አገራዊ ቀውሱን ተከትሎ ኅብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅና ወረርሽኙን ለመከላከል ያስችላል ከተባሉ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ተማሪዎች በቤታቸው እንዲቆዩ የማድረግ ተግባር አንዱ መሆኑ ይታወቃል። ይሄን ተከትሎም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ የሆኑ መስሎ እንዳይሰማቸው የሚያስችሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ ስለመሆኑ እየተነገረም፤ ንግግሩም በተግባር ሲገለጽ እየተስተዋለ ይገኛል። እኛም በዛሬው እትማችን በዚህ ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እና በተግባራቱ ቀጣይነት ዙሪያ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አስመልክቶ በትምህርት ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሐረጓ ማሞ ያደረሱንን መረጃ በሚከተለው መልኩ ይዘን ቀርበናል።
ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ተማሪዎች ቤታቸው እንዲሆኑ በተደረገበት ወቅት ከተወሰኑ ቀናት በኋላ የተወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ውጪ በቤታቸው በሚሆኑበት ወቅት ከትምህርት ወጥተው የራቁ መስሎ እንዳይሰማቸው ማድረግ ነው። ምክንያቱም ይህ ወቅት የመንፈቀ ዓመት ትምህርት ጨርሰው የሚያርፉበት ወይም ትምህርት የተዘጋበት ወቅት አይደለም። ተማሪዎችም ከምንፈቀ ዓመት ወደ ሌላኛው መንፈቀ ዓመት የሚሸጋገሩበት የሽግግር ወቅት አድርገው ሊያዩት አይገባም። ይልቁንም በገጠመው አገራዊና ዓለምአቀፋዊ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርታቸው መቋረጡን መገንዘብ ይኖርባቸዋል።
ይሄን መሠረት በማድረግም በተገኘው አጋጣሚ በተለይም የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን በመጠቀም አንድም ግንዛቤን የማስጨበጥ ሥራ ሲከናወን ቆይቷል። ሁለተኛም ተማሪዎች በቤታቸው ሆነው ትምህርታቸውን ሊከታተሉ የሚችሉበት ዕድል እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል። በዚህም በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ያሉ ተማሪዎች በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን ብሎም በሚኒስቴሩ የማህበራዊና የቴሌቪዥን የስርጭት አውታሮች ተደራሽ
የማድረግ ሥራ ተከናውኗል፤ እየተከናወነም ይገኛል።
በዚህ ረገድ በክልል ያሉ ተማሪዎች ቀደም ሲልም የሬዲዮ ትምህርት ይማሩ የነበረ ሲሆን፤ አሁንም ይሄንኑ መሠረት በማድረግ በየቤታቸው በሚገኝ ሬዲዮ በተለያዩ ጣቢያዎች ትምህርቱ እንዲሰራጭ የማድረግ ተግባር ከክልሎች ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው። ለዚህም ከክልሎች ጋር ውይይት በማድረግ ወደሥራ የተገባ ሲሆን፤ ለስርጭቱ እውን መሆንም ከክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮዎች፣ ትምህርት ቢሮዎችና የመገናኛ ብዙኃን ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ይገኛል። ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባ በኤፍ.ኤም 94.7 ያሰራጫሉ። ይሄ ከዚህ ቀደም ትምህርት ቤት ውስጥ ሆነው ትምህርት በሬዲዮ ይማሩ በነበሩበት ሰዓት ይሰጥ የነበረው ፕሮግራም አሁንም በኤፍ.ኤም ጣቢያው በተሻሻለ መልኩ እንደቀጠለ ነው።
ይሄን መሰል ስርጭት በሁሉም ክልሎችና አካባቢዎች በሚባል መልኩ እየተተገበረ ያለ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት የሬዲዮ ስርጭት ሲያካሂዱ ያልነበሩ ክልሎችን በተመለከተ ከክልሉ የሚዲያ ክፍል ወይም ከክልሉ ኮሚዩኒኬሽንና ከክልሉ መገናኛ ብዙኃን ጋር በመነጋገር ለተማሪዎች ትምህርት እንዲደርስ እየተደረገ ይገኛል። ይሄም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸውና ትምህርቱ ከዚህ ቀደም ሲካሄድ በነበረው አግባብ መሄድ እንዳለበት በመነጋገር ከስምምነት ተደርሶ እየተተገበረ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ መልኩ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ የሚካሄደውን የትምህርት ስርጭት ተግባር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የራሱን ክትትል ያደርጋል፤ ከክልሎች ጋርም በሪፖርትና ግምገማ በመገናኘት ሂደቱን ይከታተላል።
እስከ ስምንተኛ ክፍል እየተተገበረ እንዳለው የትምህርት ስርጭት ሁሉ ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ላሉ የክፍል ደረጃዎችም የቴሌቪዥን ትምህርት ስርጭት እየተከናወነ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደምም ትምህርቱ በትምህርት ቴሌቪዥን (ፕላዝማ) ይሰጥ ነበረ። አሁን ላይ በፕላዝማ ይሰጥ የነበረው ትምህርት በትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቴሌቪዥን (ኤም.ኦ.ኢ)እንዲሆን ተደርጎ ትምህርቱ እየተሰራጨ ይገኛል። ይህ ቀጥታ በፕላዝማ ይተላለፍ
