እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ባሳለፍነው ሳምንት “በሕግ የተፈቀዱ፣ የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ አድራጎቶች” በሚል ርዕሰ-ጉዳይ በወንጀል ከመከሰስና ከመቀጣት ነፃ ከሚያስደርጉ ምክንያቶች ውስጥ የተወሰኑትን ለመዳሰስ ሞክረናል።
እነዚህም በሕግ የተፈቀዱ አድራጎቶች፤ የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ ሁኔታዎች ተብለው ሕጉ ተደንግገዋል።
ሁኔታዎቹ አንድ ሰው በሕግ የሚያስቀጣ ድርጊት ቢፈጽምም በወንጀል ከመከሰስና ከመቀጣት ነፃ የሚያስደርጉ ናቸው።በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ ወንጀል ፈጽሟል በሚል የተከሰሰ ሰው እነርሱን በማንሳት ክርክሩን የሚያቀርብባቸው መከላከያዎች ናቸው።
ከእነዚህ ውስጥ ታዲያ በሕግ የተፈቀዱ ምክንያቶችን በዝርዝር ተመልክተናል።የመጀመሪያው በሕዝብ አገልግሎት ሥራ ወይም በመንግሥት ወይም በወታደር ሥራ አፈጻጸም የተከናወኑ አድራጎቶችን ይመለከታል።
የሕዝብ አገልግሎት ሥራ የሚለው መከራከሪያ ከመንግሥት ሥራ ውጪ የሚገኝ የትኛውም ሰው ወንጀል ቢያደረግ ሊያነሳው የሚችለው መከራከሪያ ነው።የመንግሥት ወይም የወታደር ሥራ አድራጎቶች የሚባሉት ደግሞ በመንግሥት ሠራተኞች ወይም በወታደሮች የሚፈጸሙ ናቸው።
በሕግ የተፈቀደ ሁለተኛው አድራጎት የማረም ወይም ዲሲፕሊን የመውሰድ ኃላፊነትን በመወጣት ሂደት የተሠሩ ተግባራትን ይመለከታል።ወላጆች፣ አሳዳጊዎች፣ የልጆች ባለአደራ ጠባቂዎች ወይም መምህራን ልጆችን በማረም፣ በማነጽ፣ በበጎ አስተሳሰብ በመቅረጽ፣ በመንከባከብና በማስተማር ለፍሬ የማብቃት ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ በማረም ሂደት ውስጥ ወንጀል ቢፈጽሙ ይህንን መከራከሪያ ያቀርባሉ።
የንብረት ባለይዞታ የሆነ ሰው ይዞታውን ለመንጠቅ ወይም ሁከት ለማንሳት የሚደረግ ማንኛውንም ኃይል በመከላከል ሂደት የሚፈጽመው መብትን የማስከበር ድርጊትም በሕግ የተፈቀደ ሦስተኛው ጉዳይ ነው።
የሙያ ግዴታን ለመወጣት የተፈጸሙ ድርጊቶችም በሕግ የተፈቀዱ ናቸው።እነዚህም ከሙያው ደንብና አሠራር ውጪ እስካልሆኑና ከባድ የሙያ ጥፋት እስካልተፈጸመ ድረስ አያስቀጡም።
የትውስታ ሰንዱቃችሁን ለመክፈት ይቻላችሁ ዘንድ ከባለፈው ሳምንት ጽሑፋችን ይህንን ያክል ከጠቃቀስንላችሁ ወደዛሬው ጉዳያችን እንሸጋገራለን።
የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ አድራጎቶች
በሕግ ከተፈቀዱ አድራጎቶች በተጨማሪ አንድ ሰው ወንጀል ፈጽሞ እያለ ከመከሰስና ከመቀጣት ነፃ የሚሆንባቸው ምክንያቶች (ቢከሰስ መከራከሪያዎቹ) የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ ሁኔታዎች ናቸው።
