ባለፉት ሁለት ሳምንታት ኪነ ጥበብ መፍለቂያዋና መፍሰሻዋ ብዙ ነው ብለናል። ኪነጥበብ አብዝታ ሰላምን ትሻለች። በሰላም ውስጥ ስትፈልቅ ታዝናናለች መንፈስን ሀሴት ታላብሳለች። እውቀትን ታጋራለች። ኪነ ጥበብ በችግር ውስጥም ትከሰታለች፤ ብሶትን፣ ቁጭትን ክፋትንና ጉዳትን እያስረሳች የተሰበረን መንፈስ ታክማለች፣ ትጠግናለች። ኪነጥበብ በጦርነት ውስጥም ትፈጠራለች፤ ለተዋጊዎቹ ጉልበትና ወኔን አላብሳ ለትግል ታነሳሳለች። ታግላ ታታግላለች ድልን ታቀዳጃለች። እንዲህ እንደ አሁኑ የከፋ የጤና ችግር ሲያጋጥምም የፈውስ ምክንያቶችን ይዛ ትመጣለች፣ ታበረታለች፣ ታጽናናለች፣ ትደግፋለች፣ ትፈውሳለችም።
ኪነ ጥበብ መንፈስ ውስጥ ስለምትፈጠር ጊዜ፣ ቦታና ሁናቴ አይገድባትም። ጋራና ሸንተረር አይጋርዳትም። ውቂያኖስና ጅረቶች አይከፍሏትም። ለሕዝባዊ ወገንተኝነቷ ወደር አይገኝላትም። ከጭቁኑ ጋር ስትሆን ጉልበቷ ይበልጥ ያይላል። ለወገነችው ተጨቋኝ አብራ ነፃ ልታወጣው ብርታት ትሆነዋለች። እንዲህ ለመነሻ ያህል ከጠቃቀስኩት በእጅጉ የምትገዝፈው ኪነጥበብ አሁን ከታመሙት ጋር አብራ ታማለችና ስለህመሟና ፈውሷ ለማውሳት ተንደርድሬያለሁ።
ኪነ ጥበብ የራሷ የሆነ ዘመን እንዳላት አስባለሁ። በየዘመኖቿ ነፃነት ስታገኝ ወደከፍታው ትወጣለች፤ ነፃነቷን በተለያዩ ምክንያቶች ሲቀሟት ደግሞ ቁልቁል ተምዘግዝጋ ትፈጠፈጣለች። ለዚህም ነው ‹‹የኪነጥበብ ወርቃማ ዘመኖች›› እያልን የጉብዝና ዘመኗን የምናወድስላት። በጉስቁልና ዘመኗም አብዝተን የምንተክዝላት።
አሁን ሀገራችን ኪነጥበብ ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የነፃነት ዘመኗ እንደሆነ ይሰማኛል። ይሁን እንጂ ይህን የነፃነት ዘመን ተጠቅሞ ወደ ከፍታዋ ሊያደርሳት ወይም ሊያቃርባት የሚተጋ ጥበበኛ አግኝታለች ብዬ አላስብም። ምክንያቱን ዘመኑን የሚያዋጁና አሁንን የሚሞግቱ፣ እንደ ነብያት መጪውን የሚያመላክቱ፣ ክፉውን ተሻግረው የሚያሻግሩ ከያኒያንን በባትሪ ተፈልገው ካልሆነ በቀር በግላጭ ማግኘት ተቸግረናል።
አሁን አሁን በብዛታቸው እንጂ በጥራታቸው የሚወዳደሩትን የኪነጥበብ ሥራዎች ለማግኘት ብዙ መማሰንን ይጠበቅብናል። ነፍስን የሚያረሰርሱ፣ የተጎዳን አዕምሮ የሚፈውሱ፣ የተከዘን የሚያስፈነድቁ ሳይሆኑ ብሶትን የሚያባብሱት፣ የሚያሳቅቁና የሚያበሽቁት በርክተውብናል። በተለያዩ መድረኮች ስንታደም በአዲስ ከተሰሩት ይልቅ በድጋሜ የተሰሩት ወይም ‹‹የሚገረቡት›› የተሻሉ የሚሆኑት ለምን ይሆን? ብለን ስንጠይቅ ብቻ ነው እውነታው ወለል ብሎ የሚገለጥልን።
የሀገራችን ኪነ ጥበብ ከራማ እንዲርቃት የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም የሃያሲ መጥፋት አንዱ ነው ብዬ አምናለሁ። ልብ ብላችሁ ከሆነ የትኛውም የኪነጥበብ ሥራ የሚሄስበት አጋጣሚ ብዙም አይስተዋልም፤ ቋሚ የሆኑ የሂስ መድረኮች አይዘጋጁም። በመሆኑም ነው ዕድሉንና አጋጣሚውን ያገኘ ሁሉ የሰራው ነገር ሁሉ ትክክል እንደሆነ እንዲያስብና ‹‹ከኔ በላይ ጥበበኛ ላሳር›› እንዲል የሚያደርገው። ሌላው ደግሞ የምን አገባኝነት ስሜት መብዛቱ ነው። አዋቂዎቹም ከታዋቂዎቹ እኩል በምናገባኝ ስሜት የተዋጡ ይመስላሉ። እዚህ ላይ የገጣሚ ኑረዲን ኢሳን ግጥም ብጠቅሳት መልካም ይመስለኛል።
እኔ ምን አገባኝ!