የነበረው የትምህርት ፕሮግራም እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በአንዳንድ ነገሮች ላይ ማስተካከያ እየተደረገበት ይገኛል።
ይሄም ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የነበረበት አካሄድ መምህር ክፍል ውስጥ ተገኝቶ አቅጣጫ እየሰጣቸው ነው ሲካሄድ የነበረው። አሁን ላይ ግን ተማሪዎች ቤት ናቸው። ቤት እንደመሆናቸው መጠን ደግሞ ቤት ውስጥ በተለይ ወላጆቻቸው እና ሌላም ቤት ውስጥ ያለ ቤተሰብ እንዲደግፋቸው ከማድረግ አንጻርም መቃኘት ነበረበት። በመሆኑም እርሱን በዚህ መልኩ የመቃኘት ሥራው ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየሰሩ ነው ያሉት። ምክንያቱም ባለው ሁኔታ ትምህርት መቼ እንደሚከፈት አይታወቅም። በፕሮግራም እየተሄደ ነው ለማለት ስለማይቻልም፤ አሁን ፕሮግራም ተደርጎ የተያዘው የሬዲዮና ቴሌቪዥን ትምህርቱን ማስቀጠል ነው።
በመሆኑም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በቴሌቪዥን እንዲከታተሉ ማድረግ ሲሆን፤ ለዚህም የተለያዩ ፕሮግራሞቹ ቆመው ትምህርቱ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ ስርጭቱን እንዲያከናውን ሆኗል። አንዳንድ ክልሎችም ተነሳሽነቱን ወስደው የበለጠ ለተማሪዎች አጋዥ ሆኗል ብለው ባሰቡት ልክ ከተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር በጋራ በመስራት ትምህርቱን በክልል ደረጃም ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ድረስ የማስራጨት ሥራ ጀምረዋል። ከዚህ ባለፈ በቴሌግራም እንዲሁም በትምህርት ሚኒስቴር ዩቲዩብ አማካኝነት የተቀረጹ ትምህርቶች እየተሰራጩ ነው። በተመሳሳይ በትምህርት ቴሌቪዥን የራሱ ቴሌግራምና ዩቲዩብ አማካኝነት ቀረጻ የተከናወነባቸው ትምህርቶች ሶፍት ኮፒያቸው ሙሉ በሙሉ በዚያ እንዲለቀቅ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው።
ይህ ተግባርና እርምጃ እየተወሰደ ያለው የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ይደርስባቸዋል ተብሎ በሚታሰብባቸው አካባቢዎች ላሉ ተማሪዎች ይደርሳል በሚል የሚከናወን ነው። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንድም ይህ ተደራሽ የማይሆንባቸው አካባቢዎች በመኖራቸው፤ ሁለተኛም በመብራትና ሌላም ምክንያት የስርጭት መቆራረጥ በሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ይኖራሉ ተብሎ ስለሚገመት እነዚህን
ታሳቢ ያደረጉ የግንዛቤ ማስጨበጥና የተማሪዎች የጥናትና ትምህርት መርሃ ግብር ተፈጻሚ የሚሆንባቸው አካሄዶችም ታስበዋል። ሆኖም በእነዚህ አካባቢ ያሉ ተማሪዎች ዋና ጉዳይ እጃቸው ላይ ያለ የትምህርት ቁሳቁስ ነው።
ምክንያቱም እነዚህ ተማሪዎች አንድም የመማሪያ መጻሕፍት እጃቸው ላይ ናቸው፤ የተማሩባቸው ደብተሮችም እነርሱው ጋር ናቸው። በመሆኑም የእነዚህ ተማሪዎች ቀዳሚ ሥራ መሆን ያለበት እነዚህን በእጃቸው ያሉ መጻሕፍትና ደብተሮችን ተጠቅመው ማንበብ እንጂ ወደ ውጪ መውጣት አይኖርባቸውም። በዚህ ሂደት ደግሞ የሚያስቸግራቸውና የሚከብዳቸው ይዘት እንኳን ቢኖር በአካባቢያቸው ወይም በቤተሰባቸው የተማረ ሰው ካለ እንዲያግዛቸው በማድረግ ለመረዳት መሞከር እንጂ ጤናቸውን በሚጎዳ መልኩ መውጣት አይኖርባቸውም። በመሆኑም የሬዲዮ ወይም የቴሌቪዥን ስርጭት አልደረሰንም ብለው መቀመጥ ሳይሆን በራሳቸው ጥረት በእጃቸው ያሉ የትምህርት ቁሳቁሶችን ተጠቅመው ለማንበብና ለመረዳት መጣር ይጠበቅባቸዋል።
ወላጆችም ቢሆኑ በተቻላቸው አቅም ልጆቻቸውን ማገዝ፤ የአጠናንና አንብቦ የመረዳት አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ መደገፍ፤ የትምህርት ፍላጎትና አቅማቸውን በቅርበት በመረዳት የሚችሉበትን የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ቀደም ሲል በትምህርት ቤት ሆነው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉበት ወቅት ባይሆን እንኳን በተሻለ መልኩ ተግተው እንዲያነቡ ማገዝ ይኖርባቸዋል። ከዚህም በላይ ይሄን ጊዜ ልጆቻቸውን የማወቂያ ጥሩ አጋጣሚ አድርገው በማየት ልጆቻቸውን በቅርበት ለመከታተልና በትምህርት ላይ ያላቸውን አተያይ መገንዘቢያ አድርገው ሊጠቀሙበት ይገባል። በዚህ መልኩ አንድም ተማሪዎቹ ለራሳቸው ሲሉ የጥናት ፕሮግራም አውጥተው በማጥናት ጊዜያቸው እንዳይባክን ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ ወላጆችም መምህራንን ተክተው መስራት ባይችሉም ለልጆቻቸው የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ጊዜያቸውን ሳያባክኑ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማስቻል ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2012
ወንድወሰን ሽመልስ