ግጭቶች የሚያስከፍሉንን ዋጋ በማስቆም ሠላማዊ ሀገር ለመገንባት

ኢትዮጵያ አሁን ባላት የኢኮኖሚና የልማት አቅም የተሻለ ዕድል ለመክፈት እና ዘላቂ ልማትን ለማጎልበት ሠላም በእጅጉ ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንጋፋ ታሪክ፣ ባሕልና ለዓለም ሥልጣኔ በረከት የሆኑ ቅርስ ካላቸው ሀገራት አንዷ እንደሆነች ይታወቃል።

ሉዓላዊነቷን በማስጠበቅ ረገድ በጥንካሬያቸው ከሚጠቀሱ ቀዳሚ ሀገራት መካከል ነች። ይሁን እንጂ የሀገሪቱ እድገት አብዛኛውን ጊዜ በውስጣዊ ግጭቶች ይፈተናል። አሁን ዓለም ከደረሰበት የሥልጣኔና የኢኮኖሚ ጥንካሬ ወደኋላ የቀረችበት ምክንያትም ይሄው ነው። የሠላም እጦት ማኅበራዊ ትስስርን የሚያውክ፤ ልማትን የሚያደናቅፍ እና የሰብዓዊ ቀውሶችን የሚያባብስ ነው።

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ዛሬ የሠላም እጦት በኢትዮጵያ ልማት ላይ እንዴት ተፅዕኖ እንደሚያሳድር እና እያሳደረ እንደሚገኝ ከዚህ እንደሚከተለው ምሳሌዎችን ለማንሳት ይሞክራል። መፍትሔ ያላቸውንም አማራጮች ያስቀምጣል።

በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶች በመሠረተ ልማት፣ በኢኮኖሚ እድገት እና በዜጎች ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፤ አሁንም እያደረሱ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና አማራ ባሉ ክልሎች የተነሳው አለመግባባት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፤ አፈናቅሏል። የግብርና ሥራን፣ የመሠረተ ልማት ግንባታን አቋርጧል፤ የሕዝብ አገልግሎቶች እክል ገጥሟቸዋል። ይህ ሁለንተናዊ የሆነ ተግዳሮት በሠላም እጦት ምክንያት የተከሰተ ነው።

እ.ኤ.አ በ2024 የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ሪፖርት መሠረት አድርገን ብንመለከት ግጭት ኢትዮጵያን ምን ያህል ወደኋላ እየጎተታት እንደሆነ እንረዳለን። ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በግጭት ምክንያት ከ3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ በትግራይ ክልል ከፍተኛውን የተፈናቃዮች ቁጥር ተስተናግዷል። ፈጣን እድገትና ልማት በምትሻው ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን መሰል ቀውስ ማስተናገድ የልማት እሳቤን በእጅጉ የሚጎዳ ነው።

ከማኅበራዊና ሰብዓዊ ጉዳት ባሻገር የሠላም እጦትና ግጭት ኢኮኖሚያዊ አንድምታው ጉልህ እንደሆነ ማወቅ በእጅጉ ቀላል ነው። የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልክተን በኢትዮጵያ እድገትና የልማት ጉዞ ላይ በሀገር ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች ምን ያህል ዋጋ እያስከፈሉ እንዳሉ ለመመልከት እንሞክር።

ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በግብርና ሥራ ላይ ችግር ስላጋጠመ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መንግሥት እየሠራ ያለውን ሥራ እያደናቀፈው ነው። በግጭት እና በዓለም አቀፍ ቀውሶች የተነሳው የኑሮ ውድነት፣ የምግብ ዋጋ ንረት አስከትሏል።

ወጣቶች፣ ባለሙያዎች ትምህርት እና ሥራን ጥለው ግጭት ካለባቸው አካባቢዎች እንዲሰደዱ ወይም ሥራቸውን እንዲተዉ ተገድደዋል። ይህ ደግሞ የሰው ካፒታል መጥፋት አስከትሏል። ሁሉን አቀፍ ለሆነ የኢኮኖሚ እድገት እንቅፋትም ነው።

ከዚህ ባሻገር በጠቀስናቸው አካባቢዎች የመሠረተ ልማት ውድመት የጤና አጠባበቅ እክል፣ ትምህርት እና አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኗል፤ የልማት ጥረቶችን በማዘግየት የሚፈለገው ውጤት እንዳይመዘገብ አድርጓል።

ከሌሎች ሀገራት ምን እንማር እንደ ሩዋንዳ ያሉ ሀገራት የውስጥ ግጭቶቻቸውን ፈትተው ወደ ልማት ፊታቸውን ያዞሩበት መልካም ተሞክሮ ለኢትዮጵያውያንም ትምህርት ሊሆን ይገባል። ይህ ጥረታቸው ሠላምን የለውጥ ኃይል እንደሆነ የሚያሳይና ከግጭት እንዴት መውጣት እንዳለብን የሚያመላክት ነው።

