቻለ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ ያም ሆኖ አንዳንድ ወጣቶች በለውጡ ዋዜማ ያደረጉትን ትግል የሚያጎድፉ ተግባራትን በለውጡ ማግስት ማከናወናቸው አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል እንዳስከፋ በውይይቱ ተሳታፊዎች ተነስቷል፡፡ ይህም ወጣቱ ላይ የታየው ያለመረጋጋት መንፈስ ግዴታና መብትን ካለማወቅና የሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አጀንዳ ለማስፈጸም በመሞከር እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በእርግጥም ኢትዮጵያ ለለውጥ እየተጋችና ወደላይ ከፍ ብላ ለመብረር እየተዘጋጀች ያለች አገር ነች፡፡ እርግብ ያለ ክንፍ ወደ ላይ መብረር እንደማትችል ሁሉ ወጣቶችም የለውጡ ዋና ሞተሮች በመሆናቸው በሁሉም ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦዋቸው ሊጠናከር ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011
ኢያሱ መሰለ