የማያስቀጡ አድራጎቶች የሚባሉት በባህሪያቸው ወንጀል ቢሆኑም፤ አድራጊዎቹ ግን በሕሊናቸው ወንጀል የማድረግ አሳብ ቋጥረው ሆነ ብለው ያደረጓቸው አይደሉም።
ይልቁንም የተፈጥሮ ወይም ሰው-ሠራሽ አደጋ በራሳቸው ወይም በሌላ ሰው ላይ በመጋረጡ ምክንያት ያንን ለመከላከልና ለማስቀረት ሲሉ የሚያደረጓቸው ተገቢነት ያላቸው ድርጊቶች (Justifiable Acts) ናቸው።አስገዳጅ ሁኔታና ሕጋዊ መከላከል በዚህ ሥር ይመደባሉ።
ይቅርታ የሚያሰጡ ሁኔታዎች (Excusable Acts) የሚባሉት በመከላከያነት የሚያነሷቸው ሰዎች ከሌሎች ወንጀል አድራጊዎች ጋር በመሆን በወንጀሉ ተሳታፊ ሆነው ነገር ግን በዕድሜያቸው፣ በጾታቸው ወይም በአዕምሯቸው ደካማነት ፍጹም ተገደው ወንጀል አድርገው ከተገኙ አልያም ትዕዛዝ ተቀባይ ሆነው በመገደድ ወንጀል ከሠሩ የሚያነሷቸው ምክንያቶች ናቸው።
በዚህ ጽሑፋችን ታዲያ አብዝተው አከራካሪ የሆኑትንና አንባብያን የግንዛቤ ስንቅ ሊቋጥሩባቸው የሚገቡትን አስገዳጅ ሁኔታና ሕጋዊ መከላከልን በዝርዝር እንቃኛለን።
አስገዳጅ ሁኔታ (Necessity)
ከቃሉ እንደምንረዳው አስገዳጅ ሁኔታ በአስጊና አሳሳቢ አጋጣሚ ውስጥ የወደቀ ሰው ከዚያ ለመውጣት አልያም አደጋውን ለመመከት የሚወስደው አማራጭ የሌለው የመፍትሔ ርምጃ ነው።
ከሕጋችን እንደምናነበው ደግሞ የራስን ወይም የሌላውን ሰው መብት በቅርብ ከሚደርስ ከባድ አደጋ ለማዳን የተፈጸመ ድርጊት አስገዳጅ ሁኔታ ነው።ይህም አያስቀጣም።
“በቅርብ የሚደርስ ከባድ አደጋ” የሚለው የሕጉ አነጋገር በሕጉ ውስጥ በግልጽ አልተተረጎመም።ያም ሆኖ ይህ ከባድ የተባለው አደጋ በተፈጥሮ የሚደርስ ወይም የፈጣሪ ሥራ ሆኖ የማይቀር አደጋ (Act of God) ስለመሆኑ ከወንጀል ሕጉ ሐተታ ምክንያት እና በጉዳዩ ዙሪያ ከተጻፉ መጻሕፍት መገንዘብ ይቻላል።
እነዚህ አደጋዎች ማዕበል፣ ጎርፍ፣ የመሬት መናወጥ፣ መብረቅ፣ እሳት፣ የመኪና መገልበጥ፣ የመርከብ መስጠምና የመሳሰሉት ናቸው።እናም በእነዚህ ውስጥ የወደቀ ሰው የራሱን ወይም የሌላውን ሰው መብት (አካልና ሕይወትን ጨምሮ) ከአደጋ ለማዳን የሚወስደው ዕርምጃ በወንጀል አያስጠይቀውም።
እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው መሰረታዊ ነጥብ በየትኛውም ዓይነት አደጋ ውስጥ ያለ ሰው የሚፈጽመው ሕግን የጣሰ ድርጊት አያስጠይቅም ማለት እንዳልሆነ ነው።በመሆኑም ይህ የተባለው አደጋ ከባድ ሊሆን ይገባል።“ከባድ” የሚለው እንደጉዳዩ የሚመዘን ሆኖ፤ አዳጋው ከባድ ከመሆን በተጨማሪም በቅርብ የሚደርስ ወይም አይቀሬ መሆን አለበት።
እንዲህ ያለ አስገዳጅ ሁኔታ የማያስቀጣው ታዲያ ሌሎች ሁለት መሰረታዊ ሁኔታዎች በጣምራ ተሟልተው ሲገኙ ብቻ መሆኑን ልብ ይሏል።የመጀመሪያው አደጋውን በሌላ መንገድ ማስወገድ የማይቻል ከሆነ ነው።ሁለተኛው አድራጊው ከሁኔታው ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ዘዴዎችን ከተጠቀመ ነው።
እነዚህ ሁለት ጣምራ ቅድመ-ሁኔታዎች ደግሞ በአስገዳጅ ሁኔታ መርህ መሰረት አንድ ሰው በወንጀል ተከስሶ እንዳይቀጣ በሕጉ ከተቀመጠው መሰረታዊ አመክንዮ የፈለቁ ናቸው።ይኸውም አንድ ሰው አይቀሬ የሆነን ከባድና ጉዳት አድራሽ አደጋ ሕግን ጥሶም ቢሆን ቢመክትና ቢያስቀረው በዚህ አድራጎቱ በወንጀል ሊጠየቅ አይገባውም።
ከማህበረሰባዊ አንድምታውም አንጻር ስናየው አንድ ሰው በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ወንጀል ፈጽሞም ቢሆን ከባድ የተፈጥሮ አደጋን ቢመክት በማህበረሰቡ ዘንድ “ይበል” ይሰኝ እንደሆን እንጂ አይወገዝም።
እንዲያውም እንዲህ ያለው ድርጊት ተገቢነት ያለው በመሆኑ ማህበረሰቡ ይቀበለዋል፤ ያበረታታዋልም – ደጀኔ ግርማ በ2007 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ ጆርናል ኦቭ ሎው ላይ “The Defense of Consent, Coercion and Necessity under the Criminal Code of the FDRE” በሚል ባሳተመው ጦማሩ ላይ እንደከተበው።
አደጋው ከባድና በቅርብ የሚደርስ ሆኖ ነገር ግን ይህንን ለመቀልበስ ሕግን ከመጣስ ወይም በሌሎች ላይ ወንጀል ከመፈጸም ውጪ ሌላ ሕጋዊ አማራጭ ካለ አስቀድሞ እሱን መተግበር ያስፈልጋል።አደጋውን ለመመከት ሌሎች አማራጮች እያሉ ሕግን መጣስ ከተጠያቂነት አያድንም፤ አስገዳጅ ሁኔታን ስለማያሟላ።
ለምሳሌ ቤቱ በእሳት እየተቃጠለበት ያለ ሰው በውሃና በአፈር ለማጥፋት ሞክሮ ባይሳካለት፤ አልያም እሳቱ በርትቶ በውሃና በአፈር የማይሞከር ቢሆንና የተዘጋ የጎረቤቱን በር ሰብሮ የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ አውጥቶ እሳቱን ቢያጠፋ በወንጀል አይጠየቅም።
ስለዚህ በአስገዳጅ ሁኔታ መከራከሪያ ራስን ለመከላከል እንዲቻል አደጋውን ለመመከት ሌላ አማራጭ ያልነበረ መሆኑን ማስረዳት የግድ ይላል።
አስገዳጅ ሁኔታ መከራከሪያ ለመጠቀም አደጋውን ለማስወገድ ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ማሳየት እንደተጠበቀ ሆኖ አድራጊው ከሁኔታው ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ዘዴዎችን መጠቀሙንም ማስረዳት አለበት።
“ተመጣጣኝነት” የሚለው መመዘኛ በሕግ ሊደነገግ ስለማይቻል መለኪያው የሚታወቀው እንደየጉዳዩ እየታየ ነው።ይኸውም በአደጋ ውስጥ የወደቀው ሰው አደጋውን ለመቀልበስ የሚወስደው ዕርምጃና ይህንን ዕርምጃ በመውሰድ የሚያድነው የእሱ ወይም የሌላ ሰው የመብት ጥቅም የተመጣጠነ መሆን ይገባዋል።
ከላይ በጠቀስነው ምሳሌ ቤቱ በከባድ እሳት እየተቃጠለበት ያለ ሰው ከጎረቤቱ የእሳት ማጥፊያ መሳሪያውን ለማምጣት ሲሄድ ጎረቤቱ ፈቃደኛ ባለመሆን ስለተከላከለው እሱን ገድሎ ቤቱ ገብቶ እሳት ማጥፊያውን ቢያወጣ ይህ ድርጊቱ በአደጋው ምክንያት እሱ ከሚያጣው ነገር ጋር የማይመጣጠን ነው።እናም የአስገዳጅ ሁኔታ መከራከሪያ ተጠቃሚ አይሆንም።
በመሆኑም ይህ ሰው ጎረቤቱን ከመግደል በአደጋ ላይ የሚገኘውን መብቱን መስዋዕት እንዲያደርግ ነው ሕጉ የሚያስገድደው። ከዚህ ውጪ ግን ጎረቤቱን ገድሎ ቤቱን ቢያድን የአስገዳጅ ሁኔታን ወሰን ተላልፏልና ከወንጀል ተጠያቂነት አይድንም።የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ግን ይሆንለታል።
በሌላ በኩል በሚቃጠለው ቤት ውስጥ አራስ ሚስቱ ከጨቅላ ሕፃኗ ጋር በአደጋ ውስጥ ወድቀው ከሆነ በጎረቤቱ ላይ የፈጸመው ድርጊት ተመጣጣኝ ይሆናል።
እዚህ ላይ “እሳቱም ይሁን አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የጣለው ሌላ አደጋ በራሱ ጥፋት የመጣ እንደሆነስ?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።እንዲህ ከሆነ በየት ኛውም ሁኔታ ከተጠያቂነት አያመልጥም፤ የቅጣት ማቅለያ ግን ይሆንለታል።
ከአስገዳጅ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ሌላው መሰረታዊ ጉዳይ ከሙያ ግዴታ ጋር የተያያዘ ልዩ ሁኔታ በሕጉ ውስጥ መቀመጡ ነው።የሰውን ሕይወት ወይም ደህንነት የመጠበቅ ልዩ የሙያ ግዴታ ያለበት ሰው የሚፈጽመው አስገዳጅ ሁኔታ ከመቀጣት እንደማያድነው ማወቅ ይገባል።የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ግን ይሆነዋል።
ለምሳሌ ተሳፋሪዎችን የጫነች የመንገደኞች ጀልባ በጉዞ ላይ ሳለች በተነሳ ማዕበልና ሞገድ ተናውጻ ልትገለበጥ ባለችበት ወቅት የሚነዷት “ጀልበኞች” ከተሳፋሪዎቹ ውስጥ አንድ ሁለቱን ወደባሕሩ ውስጥ ጥለው ቀሪዎቹን ተሳፋሪዎች በደህና ወደ ቅርብ ወደብ ቢያደርሱ የአስገዳጅ ሁኔታን መከራከሪያ ሊያነሱ አይችሉም።ምክንያቱም ከሙያቸው ልዩ ባህርይ አንጻር ሌሎችን ለማትረፍ ሕይወታቸውን እስከመሰዋት የሚደርስ ግዴታ በሕጉ ተጥሎባቸዋልና።
ሕጋዊ መከላከል (Legitimate Defence)
ከአስገዳጅ ሁኔታ በመቀጠል ተገቢነት ያለው ሁለተኛው ድርጊት ሕጋዊ መከላከል ነው።አንድ ሰው የራሱን ወይም የሌላውን ሰው መብት ሕገ-ወጥ ከሆነ ጥቃት ወይም በቅርብ ከሚደርስ ሕገ-ወጥ ጥቃት ለማዳን ሲል የሚወስደው ዕርምጃ ሕጋዊ መከላከል ይሰኛል።ይህም በወንጀል አያስጠይቅም።
እዚህ ላይ በአስገዳጅ ሁኔታና በሕጋዊ መከላከል መካከል ያለውን መሰረታዊ ልዩነት ማየት ጠቃሚ ነው።ከላይ እንደተመለከትነው አስገዳጅ ሁኔታ የሚባለው በተፈጥሮ የሚደርስ ወይም የፈጣሪ ሥራ ሆኖ የማይቀር ከባድ አደጋ ሲጋረጥ የሚወሰድ ዕርምጃ ነው።ሕጋዊ መከላከል ደግሞ ሰው-ሠራሽ የሆነ ጥቃት ሲያጋጥም የሚወሰድ ዕርምጃ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ሕጋዊ መከላከል የሚያደርግ ሰው ከሌላ ሰው የተፈጸመበትን ጥቃት ለመከላከል የራሱን ዕርምጃ የሚወስድ ሰው ነው።በሌላ በኩል በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የወደቀ ሰው የተፈጥሮ አደጋን ለመቀልበስ የሌላን ሰው መብት የሚጋፋ ሰው ነው።(የመጀመሪያው የመጡበትን የሚመክት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ወደሌሎች የሚሄድ ነው)
ሕጋዊ መከላከልን እንደመከራከሪያ ለማንሳት በቅድሚያ በራስ ወይም በሌላ ሰው መብት ላይ ከሌላ አካል (ሰው) የተሰነዘረ ሕገ-ወጥ የሆነ ጥቃት መኖር አለበት።ወይም ደግሞ ሕገወጥ ጥቃቱ ባይሰነዘርም በቅርብ መድረሱ የማይቀርና
በመብት ላይ አደጋን የጋረጠ መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል።
ከዚህ ውጪ ግን ተፈጽሞ ለተጠናቀቀ ሕገወጥ ጥቃት የአጸፋ ምላሽ መስጠት ሕጋዊ መከላከል እንዳልሆነ ማወቅ ይገባል።ወንድሙን ከገደለበት በኋላ ሸሽቶ ተደብቆ የሚገኝን ሰው ዱካውን ተከታትሎ መግደል ሕጋዊ መከላከል አይደለም።
በመሆኑም በመሰረተ-ሐሳብ ደረጃ መከላከል ሲባል እየደረሰ ያለን (በሂደት ላይ ያለን) ወይም ከመድረስ የማይቀር ሕገወጥ ጥቃትን መመከት ነው።ተፈጽሞ ለተጠናቀቀ ጥቃት ግን “ተበደልኩ” ብሎ “አቤት” ማለት ብቻ ነው መፍትሔው።
ከሁሉም በላይ ልክ እንደ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሁሉ በሕጋዊ መከላከል ተጠቃሚ ለመሆን ሕገወጥ ጥቃቱ የደረሰ ወይም በቅርብ የሚደርስ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መብቱን ለማዳን ወይም ጥቃቱ እንዳይደርስ ለማድረግ ሌላ መንገድ አለመኖሩ ሊሰመርበት ይገባል።ይህ ብቻም ሳይሆን ከሁኔታው መጠን ሳይታለፍ የተፈጸመ (ተመጣጣኝ) ሊሆን ያስፈልጋል።
አስገዳጅ ሁኔታን ስንዳስስ እንደተመለከትነው ሁሉ በሕጋዊ መከላከል ወቅትም መብቱን ለማዳን ወይም ጥቃቱ እንዳይደርስ ለማድረግ ሕግን ከመጣስ ወይም በሌሎች ላይ ወንጀል ከመፈጸም ውጪ ሌላ ሕጋዊ አማራጭ ካለ አስቀድሞ እሱን መተግበር ያስፈልጋል።
ከዚህ ውጪ ግን አደጋውን ለመመከት ሌሎች አማራጮች እያሉ ሕግን መጣስ ከተጠያቂነት አያድንም፤ ሕጋዊ መከላከል ስላልሆነ።ለምሳሌ የደረሰውን ወይም በቅርብ መድረሱ የማይቀረውን ሕገ-ወጥ ጥቃት ለመመከት ለፖሊስ ወይም ለሌላ የሚመለከተው የመንግሥት አካል የማሳወቅና ውጤቱን የመጠበቅ ዕድል እያለ ይህን ሳያደርጉ የራስን የመከላከል ዕርምጃ መውሰድ ያስቀጣል።
