አዲስ አበባ፡- ከመጪው ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ ኅብረተሰቡ የሚሸምታቸውን ምግቦችንና የፋብሪካ ውጤቶችን ጥራትና የመጠቀሚያ ጊዜ ያላለፈባቸው መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት የአዲስ አበባ የምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን አሳሰበ፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ታደሰ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በበዓላት ወቅት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ ይስተዋላል። ከዚህ መነሻነትም ከመጪው ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞም ኅብረተሰቡም የሚሸምታቸውን ምርቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያላለፈባቸው መሆኑንና ለረጂም ጊዜ ፀሐይ ላይ ያልተቀመጡ መሆኑን በማረጋገጥ መግዛት አለበት።
የተጠቃሚውና አገልግሎት ሰጪው ኅብረተሰብ ጤና እንዲጠበቅ በርካታ አማራጮችን በመጠቀም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጇ፤ ለኅብረተሰቡ የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠርና በመወያየት እንዲሁም የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም ግንዛቤ እየተፈጠረ ይገኛል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ በየእለቱ የሚጠቀማቸውን የምግብና ጤና ነክ ምርቶች ጥራታቸውን አረጋግጦ በመጠቀም ተላላፊና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ራሱንና ቤተሰቡን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
የጥምቀት በዓል የሚከበረው ከቤት ውጪ በአደባባይ ላይ እንደመሆኑ የበዓሉ ታዳሚ በዓሉን ለማክበር በሚወጣበት ወቅት ሊጠቀምባቸው የሚችላቸው ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ እንዲሠራ ስምሪት እንደተሰጠ ተናግረዋል።
ደህንነቱ የተጠበቀ የምግብና መድኃኒት አቅርቦት እንዲኖር የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አመልክተው፤ቁጥጥር በሚደረግበት ወቅትም ከተገኙ ሕገወጥ ተግባራት መካከል ከቄራ ውጪ እርድ ማከናወን፣ ከበርበሬ ጋር ባእድ ነገሮችን ቀላቅሎ ለገበያ ማቅረብ፣ ምንጫቸው የማይታወቁ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብንና መሰል ድርጊቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ባለሥልጣኑ በተሰጠው ኃላፊነት ምርቶቹን የማስወገድ እና የተጠያቂነት ሥራ መሥራቱን አውስተው፤ነጋዴው ለማህበረሰቡ በሚያቀርባቸው የፍጆታ ምርቶች ጥራትና ደህንነት በተጠበቀ መልኩ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በሚከሰቱ ሕገወጥ ድርጊቶች ተጎጂው ማህበረሰቡ በመሆኑ ሕገወጥ ድርጊት በሚያስተውልበት ወቅት በየደረጃው ለሚገኙ የሕግ አስከባሪዎች ወይም ለባለሥልጣኑ ጥቆማ በመስጠት የቁጥጥር ሥራው ባለቤት እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም