አለማችን ከምታስበው በላይ ጨካኝ፣ ከምታምነው በላይ ጀግና እና ከምትገምተውም በላይ ጠንካራ በሆነባት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከባድ የስቃይ ምእራፍ ውስጥ ትገኛለች።መላውን አለም በስጋት ያራደው ቫይረሱ ሕይወት ከመቅጠፍ ባለፈ የሰዎች ማህበራዊ የሕይወት ዘይቤና መስተጋብር በመለወጥ፣ ሟቾችን በወግ ስርአት አልቅሶ መቀበርም ሆነ ደግሶ ልጅን መዳርን ሳይቀር ከልክሏል። ቀውሱ ቀስ በቀስ ወደ ሃይማኖቱም በመዝለቅ አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጂዶችና ሌሎች ቤተ እምነቶች የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር የፀሎትና የሃይማኖት በዓላት አከባበር ላይ ለውጥ እንዲያደርጉ አስገድዷል።
አለማችን ከቫይረሱ ጋር ከተዋወቀችበት ጊዜ አንስቶም የጤናው ዘርፍ ጠቢቢን ብሎም የምርምር ተቋማት የሰውን ልጅ ከፍ ሲልም የሰው ዘር ከመጥፋት ለመታደግ የሚያስችል መድሃኒትና ክትባት ፍለጋ ሌት ተቀን መዳከራቸውን አላቋረጡም።
አገራትም የተቃጣባቸውን የቫይረስ ወረራ ለመከላከል፣ ጉዳቱን ለመቀነስና ከሆነላቸውም ድል ለማድረግ መፍትሄ ይሆናል የሚሉትን በተቻላቸው አቅም ከመሞከር አልቦዘኑም። እነዚህ እርምጃዎች ታዲያ የወረርሽኙን ስርጭትና ጉዳት ከመከላከልና ከመቀንስ አስተዋጾአቸው ባሻገር በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራንም ፈጥረዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች ከሁሉ በላይ እንቅስቃሴ ላይ መሰረቱን ያደረገውን የዓለም ኢኮኖሚ በእጅጉ አናግተውታል።ወረርሽኙ በኢኮኖሚ መስክ በርካታ ዘርፎች ላይ ያስከተለው ሁለንተናዊ ጉዳት እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ ለዕለት ተዕለት ኑሮ ወሳኝ የደም ስር የሆኑትን የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦትና ግብይት ስርአትን በእጅጉ አስተጓጉሎታል።
በአሁን ወቅትም የኮቪድ 19 ቀውስ መደበኛ እንቅስቃሴን በመገደብ ሰዎች እንደወትሮው ምግብ በቀላሉ ማግኘት ብሎም ገበያ ወይንም ሱፐር ማርኬት ሄደው መግዛት እንዳይችሉ፣ ብዙ ምግብ እንዲገዙና እንዲያከማቹ አድርጓል።በአይነትም ሆነ በመጠን መጥኖ መግዛት በማስቀረቱም ከፍተኛ የምግብ ብክነትን እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
በምግብ አቅርቦት ምህዋር ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ በርካታ ሰራተኞች በስጋት ምክንያት ራሳቸውን ከስራ እንዲያገሉ፣የሎጅስቲክ እንቅስቃሴም በእጅጉ እንዲስተጓጉልና በመልካም ተክለ ቁመና ላይ የሚገኙ የምግብ ምርቶች ሰብስቦ ከቅርጫት የሚያስገባቸው ብሎም ገበያ የሚያደርሳቸው እንዲያጡም አስገድዳል።
የወረርሽኙ ቀውሱ ከሁሉም በላይ ከምርት ዝግጅት እስከ ስብሰባ የሰው ኃይል እጥረትን በመፍጠር የምግብ ምርቶች ሰብሳቢ አጥተው እንዲበሰብሱ፣አርሶ አደሮች ስራ ፈትተው እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ፣ የምግብ ዋጋ በእጅጉ እንዲንር ምክንያት ሆኗል።በተለይ ወረርሽኙን በመስጋት በርካታ አገራት ድንበራቸው ዝግ ማድረጋቸውና የአውሮፕላን በረራዎች ማቋረጣቸው የምግብ ምርት አቅርቦት ንግዱን ብቻ ሳይሆን ረጂ ተቋማት ሳይቀር አስፈላጊውን ድጋፍ ተደራሽ እንዳያደርጉ ትልቅ አንቅፋትን ፈጥሯል።
ይሕ አይነቱ ክስተትም የአለም የምግብ አቅርቦትና ገበያን በእጅጉ ያቃወሰው ሲሆን በተለይ እለት ከዕለት እየስሩ ለሚመገቡና በድህነት ውስጥ ለሚኖሩ አገራት ዜጎች ያልተጠበቀ አስደንጋጭ ዱብ እዳና ተጨማሪ ራስ ምታትን ፈጥሯል።
