በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት የዓለም የትምህርት ሥርዓት በጎም፣ ክፉም ገጠመኞችን እያስተናገደ ነው። የመጀመሪያው ወገን የአለምን የትምህርት ስርዓት በማፍረክረክ አያሌ ተማሪዎችን በቤታቸው ተኮድኩደው እንዲቀመጡ ያስቻለ ርጉም ወረርሽኝ በሚል ይወቅሱታል። ሌላው ወገን ደግሞ ለዘመናት በርካታ ሂደቶችን ያለፉ የአገራት የትምህርት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ለመፈተሽ እድል ይዞ የመጣ ምርጥ አጋጣሚ እንዲሉ አሰኝቷቸዋል። በትምህርት ዘርፉ ሊታሰቡ የሚገባቸውን የአስቸጋሪ ጊዜ አሰራሮች ብቻ ሳይሆን ማደግና መመንደግ የሚገባቸውን በቴክኖሎጂ ባሉበት ቦታ የመማማሪያ የተለመዱ አሰራሮች ላይ ‹‹ሪቮሊውሽን›› ይዞ የመጣ ምርጥ አጋጣሚ ሲሉም እነዚሁ ወገኖች ያሞካሹታል።
የትምህርት ስርዓቱ ያልተመለከታቸውን የሥትራቴጂ አቅጣጫዎችን መፈተሽ እንዲችል አድርጓቸዋል። የ‹‹ኢንተርኔት›› የትምህርት ስርዓት በሰፊው እንዲያብብ፣ የተሻሻሉ አሰራሮች እንዲበለጽጉ፣ በዚህ ረገድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች እንዲጠናከሩና የበለጠ ለእውቀት ሸመታ ምቹ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያስቡ አድርጓዋል፣ በገበያውም ተጠቃሚዎች የሚሆኑበትንም እድል አግኝተዋል የሚሉ ሐሳቦችን በርካታ ባለሙያዎችና ጸሐፊን ሰንዝረዋል።
ሶፊያ ግሬስ የተሰኙ አሜሪካዊ በማርች 18 ቀን 2020 ለንባብ ባበቁት ጽፋቸው የኮቪድ 19ኝን የመከላከል ሂደት የኢንተርኔት የትምህርት ግብይት ኢንዱስትሪ አርበሰፊ እንዲሆን አስችሎታል ይላሉ። ሶፊያ እንደሚሉት የኮሮና ቫይረስ ከመስፋፋቱና ወረርሽኝ ስለመሆኑ አለምአቀፍ እውቅና ሳይቸረው በፊት በሀገረ አሜሪካ የመንግስት የንግድ ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች የትምህርት ተቋማት የወሰዷቸው ርምጃዎች አጠያያቂ እንደነበሩ ያነሳሉ። አውሮፓዊቷ ጣሊያን ከመድሐኒትና ከሱፐርማርኬቶች በስተቀር ሌሎች የንግድ ስርዓቶቿን ከረቸመች። ትምህርት ቤቶችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ቤተመጽሀፍትን እና መሰል አገልግሎቶች እንዲዘጉ በማወጅ ከስፔን ቀድሞ ለሌሎች አገራት ደወሉን ያሰማ
አልነበረም ትላለች።
በዚህ የተነሳም ኮሮና ቫይረስ ባሳደረው ተመሳሳይ ተጽዕኖ ምክንያት ለቁጥር ከሚያታክቱ ኢንዱስትሪዎች ራሴን ጨምሮ እስከ ተራው ግለሰብ ድረስ በ‹‹ኦንላየን››ገበያው ላይ አይናችን አርፏል። ከከፍተኛ ዩኑቨርሲቲ ተማሪዎች እስከ የሶስት አመት ሴት ልጄ ድረስ ትምህርታቸውን በ‹‹ኦንላይን›› ጀመሩ ስትል ታስረዳለች።
ከዚህ ባሻገርም የአሜሪካ ታላላቅ የንግድ አንቀሳቃሾች እንደ ኦልማርት፣ አፕል እና ኦሊቭጋርደን የመሳሰሉት የንግድ ፖሊሲዎቻቸውን ሽባ ባደረገባቸው በሽታ ምክንያት ፈትሸው እንዲያሻሽሉ ሆነዋል። በርካታ የአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወረርሽኙን የመከላከሉ አንድ አካል ሆነው እንዲሰለፍ አድርጓቸዋል። ሀርቫርድ፣ ዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ ቴክኖሎጂኮ ዲሞንተሪ (Tecnologico de Monterrey) እና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸው የትምህርት ተቋማቱን ለቀው እንዲወጡ ውትወታቸውን ቀጠሉ።
በዚህ ምክንያት የተወሰኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በርቀት ሆነው በቴክኖሎጂ መማር እንዲችሉ የሚያስች ሏቸውን ሁኔታዎች ማማተር ጀምረው ነበር፤ ይህ ሁኔታ በምን ያህል ደረጃ መሳካት ይችላል? ይህ ሂደትስ ሰፊ ከሆነው የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአሰራር ሂደት ጋር እንዴት ተጣጥሞ የተዋጣለት መንገድ ሊሆን ይችላል? ስትልም ሶፊያ በጽሁፏ ትጠይቃለች።
ወረርሽኙ ለአለም ማህበረሰብ ያበረከተው ተመሳሳይ ነገር አይደለም። ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተባት ቻይናም ማፈግፈጓ ለውጤት እንዳበቃት መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ የተነሳም 600 ሺ መምህራን እና 50 ሚሊዮን ተማሪዎች በ‹‹ኦንላይን›› ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስችሏታል።
በቻይና የኢድ ቲች (Ed Tech) ካምፓኒ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሮበርት ሀውስን እንደሚሉት እንዲህ አይነት የጤና እክሎች ፊትለፊት በሚደቀኑባቸው አጋጣሚዎች ቴክኖሎጂዎች ገላጋይ መፍትሄዎች ስለመሆናቸው ይገልጻሉ። ሁኔታዎችን ተቋቁመው ረዥም ጊዜ ያገልግሉም አያገልግሉም ፈጣን መፍትሄዎችን ይዘው ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ መሆን መቻላቸውን ያነሳሉ።
አዳዲስ የፈጠራ ሪፖርቶችን አጣቅሰው ሮበርት እንደገለጹት፤ ጥራት ያለው የ‹‹ኦንላይን›› አገልግሎት ፍላጎቶች በገፍ እየመጡ ነው። ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ በማንኛውም ደረጃ አዳዲስ የ‹‹ኦንላይን›› አሰራር አማራጮችን ይዞ ለመቅረብ በርብርብ ላይ ይገኛል። ይህ ሁኔታ አዳዲስ ካምፓኒዎች በዘርፉ እየተፈጠሩና አቅማቸውን እያሳደጉ የ “ኦንላይን” የትምህርት ሂደቱን ሊመሩ የሚችሉ እድሎች የሚፈጠሩበትን አጋጣሚም የሚፈጥር ነው።
በተለይም ደግሞ ያልተለመዱና አዳዲስ እይታዎችን ይዘው በመምጣት የጤናው ዘርፍ መደበኛ ሂደት ልክ እንደዚህ በወረርሽኝ በሚናጋበት ጊዜ መፍትሄን ይወልዳሉ ሲሉም ያብራራሉ። ይህ ሁኔታ በትምህርት ስትራቴጂዎች ላይ ዘላቂ ለውጦች እንዲመጡ የሚያስችል በመሆኑ የወረርሽኙ ፍሬዎች ተደርገው ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው ይላሉ ሮብሰን።
በከፍተኛ ትምህርት ከፍተኛ የዜና መዋዕል ጸሐፊ ባለሙያው ጎለዲ ብሉምስቴክ (Goldie Blumenstyk‚ Senior Writer for Chronicle of Higher Education) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸው በሚገኙበት ጫፍ ድረስ የሚገናኙበትን ቴክኖሎጂዎች ከተላመዱ ወደ ቀድሞው አሰራራቸው የሚመለሱባቸው መንገዶች ጠባብ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
አዲሱ ገበያው የደራለት የቴክኖሎጂው አካባቢ ሌላው ተጠቃሚ ደግሞ የርቀት ትምህርቱ ዘርፍ ባለፉት ጥቂት ወራት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ ማሻቀቡ ይነገራል። አዳዲስ ፈጠራዎችን አንግቦ ወደቴክኖሎጂው ገበያ የተቀላቀለውን ጨምሮ ከሶስት ሺህ በላይ የሥራ እድሎች በዘርፉ እንደተፈጠሩም መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢድቲች (Ed Tech) ኢንቨስትመንቱም ከ18 ነጥብ 66 ቢሊዮን በላይ ዶላሮች በአለም አቀፍ ደረጃ ማስመዝገቡ ተጠቅሷል። ፌስቡክ፣ ማትሪክስ፣ ፓርትነር፣ እና ጂጂቪ (Facebook,Matrix,partbers,and GGV) የተሰኙት በገበያው ላይ ከሚጠቀሱ ቴክኖሎጂዎች ሲሆኑ ገበያውን በቀዳሚነት ከሚመሩት አገራት ደግሞ ሕንድ በቀዳሚ ተጠቃሚነት ተጠቅሳለች።
የአፕጋርድ ቴክኖሎጂ ባለቤቱ ሮኖ ስክሪውቫላ (Ron¬nie Screwvala,the qwner of upGrad ) እንዳለው የኩባንያውን አባላት በበጀት ዓመቱ በእጥፋ አሳድጓል። እኤአ በ2021 ደግሞ ፕሮጀክቱን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ በቀሪዎቹ ሁለት ወራት እየተሰራ ነው። ወረርሽኙ በፈጠረው አጋጣሚም ከ200 በላይ አዳዲስ ምሩቃን ከ20 ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ኩባንያው እንደተቀላቀሉም አብራርቷል።
በሳንፍራንሲስኮ እና በሌሎችም የአሜሪካ ግዛት አካባቢዎች እና በሌሎች አለማት ከሶስት ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሏቸው ገልጸው፣ የቴክኖሎጂ ካምፓኒው ፕሮጀክትም በ2020 ከነበረው በ20 በመቶ እንደሚያድግ ተናግረዋል።
ከትምህርት ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች አንዱ የሆነው ኮስራ (Coursera) በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመከሰቱ ማትረፉን ገልጿል። በአለም አቀፍ ደረጃ የርቀት ትምህርትን ለማዳረስ በሚያደርገው ጥረትም በጤናው ዘርፍ የተፈጠረውን ውድቀት ለመታደግ መስራቱን ያብራራል። በዩኒቨርሲቲዎች ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዱ ነጻ ትምህርት መስጠቱንም ተናግሯል።
በ “ኦንላይን” አገልግሎቱ ዩኒቨርሲቲዎች እስከ መጪው ሰኔ እንደሚመዘገቡና ተማሪዎች ደግሞ እስከ መስከረም ድረስ በነጻ የቴክኖሎጂው አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው ያለው።
ከዚህ ቀደም በዓለም ላይ ሲከሰቱ በነበሩት ወረርሽኞች በመጠኑ ልምድ መቅሰሙን ገልጾ የአሁኑን የኮሮና ወረርሽኝ አጋጣሚ ወደ መልካም የንግድ አጋጣሚ ለመቀየር እንደረዳው በማስረዳት የሚፈጠሩ ነገሮች ሁሉ ጠባሳ ብቻ ሳይሆን በረከትም ይይዛሉ፤ ተጠቀሙባቸው ሲል መክሯል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ተማሪዎቿ በቴክኖሎጂ ትምህርት በመቅሰምም ሆነ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ሥራ ፈጣሪዎች ወደ ገበያው በመቀላቀል በኩል እስከአሁን ባለው ሂደት ከጅምር የዘለለ እዚህ ግባ የሚባል ፍሬ አግኝታለች ማለት አይቻልም።
ምንጭ፡- የተለያዩ ድረገጾች
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2012
ሙሐመድ ሁሴን