መቼም የጥምቀት በዓል ሲነሳ ከሃይማኖታዊ ሥነሥርዓቱ ባለፈ አብዛኞቻችን የምናነሳቸው ብዙ ትዝታዎች እንደሚኖሩን እምነቴ የጠነከረ ነው፡፡ ለዛሬ ላነሳ የወደድኩት ግን የጥምቀት በዓል ትዝታዎችን ሳይሆን የጥምቀት በዓልን ተከትሎ አዲስ አበባችን ከለመደችው በላይ መጽዳቷንና ማሸብረቋን በተመለከተ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የጥምቀት በዓል የጎዳና ላይ እና በአደባባይ/አውድ የሚከበር በመሆኑ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ሰፊ ቁጥር ያለው ሕዝብ በዓሉን ይታደማል፡፡ የጥምቀት በዓል ምንም እንኳን ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ቢሆንም የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ይሁን ወይም ምንም አይነት ሃይማኖት የማይከተል ሰውም ቢሆን በዓሉን ሊታደም ከፈለገ ሁኔታዎች ምቹ ናቸውና መታደም ይችላል፡፡ በመሆኑም ሰፊ ቁጥር ያለው ህዝብ በተለያዩ አልባሳት አሸብርቆ ደምቆ ወደ አደባባይ ይወጣል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጥምቀት በዓልን ተከትሎ ከተማችን አዲስ አበባ ጽዱና ንጹህ በመሆን ደምቃና አሸብርቃ ትታያለች፡፡ ጽዳቱ የሚጀመረው ከበዓሉ ቀደም ባለው ባሉት ቀናት ነው፡፡ ምዕመናኑ ታቦታቱን ከማደሪያቸው አንስተው በሃይማኖታዊ ዝማሬና ሽብሻቦ፤ እንዲሁም በተለያዩ ባህላዊ ጭፈራዎች በማጀብ ወደ ማደሪያቸው ከተራ ቦታ ያደርሷቸዋል፡፡ በሁሉም አካባቢ ታቦታቱ ከቤተ መቅደስ መንበራቸው ወጥተው እስከ ማደሪያቸው (የከተራ ቦታ) እስከኪደርሱ ያለው መንገድ ንጹህና ጽዱ ከመሆኑም በላይ በቀይ ምንጣፍ የተዋበ ነው፡፡
ይህ ሁሉ የሚሆነው በወጣቱ በጎ ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት ነው፡፡ ወጣቱ በየአካባቢው ያለውን ጉራንጉርና አስፓልቱንም ጭምር አጽድቶ ጥምቀትን በንጹህና በጽዱ ድባብ ለማክበር የሚያደርገው ጥረት በእጅጉ ያኮራል፡፡ በተለይም ታቦታቱ የሚልፉበትንና የሚያርፉበትን ቦታ በምላስ የተላሰ ያህል በማጽዳት በቀይ ምንጣፍ ያሸበርቀዋል፡፡ በቀዩ ምንጣፍ ላይም እርጥብ ቄጤማ በመጎዝጎዝ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ቀይ ምንጣፉን በየተራ እየጠቀለሉ በመቀባበል ታቦታቱን ለተሸከሙት ቀሳውስትና ለሚያጅቡት ምዕመናን መረገጫ ያነጥፋሉ፡፡
በዚህ ወቅት ታዲያ ለወትሮው አፍንጫችንን የሚሰነፍጠው የቆሻሻ ክምር ተወግዶ በምትኩ በቄጤማው፣ በአሪቲውና በሽቶው መልካም መዓዛ አዲስ አበባ ታውዳለች እንደስሟ አዲስ ትሆናለች፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ አይነቷን ጽዱና ንጹህ አዲስ አበባ ማየት ቢያስደስትም፤ በአንጻሩ ደግሞ ምነው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚል ቁጭት ይፈጥራል፡፡
ታዲያ፤ ቁጭቱ የሁላችንም ቁጭት ሆኖ ይህን መልካም ተግባር በማዝለቅ ልክ እንደበዓሉ ጽዳታችንም መለያችን ቢሆን ያሰኛል፡፡ ካለዚያ ግን እንደተረቱ ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› ብለን ወቅት ጠብቀን ብንደምቅ፤ ብናሸበርቅ፤ ዋው! ብናስብልም ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ…›› ነውና ጽዳታችን መለያችን ሊሆን አይችልም፡፡
ወጣቱ ምንም እንኳን ወቅትን ጠብቆ ብቻ በከተማዋ ጽዳት ላይ ተሳታፊ ቢሆንም ተግባሩ ያስመሰግነዋል እንጂ አያስወቅሰውም፡፡ ምክንያቱም ይህም የተገኘው ከእርሱ ነውና ይበል ልንለው ይገባል፡፡ በርግጥም ወጣትነት ትኩስነት ነውና የትኛውንም ነገር በሞቀ ኃይል በሙሉ ወኔ የመስራት፤ አዳዲስ ነገሮችን የመሞከር ፍላጎት አለው፡፡ ታዲያ ይህን እምቅ ኃይል አሟጥጦ ቢጠቀም እንኳን አዲስ አበባን ማጽዳት ይቅርና ሌላም ተዓምር መስራት ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን፤ ወጣቱ በቀን በቀን እየወጣ አስፓልት ያጽዳ ማለት ሳይሆን ሁሉም ወጣት በሳምንታት ወይም በወራት ጊዜ ውስጥ ቋሚ ቀን ቆርጦ አካባቢውን ቢያጸዳና በዙሪያው ያሉ ነገሮችን እያስተዋለ አቅምና ወኔውን ለመልካምና ለበጎ ሥራ ቢያውለው ሀገራችን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚ እንደምትሆን ዕሙን ነው፡፡
ይሁን እንጂ፤ አብዛኛው የሀገራችን ወጣት ነገሮችን በጊዜያዊ ስሜት እንጂ በስሌት ሲተገብር አናይም፡፡ በስሜት የሚከወን ተግባር ደግሞ ዘለቄታ የሌለው ነውና ለነገ የሚቀር መልካም ውጤት አይኖረውም፡፡ ነገር ግን፤ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን አሁን ወጣቱ እያደረገ ያለው መልካምና በእጅጉ ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡
አንዳንዴ ደግሞ፤ ከእገሌ ሰፈር የእገሌ ሰፈር ይበልጣል በሚል መንፈሳዊ ቅናት አካባቢውን ለማጽዳት በሚደረገው የእርስ በርስ ፉክክር አካባቢው ከለመደው በላይ ሲጸዳ እናያለን፡፡ እንዳልኳቸሁ የወጣቱ በራስ ተነሳሽነት ከተማዋን ንጹህና ጽዱ በማድረግ በዓሉን እጅግ የደመቀና ያማረ ማድረጉ ምንም ክፋት የሌለው ቅዱስ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ተግባር ቀጣይነት ኖሮት ሁሉም አካባቢውን በዘለቄታ ቢያጸዳ ንጹህ ከተማ በመፍጠር አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሃይማኖቱ ተከታይ የሆነው ወጣት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል፡፡ በመጨረሻም በንