ከቻይናዋ ዉሃን ከተማ ተነስቶ ሰው ከማይኖርበት አንታርክቲክ ውጪ ሁሉንም የዓለማችንን አህጉራት ያዳረሰው የኮቪድ 19 ቫይረስ፣ዘር፣ቀለም፣ቋንቋ፣የስልጣን ከፍታ፣የሀብት ደረጃ፣አዋቂና ታዋቂ፣መሪና ተመሪን ሳይለይ በባለፉት አራት ወራት ከሶስት ሚሊየን ሰባት መቶ ሺ በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ፣አሳዛኝ በሆነ መልኩ ከሁለት መቶ ሃምሳ ሺ በላይ ሕይወትን ነጥቃል፡፡
አገራት ወረርሽኙን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረትም የሰዎች ዝውውር ተገድቧል፡፡ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዓለም ሕዝብ 1/3ኛ ከቤቱ እንዳይወጣ ተደርጋል፡፡ ለወትሮው በሰዎች ግርግር የሚያደምቁ ታላላቅ የአለማችን ከተሞች ፀጥ ረጭ ብለዋል፡፡
በኢኮኖሚ ልእልና ስማቸው አንቱ የሚባሉት ጨምሮ በርካታ አገራት አማራጭ አጥተው ድንበራቸውን ጠርቅመዋል፡፡ ወደቦች ተዘግተዋል፡፡ ኮንፍረንሶች፣ ኮንሰርቶች፣ የስፖርት ውድሮች እንዲሁም ሌሎች ግዙፍ ሁነቶች ተሰርዘዋል፡፡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብሎም የንግድ እንቅስቃሴዎች ተዳክመዋል። ቆመዋል፡፡
የመደበኛ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ብሎም የሰዎች ቤት ውስጥ መዋል እንዲሁም ማህበራዊ ርቀቶችን እንዲጠብቁ መገደድ ታዲያ የወረርሽኙን ስርጭትና ጉዳት ከመከላከልና ከመቀነስ ትሩፋቱ ባሻገር በርካታ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ኪሳራን ፈጥሯል፡፡
የአለም ኢኮኖሚ ከሁሉ በላይ በህዝብ እንቅስቃሴ ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደመሆኑ የወረርሽኙ መንሰራፋት በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ በርካታ ዘርፎች ላይ ያስከተለው ሁለንተናዊ ጉዳት እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ ከመደበኛ እንቅስቃሴ መቋረጥ ጋር በተያያዘ በሆቴል፣ ቱሪዝምና በትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ላይ ያሳረፈው ጡጫ እጅጉን ከባድ ሆኖ ተስተውሏል፡፡ ቀውሱ በተለይም ዓለም አቀፉን የአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ክፉኛ አንገዳግዶታል፡፡
ኢንዱስትሪው እኤአ በ2001 ዩናይትድ እስቴትስ ላይ በተፈፀመው የመስከረም 11 የሽብር ጥቃት እንዲሁም ከሰባት አመት በኋላ በተከሰተው የአለም ኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ከባድ ጉዳትን መጋፈጥ ግድ ሆኖበት የተስተዋለ ቢሆን የኮሮና ግን ከሁለቱም ክስተቶች የከፋው ሆኖበታል፡፡
በእርግጥም የኮሮና ቫይረስ ቀውስ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የአለማችንን አየር መንገዶች ስራ አስፈትታል፡፡ አውሮፕላኖቻቸውን ከሰማይ ወደ ምድር አውርዳል፡፡ አብዛኞቹ ሰራተኞችን እንዲቀንሱ አንዳንዶቹም እንዲያሰናብቱ አሊያም ‹‹ወቅቱን እስክንሻገር እባካችሁ የአመት ፈቃዳችሁን ውሰዱ እንዲሉ›› አስገድዷል፡፡