ከ1994ቱ የዘር ማጥፋት እልቂት በኋላ ሩዋንዳ ለእርቅ እና ለሀገራዊ አንድነት ቅድሚያ ሰጠች። በዚህም አስገራሚ ውጤቶችን ተቀዳጅታ አሁን በእድገትና በውስጥ ሠላም በምሳሌነት የምትነሳ ሆነች። የሩዋንዳ ፈጥኖ ከውስጥ ግጭት ማገገም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን በማስመዝገብ ድህነትን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አድርጓል።

በተመሳሳይ፣ በ2016 የኮሎምቢያ የሠላም ስምምነት መደረጉ መንግሥት ከ (FARC) የሽምቅ ተዋጊ ቡድን ጋር የተኩስ አቁም እንዲያደርግና ሀገሪቱ ሃብቷን ወደ ትምህርት፣ መሠረተ ልማት እና ጤና አጠባበቅ እንድትሰጥ አስችሏታል። በዚህም አስደናቂ ውጤት ተመልክተናል።

ኢትዮጵያም የእነዚህንና የሌሎች ሀገራት ከውስጥ ግጭት ለመውጣት ከወሰዱት መፍትሔ መማር ይገባታል። እነዚህ ምሳሌዎች ሠላም የሞራል ግዴታ ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚ ብልጽግና እና ማኅበራዊ መረጋጋት መሠረት መሆኑን እንድንገነዘብ የሚያደርግ ነው።

የኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ግጭቶች እና የእድገት ተፅዕኖዎቻቸው የኢትዮጵያ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2022 መገባደጃ ላይ ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጋር ያደረገው የሠላም ስምምነት የመረጋጋት ተስፋን ሰጥቷል። ይሁን እንጂ በሌሎች ክልሎች ለምሳሌ በኦሮሚያና በአማራ የተነሳው ግርግር የልማት ጥረቶችን እያደናቀፈ ነው።

ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ እንደ ድርቅ፣ ጎርፍ እና የዋጋ ንረት የመሳሰሉ ውስብስብ ቀውሶች ተጋርጠውባታል። ለምሳሌ የትግራይ ግጭት ይፋዊ የተኩስ አቁም ባጋጠመበት ወቅት የአየር ንብረት መናወጥ እና የሃብት እጥረት በአካባቢው ያለውን ውጥረት አባብሶታል እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። እ.ኤ.አ በ2024 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በተደራራቢ ቀውሶች ምክንያት ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ (አይአርሲ) ገልጿል።

መፍትሔው

ልማትና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ትኩረት መስጠት አለባት። አካታች አስተዳደርን ማሳደግ አንዱ ቀዳሚ ሊሆን የሚገባው እርምጃ ነው። ቅሬታዎችን መፍታት እና በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ውይይት መፍጠር ውጥረቶችን በመቀነስ ወደፊት ግጭቶችን ለመከላከል ያስችላል።

የማኅበራዊ ሴፍቲኔት መረቦችን ማጠናከር ሌላው የመፍትሔው አካል ሊሆን ይገባል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ የተተገበሩ ምርታማነት የሚያሳድጉ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራሞች ተጋላጭ ሕዝቦችን በመደገፍ ውጤታማ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ሆኖም፣ ተከታታይ የገንዘብ ድጋፍ እና ሰፊ ተደራሽነት አሁንም እንደሚያስፈልግ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተጨማሪ በልማት ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ያሻል። የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ትምህርት እና ጤና አጠባበቅ ለሁሉም አካታች በሆነ መንገድ ተቋዳሽነትን ማጎልበት ያስፈልጋል። የሥራ ዕድሎችን ለሁሉም ዜጎች መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት።

ለማጠቃለል

ኢትዮጵያ ወደ ሠላም እና ልማት የምታደርገው ጉዞ ከመንግሥት፣ ከዜጎች እና ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል። የኢትዮጵያውያን የቆየ ታሪክ እንደሚያሳየው ከግጭት በኋላ እንደገና ማገገምና ማደግ እንደምንችል ነው። ነገር ግን ሠላም ከሌለ የዚህ አይነት መልሶ ማገገምና ወደ እድገት መመለስ የማይታሰብ ነው። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ይህንን ዕድል ተጠቅማ አንድነቷን ዳግም ለመመለስ እና ለመላው ሕዝቦቿ ብሩህ የወደፊት ዕድል ለመፍጠር እንድትችል ሁላችንም በጋራ ልንሠራ ይገባል።

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You