ይሕን ዋቢ የሚያደርጉ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና ምሁራንም‹‹የኮረና ቫይረስ ፈጣንና አንደኛ በሆነ ጥፋቱ ዛሬ ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህሙማንና ሟቾችን እያስመለከተን ይገኛል፣በሁለተኛው ክፋቱ ደግሞ ነገ በተለይ በደሃ አገር ለሚኖሩ በርካታ ዜጎች ረሃብ ብሎም ህይወት መጥፋት ምክንያት ይሆናል››ብለዋል።
ቀውሱ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ በገፍ ለምታስገባው አፍሪካ መጪውን ጊዜ የሰቆቃ ሊያደርግባትና በተለይ የምግብ አቅርቦትና ዋስትና ላይ የሚያሳርፈው ጉዳት ከሁሉ የከፋ ረሃብን ሊከስት እንደሚቸል ተገምቷል።
ወረርሽኙ ከመከሰቱም በፊት ቢሆን አንዳንድ አገራት በድርቅና በበረሃ እንዲሁም በአንበጣ ወረራ ምክንያት የምግብ እጥረት ገጥሟቸው እንደነበር የሚያስታውሱት በጉዳዩ ላይ ሙያዊ አስተያየቶችን የሚያጋሩ ባለሙያዎች፣የወረርሽኙ ተጽዕኖ ቀድሞውንም ህይወታቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑ በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ተመስርተው የሚኖሩ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አሰቃቂ እንደሚሆንም አፅእኖት ሰጥተውታል።
በዚህም ምክንያት ‹‹በደሃ አገራት በተለይም በአፍሪካ ምድር አለም አቀፍ እርዳታን የሚማፀኑ አንደበቶችና ለመቀበል የሚዘረጉ እጆች ቁጥር በእጅጉ ይጨምራል››የተባለ ሲሆን፣የኮሮና ቀውስ የምግብ አቅርቦትና ሌሎችም ድጋፎችን በከተማም ሆነ በገጠር ለማዳረስ የሚያስፈልገውን በጀት በእጅጉ እንደሚያሻቅበው ተመላክቷል።
የዓለም ምግብ ድርጅትም ከቀናት በፊት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአለም አቀፍ ደረጃ የአስቸኳይ ምግብ ፈላጊዎች ቁጥርን ከፍ እንዲል ማድረጉን አሳውቃል።ድርጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር የዓለም አገራት ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል››ሲልም ማሳወቁንም የቢቢሲ ዘገባ አስነብባል።
በረሃቡ ይጠቃሉ ተብለው ከተቀመጡ መካከል አስሩ በግጭት፣ በኢኮኖሚ ቀውስና በአየር ጠባይ ለውጥ የተጎዱ መሆናቸውን ያመላከተው የድርጅቱ ሪፖርት፤ የመን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዝዌላ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ ናይጄሪያ እና ሄይቲ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ የተደቀነባቸው አገራት መሆናቸውን አሳውቃል።ከአገራቱ መካከልም የመን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዙዌላ እና ኢትዮጵያ ረሃቡ እንደሚከፋባቸው ታውቋል።
የድርጅቱ መረጃ እንደሚያመላክተው፣ እኤአ 2019 በመላው ዓለም አስቸኳይ የምግብ እርዳት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 135 ሚሊየን ነበር።ከእነዚህ መካከል 77 ሚሊየኑ የግጭት ሰለባ፣ 34 ሚሊየኑ በአየር ንብረት ለውጥ የተጎዱ፣ 24 ሚሊየን ደግሞ በአገራቸው የተከሰተ የኢኮኖሚ ቀውስ ሰለባዎች ናቸው።
በዚህ ዓመት በኮረና በቫይረሱ ስርጭት ምክንያት ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ ከመደረጉ ጋር ተደራርቦ የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸውና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በእጥፍ በመጨመሩ 265 ሚሊዮን እንደሚደርስ ያስታወቀው የድርጅቱ ሪፖርት፣በቫይረስ ቀውስ በሚፈጠር ረሃብ ይበልጡን የሚቀጡት ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉና በስደተኛ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ፣አረጋውያን፣ ህፃናት፣ነፍሰጡሮች፣ እንዲሁም አካል ጉዳተኞች መሆናቸውን አሳውቋል።
የአለም ምግብ ፕሮግራም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት አርፊ ሁሴንም፣በተለይ የመን፣ በአፍጋኒስታን፣ኮንጎ፣ ቡርኪና ፋሶ እንዲሁም ደቡብ ሱዳን በቀውሱ ምክንያት የረሃብ ቸነፈር እንደሚፀናባቸውና የአገራቱ ዜጎችም በህይወት ለመቆየት ሙሉ በሙሉ በአለም አቀፍ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አፅእኖት ሰጥተውታል።
በአሁን ወቅት 30 ሚሊየን ሕዝብ አስቸካይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ያስገነዘቡት ስመጥሩ ኢኮኖሚስት‹‹አስፈላጊውን አስቸካይ የምግብ ድጋፍ በማድረግ እነዚህን ዜጎች መታደግ ካልተቻለም ለቀጣዮቹ ሶስት ወራት በየቀኑ ሶስት መቶ ሺ ሰው በረሃብ ምክንያት መቅበራችን አይቀርም››ብለዋል።
ኮሮና ቫይረስን ለመግታት በተጣሉ የመዘዋወር ገደቦች ምክንያት፣ሌላው ቀርቶ በትምህርት ቤት ውስጥ ምግብ ያገኙ የነበሩ ተማሪዎች ትምህርት በመዘጋቱ እንዲራቡ ማድረጉ አይቀሬ ነው››የሚሉት ምሁራኑ፣ ምናልባትም በኢኮኖሚው ላደጉት አገራት ተማሪዎቹን በየቤታቸው መመገብ አስቸጋሪ ባይሆንም በደሃ አገሮች ግን እጅጉን ከባድ ስለመሆኑ አስምረውበታል።
በአለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የምግብ ቀውስ፣ የዋጋ ንረትና ረሀብ በቀላሉ የሚታዩ ቀውሶች እንዳልሆኑና አፋጣኝ እልባት ካልተሰጣቸው አገርን ማናጋት አቅም እንዳለቸው አፅእኖት የሚሰጡ ምሁራን ቁጥርም በጣም ከፍተኛ ነው።
ስመጥር የዘጋርዲያን ፀሐፊ ፊዮና ሃርቬይ፣ለዚህ እሳቤ ብዙም መድከም ሳያስፈልግ እኤአ 2007-08 የተከሰተው የምግብ ዋጋ ንረት በአንዳንድ አገራት ከኢኮኖሚም በላይ ፖለቲካዊ ቀውስ ስለመፍጠሩ መለስ ብሎ ማስታወስ በቂ ስለመሆኑ ጠቁማለች።
ይሕን እሳቤ የሚጋሩ ሌሎች ጸሐፍቶችም በኮሮና ቀውስ የሚከሰት ረሃብ በአፍሪካ ምድር የፖለቲካ ምስቅልቅል በመፍጠር በርካቶች ለተቃውሞ አደባባይ እንዲወጡ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም፣ ‹‹ይሕም ዜጎችን ከረሃብ ለመታደግ አስፈላጊውን የምግብ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ሳይቀር ሊያደናቅፈው ይችላል›› ብለዋል።
የአለም ምግብ ድርጅትም ሆነ ሌሎች የተራድኦ ተቋማትም ሚሊየኖችን ከረሃብ ለመታደግና ከሁሉም በላይ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ተደራሽ ለመሆን በተለያዩ አገራት ነፍጥ አንግበው የሚታኮሱት አካላት ከቻሉ ይቅር እንዲባባሉ ካልቻሉም ለጊዜውም ቢሆን መታኮስ እንዲያቆሙ ተማፅነዋል።
በአፍሪካ ምድር ከኮሮና ጎን ለጎን የበረሃ አንበጣ ያስከተለው የምግብ ዋስትና አደጋም አፋጣኝ እልባት የሚፈልግ ሌላው ራስ ምታት መሆኑ ተመላክታል።በየቀኑ የራሱን ክብደት ያሕል የሚመገበው የአንበጣ መንጋ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ የወቅቱ የአየር ጠባይ በፈጠረለት ምቹ አጋጣሚ ግዛቱን እያስፋፋ 25 ዓመታት ታይቶ በማያውቅ መልኩ ከፍተኛ ውድመት እያስከተለ መሆኑም ታውቃል።
በአሁን ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለብቻ የሚደረግ ግብግብ ብዙ ርቀት መጋዝ እንዳማያስችል ይልቁንስ የተባበረ ክንድ ቀውሱን ለመደቆስ ግንባር ቀደም አማራጭ ስለመሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ይሕ እስካልሆነ ድረስ የአንበጣ መንጋው በሚያስደነግጥ ፍጥነት ወደ ተለያዩ አገራት በቀላሉ እንደሚሠራጭ ተገልጿል።
