ክቡራንና ክቡራት
ኢትዮጵያውያን
በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ጎልተው ከወጡ የሕዝብ ፍላጎቶች አንዱ ሕዝብ የሚሳተፍበትና የሚሰማበት የአስተዳደር ሂደት፣ በሌላ አነጋገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባት ፍላጎት ነው። ይህ ፍላጎት ከዘመን ወደ ዘመን እያደገ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ዛሬ ላይ ደርሷል። በዚህ ባለንበት ዘመንና ትውልድ ይህ ፍላጎት እውን ሆኖ ዲሞክራሲያዊ አገር እንድንገነባ ትልቅ ፋይዳ የሚኖረው አንዱ ኩነት ቀጣዩ ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ መሆኑ ግልጽ ነው። ለዚህም ነው ይህ ምርጫ በብዙዎች በጉጉት እየተጠበቀ ያለው። አንዳንድ ፓርቲዎችና ልሂቃን ምርጫው መደረግ የለበትም የሚል አቋም በያዙበት ጊዜ መንግሥት ምርጫው በጊዜው መደረግ እንዳለበት አምኖ በቁርጥ ሲዘጋጅ የነበረው የምርጫውን አገራዊ ፋይዳ በሚገባ በመረዳትና በማመን ነበር።
ሆኖም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሠት የተነሣ ይህን ምርጫ፣ በኮቪድ 19 ምክንያት፣ ቀድሞ በተያዘው ሰሌዳ ማካሄድ እንደማይቻል፣ በየደረጃው ላሉ ምክር ቤቶች የሚደረገውን የሀገሪቱን ምርጫ ለማከናወን በሕግ ብቸኛ ሥልጣን የተሰጠው የምርጫ ቦርድ፣ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም አስታውቋል። በዚህም የተነሣ ምርጫውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ የግድ ሆኗል።
ከኮቪድ የተነሣ የምርጫ መተላለፍ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በብዙ አገራት እየተከሠተ ነው። ከዚህ በተቃረነ መልኩ ምርጫ ላለማስተላለፍ ወስኖ፣ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ሙሉ በሙሉ በፖስታ ለማድረግ የወሰነው የፖላንድ መንግሥት ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ከፍተኛ ውግዘት ደርሶበታል። የሀገሪቱ የዲሞክራሲ ተቋማት፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ እና ምርጫውን ነፃና ፍትሐዊ ለማድረግ ምርጫው መተላለፍ እንዳለበት እየሞገቱ ነው። ከፖለቲካዊ ምርጫዎች በተጨማሪ በኮቪድ 19 ምክንያት የዓለም ትልቁ የስፖርት ውድድር የሆነው ኦሎምፒክ ለአንድ ዓመት ተራዝሟል። ዘመናዊ ኦሎምፒክ ከተጀመረበት ከ1896 ጀምሮ ኦሎምፒክ ተቋርጦ የሚያውቀው በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ምክንያት ብቻ ነበር። ኮሮና በዓለም ላይ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ይህ ሁኔታ በግልጥ ያሳየናል።
በዱባይ ሊደረግ ታቅዶ በብዙ ቢሊዮን ዶላሮች የተዘጋጀውና ለስድስት ወራት ይቆይ የነበረው የዓለም ኤክስፖም ለአንድ ዓመት ተሸጋግሯል።
የምርጫ ቦርድ ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ እንደማይችል ከገለጠበት ከመጋቢት መጨረሻ ጀምሮ መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን በታወቁና በበሰሉ የሕግ ባለሞያዎች ሲያስጠና ነበር። በሦስት ቡድን ተከፋፍለው፣ አንዳቸው ከሌላኛው የማይገናኝ
ቡድን መስርተው፣ ባለሞያዎቹ አጥንተዋል። ከሪፖርቱ እንደተረዳነውም የሀገሪቱን ሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጎች፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና የሌሎች አገሮች ልምዶችን በሚገባ ተመልክተዋል። በመጨረሻም የተለያዩ አማራጮቻቸውን ይዘው በአንድነት በመገናኘት የተቀራረቡ የሐሳብ አማራጮችን አቅርበዋል።
ባለሞያዎቹ ያቀረቧቸውን አማራጮች በመያዝ ምርጫው ሊተላለፍ የሚችልበትን ሕጋዊ አግባብ በተመለከተ ከልዩ ልዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ምክክር ተደርጓል። ይህንንም ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በጉዳዩ ላይ ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ እንዲሰጥበት ጉዳዩን ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ መርቶታል። በዚህ መልኩ በሕግ አውጭው የሚቀርብ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ በብዙ አገራት የተለመደ ሕገ መንግሥታዊ ሐሳቦችን ወደ መሬት የማውረጃ መንገድ ነው። ለምሳሌ በፈረንሳይ የሕገ መንግሥት ካውንስል የሚባለው የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ተርጓሚ ብዙ ጉዳዮችን የሚያየው በሀገሪቱ ፓርላማ እየተመራለት ነው። የኛም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረገው ይሄንኑ ነው።
በኮቪድ 19 የተነሣ ስድስተኛው አገራዊ ጠቅላላ
ምርጫ በታቀደለት ጊዜ ሊካሄድ እንደማይችል የምርጫ ቦርድ ካስታወቀ በኋላ ምላሽ የሚፈልጉ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የቀረቡ አማራጮች ለሕዝብ ይፋ ሆነዋል። አማራጮቹ ይፋ ከሆኑ በኋላ ጉዳዩ የሕዝብን አትኩሮት የሳበ መነጋገሪያ ሆኗል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከሕዝቡ፣ ከሕግ ባለሞያዎችና ከተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የተለያዩ አስተያየቶች እየቀረቡ ይገኛሉ። በጉዳዩ ላይ የሚቀርቡት ዋና ዋና አስተያየቶች በሦስት ሊከፈሉ ይችላሉ፤
1) ሕጋዊ/ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ የሚቀበሉ፤ ነገር ግን ከሕገ መንግሥት ትርጉም ውጭ ያሉ ሕገ መንግሥታዊ አማራጮችን የሚያቀርቡ፤
2) ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜን የተሻለ አማራጭ አድርገው የሚያቀርቡ፤
3) ጉዳዩ በሕጋዊ አካሄድ ሳይሆን በፖለቲካ መፍትሔ የሚፈታ ነው የሚሉ፤ ለዚህም የሽግግር መንግሥት መቋቋም (ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ያቀፈ መንግሥት) ፖለቲካዊ መፍትሔ ነው ብለው የሚከራከሩ ናቸው።
የመጀመሪያውን ሐሳብ የሚያራምዱት የተወሰኑ የሕግ ባለሞያዎች አንዳንዶቹ ምርጫን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማራዘም እንደሚቻል እና የተሻለው አማራጭ ይሄ እንደሆነ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። በዚህ መልክ ምርጫው በመተላለፉ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እስከ ቀጣዩ ምርጫ በሥራ ላይ የሚቀጥል እንደሆነ እነዚህ የሕግ ባለሞያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል አንዳንድ ፓርቲዎች እና የሕግ ባለሞያዎች ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የተሻለ አማራጭ ነው ብለው መከራከሪያ ያቀርባሉ።
መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብቻውን ብዙ ርቀት መሄድ እየቻለ ወይም በቀላሉ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ እየቻለ ጉዳዩን ለምክክርና ለውይይት ማቅረቡ አሳታፊ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል። በዚህ ሂደት ቀደም ተብሎ የተገለፁትን ዓይነት በሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ገንቢ አስተያየቶች፣ ግብዓቶችና ትችቶች እያቀረቡ ላሉ ሁሉ ምስጋናችንን እናቀርባለን። እንዲህ ያሉ ምክንያታዊ እና በሕግ ላይ የተመሠረቱ ውይይቶች እና ክርክሮች ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው። የሐሳብ ፍጭቶች በጠረጴዛ ዙሪያ፣ በአንደበትና በብእር ከተደረጉ ሀገር ይገነባሉ።