«እኔ ምን አገባኝ የምትሉት አረግ፣
እሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደበግ።
የሚል ግጥም ልጽፍ
ስሜት አንዘርዝሮኝ ብድግ አልኩኝና፣
«ምን አገባኝ›› ብዬ ቁጭ አልኩ እንደገና»
በርግጥም ብዙዎቻችን በ‹‹ምን አገባኝ›› ስሜት ማህበረሰባችንን ብሎም ሀገራችንን እንደበግ እያረድናት እንደሆነ ሊሰማን ይገባል። ምክንያቱም
በሀገራችንና በማህበረሰባችን ጉዳይ የማያገባን ጉዳይ ሊኖር አይግባምና። ማናችንም ብንሆን የምንኖረው ለራሳችን ብቻ ሳይሆን የምንኖርለት፣ ሲደክም የምናግዘው፣ ሲሰበር የምንጠግነው፣ መልካም ሲሰራ የምናደንቀው፣ የምናከብረው፣ የምንቆረቆርለት
ማህበረሰብ ሊኖረን ግድ ይለናል። የዛሬ አነሳሴም በሀያሲ መንጠፍና በ‹‹እኔ ምን ያጋባኛል›› ጦስ ወደከፍታው እንዳታቀና እንቅፋት ስለሆንባት ኪነጥበባችን በስሱ ለመዳሰስ ይሆናል።
በወቅታዊው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ የማህበራዊ ሚዲያው በመልካምም ይሁን በመጥፎ መነጋገሪያ የሆኑ በርካታ የኪነጥበብ ሥራዎችን አይተናል። ነገር ግን ሁሉም የኪነጥበብ ሥራዎች በሂስ ታሽተውና ከምንአገባኝ ስሜት ተላቀው ተሰርተዋል ወይ? ብሎ መጠየቅ ይገባል።
እዚህ ላይ የማደንቃት ድምጻዊት በቲዩተር ገጿ ላይ ያሰፈረችውን ለመጥቀስ ወደድኩ። ‹‹ኢትዮ ውስጥ በኮሮና ከተያዙት ሰዎች ይልቅ ለኮሮና የተዘፈኑት ይበልጣሉ፤ በዚህ ከቀጠሉ ከበሽታው በላይ እነሱን መቆጣጠር ነው የሚከብደው›› እኔ ይህ ወፍራም ሂስ እንደሆነ አስባለሁ። ሁሉም መስራታቸውን ሳይሆን ሥራቸውን ቆምብለው እንዲያስተውሉ የሚያሳስብም ጭምር ነው።
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ የኪነጥበብ ሥራዎች በብዛት መሰራታቸው በራሱ እሰየው የሚያስብል እንደሆነ አምናለሁ። የኪነጥበብ ሰዎች ምን ያህል በጉዳዩ ላይ ትኩረት እንደሰጡና በሙያቸው ማድረግ የሚገባቸውን ለማደረግ መጣራቸውንም ያሳየናል። ነገር ግን ችግሩ ያለው የሚቀርቡት ሥራዎች ምን ያህል በአማካሪ ታግዘው፣ በፈጠራና ሙያዊ ብቃትን ተላብሰውና ታሽተው ተሰርተዋል የሚለው ነው።
በኮቪድ19 ኮሮና ላይ ከተሰሩት የኪነጥበብ ሥራዎች ውስጥ ምን ያህሉ የማህበረሰቡን አመለካከት ቀይረዋል ተብሎ ቢጠና ውጤቱ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ለመረዳት ብዙ ጥናት የሚጠይቅ አይመስለኝም። ምክንያቱም የማንኛው ሥራ ስኬት የሚለካው በጭብጨባው ብዛት ሳይሆን በሚያመጣው አወንታዊ አስተዋጽኦ መሆኑ ግድ ነውና። በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ዘመን የተሰሩትንና እንደብሔራዊ መዝሙር በህሊናችን ገዝፈው ዛሬም ድረስ የምናስታውሳቸውን የኪነጥበብ ሥራዎች ማስታወስ ተገቢነው። ለአሁኑ ደግሞ ለክሽፈቱ ማህበረሰባችን አሁን ያለበትን መዘናጋትና ግድየለሽነትን ማጤን በቂ ነው።
ለዚህም ነው የህክምና ባለሙያዎች ማህበር በኪነጥበብ ባለሙያዎችም ሆነ በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡት ሥራዎች እውቀትን መሠረት ያላደረጉ መሆናቸው እንዳሳሰበው የገለጸው። የሙያ ማህበሩ ስጋቱንና ሙያዊ ሂሱን በይፋ መግለጹ ሊያስመሰግነው እንጂ ሊያስነቅፈው አይገባም። ይህን መሰል ሂስ ነው በየሙያ መስኩ እንዲኖር የምንፈልገው።
የኪነጥበብ ማህበራትና በሙያው ላይ የበቃ እውቀት ያላቸው ጉምቱ ባለሙያዎች እንዳሉን አንክድም። ነገርግን ስለቀረቡት የኪነጥበብ ሥራዎች በይፋ አድናቆታቸውንም ሆነ ትችታቸውን ለመሰንዘር ለምን አልደፈሩም? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል።
ምክንያቱም አንድ የጥበብ ሥራ መመዘን ያለበት በማህበረሰቡ ላይ የሚኖረው አወንታዊ አስተዋጽኦ መሆን አለበት። ይህ ባለመሆኑ ከቀረቡልን የኪነጥበብ ሥራዎች በአብዛኞቹ የፈጠራ ንጥፈቶችን አይተን አፍረናል ተሳቀናልም። ይህ በእንዲህ የሚቀጥል ከሆነም ድምጻዊቷ እንዳለችው ከወረርሽኙ ይልቅ እነርሱን መቆጣጠር እንደሚሳነንና ይበልጥ ማፈራችንና መሳቀቃቸችን እንደማይቀር ለመገመት አያዳግትም።
ፈጠራ የነጠፈባቸው የኪነጥበብ ሥራዎች በብዛት እንዲመረቱ የሚበረታቱት በሁለት መንገድ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ። መጀመሪያው ‹‹እኔ ምን አገባኝ›› የሚለው አስተሳሰብ ሲሆን ሌላው የሀገራችን ኪነጥበብ በሯን የከረቸመችበት ‹‹የሰላ ሂስ›› መንጠፍ ናቸው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በሚወጡ የኪነጥበብ ሥራዎች ላይ በጋዜጦችና በመጽሔቶች ይነስም ይብዛም ሂሶች ይስተናገዱ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል።
አሁን አሁን ግን የሂስ አምድ ያላቸው የህትመት ሚዲያዎች ወይም ከማሽቃበጥና ከአጉል መደናነቅ የዘለለ የሂስ ፕሮግራም ያላቸው የራዲዮና የቴሌቪዥን
ጣቢያዎች ስለመኖራችን እርግጠኛ አይደለሁም። በሃያሲነታቸው የምናውቃቸው ጥቂት ባለሙያዎችም ሂስ አንዱ የጥበብ መገለጫና ማሳደጊያ መሆኑን አምኖ ቀና ምላሽ የሚሰጥ የኪነጥበብ ባለሙያ ባለመኖሩ ሂስ መስጠት አንዳቆሙ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
በመሆኑም አድናቆችንም ሆነ ነቀፌታዎችን ለመተንፈስ ያለው ብቸኛ አማራጭ ማህበራዊ የመረጃው መረብ ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ይሆናል። የማህበራዊ የትስስር መረብ ደግሞ የተጠያቂነት ችግር ያለበትና ትክክለኛውን የሂስ ሳይንስ ተከትሎ የሚሰጥ ባለመሆኑ በቲፎዞ ሊዘወር እንደሚችል መረዳት ይገባል። እንደ ሂስ ሠጭው እውቀት ሳይሆን እንደሚጽፍበት ስሜትና ዓላማ መወሰኑም የማይቀር ነው። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት አብዝቶ የሚያስፈልገን በግልጽ ‹‹አካፋን አካፋ›› የሚል አዋቂ ሀያሲ መሆን አለበት።