በርካታና ግዙፍ የሚባሉ አየር መንገዶች የኪሳራ መዝገባቸውን አደባባይ ይዘው በመውጣት ኮሮና ቢሊየን ዶላሮችን እንደነጠቃቸው እንዲያሳውቁ ከአቅም በላይ የሆነባቸው ደግሞ የመንግስትን ድጋፍ እንዲጠይቁ ምክንያት ሆኗል፡፡
ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር በመጋቢት ወር መጨረሻ ይፋ ባደረገው ጥናት የወረርሽኙ ቀውስ በሚያስከትለው ኪሳራ ዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪው 252 ቢሊዮን ዶላር፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች ደግሞ አራት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያጡ ተንብዮአል፡፡
የአፍሪካ አቭየሽን ኢንዱስትሪ ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንዲሁም የ56 ቢሊየን ዶላር የአገር ውስጥ ጠቅላላ ነፍስ ወከፍ ገቢ ዋስትና መሆኑን ያመላከተው ማህበሩ፣ የወረርሽኙ ቀውስም በአህጉሪቱ በዘርፉ ከተሰማሩት መካከል ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑትን ስራ አልባ እንደሚያደርግ፣ የአገር ውስጥ ጠቅላላ ነፍስ ወከፍ ገቢውን በ17 ቢሊየን ዶላር እንደሚቀንሰው ጠቁሟል፡፡
ከአፍሪካ ትልቁና ምርጡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወረርሽኝ በፈጠረው ቀውስ ምክንያት ወደ ተለያዩ ሃገራት የሚያደርገውን በረራ በማቋረጡ ከግማሽ ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማጣት ግድ ብሎታል፡፡ የ73 ዓመት ልምድ ያለውና ሁሌም በትጋት አገልግሎት የሚሰጠው አየር መንገድ በኮሮና ምክንያት ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ቢገጥመውም ከመንግስት ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ ከመጠየቅ ይልቅ የተጋረጡበትን ፈተናዎች ለመቋቁም አማራጭ የሚለውን ሁሉ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡
አስከፊውን ጊዜ ለመሻገር በተለይም የካርጎ ወይንም ጭነት በረራ አገልግሎቱን ይበልጥ በማስፋት ጉዳቱን የመቀነስ አቅጣጫ የተከተለ ሲሆን፣ በወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ የሕክምና መሳሪያዎችና መድኃኒቶች ፍላጎት በመናሩና ከፍተኛ የጭነት በረራ ፍላጎት መፈጠሩም አየር መንገዱን አማራጭ ይበልጥ ውጤታማ አድርጎለታል፡፡
የአየር መንገዱ በተለይ የግዙፉ አሊባባ ኩባንያ ሊቀመንበር ቻይናዊው ጃክ ማ ለአፍሪካ አገሮች የለገሱዋቸው የህክምና ዕቃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተለያዩ አገሮች ማዳረሱን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት ከፍተኛ አድናቆትና ምስጋና አስችሮታል፡፡
ጆን ግራንትን የመሳሰሉ ታዋቂ የአቪየሽን መረጃ ተንታኞችም፣ በርካታ አየር መንገዶች ህልውናቸውን ለማስቀጠል ደፋ ቀና በሚሉበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተለያዩ አማራጮችን በመተግበር ከሌሎች በተሻለ ቀውሱን መቋቋም ችሏል፣ ማኔጅመንቱ አስደናቂ ስራ ሰርታል›› ሲሉ መስክረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁን ባለው ሂደት የወረርሽኙን ጉዳት ተቋቋሙ በኢንዱስትሪው ሰማይ ላይ መዝለቅ ቢቻለውም አንዳንዶቹ የአህጉሪቱ አየር መንገዶች ግን ቀውሱን መቋቋም የሆነላቸው አይመስሉም፡፡ ሞሪሺየስን ጨምሮ የአንዳንድ አገራት አየር መንገዶች ከባዱን ኪሳራ መቋቋም ተስኗቸው ‹‹ሩጫችንን ጨርሰናል፣ ፍላጎት ያለው ይረከበን›› ብለዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካው አየር መንገድ ለቀብር ከምትመጡ አሁን አድኑኝን እያለ በማማፀን ላይ ስለመሆኑ ተሰምቷል፡፡
ይሕን ያስተዋለው አለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበርም፣ ቀደም ሲል እንደገመትኩት በወረርሽኙ ምክንያት የአፍሪካ አየር መንገዶች አራት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ሳይሆን ስድስት ቢሊየን ዶላር ገቢ ይነጠቃሉ፣ ከዘርፉ ስራ የሚሰናበቱ ዜጎች ቁጥርም ከሁለት ወደ ሶስት ነጥብ አንድ ሚሊየን ያሻቅባል፣ የአቪየሸን ዘርፉ አህጉራዊ የጠቅላላ ምርት ድርሻም በግማሽ በመቀነስ ከ56 ወደ 28 ዝቅ ይላል›› ብሏል፡፡
የአፍሪካ መንግስታት የአህጉሪቱን የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ለመታደግ ከፍተኛ የእፎይታ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ምንም አይነት ድጋፍ የማያደርጉ ከሆነም አደጋው በእጅጉ ግዙፍ ስለመሆኑ አስጠንቅቋል፡፡
አንዳንድ አገራትም አየር መንገዶቻቸውን ከአስከፊ ኪሳራ ለመታደግ ብሎም ከስራ ውጭ እንዳይሆኑባቸው የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ ጀምረዋል፡፡ የሴኔጋል መንግስት 128 ሚሊየን ዶላር ለቱሪዝምና ለአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ድጎማ ሲያደርግ ሲሸልሽ ደግሞ የፓርኪንግና የመነሻ ክፍያዎችን ማስቀረቱ ተጠቁሟል፡፡
ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበርም የአገራቱ ድጋፍ የሚበረታታና ይበልጥ ሊጠናከር የሚገባው መሆኑን ከማስገንዘብ ባሻገር በቀጣይ ሊደረጉ የሚገባቸውን አበይት ተግባራትም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በተለይ ከቀጥታ የፋይናንስ ድጋፍ ባሻገር የብድርና የብድር ማስተማመኛ እንዲሁም የታክስ እፎይታ ማድረግ እንደሚገባ አመላክቷል፡፡
የተለያዩ ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃንም የአፍሪካ አየር መንገዶች ይሕን አስጨናቂ ጊዜ ለመሻገር ማድረግ
ስለሚገባቸው አበይት ተግባራት አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ግርማ ዋቄም ከሩዋንዳው ዘ ኒው ታይምስ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ‹‹ይሕን አስጨናቂ ጊዜ ለማለፍና ከኢንዱስትሪው ገበያ ውጭ ላለመሆን ከማንኛውም ጊዜ በላይ የአፍሪካ አየር መንገዶች የጋራ ትብብርን ማጠናከርና የእርስ በእርስ ፉክክርን ማስወገድ አለባቸው ››ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ሲቪል አቪየሽን ኮሚሽን ዋና ፀሃፊ አቶ ተፈራ መኮንንም በበኩላቸው፣ የአፍሪካ መንግስታት ለአየር መንገዶቻቸው መከታ መሆን እንዳለባቸው ከመጠቆም ባለፈ ብድርን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ዋና ፀሓፊ አብዱረህማን ባርዝ በበኩላቸው፣ አህጉሪቱ ከኮሮና ቀውስ ዛሬ ሳይሆን ነገንም ለመሻገር የአንድ የአፍሪካ አየር ትራንስፖርት ገበያን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባት፣ ይሕም ፋይዳው ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም ምክንያቱ በወረርሽኙ ማብቂያ ማግስት ‹‹በርካታዎቹ አለም አቀፍ መዳረሻዎች አየር መንገዶች ለአፍሪካ አቻዎቻቸው ሰማይና ምድራቸውን ከመፍቀዳቸው ቀድሞ የተወሰኑ ወራቶችን ስለሚወስድባቸው ነው›› ብለዋል፡፡
አንዳንድ ባለሙያዎችም የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት ነጻ የአየር ትራንስፖርት የጋራ የአቪየሽን ስምምነት በአህጉሪቱ የሚገኙ የአየር መንገዶች የሃገራትን ፈቃድ ሳይጠይቁ በፈለጉት ጊዜና ሰአት ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር በረራ ማካሄድ የሚስችል እንደመሆኑ መሰል ቀውሶች ከመሻገር ባለፈ የአህጉሩን ውህደትና ትስስር በማጠናከር በኩል ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አስምረውበታል፡፡
ከዚህም ባሻገር መንግስታትና የኢንዱስትሪውን ባለድርሻዎች የሚያቀራርብ፣ ዘርፉን ከቀውስ ውስጥ ለማውጣት የሚያስችል መፍትሄ ለመስጠትና ዳግም ወደ ውጤታማነት ለመመለስ የሚያግዝ ቀጠናዊ የሆነ ትብብርና ውይይት መፈፀም እንደሚገባም አፅእኖት ሰጥተውታል፡፡
አየር መንገዶች አንዳቸው ከአንዳቸው ጎን ስለመቆም ማሰብ፣ የቢዝነስ ሞዴላቸውን፣ ኔትወርካቸውን እንዲሁም ክፍያቸውን ዳግም መከለስ፣ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥገና ስልጠና ሌሎችም አማራጮች መተግበር እንደሚገባቸውም ተመላክቷል፡፡
የአለም አቀፉ የአየር ካርጎ ማህበር ምክትል ሃላፊ ሳንጂቭ ጋዲያ፣ የጭነት በረራው የካርጎው ቢዝነስ በዚህ ከባድ ወቅት አየር መንገዶቹን ለመደገፍ ግዙፍ ልዩነት የሚፈጥርና በኢንዱስትሪው ላይ እንዲቀጥሉ ዋስትና የሚሆናቸው መሆኑን በመጠቆም ይሕ አይነቱ አማራጭ ለትላልቆቹ አየር መንገዶች ብቻም ሳይሆን ለትናንሾቹም ፋይዳው የላቀ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል፡፡
አንዳንዶቹ በአንፃሩ የወረርሽኙን ስርጭት እንዴት በማያዳግም መልኩ መግታት ይቻላል የሚለው እስካልታወቀና የዚህ ፈተና መልስ የሚርቅ ከሆነም ዘርፉ ለመታደግ አስቸጋሪ መሆኑንና ኢንዱስትሪውን ዳግም ወደ ቀደመ ተክለ ቁመናው ለመመለስም ምናልባት አመት ሳያስፈልገው እንደማይቀር ገምተዋል፡፡
በወረርሽኙ ማግስት የአቪየሽን ኢንዱስትሪውን ምን መልክ ይኖረዋል በሚል ሰፊ ትንታኔ የሚሠጡ ምሁራንና
ፃሃፍት ቁጥርም በርካታ ሆናል፡፡ ሪቻርድ አቦላፊያ ፎርብስ ላይ ባሰፈረው ሰፊ ትንታኔ፣ በወረርሽኙ ማግስት የአቪየሽን ምህዋሩ በእጅጉ እንደሚለወጥና ከሁሉም በላይ በግል ተዋናዮች እንደሚጥለቀለቅ አትቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ወረርሽኝም ሆነ የሽብር ጥቃት ሲከሰቱ በርካቶች ለአውሮፕላን በረራ የግሉን ዘርፍ ምርጫው ሲያደርጉ መስተዋላቸውንም ለእሳቤውም ምስክር አድርጎ አቅርቧል፡፡
ወረርሽኙ የሰዎችን እንቅስቃሴ ከማገድ ባለፈ የመሰብሰብን ፈቃድ መከልከሉን ተከትሎ በአሁን ወቅት በርካቶች ስብሰባዎች ቴክኖሎጂን በመጠቀም በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ያስታወሰው ፀሃፊው፣ በኮሮና ቀውስ ማግስትም ይሕ አይነቱ የመሰብሰብ አማራጭ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አትታል፡፡ እንደዚሕ አይነት ለውጦችም የኮንፍረስን ቱሪዝሙን በተለይም የአቪየሽን ዘርፉን ክፉኛ እንደሚጎዱት አስምሮበታል፡፡
ሲኤን ኤን የቢዝነስ አምድ ጸሃፊ ክሪስ ኢስዶር ‹‹ከወረርሽኙ በኋላ አየር መንገዶች ጥቂት አማራጮች ከማቅረባቸው ባሻገር ከፍተኛ ክፍያን ማስቀመጣቸው አይቀርም፣ በርካታ መንገደኞች በመጠነኛ ክፍያ የሚያስተናገዱባቸው የበረራ ወንበሮች እንዲታጠፉና ደብዛቸው እንዲጠፋ ያደርጋልም›› ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡
በአነስተኛ የበረራ መስመር ጥቂት የሚባሉ አየር መንገዶች ብቻ ሰማይ ላይ መውጣታቸውን ተከትሎም፣ ‹‹መንገደኞች ውስን ምርጫ እንዲኖራቸው ያደርጋል፣ የአማራጮቹ ማነስ ደግሞ ከሁሉም በላይ መንገደኞች ተጨማሪና እጅግ ውድ የሚባል ክፍያን እንዲከፍሉ ሊያስገድዳቸውም ይችላልም›› ብሏል፡፡
በአየር መንገዶቹ መካከል የሚደረገው ፉክክርም የትኬት ዋጋ ቅናሽ እንዲኖር ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ተገምታል፡፡ የወረርሽኙ ስጋቶች በቶሎ የሚወገዱ ባለመሆኑ በረራዎች ቢካሄዱም ክፍት ወንበሮች ማስተዋል አይቀሬ ስለመሆኑ የሚገልፁ በርካቶች ሆነዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኙ ቀውስ ማግስትም ከማንኛውም የበረራ ጉዞ በፊትም ሆነ በኋላ ለመንገደኞች የጤና ምርመራ መደረጉ የማይቀር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአቪየሽን ዘርፉን አሰራር ጉልህ በሆነ መልኩ እንደሚለወጥም ተሰግቷል፡፡
አየር መንገዶች ደህንነቱ የተጠበቀ ጉዞ ለማድረግና የመንገደኞች እምነት ዳግም ለማግኘት፣ በረራዎቹን በሚያከናውኑበት ወቅት የሚያደርጋቸው ከፍተኛ ጥንቃቄዎች ከጥቅማቸው ባሻገር ጉዳታቸውም በግልፅ የሚታይ እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡
የኢንዲያን ቱዴይ ናግራጁን ዱዋራካንዝ፣ ‹‹በተለይ ማህበራዊ ርቀቶችን ጠብቆ የቅድመ ፍተሻ መርሃ ግብርን ማስፈፀም ተጨማሪ ጊዜን የሚወስድ እንደመሆኑ መንገደኞች ምናልባትም በአየር መንገድና አካባቢው መገኘት ግድ የሚኖርባቸው ከሶስትና አራት ሰአታት በፊት ይሆናል ››ብሏል፡፡
ከሁሉም በላይ የወረርሽኙ ማግስት ደካማ አየር መንገዶችን ተሰናብተው፣ አንዳንድ አየር መንገዶችም ጥምረት ፈጥረው ሊያስመለክት ይችላል፣ ‹‹እንደወትሮው ለሆነውም ላልሆነው የሚደረግ ጉዞ አይታሰብም›› ሲልም ተናግሯል፡፡.
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2012
ታምራት ተስፋዬ