ለጥፋት መቀስቀሻና ለደም ማፍሰሻ ከዋሉ ግን የሥልጣን ጥመኞችን ያፈራሉ። ወደ ሁለተኛው ሐሳብ ስንመጣ፤ ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ሐሳባቸውን በተለያዪ የመገናኛ ብዙኃን እየገለፁ ያሉ የሕግ ባለሞያዎችና ሌሎች ሐሳብ አቅራቢዎች አሉ። ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በነበረን ውይይትም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ በብዙ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለ ተቀባይነት ያገኘ አማራጭ እንደሆነ ለማየት ችለናል።
ይህ አማራጭ የተሻለ ነው የተባለው፣ ዛሬ የገጠመንን ፈተና በማየት ብቻ አይደለም። ለወደፊቱም ሕገ መንግሥታዊነትን በሀገራችን እንዴት ልናጎለብት እንችላለን? የሚለውን በማሰብ ጭምር ነው። ከእኛ ሕገ መንግሥት ተቀራራቢ ዕድሜ ያለው የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት በሕገ መንግሥት ትርጓሜ ዳብሮ ከአፍሪካ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሆኗል። በጎረቤታችን ኬንያ አሥር ዓመት ብቻ ያስቆጠረው ሕገ መንግሥት በትርጉም እየደረጀ ለጥናትና ምርምር የሚፈለግ ሥርዓት ሆኗል። ይህ አጋጣሚ እኛም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታችንን በትርጓሜ የምናዳብርበት አዲስ ምዕራፍ ይከፍትልናል። ጀርመን፣ ሕንድ፣ አሜሪካ፣ ኮሎምቢያ፣ ካናዳ ግንባር ቀደም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ተደርገው የሚቆጠሩት በሕገ መንግሥት ትርጓሜ ሕገ መንግሥቶቻቸው እንደ ሰነድ ያሉባቸውን ክፍተቶች ለመሙላት ስለቻሉ ነው።
ወደ ሦስተኛው ሐሳብ ስንመጣ በዋነኛነት እንደ መፍትሔ ተደርጎ የሚቀረበው “የሽግግር መንግሥት” አማራጭ ነው። ለዚህ አማራጭ መነሻ ተደርገው የሚቀርቡት መከራከሪያም ደግሞ፤-
1) የገጠመን ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ነው፣ ሕገ መንግሥቱ ለዚህ ችግር መልስ የለውም፣ ምንም ዓይነት ምርጫን የማራዘሚያ መንገድ በሕገ መንግሥቱ የለም፤
2) ለሕገ መንግሥታዊ ትርጉም መነሻ የሚሆን እና ይህን ጉዳይ የተመለከተ ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ የለም፤
3) ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜም ሆነ ማሻሻያ የብልጽግና ፓርቲ ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠራቸው ምክር ቤቶች የሚተገበሩ ስለሆኑ፣ ገለልተኛ ባልሆነ አካል ተግባራዊ ከተደረጉ ተቀባይነት የሌላቸው መፍትሔዎች ናቸው የሚል፤
4) ገዢው ፓርቲ የሚቆጣጠራቸውን የምክር ቤት
ወንበሮች ነፃ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ያገኘው አይደለም፣ ስለዚህም ከመጀመሪያውም ቅቡልና ያለው መንግሥት አይደለም፣ ከመስከረም በኋላ ደግሞ ምንም ዓይነት ቅቡልና እና ሕጋዊ መሠረት የሌለው፣ ዓለም አቀፍ ዕውቅናም የማይኖረው መንግሥት ይሆናል የሚል መከራከሪያ ነው።
እነዚህ መከራከሪያዎች መቅረባቸውና የውይይት አጀንዳዎች መሆናቸው ለሐሳብ ፍጭትና ለሰላ መፍትሔ መገኘት እጅግ ጠቃሚ ናቸው። የቀረቡት አማራጮች ግን በአግባቡ መመርመር አለባቸው።
