አዲስ አበባ፡- በሲዳማ ክልል በተያዘው ዓመት መጨረሻ በልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ ግብር ተጠቃሚ የሆኑ ተረጂዎችን ለማስመረቅ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አቶ አበራ ዊላ አስታወቁ፡፡
አቶ አበራ ዊላ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በክልሉ ልማታዊ ሴፍትኔት መርሐ ግብር በቀጥታ ድጋፍ ከሚደረግላቸው በተጨማሪ በማኅበረሰብ ሥራ 134 ሺ 716 ተጠቃሚዎች የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው እንዲሠሩ ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም ከ50 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን እንዲችሉና ከመርሐ ግብሩ ተመርቀው እንዲወጡ እየተሠራ ነው።
‹‹በክልላችን 31 የገጠርና ስድስት የከተማ አስተዳደር አደረጃጀቶች ውስጥ ያሉ 20 ወረዳዎች በገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ታቅፈዋል›› ያሉት አቶ አበራ፤ በክልሉ ካለው አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ውስጥ 153ሺ159 የመርሐ-ግብሩ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። ከዚህ ወስጥ ደግሞ 18 ሺ 443 የቋሚና ቀጥታ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ተናግረው፤ እነዚህም ዓመቱን ሙሉ የሚደገፉ፤ በቤተሰባቸው ጉልበት የሌላቸው መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡ ቀሪዎቹ 134 ሺ 716 ተጠቃሚዎች በአንፃራዊ መልኩ የተሻሉና በቤተሰባቸው ውስጥ ጉልበት ያላቸው፤ ነገር ግን ዓመቱን ሙሉ የምግብ ክፍተታቸውን እንደማይሸፍኑ ታውቆ የተለዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በመርሐግብሩ የሚደገፉና ሥራ የመሥራት አቅም ያላቸው ተጠቃሚዎች ተለይተው በዶሮ እርባታ፤ በከብት ማድለብና ማሞከት፣ በንብ ማነብ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው እንዲሠሩ የክልሉ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን ያደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የብድር አቅርቦት፤ ሥልጠና የመሥሪያ ቦታ እንዲያገኙ በመደረጉ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ተጠቃሚዎች የምግብ ክፍተታቸውን ከመሸፈን አልፈው ጥሪት በማፍራት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩልም እንደሀገር በተለይ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ ‘ከተረጂነት ወደ ምርታማነት’ የሚለውን መርሐ-ግብር ውጤታማ ለማድረግም መንግሥት ከ45 ቢሊዮን ብር መመደቡን አስታውሰው፤ ‹‹እኛም በክልላችን ዜጎችን ከተረጂነት ለማላቀቅ 600 ሚሊዮን ብር መድበን እየሠራን ነው›› ብለዋል፡፡ ይህንን ሀብት ከዚህ ቀደም በማጥራት ሂደት የተለዩት ተጠቃሚዎች ራሳቸው በመረጡት ፓኬጅ የቢዝነስ ፓኬጆች ወደ ሥራ እንዲገቡም ጭምር በማድረግ በየደረጃው ከፕሮግራሙ እየተመረቁ እንዲወጡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹እኛ እንደ ሲዳማ ክልል ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚለው መርሐ-ግብር እንደሀገር ከመነደፉ በፊት በክልላችን አጠቃላይ ‘የቤተሰብ ብልፅግናን የማረጋገጥ ተግባር’ ብለን ያፀደቅነው ኢኒሼቲቭ አለ›› በማለት የተናገሩት ኮሚሽነሩ፤ በዚህ መርሐ ግብር ውስጥ ደግሞ ስምንት ኢኒሼቲቮችና 69 ፓኬጆች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም አግሮ ኢኮሎጂውን መነሻ በማድረግ በግብርና ዘርፉ ወደ 19 ፓኬጆች መለየታቸውን አመልክተዋል፡፡
አክለውም ‹‹በክልላችን ከፍተኛ የሕዝብ ጥግግት ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምን ላይ ቢሰማሩ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት የሚል ጥናት ተደርጓል። በመሆኑም አነስተኛ መሬት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ የቤተሰብ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ነው ሲሰራ የቆየው›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም