ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች አሏትመውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም ይኖራልከመውረድ ውስጥም በትጋት መውጣት ይቻላልአግኝቶ ማጣት እንዳለ ሁሉ አጥቶም ይገኛል።ይህ የህይወት እውነታ ነውበጥቂቶች የህይወት መውጣትና መውረዶች ውስጥ ብዙዎች ይማራሉየህይወትን ፈተናዎችም ያውቃሉበከፍታ ውስጥ የሚገኙት ‹‹እንዲህም ይኖራል እንዴ?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉለተቸገሩት ያዝናሉካላቸው ቀንሰው የሌሎችን ችግር ይካፈላሉበተጨማሪም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ ከችግር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ ለመፍትሄ የሚታትሩትንም ያበረታታሉበመሆኑም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን በከፈትነው አምዳችን ህይወትን በየፈርጁ ታስተውሉበት፤¸አስተውላችሁም ትማሩበት ዘንድ ጋበዝናችሁለአስተያየቶቻችሁ፤ ለመሰል ታሪኮች ጥቆማችሁ እንዲሁም ለድጋፋችሁ የዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ትጠቀሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
በቃ ሕይወት አንዳንዴ አንዲህ ናት። የሰቀልነው ይወርድና የወረደው ከማማ ላይ ሆኖ በድምቀት ይታያል። ሕይወት የራሷን ፈርጅ እስክታገኝ ታለፋለች፤ ታወርዳለች። በእርግጥ በፈለግነው መስመር ለመዘወር የራሳችን ጥንካሬ፣ ታታሪነት ብሎም አይበገሬነት ትልቅ አድርሻ አለው። ያለንበት ሁኔታ እና ከዙሪያችን ያሉ ሰዎች ሚናም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከምንም በላይ ግን በጠንካራ ሥነ ልቦና የተገነባ ሕይወት የሌሎችን ሕይወት መታደጉ አይቀሬ ነው።
በዛሬው ‹‹እንዲህም ይኖራል›› አምዳችሁ የሕይወትን ውጣ ውረድ ለማሸነፍ ውጣ ውረዶችን በጥበብ ስላለፉት አንዲት ዶክተር የሕይወት ተሞክሮ እና በአሁኑ ወቅት ዓለምን እየፈተነ ያለው የኮሮና ቫይረስ በጋዜጠኞች ሕይወት ላይ እየፈጠረ ያለውን ጠባሳ በጥቂቱ እናስቃኛለን።
ዶክተር ሕይወት ጥላሁን ይባላሉ። በአገው ግምጃ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጠቅላላ ቀዶ ሕክምና ሐኪም እና የፈውስ ሕክምና ክፍል መሪ ናቸው። ተወልደው ያደጉት በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባንጃ ወረዳ ነው። የእርሳቸው ቤተሰቦች ‹‹ልጅህን ለልጄ›› በሚል ልማድ ገና የስምንት ዓመት ታዳጊ እያሉ ድረዋቸው እንደነበር ከአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት (አብመድ) ጋር በነበራት ቆይታ ያለፈ ታሪካቸውን በዓይነ ህሊና የኋሊት ተጉዘው ይናራሉ። ታዳጊዋ የዚህች ዓለም ውጥንቅጥ በቅጡ ሳይገባት ‹‹ትዳር ይዘሻል፤ ጎጆም ቀልሰሻል›› ትዳርሽ የሞቀ ይሁን ተብላ ለሦስት ዓመታት ቆይታለች።
በእነዚህ ዓመታት በነበረችበት ቤት በጣም
ጥሩ እና አዛኝ እናት አጋጥመዋት ተንከባክበው አቆይተዋታል። ‹‹ዛሬ በሕይወት ባይኖሩም የእርሳቸው ውለታ ዛሬ ለደረስኩበት ስኬት ትልቅ ቦታ