ሕገ መንግሥቱ ለዚህ ጉዳይ የሚሆን መፍትሔ የለውም የሚለው መከራከሪያ ያላየው ነገር አለ።
በመጀመሪያ ደረጃ እጅግ ብዙ ቁጥርና ሰፊ ልምድ ያላቸው የሕግ ባለሞያዎች እና ምሁራን አማራጮች አሉ እያሉ (አማራጮቹ የየራሳቸው ውሱንነት ያላቸው ቢሆንም) በጉዳዩ ላይ ምንም ምርምር እና ጥናት ያላደረጉ፣ ባለሞያም ያልሆኑ ሰዎች በድፍረት ሕጋዊ መፍትሔ የሌለው ችግር ነው፣ ማለታቸው ምኞታቸውን እንጂ እውነታውን አያሳይም።
ሲቀጥልም፣ ነገሩ “መድኃኒት የለውም ሲልህ መድኃኒቱ እኔ ጋር ብቻ ነው ማለቱ ነው” እንደሚባለው ሆኖ እናገኘዋለን።
አስቀድመው፣ ነገሩን ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝ የተፈጠረ፣ ሕጋዊ መፍትሔም የሌለው ቀውስ ያደርጉታል። ቀጥለውም ራሳቸውን መፍትሔ እና መድኃኒት አዋቂ አድርገው ያቀርባሉ። ‹ሕጋዊ መፍትሔ የለም› ማለታቸው ‹ሕጋዊ መፍትሔን አንፈልግም› ማለታቸው ነው። ሕጉ በአቋራጭ ሥልጣን እንድንቆናጠጥ አያደርገንም ማለታቸው ነው።
እንደሚታወቀው፣ ማንኛውም ሕገ መንግሥት ሰፊና ጥልቅ ሐሳቦችን የያዘ ነው። ሕገ መንግሥቱ የያዛቸው አንቀጾችና አንቀጾቹ የተዋቀሩባቸው መሠረተ ሐሳቦች አሉ። ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት (Constitiution and Constitutionalism) ሁለት
የተሣሠሩ ግን የየራሳቸው ትርጉም ያላቸው ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው። ሕገ መንግሥት የተጻፈው ነው፣ ሕገ መንግሥታዊነት ግን ሥርዓቱ ነው። ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ ማለት ከሁለቱም የሚገኝ መፍትሔ ነው።
የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ የማዋለድ ሥራ ነው። ለምሳሌ የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት ስለሞት ቅጣት አያወራም። በዚህ ጉዳይ ላይ
ሕገ መንግሥታዊው አቋም ምን እንደሆነ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ በሰጠው ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ ምላሽ ለማግኘት ችሏል።
በኮሎምቢያ ‹አንድ ፕሬዚዳንት ከአንድ የሥልጣን ዘመን በላይ ማገልገል አይችልም› የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ማሻሻል ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለውን ጥያቄ አስመክልቶ ሕገ መንግሥቱ በቀጥታ የሚለው ነገር ባይኖርም ጉዳዩ በሕገ መንግሥት ትርጓሜ ምላሽ ማግኘት ችሎዋል። በሀገረ አሜሪካ ሕገ መንግሥቱ ስለ ጤና ኢንሹራንስ (Obamacare ) የሚለው ምንም ነገር የለም፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን የማን እንደሆነ እንኳን ሕገ መንግሥቱ በቀጥታ የሚለው የለውም።
ነገር ግን እነዚህን እና ሌሎች መሰል ወሳኝ ጥያቄዎችን በትርጉም ምላሽ መስጠት ተችሏል።
በሰሞኑ ክርክር፣ ለሕገ መንግሥታዊ ትርጉም መነሻ የሚሆን እና ይህን ጉዳይ የተመለከተ ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ የለም የሚለው መከራከሪያም ወሳኙ አካል ሊመልሰው የሚገባውን ጥያቄ ቀድሞ የሚመልስ ነው።
አንደኛ፣ የሚተረጎም ነገር አለ ወይም የለም? የሚለው የሞያ ውሳኔ ነው። ትርጓሜ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም? የሚለውን በሞያዊ መመዘኛ አይቶ የመወሰን ሥልጣን ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በሕግ ተሰጥቶታል። መመለስ ያለበት እርሱ ነው። ሁለተኛ፣ በጉዳዩ ላይ የተካኑት ባለሞያዎች የሚተረጎም ነገር እንዳለ ሞያዊ አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው። የሌሎች አገራት ልምድም ለዚህ ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝ፣ ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ያመለክታል።
ሦስተኛ፣ እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ከአንዳንድ ወገኖች የታየው ብዥታ የትርጉምን አስፈላጊነት የሚመሰክር ነው። ማባሪያ ከሌለው የሥልጣን ንትርክ ተቋማዊና ሕገ መንግሥታዊ በሆነ አካሄድ ለገጠመን ፈተና መፍትሔ መፈለግ የተሻለውና ወደፊት የሚያራምደን አማራጭ ነው።
አራተኛ፣ ‹የሚተረጎም አንቀጽ የለም› የሚለው ክርክር አውቆ ላለማወቅ ከወሰነ ሰው፣ ወይም ጥልቅ በሆነ የአላዋቂነት አረንቋ ውስጥ ከተዘፈቀ ሰው የሚጠበቅ መከራከሪያ ነው። ስለ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም በጥቂቱ እንኳን ለመረዳት በቅን ልቡና ለሞከረ እና ጥረት ላደረገ ሰው ይህ ጉዳይ ትርጉም የሚያሻው እና በትርጉም ሊፈታ የሚችል እንደሆነ ግልጽ ነው።
ሌላም የተነሣ መከራከሪያ አለ፤- ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜም ሆነ ማሻሻያ የብልጽግና ፓርቲ ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠራቸው ምክር ቤቶች የሚተገበሩ ስለሆኑ፣ ገለልተኛ ባልሆነ አካል ተግባራዊ የሚደረጉ ተቀባይነት የሌላቸው መፍትሔዎች ናቸው የሚለው ጉዳይ፤ ነገሩ ወንዝ ባያሻግርም፤ በሕገ መንግሥት ትርጉም የማይተካ ሚና የሚጫወተው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ፣ በዋነኝነት በገለልተኛ ባለሞያዎች የሚመራ ተቋም ነው። በሕገ መንግሥቱ ይህን ጉባኤ የተመለከቱ ድንጋጌዎች ፍርድ ቤቶችን ከተመለከቱ ድንጋጌዎች ጋር አብረው የተቀመጡ ናቸው። ጉባኤው ወደ ፍርድ ቤትነት የተጠጋ/ ሕገ መንግሥታዊ ተቋም ነው። ከዚህም በተጨማሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚመራው በብልጽግና ፓርቲ አይደለም። ስለዚህ የትርጓሜው ሂደት በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ያለ ነው ለማለት አይቻልም። የትርጓሜውን የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርበው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና በምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ ገለልተኛ አካል ነው።
የሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ ሥርዓታችን ወደፊት መሻሻል ቢኖርበት እንኳን፣ ለሕገ መንግሥታዊነት ተገዥ የምንሆነው፣ አሁን ያለውን እና በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን ሥርዓት አክብረን መሆን አለበት። ዛሬ ያሉንን ተቋማት እና ሥርዓት ማክበር ካልቻልን፣ ሕገ መንግሥታዊነት ሥር ሊሰድ አይችልም። ለምሳሌ በሀገረ አሜሪካ፣ ጥቁሮች እንደ ዜጋ ያላቸውን መብት ለማስከበር ከነውሱንነቱም ቢሆን በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ማሕቀፍ ውስጥ ተግባራዊ ያደረጉት ትግል ነው። እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ድረስ ያቀረቡዋቸው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች በመጨረሻ ዘላቂ እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ መብታቸውን እንዲያስከብሩ አስችሏቸዋል። ያሉትን ተቋማት እና ሥርዓት እየተጠቀሙ፣ እያዳበሩ መሄድ ብልህነት እና ለሀገር እጅግ ጠቃሚ አካሄድ ነው።
የሕገ መንግሥታዊነት አንዱ መገለጫ ሕገ መንግሥቱን የተመለከቱ አለመግባባቶች ሲኖሩ፣ የመንግሥት ውሳኔና ተግባር ሕገ መንግሥታዊ አይደለም የሚል ቅሬታ ሲኖር ጉዳዩን ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ ለተሰጠው አካል ማቅረብ ነው። ከዚያ ውጭ
ሁሉም ሕገ መንግሥቱን ተርጓሚና የሕገ መንግሥት ዳኛ እሆናለሁ ካለ ለዲሞክራሲም ሆነ ለሕገ መንግሥታዊነት የማይበጅ ምስቅልቅል የሚያስከትል አካሄድ ነው። በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ሥርዓትና የተቋቋሙ ተቋማትን አክብረን መንቀሳቀስ ጉድለታቸውን በሂደት እየሞላን መሄድ የሁላችንም ግዴታ ነው።
ሌላም የተሠነዘረ መከራከሪያ አለ፤- የገዢው ፓርቲ የሚቆጣጠራቸውን የምክር ቤት ወንበሮች ነፃ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ያገኘው አይደለም፣ ስለዚህም ከመጀመሪያውም ቅቡልነት ያለው መንግሥት አይደለም፣ ከመስከረም በኋላ ደግሞ ምንም ዓይነት ቅቡልነት እና ሕጋዊ መሠረት የሌለው፣ ዓለም አቀፍ እውቅናም የማይኖረው መንግሥት ይሆናል የሚል ነው። ይህ አስተያየት መመለስ ያለበት በሕግ ነው፤
ስለ 2007 ምርጫ መከራከር ሳያስፈልገን፣ አሁን ያለው መንግሥት ሕግ የሚያወጣ፣ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን የሚፈርም፣ በጀትና ዕቅድ የሚያፀድቅ ሕጋዊ መንግሥት ነው። ብልጽግና ፓርቲም በመላው ሀገሪቱ አባላት እና ደጋፊዎች እንዲሁም መዋቅር ያለው፤ አገራዊ ለውጥን በመምራት የብዙዎችን ድጋፍ ያገኘ ፓርቲ ነው። ሕጋዊ በሆነ አግባብ የኮቪድ 19 ሥጋት እስኪወገድ ድረስ እና ቀጣይ ምርጫ እስኪካሄድ ደግሞ ሀገር የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት ፓርቲ ነው።
ከጥቂት ከባቢ ያልዘለለ ድጋፍ ያላቸው ፖለቲከኞች በሕግም፣ በፖለቲካም ሆነ በሞራል መስፈርት ከእነርሱ ብዙ እጥፍ የተሻለ ቅቡልነት ያለው ፓርቲ እና መንግሥት ሀገሪቷን እየመራ መሆኑን መረዳት አለባቸው።
የቀድሞውን የምርጫ ሰሌዳ የተወካዮች ምክር ቤት ሲፀድቅ ያልተነሣ የሕጋዊነትና የቅቡልነት ጥያቄ፣ ምርጫው እንዲራዘምና ሌላ ለመራዘሙም ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ እንዲገኝለት ሲወስን የቅቡልነትና የሕጋዊነት ጥያቄ ማንሣት በአንድ ጉዳይ ሁለት አቋም ማያዥ ነው።
የመጨረሻው ነገር ግን በቀላሉ የማይታየው ሐሳብ ደግሞ ‹መፍትሔው የሽግግር መንግሥት ነው› የሚለው ነው። ይህ መንገድ በሕገ መንግሥቱም ያልተደነገገ፤ ሕገ መንግሥታዊም ያልሆነ ሐሳብ ነው፤ ያለምርጫ እንዲሁ ተጠራርቶ ሥልጣን የሚከፋፈልበት ምንም ዓይነት ሕጋዊም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ የለም። የፖለቲካ ፓርቲ ስለሆንኩ ሥልጣን ይገባኛል የሚለው ፈሊጥ ዲሞክራሲያዊም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም። ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን በምርጫ ብቻ እንደሚገኝ ይደነግጋል። ይህንን መሠረታዊ መርሕ በጣሰ ሁኔታ ሥልጣን እንደ ድግስ ትሩፋት ለሁላችንም ይዳረስ የሚለው አካሄድ በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የምናደርገውን ጥረት ወደ ኋላ የሚመልስ፣
ከሕዝብ እና ከሀገር ይልቅ የሥልጣን ፍላጎትን የሚያስቀድም አስተሳሰብ ነው።
ለመሆኑ የተመረጠ መንግሥት እያለ፣ ያልተመረጡ ፓርቲዎች ተሰብስበው መንግሥት የሚመሠርቱት በየትኛው የሞራል፣ የሕግና የሥርዓት አካሄድ ነው?
የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ የሕዝብ ይሁንታ፣ በአንድም በሌላም መልኩ ሳይኖረው፣ በፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ብቻ እንዲወሰን ሥልጣን የሚሰጠው የትኛው የሕግ መሠረት ነው?
ከአንድ መቶ በላይ ፓርቲዎች ተደራድረውና ተስማምተው ወደ ፖለቲካዊ መፍትሔ እስኪመጡ ድረስ ምርጫው የሚራዘምበት ችግር ተፈትቶ ከሕጋዊ ምርጫው ቀን እንደርስ የለም ወይ? ለወራት ምርጫን ማራዘም ወይስ ለዓመታት ለሽግግር መንግሥት ብሎ የብጥብጥ እና የንትርክ መንግሥት መፍጠር ነው ኢትዮጵያን ለአደጋ የሚያጋልጠው?
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የቆየ ተሳትፎ ያላቸው ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የሲቪክ ተቋማት መሪዎች አሉ። እነዚህን ሁሉ ወይ በተደራዳሪነት ወይም በመራጭነት፣ አለያም በተመራጭነት ያገለለ የፓርቲዎች የሽግግር መንግሥት፣ እንዴት አሁን ካለው መንግሥት በተሻለ ቅቡልነት ይኖረዋል?
የሽግግር መንግሥት የተመሠረትባቸው አገራት እና አጋጣሚዎች ብዙውን ጊዜ ከወታደራዊ ወይም አምባገነናዊ የጥቂቶች አስተዳደር ወደ ዲሞክራሲያው ሥርዓት ሽግግር ለማድረግ የፈለጉ እና ተሰናባቹ ገዥ ቡድን እና ወደ ሥልጣን እየተንደረደረ ያለ፣ የሕዝብ ድጋፍ ያለው ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እስኪካሄድ፤ አዲስ ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ እስኪዘጋጅ ተግባራዊ የሚያደጉት አማራጭ ነው። ለምሳሌ በድቡብ አፍሪካ የነጮች ብቻ የሆነው ፓርቲ እና የአፓርታይድ መንግሥት፣ የብዙኃን ድጋፍ ላለው የ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን እስኪያስረክብ እና አዲስ ሕገ መንግሥት እስኪፀድቅ በጋራ የሽግግር መንግሥት መሥርተዋል። በፖርቱጋል፣ በፖላንድ እና ሌሎችም በመሰል የሽግግር ሂደት ያለፉ አገራት ልምድም ተመሳሳይ ነው። የደቡብ አፍሪካን፣ የደቡብ እና የምሥራቅ አውሮፓን እንዲሁም የላቲን አሜሪካን የሽግግር ተሞክሮ ስናይ አብዮታዊ ሊባል የሚችል ለውጥ፣ ሙሉ የሕገ መንግሥት ለውጥ የሚካሄድበት፣ በሥልጣን ላይ ያለው ኮሙኒስት ፓርቲ ወይም ወታደራዊ አገዛዝ ከሥልጣን ለመውረድ በሚንደረደርበት ሂደት ውስጥ ነው የሽግግር መንግሥት የመሠረቱት።
በዚህ አጋጣሚ በግልጽ መታወቅ ያለበት ነገር አለ። በኢትዮጵያ ያለው ለውጥ ሪፎርም እንጂ አብዮት
አይደለም። ሕገ መንግሥት ቀይረን አዲስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እየገነባን አይደለም። ገዢው ፓርቲም ታድሶ እና የሕዝብ ተቀባይነቱ ጨምሮ ገና ጀንበሩ እየወጣ ያለ፣ አዲስ ጉልበት እና አቅም ያለው፣ በቀጣይም ምርጫ እጅግ ሰፊ የማሸነፍ ዕድል ያለው ፓርቲ እንጂ ተሰናባች እና ጀንበሩ ያዘቀዘቀ ስብስብ አይደለም። ስለዚህ የሽግግር መንግሥት የሚለው ሐሳብ ከሕግ አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ፣ በንድፈ ሐሳብም ሆነ ከሽግግር ተሞክሮ አንፃር ለኢትዮጵያ የሚሆን እና የሚበጅ አይደለም።
በተለይም የኮቪድ 19 ሥጋት ባለበት እና የቀጣናችን ሁኔታም ለሀገር ሉአላዊነት ሥጋት በደቀነበት ወቅት የሽግግር መንግሥት እንመሠርታለን ብሎ መቋጫ የሌለው ውይይት ይባል ድርድር መጀመር ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። ሕገ ወጥ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው።
