አዲስ አበባ:- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የታክሲ ባለንብረቶች፣ ሾፌሮችና ነጋዴዎች በነዳጅ እጥረት ምክንያት ስራቸውን ማከናወን እንደተቸገሩና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው ገለፁ።
አራት ኪሎ ከቱሪስት ሆቴል ጎን በሚገኝው ቶታል የነዳጅ ማደያ ነዳጅ ለመሙላት ሰልፍ የያዙ የታክሲ ሹፌሮችና ሌሎች አሽከርካሪዎች ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ችግራቸውን እንደሚከተለው ገልጸዋል።
የታክሲ ሹፌርና ባለቤት የሆኑት አቶ በቀለ ካሳ እንዳሉት፤ እኔ ህዝብ የማገለግልበት ታክሲ ነው ያለችኝ። የነዳጅ አቅርቦት ባለመኖሩ የሚጠበቅብኝን አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለመስጠት ተቸገሬያለሁ። እዚህ ማደያም ከጧቱ አንድ ስአት እስከ ቀኑ ስምንት ስዓት ቤንዚን ለመሙላት ተሰልፌ ወረፋ አልደረሰኝም።
በዚህም ማግኝት የምችለውን ገቢ ሳላገኝ ውያለሁ ጊዜየንም በከንቱ አባክኛለሁ። ማታ ላይ እረዳቴ የሰራበትን ገንዘብ ይጠይቀኛል ስለዚህ ምንድነው የምከፍለው? በማለት የነዳጅ እጥረቱ ያስከተለባቸውን ተጽዕኖ ገልጸውልናል።
አሽከርካሪ እያሱ ተላይነህ በበኩላቸው ነዳጅ ለማግኝት ከጧቱ ሁለት ስአት ጀምሮ እስከ ስምንት ስዓት ወረፋው እንዳልደረሳቸው ጠቁመው፤ ለዛሬ ያቀድኋቸውን ብዙ ፕሮግራሞች ሰርዣለሁ። በእነዚህ ስዓታት ውስጥ ነጋዴ እንደመሆኔ መጠን ሰርቼ ማግኝት የሚገባኝን ገንዘብ አጥቻለሁ ብለዋል።
የታክሲ ሾፌር አንተነህ ሀይሌ በበኩላቸው ጧት እዚህ ማደያ የተሰለፍሁት ሁለት ሰዓት ከሀያ ነው፤አሁን ስምንት ሰዓት እያለ ነው እስካሁን ድረስ ወረፋው አልደረሰኝም። ተቀጣሪ ሹፌር ነኝ ከስድስት ሰዓት በላይ ቁሜ ውየ የት አምጥቼነው ለባለ ሀብቱ የቀን ገቢ ማታ ላይ የማስገባው? በአጠቃላይ ዛሬ የቀን ገቢዬንና “ጆርናታየን” አጥቻለሁ፤ ምሳ እንኳን ለመብላት ከኪሴ ነው የተጠቀምሁት።
ስለዚህ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ገብቻለሁ ብለዋል። በዚህ ላይ ይህን ያክል ጊዜ ተሰልፈን ውለን በጣም ትንሽ መጠን ያለው ነዳጅ ነው የምንሞላው ብለዋል።
የነዳጅ እጥረቱ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ በጣም እንደሚቸገሩ የገለፁት አሽከርካሪዎቹ መኪኖች በየመንገዱ ነዳጅ አልቆባቸው በመገፋት መንገዶች በመዘጋጋታቸው በሰው ህይወት ላይ አደጋ እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ሁሉም ታክሲዎች ማደያዎች ላይ ነዳጅ ለመሙላት ሰልፍ ላይ በመሆናቸው፤ ማህበረሰቡ ለመጓጓዛ ለትራንስፖርት እጥረት በመጋለጡ በሰዓቱ ወደ ቤቱ እየገባና ያሰበበት ቦታ እየደረሰ አይደለም፤ ላልተፈለገ ወጭም እየተጋለጠ ነው በማለት ጠቁመዋል።
በአጠቃለይ መንግስት የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት ችግር ከመሰረቱ በመለየት፤ ችግሩን ለመፍታት አይነተኛ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድርም ችግሩን ለመፍታት ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶችና ማደያ ባለሀብቶች ጋር ዛሬ ውይይት ማድረግ ጀምሯል፡፡
በሰለሞን በየነ