በሚቀጥሉት ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ የሰብል ስብሰባን ለማከናወን አመቺ ነው

አዲስ አበባ፡- በሚቀጥሉት ቀናት በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚኖረው የበጋው ደረቅ የእርጥበት ሁኔታ የድህረ ሰብል ስብሰባ ተግባራትን ለማከናወን አመቺ ሁኔታ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ እ.ኤ.አ ከጃንዋሪ 11 እስከ 20 ቀን 2025 የሚኖረው የአየር ሁኔታ ትንበያ አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መረጃ እንዳስታወቀው፤ በሚቀጥሉት ቀናት በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚኖረው የበጋው ደረቅ የእርጥበት ሁኔታ የድህረ ሰብል ስብሰባ ተግባራትን ለማከናወን አመቺ ሁኔታ ይኖረዋል፡፡

በመሆኑም አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት ለድህረ ሰብል ስብሰባ ተግባራት የሚኖረውን ምቹ የአየር ሁኔታ በመረዳት የተሰበሰቡ ሰብሎችን አጠናቆ የመውቃትና የማጓጓዝ ሥራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል።

በተለይም የበልግ አብቃይ የሆኑ አካባቢዎች የሰብል ማሳዎችን ከማንኛወም ተረፈ ምርት ከአሁኑ ነጻ የማድረግ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል ያለው ኢንስቲትዩቱ፤ በሌላ በኩል በሳምንቱ የመጀመሪያዎቹ ቀናቶች ላይ በጥቂት ኪስ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የምሥራቅ፣ የሰሜን ምሥራቅና የመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው እርጥበት ይጠበቃል ብሏል፡፡

ይህም ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች መጠነኛ የግጦሽ ሳር እና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማሻሻል አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሶ፤ በሌላ በኩልም የበልግ ወቅትን ቀድመው ለሚጀምሩ አካባቢዎች ማሳን አስቀድሞ ከማዘጋጀት አንጻር ጠቀሜታ ይኖረዋል ብሏል፡፡

እንደ ኢንስቲትዩቱ መግለጫ፤ በሚቀጥሉት ቀናቶች ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት በጥቂት የመካለኛው፣ በምሥራቅ፣ በሰሜን ምሥራቅ፤ በሰሜን ምዕራብ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ የሀገራችን አካባቢዎች ላይ አንጻራዊ የእርጥበት መጠንና የደመና ሽፋን መጨመር እንደሚኖር የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የደቡብ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ እና የምዕራብ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው የበጋው ደረቅ፣ ጸሀያማ እና ነፋሻማው የአየር ሁኔታ በሚቀጥሉት ቀናትም ቀጣይነት እንደሚኖረው አሀዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በሚቀጥሉት የጃንዋሪ ሁለተኛ አሥር ቀናት አብዛኛው ተፋሰሶች ላይ በደረቅ የእርጥበት ሁኔታ ስር ሆነው ይቆያሉ ያለው መግለጫው፤ ይሁን እንጂ በጥቂት ላይኛው ተከዜ፣ አፋር ደናክል እንዲሁም በጥቂት ላይኛው ባሮ አኮቦ ተፋሰሶች ላይ መጠነኛ እርጥበት ያገኛሉ። ይህም ሁኔታ የገጸ ምድር የውሃ ሀብትን በጥቂቱም ቢሆን እንደሚያሻሽል ይጠበቃል።

በአንጻሩ በአብዛኛው አዋሽ፣ አይሻ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ኦጋዴን እና ዋቤ ሸበሌ ተፋሰሶች ላይ ደረቃማው የእርጥበት ሁኔታ የሚያመዝን መሆኑን ጠቅሶ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያለውን የውሃ ሀብት ከብክነትና ከብክለት ጠብቆ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You