ከሰሞኑ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የሀገራችን የሰላም ሁኔታ መስመር መያዝ አለበት ፤ ከመንግሥት ጎን ቆመን ያለብንን ኃላፊነት መወጣት አለብን የሚል ተልዕኮ ይዘው የአማራና የትግራይ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችን አነጋግረዋል፡፡ ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ መልስ በመስጠት ጥሪውን ተቀብለው በቦታው በመገኘታቸውም ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡
ከዘጠና በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃይማኖተኛ ነው ያሉት የሃያማኖት አባቶቹና የሀገር ሽማግሌዎቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየትኛውም ሃይማኖት ተቀባይነት የሌላቸው ድርጊቶች እየተፈጸመ መሆኑ አሳስቦናል ይላሉ፡፡ አመራሮቹ ህዝቦችን በማቀራረብ ወደ ነበሩበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ሁሉንም መልካም አማራጮች እንዲጠቀሙ አደራ ተብለዋል፡፡ በአማራና በትግራይ ክልል ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ጊዜያዊ አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ለሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድራን የአደራ ቃል አስተላልፈዋል፡፡ ለሰላም ሂደቱ ለሚያደርጉት ትብብርም በጸሎትና በሃሳብ ከጎናቸው እንደሚቆሙ ገልጸውላቸዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጥሪውን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሰላም አጀንዳ ይዛችሁ በዚህ ወቅት መንቀሳቀሳችሁ የሚያስመሰግን ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን የምንፈልገውና የምንመኘው ለሆነ አካል ብለን ሳይሆን ሰላም ለራሳችን፣ ሰላም ለምንመራው ህዝብ፣ ሰላም ለልጆቻችን በእጅጉ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ ሰላም የሁሉም መሰረት ነው፤ ሰላም ከሌለ ሁሉም የለም፡፡ የሰላም መጥፋት ትንሽ ጊዜ እንኳን ግጭቶች ሲከሰቱ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርሱ ተገንዝበናል፡፡ ይሄ በሩቁ ሳይሆን በራሳችን እየደረሰ የምንመለከተው ነው፡፡
የአማራ ሕዝብ ከምንም በላይ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን ይፈልጋል፡፡ ከሰላም እርሱም ተጠቃሚ ስለሆነ፡፡ የአማራ ህዝብ ከወንድሞቹ፣ ከጎረቤቶቹ እና ከሌሎች ሰላም መሆን ይፈልጋል፤ ለምን ቢባል የሚጠቀመው ከሰላም ስለሆነ፡፡ የአማራ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጋር ሰላም እንዲወርድ ይፈልጋል ለምን ቢባል ይህ እንዲሆን የሚያስገድድ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ትስስር አለውና፡፡ ስለዚህ የሰላምን አጀንዳ ይዛችሁ በመንቀሳቀሳችሁ ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ በእኔ በኩል እኔ የምመራው ህዝብ የሰላም አጀንዳ አንገብጋቢ ጉዳዩ እንደሆነ እመሰክራለሁ፡፡ ሰላም የሁሉም ቀዳሚ ነው፤ ለልማቱም፣ ለለውጡም ፣ ለእርስ በርስ ግንኙነትም፣ ኑሮን ለማሻሻልም፣ በህይወት ለመኖርም ሰላም ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው እንገነዘባለን፡፡ ስለዚህ ይህ የያዛችሁት የሰላም አጀንዳ እንዲሳካ ሕብረተሰቡን በአካል ባወያያችሁበት ጊዜ ሃሳቡን ገልጾላቹኋል፤ እኔም የዚህን ህዝብ ፍላጎት ለማሳካት ሌት ተቀን የምሠራ መሆኔን አረጋግጥላችኋለሁ፡፡