ከተመጣጣኝነት ጋር በተያያዘም እንዲሁ በአስገዳጅ ሁኔታዎች እንዳየነው ሕገወጥ ጥቃቱ የተፈጸመበት ወይም እንደሚፈጸምበት እርግጥ የሆነበት ሰው ጥቃቱን ለመቀልበስ የሚወስደው ዕርምጃና ይህንን ዕርምጃ በመውሰድ የሚያድነው የእሱ ወይም የሌላ ሰው የመብት ጥቅም የተመጣጠነ መሆን ይገባዋል።
በሕጉ አነጋገር ተመጣጣኝነት የሚወሰነው “ከሁኔታው መጠን ሳይታለፍ የተፈጸመ” ከሆነ ነው።ይህ ማለት ከጉዳዩ ሁኔታዎች በመነሳት ሕጋዊ መከላከሉ የተወሰደበት ዘዴ ወይም መሣሪያ እንዲሁም የግራ ቀኙ ግላዊ ሁኔታ (ጾታ፣ ዕድሜ፣ የጤና ሁኔታና የአካል ጥንካሬ) ተመጣጣኝነትን ለመወሰን ጠቃሚ ናቸው ማለት ነው።
ለምሳሌ ምንም ዓይነት መሳሪያ ሳይዝ ጥቃት እየፈጸመበት ያለን ባላጋራውን በሽጉጥ ተኩሶ የአካል ጉዳት ያደረሰ ወይም የገደለ ሰው ሕጋዊ መከላከልን አንስቶ ሊከራከር አይችልም።በቁንጥጫ የሚመልሰውን ሕፃን ልጅ ጥቃት እየፈጸመብኝ ነው በሚል በዱላ ደብድቦ የአካል ጉዳት ያደረሰም ሰው ድርጊቱ ሕጋዊ መከላከል አይደለም።
እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ሕጋዊ መከላከልን ከመጠን ማለፍ በመሆናቸው በወንጀል ተጠያቂ ያስደርጋሉ።ይሁንና የቅጣት ማቅለያዎች ይሆናሉ።
ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ጥቃትን ለመከላከል ሲል ያደረሰው ጥፋት ከመጠን ሊያልፍበት የቻለው በጥቃቱ ምክንያት በተከሰተበት ፍርሐት፣ ድንገተኛ ድንጋጤ ወይም ደምፍላት ምክንያት እንደሆነ ምንም እንኳ ሕጋዊ መከላከልን ከመጠን በማሳለፉ ከወንጀል ተጠያቂነት ባይድንም ፍርድ ቤት ቅጣትን ከማቅለል አልፎ ከቅጣቱ ሙሉ በሙሉ ነፃ አድርጎ ወደቤቱ ሊሸኘው ይችላል።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተቋጨን አንድ ጉዳይ ለማሳያነት አቅርበን እናጠቃል። ከዓመታት በፊት በደቡብ ክልል ሐዋሳ ከተማ በአንድ ሆቴል ውስጥ ሁለት ግለሰቦች የፈጠሩት አለመግባባት ወደ ጠብ ያመራል።ገላጋይ ገብቶ “አንተም ተው አንተም ተው” ይላቸዋል።
ብዙም ሳይቆይ አንደኛው ጠበኛ ወደሌላኛው ጠበኛው ለጠብ ተመልሶ ሲመጣ ያኛውም ሽጉጥ አውጥቶ ብብቱ ሥር መትቶ ይገድለዋል።ገዳዩም ተከሶ በስምንት ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጣል።
ይህ ጉዳይ በየደረጃው ባሉት ፍርድ ቤቶች ከታየ በኋላ በመጨረሻም ለፌዴራል ሰበር ችሎት ቀርቦ እልባት አግኝቷል። በክርክሩ ወቅት የገዳዩ ዋነኛ የመከራከሪያ ነጥብ ሕጋዊ መከላከል ነው የሚል ነበር።
ይሁንና የወንጀሉ አፈጻጸም ከመነሻው ራስን ከመከላከል ጋር የሚገናኝ ሳይሆን ተራ የሰው ግድያ በመሆኑ ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ ነው የተገኘው።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2012
ከገብረክርስቶስ