አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቅርቡ ያከናወነው የንግድ ቤቶች ኪራይ ዋጋ ማሻሻያ ተገቢ በመሆኑ መጠናከር እንጂ ወደኋላ መመለስ እንደሌለበት የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ትናንት የኮርፖሬሽኑን የ2011 በጀት ዓመት የስድስት ወር አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት እንደገለጸው፤ ኮርፖሬሽኑ በጀመረው የሪፎርም ሥራ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በስድስት ወሩም አበረታች ውጤቶችን አሳይቷል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም በቅርቡ ያደረገው የንግድ ቤቶች ኪራይ ማሻሻያ ‹እኔ ከተጠቀምኩ ስለሌላው ምን አገባኝ› የሚለውን ስር የሰደደ አስተሳሰብ ለመቀልበስ የሚያስችል ብቻ ሳይሆን፤ በአንድ አገር ሁለት ዜጎች እንዳይኖሩ የሚያደርግ ተገቢ እርምጃ ነው፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ እና ሌሎች የቋሚ ኮሚቴው አባላት እንዳሉት፣ ከዋጋ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ ለዓመታት በ ‹‹እኔ ብቻ ልጠቀም›› ስሜት ጥቂት ግለሰቦች ሲጠቀሙበት የነበረ፤ የብዙሃኑን ባለቤትነትም የዘነጋ ነበር፡፡ ኮርፖሬሽኑም ይሄን አስተሳሰብ ሰብሮ በዚህ መልኩ ማሻሻያ ማድረጉ ተገቢና የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ሂደቱ «የነብርን ጭራ ከያዙ» የሚሉት አይነት ትጋትን የሚፈልግ በመሆኑ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በተመሳሳይ የቀረቡለትን ቅሬታዎች የመለሱበት አግባብ የሚበረታታ ሲሆን፤ አሁንም ቀሪ ቅሬታዎች ካሉ በፍትሃዊነት በአሰራሩ መሰረት መመለስ ይኖርበታል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ለሚያከናውናቸው የለውጥ እርምጃዎችም ቋሚ ኮሚቴው ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ፣ ከዋጋ ማሻሻያ ሥራው ባለፈ ገቢን ከማሳደግ፣ የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች ከመለየት፣ የቤትና ውል እድሳት በማድረግ ረገድ ያከናወናቸው ተግባራት የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የተቋቋመበት አንዱ ዓላማ ቤት የመገንባት፣ ኪራይ የመሰብሰብና ተጨማሪ ገቢን በማግኘት የቤት ልማት ሂደቱን ማገዝ ቢሆንም፤ እስካሁን የሚታይ ነገር የለውም፡፡ በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ የቤት ልማት ሂደቱን ወደሚታይ ደረጃ ማሳደግ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከተጠሪ ተቋማት ጋር ያለውን የክትትልና ድጋፍ ሥራ ወጥ ማድረግ፤ የውስጥና የውጭ ኦዲቶችን ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ፤ ለሚንከባለሉ የተሰብሳቢ ሂሳቦች መቋጫ መስጠትና በመጋዘን የተዘጋባቸው ንብረቶች ለይቶ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል በበኩላቸው እንዳሉት፤ የዋጋ ማሻሻያው ለረጅም ጊዜ ያልተከለሰና ግለሰቦችም ለዓመታት ይዘውት በመቆየታቸው ተከራዮች በቤቶቹ ላይ ያልተገባ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠርባቸው አድርጓል፡፡ ከዚህ ባለፈም በአምስት መቶ ብር በተከራዩት ቤት ደጃፍ ላይ የጀበና ቡና ከምትሸጥ ሴት ከሰብዓዊነት ባፈነገጠ መልኩ እስከ 3ሺ ብር ይቀበላሉ፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን በቤቶቹ የሚሰሩ ነጋዴዎች ገበያን በማረጋጋቱ ሂደት ውስጥ ሚና አልነበራቸውም፡፡ እናም ማሻሻያውንም ሆነ ሌሎች ተግባራትን አስመልክቶ ከቋሚ ኮሚቴው የተገኘው ግብረ መልስ ለቀጣይ ሥራቸው የሚያግዝ ነው፡፡ የኮርፖሬሽኑ ጅምሮች ለውጤት እንዲበቁ ግን በቀጣይ የመንግሥትም ሆነ የቋሚ ኮሚቴው ያላሰለሰ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011
ወንድወሰን ሽመልስ