አለው፤ ግን ተመልሼ ሳላያቸው ሞት ቀደመኝ›› በማለት በእነዚያ ዓመታት እንደ ልጅ አቅፈው ተንከባክበው ያቆዩዋቸውን እናት ባለማግኘታቸው ያደረባቸውን ቁጭት በሐዘን ስሜት ይገልፁታል።
ከሦስት ዓመታት የትዳር ቆይታ በኋላ ግን ወደ ቤተሰቧ ተመልሳ ትምህርት የመማር ዕድል አግኝታለች። በትምህርት ቤት ቆይታዋ በርትታ በማንበብ አንዳንድ ጊዜም በየወሰነ ትምህርቱ ወይንም (ደብል በመምታት) ከክፍል ክፍል በመዘዋወር በትዳር ምክንያት የዘገየባትን ትምህርቷን ማካካስ ችላለች። የሕይወት ውጣ ውረዶችን በማለፏና በርትታ ትምህርቷን በመከታተሏ ውጤታማ ሆና በ2000 ዓ.ም የጥቁር አንበሳ የሕክምና ትምህርት ቤትን ተቀላቅላለች። የሕክምና ትምህርቷንም በጥሩ ውጤት አጠናቅቃለች።
ዶክተር ሕይወት ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በሰሜን ሸዋ ዞን መሐል ሜዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመድበው በጠቅላላ ሕክምና እና የፈውስ ሕክምና ክፍል ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። በተመደቡበት አካባቢም ከሕክምና ሥራቸው ጎን ለጎን በማህበረሰብ አገልግሎት ተሠማርተው ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። በተ
ለያዩ ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር ሴት ልጆች ያለዕድሜያቸው እንዳይዳሩ እና በትምህርታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ብሎም እንዲጠነክሩ ግንዛቤ ይፈጥሩም ነበር።
በአሁኑ ወቅት በአገው ግምጃ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጠቅላላ ቀዶ ሕክምና ሐኪም እና የፈውስ ሕክምና ክፍል ኃላፊ በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ። ገና በልጅነታቸው ያጋጠማቸውን የሕይወት ሳንካ አልፈው አሁን ላሉበት ደረጃ የበቁት ዶክተር ሕይወት ቀጣይ ብዙ ነገሮችን የመሥራት ዕቅድ ይዘው እየሠሩ ይገኛሉ። በሚሠሩበት ሆስፒታል ሙሉ ጊዜያቸውን በመስጠት ከማገልገል ጎን ለጎን በወረዳው የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ሴት ልጆችን የማበረታታት ተግባራት እያከናወኑ ይገኛሉ። እርሳቸው ያለፉበትን አስቸጋሪ የሕይወት ውጣ ውረድ እና ተቋቁመው ያለፉበትን ምስጢርም በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለሴት ልጆች እያካፈሉ ነው። በርከት ያሉ ተማሪዎችም የእርሳቸውን ምክር በመፈለግ ስልክ ጭምር እየደወሉ እንደሚጠይቋቸው ይናገራሉ።
የእርሳቸው ቤተሰቦች በልጅነታቸው የዳሯቸው ያለዕድሜ ጋብቻ ጉዳት እንደሚያደርስ የግንዛቤ እጥረት ስለነበረባቸው መሆኑን ይናገራሉ። ሴት ልጆችን ያለ ዕድሜ መዳር ሀገርን ወደኋላ እንደሚያስቀር የሚናገሩት ባለራዕይዋ ዶክተር ሕይወት በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ አካላት ካሉም ነገሮችን ቆም ብለው እንዲያስቡ ይመክራሉ። ከመውደቅ ማግስት መነሳት፤ ከጨለማ በኋላ ብርሃን እንዳለ በመግለፅና ዓርዓያ ለመሆን እየታተሩ የብዙዎችንም ሕይወትም መስመር እንዲይዝ የአቅማቸውን እያደረጉ የዜግነት ግዴታቸውንም እየተወጡ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር