አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት የአኩሪ አተርና የሽምብራ ምርትን ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት በማስገባት ግብይቱን በይፋ ጀመረ፡፡
አኩሪ አተርና ሽምብራን በዘመናዊ የግብይት ስርዓት በማስገባት በይፋ ማገበያየት መጀመሩን አስመልክቶ ትናንት በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ እንደገለጹት፤ ምርት ገበያው ተፈላጊነት ያላቸውን የአኩሪ አተርና የሽምብራ ምርቶች ወደ ግብይት ሥርዓቱ ያስገባው አርሶ አደሩ፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች ብሎም አገሪቷ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም ምርቶቹን ከታህሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በዘጠኝ ቅርንጫፎች መቀበል መጀመሩንና አቅራቢዎች ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየታቸው በሁለት ሳምንት ውስጥ ከ29,787 ኩንታል ቶን በላይ አኩሪ አተር መቅረቡንና በአራት የግብይት ቀናትም 2,550 ኩንታል ምርት መገበያየቱን ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ምርቶች በዓለም ገበያ ላይ ተፈላጊነት ያላቸው መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በ2010 ዓ.ም 110 ሺ ቶን አኩሪ አተርና 49 ሺ ቶን ሽምብራ ወደ ውጭ አገር ተልኮ ከ91 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ማብራሪ ከዚህ በኋላ ግብይታቸው በምርት ገበያ በኩል መፈጸሙ ለወጪ ንግዱ እድገት አስተማማኝ አቅርቦት እንዲኖርና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለመላክ ከማስቻሉም በላይ አቅራቢዎች ግብይት በተፈጸመ ማግስት የምርታቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ ይህ ምርትና ምርታማነትን እያሳደገ እንዲሄድ ያስችላልም ተብሏል፡፡
ምርት ገበያው የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት እያስገባ የቆየ እንደመሆኑ አኩሪ አተርና ሽምብራንም ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ ለማስገባት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የመጡ ግፊቶች ነበሩ የሚሉት የጂፋይፍ ቢዝነስ ፒኤልሲ ድርጅት ሥራ አስኪያጅና የመድረክ ወኪል አቶ መላኩ ጉልላት ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ የተለያዩ ምርቶች ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ መግባታቸ፤ የውጭ ገበያን ከማሳለጥና ግልጽ የሆነ ዋጋን ከመስጠት አንጻር፤ እንዲሁም ለአቅራቢዎቹ ዋጋቸውን በወቅቱ በመክፈል አምራቹን ያበረታታል፡፡ ከዚህም በላይ በሀገር ኢኮኖሚም ሆነ በምርት ገበያው ላይ ጉልህ ሚናን ይጫወታልም ብለዋል፡፡
አያይዘውም በዕለቱ በሁለት መጋዘኖች ግብይት የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ፤ ቡሬ ላይ ደረጃ ሁለቱ 1,340 ብር፣ ደረጃ ሦስቱ 1,300 ብር እንዲሁም በፓዌ ደረጃ ሁለቱ 1,300 ብር መሸጡን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ጥቂት ወራትም ኑግና ባቄላ የዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱን እንደሚቀላቀሉ በመክፈቻ ሥነሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011
በፍሬህይወት አወቀ