በክልሉ ጥምቀትን ጨምሮ በጥር ወር የሚከበሩ በዓላት በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል

አዲስ አበባ፡– በአማራ ክልል የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላትን ጨምሮ በጥር ወር የሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡ ጥምቀት፣ ቃና ዘገሊላ፣ ጊዮን፣ አስተርዕዮ፣ መርቆሪዮስ በክልሉ በጥር ወር ከሚከበሩ በዓላት መካከል መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዓባይ መንግሥቴ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በክልሉ ጥምቀትን ጨምሮ በጥር ወር የሚከበሩ በዓላት በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

በወርሐ ጥር በክልሉ በርካታ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት ይከበራሉ ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ከበዓላቱ የሚገኙ የተለያዩ መንፈሳዊና ቁሳዊ ጠቀሜታዎች የተሟሉ ለማድረግ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ሥራ መገባቱን አመልክተዋል፡፡ በተለይ በጎንደር ለሚከበረው የጥምቀት በዓል በድምቀት ለማክበር ከጥር ሁለት ጀምሮ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የጎርጎራ ኢኮ ሪዞልት ግንባታ፣ የፋሲል ቤተ መንግሥት ግንባታና በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት የዘንድሮን የጥምቀት በዓል ልዩ የሚያደርገው መሆኑን አቶ ዓባይ ጠቁመዋል።

እነዚህም የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸው እንዲጨምርና ጎንደር ከተማ ከጥንታዊነቷና ከታሪካዊነቷ በተጨማሪ የዘመናዊ ስማርት ሲቲ ማዕከል እንድትሆን የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በአካበቢው ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ፤ በቅዱስ ላሊበላ በተከበረው የገና በዓል ላይ የታየው መነቃቃት ለማስቀጠል፤ የክልሉ ኅብረተሰብ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የፀጥታ ዘርፉ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን አመልክተዋል።፡

እንደ አቶ ዓባይ ገለጻ፤ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንግዶች በስፋት ክልሉን እንዲጎበኙ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የግንዛቤ መፍጠር እና የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

በዓሉን ለመታደም ወደ ስፍራው ያቀኑ ጎብኚዎች ምቹ አገልግሎት እንዲያገኙም የተለያዩ መሠረተ ልማት የማሟላት፣ የሆቴሎች ዝግጅት እንዲሁም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የተለያዩ የቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጥምቀት በዓል ከጎንደር ከተማ በተጨማሪ በሁሉም የክልሉ ከተሞች ላይ በድምቀት የሚከበር ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በሰሜን ሸዋ ኢራንቡቲ አረርቲ ከተማም በድምቀት እንደሚከበር አመልክተዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You