በዕድሜው ገና ለጋ የሚባል ወጣት ነው።ልጅነቱ ከብዙ ቢያውለው ጠብና ግርግር ከሚበዛበት ጥግ አይታጣም።የዘወትር ግልፍተኝነቱ ከብዘዎች ሲያጋጨው ይውላል።ችኩልነቱም ከስህተት ይጥለዋል።ትዕግስት ይሉት ባህሪይን አያውቅም።ከማዳመጥ መጮህ፣ ከመሸሽም ቀድሞ መጋፈጥ ይቀነናዋል።የአስራ ስምንት አመቱ ወጣት ስለሺ ተገኑ፡፡
ስለሺ ከቤተሰቦቹ ጋር ይኖራል።እህትና ወንድሞቹን አብዝቶ ስለሚወድ ክፏቻውን ማየትና መስማትን አይሻም።ኮሽ ባለ ቁጥር ለጠብ የሚጋበዘው ወጣት ሁሌም ቢሆን ለሽንፈት እጅ ሰጥቶ አያውቅም።ጥቃትን ስለሚጠላ ሳይቀደም መቅደምን ልምድ አድርጎት ኖሯል።ወጣቱ የድብድብ ልምዱ ብዙ አስተምሮታል፡፡በእሱ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ከሌሎች ሲጣሉ ቢላዋና ጩቤ ይዘው እንደሚዞሩ ያውቃል፡፡ይህን ማድረጋቸው ቀድሞ ላለመጠቃት መሆኑን አሳምሮ ይረዳል።እሱም ቢሆን እንደነሱ ቢያደርግ ፈቃዱ ነው።ለጠብ የሚሹትን ሁሉ በያዘው ድምጽ የለሽ መሳሪያ እየመከተና ራሱን እየጠበቀ ቢንቀሳቀስ ደስ ይለዋል።ስለሺ አንዳንዴ ይህ ሀሳቡ ብቻ በቂ እንደማይሆን በተረዳ ጊዜ አለፍ ብሎ ያስባል።የዕድሜው ለጋነት ያቀደውን ለመፈጸም እንደማያስችል ያውቃል።ያም ሆኖ ግን ሁሉንም መሞከር ይፈልገል።በፊልም ላይ እንደሚያያቸው ታዋቂዎች ሽጉጥ ከወገቡ ታጥቆ የሚያጠቁትን ሁሉ እየመታ መጣልን ይሻል።ይህኔ ሁሌም በአሸናፊነት ድልመንሳት የሚወደው ልቡ በሀሴት ሲመላ ይሰማዋል፡፡
ስለሺ በዚህ ህልሙ ውሎ ማደር ከጀመረ ቆይቷል።የልቡን አድርሶ ከሀሳቡ ጥግ ለመድረስ ግን አጋጣሚውን ማግኘት አልቻለም።ሽጉጥ ቢኖረው ራሱን ከጠላቶቹ ጠብቆ ክብሩን እንደሚይዝ ውስጡን አሳምኗል፡፡ይህን ማድረግ ከቻለ ደግሞ ማንም ሊዳፈረው አይሞክርም።ባለሽጉጥ መሆኑ ከታወቀ ለእህትና ለወንድሞቹ ጭምር መኩሪያና መከበሪያ መሆን ይችላል፡፡
አንድ ቀን…
ስለሺ መሳሪያ የመያዝ ፍላጎቱ አሁንም እንደጨመረ ቀጥሏል።ከውስጡ ሀሳብ ለመገናኘት ግን መንገዱቀላል አልሆነም።ሁሌም የሚያስበውን ሽጉጥ ገዝቶ በእጁ ለማድረግ ሁኔታዎች
በሚስጥር መያዝ ይኖርበታል፡፡መሳሪያን እንደማ ንኛውም ዕቃ ከሱቅ ገዝቶ የሚወስደው
አይደለም።ፍላጎቱንና የመግዛት አቅሙን የሚጠራጠሩ የድብቅ መሳሪያ ሻጮችንም ቢሆን
ማግባባትና ማሳመንም ይጠበቅበታል፡፡
አንድ ቀን ግን ስለሺ የዘወትር ህልሙን የሚያሳካበት ጊዜ መድረሱን አወቀ።በድንገት ካወቀው ህገወጥ የጦር መሳሪያ ሻጭ ጋር ለመነጋገር በተቃጠረበት ስፍራ በሰዓቱ ተገኘ።በገንዘብ ተስማምቶ ሽጉጡን ከእጁ ሲያስገባ በዋዛ አላመነም።ከዚህ በኋላ ባለ መሳሪያ እንደሚሆን ባወቀ ጊዜ ልቡ በደስታ ተሞላ።አስከዛሬ ሲያስበው የቆየው ምኞቱ እውን መሆኑ ከልብ አስደሰተው።ሳያንገራግር የተጠየቀውን አምስትሺ አምስት መቶ ብር ቆጠረ።በምትኩም ቱርክ ሰራሹን ሽጉጥ ከመሰል ስምንት ጥይቶቹ ጋር ተረከበና ሻጩን በምስጋና ተሰናበተው፡፡
ስለሺ ገንዘቡን ቆጥሮ ሽጉጡን በወሰደ ጊዜ ስለሻጩ ማንነት እልጠየቀም።የሚፈልገውን ከእጁ ማድረግ እንጂ የሰውየው ስምና አድራሻ አላስጨነቀውም።ሽጉጡን ወስዶ ቤቱ ከደበቀው በኋላ በራስ መተማመኑ ጨመረ።አንዳንዴ ከሰዎች ሲጋጭና አለመግባባት ሲፈጠር የድብቅ ሚስጥሩ ትውስ ይለዋል።ጉዳዩን በትዕግስትና በመግባባት ካለፈው በኋላም ሽጉጡ ከቦታው ስለመኖሩ ያረጋግጣል፡፡እንዲህ ሲሆን የተለየ ወንድነት የተሰማው ይመስለዋል።የገዛው ሽጉጥ ከሚጣሉት ሁሉ መጠበቂያው መሆኑን ሲያስብ ፍርሀት ይሉት ነገር ከውስጡ ይጠፋል፡፡ባለመሳሪያ መሆኑ ከሌሎች ሁሉ እንደሚለየው በገባው ጊዜም የተለየ ኩራትና ደስታ ይሰማዋል፡፡
አሁን ከእኩዮቹ በላይ ታላቅነቱን አረጋግጧል።ከቢላዋና ጩቤ በተለየም የእሱ ዋጋ መጨመሩ ገብቶታል።በእሱ ዕምነት ሽጉጡ ማለት ከራስ መጠበቂያም በላይ መከበሪያና መወደሻ ነው። ከመሳሪያው ጋር መዋል ማደር ከጀመረ ወዲህ አተኳኮሱ ጭምር ይናፍቀዋል።እስከዛሬ የሽጉጡን ድምጽም ሆነ ስልትና ዒላማ የመሞከር ዕድልን አላገኘም።
ያም ሆኖ ግን ባለመሳሪያ መሆኑ ብቻ ደስታን ይሰጠዋል።ደብቆ ያስቀመጠውን የሚስጥር ንብረት እያሰበም ሁሉን ነገር በሀይልና ጉልበት መፍታት እንደሚቻል ለራሱ ይነግረዋል።
ባለሽጉጡ ስለሺ የገዛውን መሳሪያ በሚስጥር ደብቆ ኑሮውን ቀጥሏል።ወላጆቹ ትንሹ ልጃቸው የጦር መሳሪያ ሸሽጎ ስለማኖሩ ጠርጥረው አያውቁም።አንዳንዴ የዕድሜውን ለጋነት ከአዋዋሉ ጋር እያሰቡ ምክርና ተግሳጽ ያደርሱታል።እሱም እንደልጅ የቤተሰቦቹን ቁጣና ምክር እየተቀበለ ካሰበው ውሎ ይመለሳል።
ስለሺ አስከዛሬ ከአንዳንድ የሰፈሩ ልጆች ጋር ሲጋጭና ሲጣላ ቆይቷል፡፡ከነዚህ መሀልም በቅጽል ስሙ ቾምቤ የሚባለውን ወጣት ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ቾምቤ ትዕግስት የለሽና ተደባዳቢ ነው።ሁሌም ከእጁ በማይለየው ጩቤ የተጣሉትን እያስፈራራና ባስ ሲልም እየወጋ ራሱን ሲያስከብር ቆይቷል፡፡የቾምቤን ማንነት የሚያውቁ ብዙዎች ባልንጀርነቱን አይመርጡም።ከጠብ በኋላ የሚከተለውን የሚያውቁ አንዳንዶችም ከስፍራው መራቅን ይመርጣሉ፡ ፡ቾምቤ ከሰዎች ከተጣላ ስለታም ጩቤውን ከመጠቀም አይመለስም፡፡
ሀምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም የክረምቱ ወራት ከገባ ሰንበት ብሏል።ዕለቱን ሲጥል የዋለው የሀምሌ ዝናብ ምሽቱንም ቀጥሎ ብርዱን አብሶታል።በጊዜ ወደቤታቸው የገቡ ብዘዎች ቅዝቃዜውን አምልጠዋል፡፡መዝናናትን የሻቱ አንዳንዶች ደግሞ የመለኪያ አንገት እንደጨቡ ጨዋታቸውን ቀጥለዋል።ቾምቤና የቅርብ ጓደኛው ከአንድ ግሮሰሪ ተቀምጠው አንድ ሁለት ማለት ከጀመሩ ቆይተዋል።ሰዓቱ እየገፋ ቢሆንም ካሉበት ለመነሳት ያሰቡ አይመስልም፡፡
ምሽት 4 ሰዓት ከ30 ድንገት ያቃጨለውን የእጅ ስልኩን ፈጠን ብሎ ያነሳው ስለሺ የሰዓቱን መምሸትና የደዋዩን ማንነት ባየ ጊዜ ደነገጠ።በዚህ ጊዜ የወንድሙ ጓደኛ ያለምክንያት እንደማይፈልገው ያውቃል።ይህን እያሰላሰለ ሁኔታውን ለማወቅ ደዋዩን በጥያቄ አጣደፈው፡፡
ውስጡ በድንጋጤና ፍርሀት የራደው ወጣት ቃላቱን እየቆራረጠ ለመናገር ሞከረ።ስለሺ ሀሳቡን ለማስታመም ትዕግስት ቢያጣ የመደወሉን ምክንያት ፈጥኖ እንዲነግረው ደጋግሞ ጠየቀ።ደዋዩ እንደምንም ራሱን አበረታ።ትንፋሹን ሰብስቦም ወንድሙ በጩቤ መወጋቱንና ሀኪም ዘንድ መወሰዱን አሳወቀው።
ስለሺ ስልኩን እንደዘጋ ወንድሙ ይገኝበታል ወደተባለው የህክምና ስፍራ ገሰገሰ።በቦታው ደርሶም በጩቤ ተወግቷል የተባለውን ወንድሙን ፍለጋ ባዘነ።እንዳሰበው አላገኘውም።እየጮኸ የወንድሙን መገኛ ጠየቀ።በቦታው የነበሩ ሰዎች ጠጋ ብለው ሊያረጋጉት ሞከሩ።የደረሰበትን የከፋ ጉዳት ጠቅሰውም ለተሻለ ህክምና በአምቡላንስ ወደ አቤት ሆስፒታል መላኩን አስረዱት፡፡
እየፈጠነ ከኋላው ደረሰና የወንድሙን የከፋ ጉዳት አስተዋለ።ተጎጂው አንገቱ ላይ በደረሰበት የጩቤ መወጋት እየደማ ነው።የህክምና ባለሙያዎች ደሙን ለማቆምና ህይወቱን ለማትረፍ መሯሯጥ ይዘዋል።ስለሺ ይህን ሲመለከት ከልቡ ደነገጠ፡ የወንድሙ ሁኔታ ተስፋ ቢያስቆርጠው ስለመትረፉ ተጠራጠረ።ጥቂት ቆይቶ ራሱን ለማረጋጋት ሞከረ።አልቻለም።እንባ እየተናነቀው የድርጊቱን ፈጻሚ ማንነት ጠየቀ።በአካባቢው ‹‹ነበርን› ያሉ የአይን እማኞች ፈራ ተባ እያሉ ይህን ያደረገው ቾምቤ የተባለው ልጅ መሆኑን ነገሩት።
ስለሺ ጉዳዩን እንዳወቀ ቾምቤ ይገኝበታል ወደተባለ የመጠጥ ግሮሰሪ ፈጠነ።በስፍራው ሲደርሰ ከበር ቆሞም በአይኑ ፈለገው።አላጣውም።ከአንድ ጓደኛው ጋር ተቀምጧል።ቾምቤ የስለሺን አመጣጥ ለጤና አለመሆን ሲረዳ ካለበት ተነስቶ ጠበቀው።ስለሺ በንዴት እንደጋየ ወደ እነሱ ቀረበ።ተፋጠጡ፡፡
አብሮት የነበረው ጓደኛው ሁለቱን መገላገል አልፈለገም።ነገሩን አባብሶ ለጠብ ተጋበዘና ከጓደኛው ጎን ቆመ።ባልንጀሮቹ ስለሺን በድንጋይ እያሯሯጡ ከአካባቢው አራቁት።ስለሺ የሁለቱን ጡጫ መቋቋም አልቻለም።እነሱ አባራሪ እሱ ተባራሪ ሆኖ ከነሽንፈቱ አመለጠ፡፡ ጉዞ ወደ ቤት ስለሺ በእሱና በወንድሙ ላይ የሆነውን ሁሉ ማመን አልቻለም።በተለይ በጩቤ ተወግቶ በሞትና ህይወት መካከል ያለው ተጎጂ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖበታል።በእልህና ንዴት እየተንጨረጨረ የሰፈሩን አቅጣጫ ጀመረ።መራመድ አልቻለም ።ታክሲ አስቁሞ ዋጋ ተነጋገረና ወደቤቱ ገሰገሰ፡፡
ቤቱ እንደገባ ደብቆ ያስቀመጠው ሽጉጥ ትዝ አለው።ጊዜ ማጥፋት አልፈለገም።ከተደበቀበት አውጥቶ ጥይት አቃመውና ከግቢው እየተቻኮለ ወጣ።አሁንም የወንድሙ ስቃይ፣ የቾምቤና የጓደኛው ድርጊት በአይኑ ውል እያለበት ነው።ንዴትና ጭንቀትም ይፈትኑት ይዘዋል ፡፡
ከግቢው ወጥቶ የመንገዱን አቅጣጫ ሲጀምር ወዴት እንደሚሄድ አላጣውም።ከዚህ ቀድሞ የእነ ቾምቤን ቤት አሳምሮ ያውቀዋል።እየተጣደፈ መንገዱን አቋረጠና ቀጣዩን ቅያስ ጀመረ።ቾምቤ ከዚህ በኋላ ወደቤቱ እንደሚመለስ እርግጠኛ ሆኗል።ቀድሞ በድንጋይ ያበረረውን የወንድሙን አጥቂ አሁን ከፊት ለፊቱ ገጥሞ ሊፋለመው ተዘጋጅቷል።
በፈጣን እርምጃው እየተዋከበ የመንገዱን ጠርዝ ሲጨርስ ከርቀት የነ ቾምቤን ቤት ተመለከተ።ፍጥነቱን ሳይቀንስ ከበሩ ደረሰና እጁን ጠንከር አድርጎ የውጩን መዝጊያ በሀይል ደለቀው።ብዙም ሳይቆይ ከውስጥ በኩል «ማነው?» የሚል የሴት ድምጽ ተሰማ።የቾምቤ እናት ናቸው፡፡
ስለሺ ትኩስ ትንፋሹ እየተቆራረጠ የበሩን መከፈት ናፈቀ።ወዲያው በድምጽ የሰማቸው ወይዘሮ በሩን ወለል አድርገው ምን እንደሚፈልግ ጠየቁት።ስለሺ ወይዘሮዋን ሲያይ በመጠኑ ለመረጋጋት ሞከረ።እንደምንም አንደበቱን አለስልሶም ቾምቤን ፈልጎ እንደመጣ ነገራቸው፡፡
ሁለቱ ሲነጋገሩ ከሳሎን ወደ በረንዳው መውጣት የጀመሩት የቾምቤ ወንድሞች ትኩረታቸውን ወደ በሩ አድርገው ንግግራቸውን በትኩረት አደመጡ።ወይዘሮዋ የቾምቤን አለመግባት ደጋግመው እየገለጹ ነው።ስለሺ ግን አምኖ መቀበል የፈለገ አይመስልም።በጥርጣሬ እየተገላመጠ ደግመው እንዲያረጋግጡለት መጠየቅ ይዟል።ይህን ያዩትና ከበረንዳው የቆሙት ወጣቶች በሁኔታው ቢናደዱ እናታቸውን ወደውስጥ እንዲገቡ አድርገው ከስለሺ ጋር ተፋጠጡ።ዳንኤል የተባለው የቾምቤ ወንድምም ቾምቤ ያለመኖሩን ጠቅሶ ስለሺ በአስቸኳይ ከስፍራው እንዲርቅ በእልህ ተናገረው፡፡
ስለሺ ይህን ሲሰማ መብረድ የጀመረው ንዴቱ አገረሽ።ከበር የቆሙትን እናት አልፎም ወደውሰጥ ዘለቀ።ከበረንዳው ሲደርሰ በወገቡ የነበረውን የተቀባበለ ሽጉጥ ዳበሰውና ፈጥኖ አወጣው።ጊዜ አልፈጀም።አነጣጥሮ ከዳንኤል አንገት ላይ ተኮሰበት።ዳንኤል የጥይቱ አርሳስ ከሰውነቱ እንዳረፈ በቁመናው የኋሊት ተዘረረ።ይህን አስደንጋጭና ፈጣን ድርጊት ያዩ ቤተሰቦች እየተጯጯሁ ወደእሱ ተረባረቡ።
ስለሺ ቆም ብሎ ዙሪያ ገባውን ቃኘ።መላው ቤተሰብ ወደወደቀው ዳንኤል አተኩሯል።አጋጣሚው ተመቸው።ግርግሩን ተጠቅሞ ከአካባቢው በፍጥነት አመለጠ።እየሮጠ ከስፍራው ሲርቅ ልቡ ክፉኛ ይመታ ጀመር።እግሩ ወዴት እንደሚያመራ ባያውቅም የሆስፒታሉን መንገድ ያዘ።በአይኑ በጩቤ የተወጋው ወንድሙ ውል አለበት።
አሁን በቾምቤ ጦስ ምንም የማያውቀው ወንድሙን መጉዳቱ ይቆጨው ይዟል።ከቤት ሲወጣ ይህን ለማድረግ አላሰበም።የነበረው እንዳልነበረ መሆኑን ሲያስታውስ ልቡ በጸጸት መናጥ ጀመረ።ደጋግሞም ራሱን ወቀሰ።እየሮጠ አቤት ሆስፒታል ግቢ ደረሰ።በስፍራው የነበሩ ዘበኞች ሊያስገቡት አልፈቀዱም።ስለሺ አሁንም ቆም ብሎ ማሰብ ያዘ።በጥይት የተመታው ወጣት አወዳደቅና በጀርባው ሲወርድ ያየው ትኩስ ደም ሰላም ነሳው።ባልተገባ ወጥመድ የማይገባውን ንጹህ ሰው ጠልፎ መጣሉ አናደደው።ልቡ ስጋት ተመላ።ዓይኖቹ ውሀ መያዝ ጀመሩ፡፡
ካለበት ሆኖ ከወዲያ ወዲህ አማተረ።በርቀት ሁለት ፖሊሶችን አያቸው።በእጁ የጨበጠውን ሽጉጥ አሁንም ደጋግሞ ዳበሰው።በቅርበት የቆመውን ኮድ 3 መኪና ተጠጋና በሾፌሩ በኩል ባለው ያልተዘጋ መስታወት አሻግሮ ከጋቢናው ላይ ወረወረው።ወዲያው ወደ ፖሊሶቹ ቀረበ።የሆነውን ሁሉ ተናግሮም እጁን ለህግ አሳልፎ ሰጠ፡፡
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ከስለሺ የደረሰውን መረጃ ዋቢ አድርጎ ወንጀሉ ወደ ተፈጸመበት ቦታ አመራና እውነታውን አረጋገጠ።በአንድ ጥይት ከአንገቱ ላይ የተመታው ወጣት ዳንኤል በህክምና ሲረዳ ቢቆይም ህይወቱን ማትረፍ አልተቻለም።በዋና ሳጂን ሲሳይ በላይ መሪነት የተጀመረው ምርመራ በመዝገብ ቁጥር 099/18/11 በተከፈተው ፋይል የምስክሮችና የተጠርጣሪው ቃል በአግባቡ ተካተተበት።የህክምናና ተጨማሪ የቴክኒክ ማስረጃዎች ታክለውም ጉዳዩ ወደ ፍርድቤት እንዲዞር ለዓቃቤ ህግ ተላለፈ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2012
መልካምስራ አፈወርቅ