ከችግሩ ይልቅ መፍትሄው ላይ ማተኮር ምርጫቸው ያደረጉት በአንፃሩ፣የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ሆነ ሚሊየኖችን ከረሃብ ለመታደግ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሰብዓዊና የደግነት ተግባሮችን ብሎም ድጋፎችን ማስተባበርና መጠናከር ግድ እንደሚል አፅእኖት ሰጥተውታል።
የአለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ የኮሮና ቀውስ የምግብ አቅርቦትና ሌሎችም ድጋፎችን በከተማም ሆነ በገጠር ለማዳረስ የሚያስፈልገውን በጀት በእጅጉ እንዳሻቀበው የረሃብ አደጋ ለተጋረጠባቸውን በሚሊየን ለሚቆጠሩ ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረስ ከ10 እስከ 12 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልገው አሳውቋል። ‹‹ይሕ የገንዘብ እርዳታው ፈጥኖ ካልደረሰው መጪው ጊዜ አሰቃቂ እንደሚሆን እወቁት›› ብሏል።
አንዳንዶች በአንፃሩ‹‹በአሁን ወቅት በርካቶቹ ምእራባውያን አገራት በቫይረሱ ወረርሽኝ ክፉኛ በመጎዳታቸው አስፈላጊ የሚባለውን ድጋፍ በቀላሉ ሊለግሱ አይችሉም፣ድጋፍ ካደረጉም መጠኑ በሚፈለገው ልክ አይሆንም››ብለዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ዴቪድ ቤስሊም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አስከፊ ቀውስ ከማስተናገድ ቀድሞ መተባበርና መደጋገፍ ቢቻል ነገን ማሳመር እንደሚቻልና ለዚህ ሌላ ምንም አይነት አማራጭ አለመኖሩን አስገንዝበዋል።በኮቪድ 19 ቀውስ በጣም በቅርብ ወራት ተደራራቢ ድርቅ አስከፊ በሆነ መልኩ ሊገጥመን ይችላል፣ይሕን ለማስወገድም በአግባቡና በፍጥነት ልንሰራ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ለመፍትሔው ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል››ብለዋል።
አለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበርም፣‹‹ይሕ ቀውስ አስደሳች በሆነ መልኩም ባይሆን ሁላችንንም አስተሳስሮናል፣ በዚህ ወቅት ለአለም ጤና አንዳችን ለአንዳችን ደህንነት ዋስትና መሆን ግድ ይለናል፣ በተለይም የረሃብን ጉዳት ለመከላከል ሁላችንም በጋራ ልንቆም ይገባል››ብሏል።
በጋራ ከመቆምና ከመተባባር ባለፈ በባለሙያዎቹ ዘንድ የወቅቱን ፈተና ለመሻገር መደረግ ስለሚኖርባቸው አበይት ተግባራት ተጠቁመዋል። ከምክረ ሃሳቦቹ መካከልም በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በርካቶች በረሃብ እንዳያልቁ መንግስታት፣ፈጣን ግብረ መልስ መስጠት የሚያስችል አቅም፣አማራጭና ብሄራዊ ፕሮግራም በመፍጠር በተለይ በተለያዩ ቦታዎች የምግብ ባንኮቸን በማዘጋጀት ዜጎቻቸውን ተደራሽ ማድረግ፣የምግብ አቅርቦትን ለማስፋትና የገቢ ምንጭ ለመፍጠር የከተማ ግብርና ይበልጥ መተግበር፣በግብርና ዘርፉ ለተሰማሩም ተገቢውን ማበረታቻና ጥበቃ መስጠት እንዲሁም በወጪና ገቢ ምርቶች ላይ ታክስን ጨምሮ የተለያዩ ገደብና ክልከላና ማስወገድ እንዳለባቸው የሚያስገነዝቡት ጎልተው ተብራርተዋል።
‹‹የምግብ ምርትና አቅርቦት ኡደቱ እንዳይደናቀፍ በዘርፍ ውስጥ የተሰማራ የሰው ሃይልና ሌሎች ባለድርሻዎች ራሳቸውን ከቫይረሱ ጠብቀው በስራ ላይ እንዲቆይ የሚያስችል የተለያዩ አቅጣጫዎቸን ማስቀመጥ ድጋፎችን ማድረግ ይገባልም››ተብሏል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2012
ታምራት ተስፋዬ