ሰላምን እየዘመረ ለጦርነት የሚዘጋጅ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ሊባል አይችልም፡፡ ከሰላም ብዙ ይገኛል፡፡ ሰላምን በማጥፋት ከጉዳት በስተቀር የሚገኝ ምንም ትርፍ የለም፡፡ የአማራ ህዝብና የትግራይ ህዝብ ለሺህ ዘመናት የሚቆጠር የጋራ እሴት የገነቡ ሕዝቦች ናቸው፡፡ እነዚህ ሕዝቦች የጋራ ታሪክ ያላቸው፣ የጋራ ሃይማኖት ያላቸው፣ የጋራ ጥቅም ያላቸው፣ አንዱ በአንዱ የሚሰጋ፣ የሚፈራ ሳይሆን አንዱ በአንዱ የሚኮራ እርስ በርሳቸው ተከባብረው የሚኖሩበት ታሪክ ባለቤት ሕዝቦች ናቸው፡፡ ይሄ መልካም እሴታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡
የአማራ ህዝብ የተለያዩ አጀንዳዎች አሉት፡፡ እነዚህ አጀንዳዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ ነው እንጂ ከወንድሙ ከትግራይ ህዝብ ጋር እንዲጣላና እንዲጋጭ ምንም አይነት ፍላጎት የሌለው መሆኑን አረጋግጥላችኋለሁ፡፡ የአማራ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጋር ምንም አይነት ግጭት እንዲኖረው አይፈልግም፡፡ ያሉትን ጥያቄዎች በሰላማዊና በውይይት የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲኖር ነው የሚፈልገው፡፡ አሁን አገራችን በለውጥ ሂደት ላይ ናት፡፡ ለዚህ ለውጥ መምጣት አንዱ ተዋናይ የነበረው ሕዝብ ነው፡፡ አሁን ይሄንን ለውጥ የአማራ ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ ነው የሚንከባከበው፣ ለውጡ እንዳይቀለበስ ከፍተኛ ጉጉት ያለው እና ወደ ፊት እንዲራመድ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ ህዝብ ነው፡፡
ይሄ ለውጥ ደግሞ ወደ ፊት የሚራመደው ሕዝቡም የሚጠብቀውን ውጤት ማምጣት የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው ብሎ ያምናል ሕዝባችን፡፡ ስለዚህ የአማራ ህዝብ የተለያዩ ቅሬታዎች አሉት፤ ተበድያለሁ ብሎ የሚያነሳቸው ጉዳዮች አሉት፡፡ እነዚህ ችግሮቹ የሚስተካከሉትና የሚታረሙት ግን በሰላምና በሰላም ብቻ ነው ብሎ ያምናል፡፡ እኔም በምመራው ህዝብ ከዚህ ውጭ አፈንግጬ ብሄድ ሕዝቤ ይጠይቀኛል፡፡
ምክንያቱም ፍላጎቱ ሰላም ነውና፡፡ የአማራ ህዝብ ችግሮቹን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ሲል ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ የታገለ ህዝብ ነው፡፡ ይሄ እንዲሆን ነው የሚፈልገውም፡፡ የአማራ ህዝብ ከማንም ሳያንስ ከማንም ሳይበልጥ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በሰላም መኖር ነው የሚፈልገው፡፡ ይህ ፍላጎቱ የሚሳካው ደግሞ መደማመጥ፣ መወያየት፣ መነጋገር በአጠቃላይ ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ይህን የምላችሁ ከአንጀቴ ነው ፤ ከልቤ ነው የምነግራችሁ፡፡ አሁን እዚህ ስለሰላም ተናግሬ እዛ ስመለስ ሌላ ብናገር ሕዝቤ ይጠይቀኛል፡፡
እኔ እዚህ የምነግራችሁ እና እዛም ስመለስ የምሠራው አንድ ነው ስለሰላም፡፡ ይህንን ህዝብ ለሰላም እቀሰቅሳለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ ብሄድ አይፈቅድልኝም፤ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎች የድርጅት ጓዶቼንም የሚመለከት ነው፡፡ ለሰላም በቁርጠኝነት እንሰለፋለን፤ አትጠራጠሩ ከትግራይ ህዝብ ጋር የአማራ ሕዝብ ግጭት ጀማሪ ሊሆን በፍጹም አይችልም፡፡
ግጭት ጀማሪ በፍጹም ሊሆን አይችልም ስላችሁ ለሚዲያ ፍጆታ ወይም እናንተን ለመሸንገል አይደለም፡፡ የአማራ ህዝብ ከልብ በመነጨ ሁኔታ ሰላም ወዳድ ህዝብ ስለሆነ፣ የሰላምን ጠቀሜታ በእጅጉ የሚረዳ ስለሆነ፣ ሁኔታውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ የሆነ ህዝብ ነው፡፡ እኔም የዚህ ህዝብ መሪ እንደመሆኔ መጠን ይህ እንዲሳካ ነው የምሰራው፤ ከወንድሞቻችን ከትግራይ ሕዝብና አመራሮች ጋር ያሉንን ጉዳዮች በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት እና በመከባበር መፍታት እንችላለን፡፡
ያሉትን ጉዳዮች በሙሉ በራስ መተማመን መንፈስ፣ በሃሳብ ችግሮቻችንን ፈትተን አገራችንን የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንችላለን የሚል እምነት ነው ያለኝ፤ ይህን ደግሜ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ እዚህ ከእናንተ ፊት ያልኩትን ሄጄም ከህዝቤ ፊት የምደግመው አንድ ቃል ነው ያለኝ፤ቃሌም ፊርማዬ ነው ለሰላም እሰራለሁ፡፡
የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳ ድር በበኩላቸው፤ እንናተ የእምነት አባቶች እና የአገር ሽማግሌ በመሆናችሁ ማክበር ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብንም የምትወክሉ በመሆናችሁ ፤ሕዝብን በሚወክል አካል ጥሪ እዚህ በመገኘቴ እኔ ደስተኛ ነኝ፡፡ ባለፈው ሳምንት ወደ እኛ ክልል መጥታችሁ ተወያይተናል፡፡በውይይቱም በአንድ በኩል አዝኛለሁ፡፡ እኛ የፖለቲካ አመራሮች መሥራት የሚገባንን መስራት ስላልቻልን እናንተን ጭምር አስጨንቀናል፣አስቸግረናል፡፡
አገራችን አሁን ባለው ሁኔታ ተስፋ ቢኖራትም ሥጋትም ተፈጥሮባታል፤ከባድም ስለሆነ ያላየነው፣ ያለመድነው፣ በታሪካችንም የማንቀበለው ትልቅ ችግር በመሆኑ ይሄን መሸከም አንችልም ብላችሁ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የፖለቲካ አመራሮች ማነጋገር አለብን ብላችሁ እና እኛም ኃላፊነት አለብን ብላችሁ በመምጣታችሁ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡ እኛ ሥራችንን ባለመስራታችን የተፈጠረውን የምታዩት ነው፡፡ የሁለት አገሮች ዓይነት የቃላት ጦርነት እያነሳን ከምንጨ ቃጨቅ ኑ ብሎ ማሸመጋገል ተገቢ ነው፡፡
ሁለቱ ህዝቦች ወንድማማቾች ብቻ አይደሉም፤ከዚያም በላይ ናቸው፡፡ የሚያሳዝነው ግን በአሁኑ ጊዜ በርካታ ልዩነቶች አሉባቸው፡፡ ችግሮቹ መፈታት ይኖርባቸው ነበር ነገር ግን በኛ ደካማነት አልተፈቱም፡፡ የአገራችን ማሕበራዊ እሴቶች ብቻ ሳይሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን እሴቶችም ጭምር መሸርሸር ጀምረዋል፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ችግሮችን መፍታት በተቻለ ነበር፡፡ እናንተም አሁን እያደረጋችሁ ያላችሁትን ቀድማችሁ ማድረግ ትችሉ ነበር፡፡ የማመሰግናችሁ እያዘንኩ ጭምር ነው፡፡ ከእነዚህ ችግሮች በቶሎ መውጣት አለብን ፤እናንተ ስላላችሁ ብቻ ሳይሆን ሕዝቦች ጭምር ቶሎ እንዲረጋጋ ስለሚፈልጉ፡፡ መጨነቅ በራሱ የሚፈጥረው ችግር ቀላል አይደለም፤ ህዝቦች ብዙ ችግሮች ደርሰው ባቸዋል፡፡
በአገራችን ታሪክ ሰምተነውም አይተ ነውም የማናውቀውን አዳዲስ ክስተት እያየን ነው፤እንደገና ወደኋላ ተመልሰናል ማለት ይቻላል፡፡ የነበረው የመከባበር ታሪካችን አሁን የለም፡፡ አሁን ያለው ተግባራችን ታሪካችንን የሚያስቀጥል አይደለም፡፡ እየታየ ያለው ጥላቻ፣ ፍረጃ፣ ጥቃት፣ ከሰው የማይጠበቅ ግፍ፣ መጠራ ጠሮች፣ መገለጫ የሌላቸው በደሎች፣ በዝተዋል፡፡ ከየትኛውም ታሪካችን ጋር አብረው የማይሄዱ ተግባራት እየተፈጸሙ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ከትግራይ እስልምና ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጋር አልነጃሽ መስጊድ ሄደን ነበር፡፡ እናም የእኛን ታሪክ ወደ ኋላ ተመልሰን ስናይ የሌላም አገር ሰላም ያጣ ወገን መጠለያ ሆነን ነበር፡፡ አገራቸው ሰላም ባጡ ጊዜ ሀበሻ አገር የሰላም አየር መተንፈስ ችለው ነበር፡፡ ተሰደው ለመጡና አዲስ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሰዎችን ማስጠለል ችለን ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩ የአገሪቱ አመራሮችም ህዝቦችም ከራሳቸው አልፈው ለሌለው ወገን ተቆርቋሪ ነበሩ፡፡ ሰላምና ፍትህ ላጣ ሕዝብ ሰላምና ፍትህ የሚለግስ ህዝቦች ባለቤት የሆነች አገር ነበረች፡፡ የማንኛውንም እምነት ተከታይ በእኩል የሚያስተናግዱ ነበሩ ሕዝቦቻችን፡፡
ልዩነት የግል ጉዳይ ቢሆንም እንደሰው ግን መከባበር፣አብሮ መኖር ላይ መስራት አለብን፡፡ በጋራ አገር የመጠበቅ ታሪካዊ እሴት አለን፡፡ ከባህላችንም ሆነ ከፖለቲካችን ጋር አብሮ የማይሄድ ድርጊት እየተፈጸመ ነው፡፡ እየተሰራ ያለው ህገወጥ ድርጊት በፍጹም የሚያከባብርና የሚያቻችል አይደለም፡፡ ያለንበት የአስተሳሰብ ደረጃና የሚሰራው ተግባር የውርደት ውርደት ነው፤ ፖለቲካችንም እንዲሁ፡፡
እኛ ያለንን እሴት ጠብቀን ብንሄድ ብዙ እርቀት መሄድ እንችላለን፡፡ ግን መከባበር አልቻልንም፡፡ ለመከባበር ትምህርት ቤት አያስፈልገንም፡፡ የድሮውን ማስታወስ ይኖርብናል፤ በድሮው እንኑርም አንልም፡፡ በጣም ጥሩ የሆነ ታሪክ ያለን ሕዝቦች እንዴት ወደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ገባን? ሄዶ ሄዶ ተጠያቂው ሕዝቡ አይደለም፤ ህዝቡ ምንም ችግር የለበትም፡፡ አሁን እዚህ የአማራና የትግራይ እያልን እንተርካለን እንጂ በኦሮሞም ሆነ በሌሎች የትኛውም አካል ዘንድ የሚታይ የከፋ ችግር ነው፡፡ የሕዝብን ጥቅም በሰላም ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ከሰላም በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ የአስተዳደር ድንበርም ይሁን ሌላ ችግር ከሰላም ውጭ እንዴት ይታሰባል ?
ከሌላው የውጭ አካል ጋር በድንበር ችግር የለብንም፤ በውይይትና በድርድር መፍታት ችለናል፡፡ ዘመናዊነት ማለት በአስተሳሰብ መለወጥ፣ መከራከርን መልመድ፣ በመወያየትና መተማመን እንጂ መገዳደል ማለት አይደለም፤ መገዳደል ኋላቀርነት ነው፡፡ እናንተ እንዳወገ ዛችሁት ሁሉ እኛም እናወግዘዋለን፡፡ አሁን ላይ ፖለቲካውን ለብቻው ይዘን የሰላምን መንገድም ለብቻው ይዘን ማየት ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው ፖለቲካ የተበላሸ ስለሆነ ቀላቅለን መሄድ የለብንም፡፡ ለፖለቲካው የራሳችን መድረክ አለን፡፡ ስለዚህ የሰላምን ጉዳይ ማስቀደም ይኖርብናል፡፡ ሌላው በቀጣይ ሰላም ውስጥ ይፈታል፡፡ ተከባብረን፣ተረጋግተን መስራት እንዳለብን የምቀበለውና የማምንበት ነው፡፡ ሁላችንም አመራሮች በመሆናችን የእገሌ የእገሌ መባባሉን ትተን የተበላሸውን ማስተካከል አለብን፡፡
የሰላም ጉዳይ ግን ጊዜ የምንሰጠው አይደለም፡፡ በሰላም ጉዳይ ለነገ የሚባል ነገር የለም፡፡ ፖለቲካውን ነገ ከነገ ወዲያ ማየት ይቻላል፤ማስተካከል ይቻላል፡፡ በእኛ በኩል አሁንም ማረጋገጥ የምፈልገው የፖለቲካ ልዩነት አለን ብለን፣ በፖለቲካው አለመግባባት አለን ብለን የሰላምን ጉዳይ ችላ እንደማንለው ነው፡፡ ሰላሙን ማስጠበቅ ግዴታችን ነው፡፡ ብዙ ፈታኝ ነገሮችንም አልፈናል፡፡ እኛ ጥያቄ የምናነሳው ለራሳችን ብቻ አይደለም ለሁላችንም ነው፡፡
በግልጽ ለመናገር ከአማራ ክልል ጋር ከሌለው በተለየ ችግር የለብንም፡፡ በአማራ ላይ ለይተን የምናነሳው ጉዳይ ምንም የለም፡፡ ፖለቲከኞች ነን የሚሉ እነሱ የራሳቸው አጀንዳ እንዳላቸው እናውቃለን፡፡ የወሰን ጉዳይም ሁሉም ጥያቄ የራሱ ሥርዓት አለው፡፡ ይች መሬት ሄደችብን የሚባል ነገር ለእኛ አጀንዳ አይደለም፡፡ አጀንዳ መሆንም የለበትም፤አንድ ነን እና፡፡ በመካከል ያለው እኮ አስተዳደር ነው፤ ሌላ ትልቅ ጉዳይ አይደለም፡፡
የአማራ ህዝብም ምንም ግጭት አይፈልግም፤ ሌላ ብዙ የሚያሳስቡት ጉዳዮች አለው፡፡ እየተፈጠረ ያለው ችግር የህዝቦች ሳይሆን የፖለቲከኞች ነው ፤ያውም የጥቂት ፖለቲከኞች፡፡ ህዝቡማ በሌለበት ለከፋ ችግርና በደል እየተዳረገ ነው የሚገኘው፡፡ እናንተ የሰላምን ጉዳይ እንደጠየቃችሁ ሁሉ ህዝቡም እየጠየቀ ነው፡፡ አደራ ለግጭት እንዳትዳርጉን እያለ እየለመነ ነው፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት የሚባል ነገር በምንም ዓይነት የማይታሰብና የማይደረግ ነው፡፡ በአመራሩም በኩል የሚጋጭ የለም፡፡ ማንኛችንም አንፈልግም፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011
ሙሀመድ ሁሴን