በማህበራዊው የመረጃ መገናኛ በእውቀታቸው የተመሰከረላቸው የጎንዮሽ ወልጋዳ አላማ የሌላቸው ሀያሲያን የሚሰጡት ሂስ መኖሩ አይካድም። በሁሉም የኪነጥበብ መስኮች ብቁና በእውቀት የሰከኑ፤ አስተውለው የሚራመዱ፤ ለሚኖሩላት ጥበብ የታመኑ፤ ለመታወቅ ሳይሆን ለሙያቸው ክብር የሚሞቱ ብዙ ሙያተኞች እንዳሉንም አንክድም። ችግሩ ያለው የካበተውን ልምዳቸውን በቅን ልቦና የሚካፈላቸው፤ እንደ ወይን እያደር የበሰለውን እውቀታቸውን የሚቀበላቸው ተተኪ ማጣታቸው ዋናው ችግር እንደሚሆንም ይታመናል።
አንዳንዶች እንደሚሉት ሂስ ለመሰንዘር እንዳይደፍሩ ከስህተቱ ተምሮ ለተሻለ ሥራ ከሚሽቀዳደመው ይልቅ በቲፎዞና በሆይሆይታ ወደ እውቅና መንበር መፈናጠጥ እንደሚቻል እርግጠኛ የሆነው ተበራክቷል። ለሌሎችም ያች ‹‹እኔ ምን አገባኝ›› የምትለው አዚም እየተጠናወቻቸው እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም።
በዘመናችን በርካታ ጥበበኞች ለጥበብ ሲሉ የኖሩትን አይተናል። አንድም ጊዜ ‹‹ኤጭ›› ሳይባሉ እንደተከበሩ ያለፉትም ብዙ ናቸው። አሁንም የሀገሬ ማኅጸን ጥበበኞች ነጥፎባታል ብዬ አላምንም። ብዙ የልጅ አዋቂዎች፤ ከመታወቃቸው በፊት አዋቂነታቸው የሚገዝፍ ብዙ ከያኒያን አሉን። ችግሩ ያለው በታዋቂነት ስም በቁመታቸው ልክ ከፊት እንደ ጅብራ ተገትረው ሌሎች እንዳይታዩ የሚጋርዱት በመብዛታቸው ነው።
እኔ ከፈጠራ ንጥፈት ለመውጣት እንዲህ ቢሆን ብዬ አስባለሁ። የትኛውም ጥበባዊ ሥራ ለሕዝብ ከመቅረቡ በፊት ከምን አገባኝ ስሜት በመውጣት ታዋቂዎች ሳይሆኑ አዋቂዎች እንዲያማክሩ ቢደረግ፤ የመድረክ ሥራዎች ሲዘጋጁ ግልጽ የውድድር መስፈርት ወጥቶ ለሁሉም የጥበብ ቤተሰብ ክፍት ቢደረግ፤ በተለይ በቀጥታ ለሕዝብ የሚተላለፉ የጥበብ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢደረግባቸው፤ በእውቅናና በመጠቃቀስ ከመስራት ይልቅ አዳዲስ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች የሚሳተፉበት ዕድል ቢመቻች፤ የቴሌቪዥን ባለቤቶችም ሆኑ መሪዎች የሚቀረቡላቸውን ፕሮፖዛሎች በጥበባዊ ፋይዳቸው እንጂ በታዋቂዎች ብዛት ባይመዝኑ፤ በፈጠራ የደመቀች ቀልባች ውስጥ ተሰንቅራ የምትቀርና ለውሳኔ የምታፈጥነንን ጥበብ ማየት እንችላለን።
የሀገሪቱን ባህልና ኪነ ጥበብ እንድታሳድጉ የተቋቋማችሁ የመንግሥት ተቋማት ከምን አገባኝነት ርቃችሁ በርግጥም ለጥበብ አድገት የምታስቡ ከሆነ በዙሪያችሁ ከከበቧችሁ የማህበር መሪዎችና ታዋቂዎች ይልቅ ጥበብ ፈጣሪዎችንና አዋቂዎችን በአማካሪነት ይዛችሁ ብትሰሩ፤ አንድም የተቋቋማችሁበትን አላማ ታሳካላችሁ፤ ሁለትም የሀገራችሁን ኪነ ጥበብ ወደ ከፍታው ትመሯታላችሁ። ይህን ስታደርጉ የሀገራችሁን ጥበብ ከ‹‹ግረባ›› አላቃችሁ በአዳዲስ ፊቶች የሚደምቁ ሀገር ተረካቢ ጠቢባንን ታፈራላችሁ። ያን ጊዜ በባህሉ የሚኮራ፣ ለፈጠራ የበረታ፣ በጥበቡ የሚታነጽ ማህበረሰብንስ ትፈጥራላችሁ። የጋራችን ኢትዮጵያ በጥበቧና በባህሏ ተሸምና አምራና ደምቃ እንዲሁም በልጽጋ እናያታለን። መልካም ቅዳሜ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2012
ዳንኤል ወልደኪዳን