መገንባት የምንፈልገው ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲ ነው፤ ይህም ማለት ሕገ መንግሥታዊነት የሰፈነበት፣ የሕገ መንግሥት የበላይነት የሚከበርበት ሥርዓት ነው። ሕገ መንግሥቱ ከደነገገው ሥርዓት ውጭ ያለምርጫም፣ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና በሌለው ሕገ ወጥ “ምርጫ” ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት የለውም። እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ የኢፌዴሪን ሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች የአገራችንን ሕጎችና ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጥስ ነው። በዚህ ረገድ ኢ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን መያዝን አጥብቆ የሚያወግዘውና የሚከለክለው እንዲሁም በግለሰብ ደረጃም ሆነ በአገር ላይ ቅጣት የሚደነግገው የአፍሪካ የዲሞክራሲ፣ የምርጫና የአስተዳደር ቻርተር /African Charter on Democracy, Elections and Governance/ ተጠቃሽ ነው።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 50 የፌደራል መንግሥትን ሥልጣንና ተግባር ሲዘረዝር ቁጥር አንድ አድርጎ ያስቀመጠው ሕገ መንግሥቱን የመጠበቅና የመከላከል ኃላፊነት ነው። ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት አስፈላጊውን ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን፤
ይህንን ማድረግ የማንደራደርበት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታችን ነው። በሕገ መንግሥቱና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ካልሆነ በስተቀር የጨረባ ምርጫ ለማድረግ መነሣት ሀገርንና ሕዝብን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመሆኑ መንግሥት ሀገርንና በየትኛውም በኩል ያለን ሕዝብ ደኅንነት ለመጠበቅ ሲል ወሳኝ ርምጃ እንዲወስድ ይገደዳል።
ሥልጣን የሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች የሐሳብ ክርክሮቻቸው ወጣቱንና እናቶችን በማይጎዳ መልኩ እንዲያደርጉት ይመከራሉ።
ፖለቲከኞች ሥልጣን እንዲይዙ ወጣቶች ማለቅ፣ እናቶች ማልቀስ፣ ቤቶች መፍረስ፣ ሕዝቦች መፈናቀል የለባቸውም።
የኢትዮጵያውያን ጫንቃ ይሄንን ከሚሸከምበት ደረጃ አልፏል።
የኮቪድ 19 ሥጋት ተጋርጦብን፣ የሀገር ሉዓላዊነትና ደኅንነት ለአደጋ ተጋልጦ ባለበት ጊዜ፣ ሥልጣንን ያለምርጫና ከሕግ አግባብ ውጭ፣ በሁከትና በብጥብጥ፣ ካልሰጣችሁኝ አገር አተራምሳለሁ የሚለውን ማንኛውንም ኃይል እንደማንታገሥ ከወዲሁ በግልጽ ለመንገር እንፈልጋለን። ለዚህም በሁሉም ረገድ በቂ ዝግጅት አለን።
በአጠቃላይ የሚኖረን የመፍትሔ ሐሳብ ሁላችንንም በፍፁምነት የሚያረካ ባይሆንም
- ከሕግና ከሕገ መንግሥታዊነት ያልወጣ
- ሀገሪቱን ያለ መንግሥት የማያስቀር
- በቀጣይ ምርጫውን የማድረጊያ ጊዜውን አጭርና ምቹ የሚያደርግ
ኢትዮጵያ: አዲሲቷ የተስፋ አድማስ Ethiopia: A New Horizon of Hope - ኮቪድ 19ን ለመከላከል ያለንን አቅምና ዕድል የማያበላሽ
- የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብት ለጥቂቶች አሳልፎ የማይሰጥ
- አካሄዱ ለወደፊቱ ሌሎች ችግሮችንም እንድንፈታ መንገድ የሚከፍት መሆን እንዳለበት መንግሥት ያምናል። ለዚህም ነው ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም የገጠመንን ፈተና ከሌሎች በተሻለ መልኩ ይፈታዋል ብለን የምናምነው።
ይሄንንም በውይይት፣ በምክክር፣ በጥበብና በዕውቀት ለኢትዮጵያና ለሕዝባችን በሚበጅ መልኩ እናድርገው፤ ለዚህም እንደ ወትሮ የሚጠበቀውን ለማድረግ ዝግጁ ነን። ይሄንንም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በትኩረትና በጥሞና እንዲከታተል አድራ ማለት እፈልጋለሁ። አመሰግናለሁ። ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ፤ ያሻግርም።
ሚያዚያ 29, 2012
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2012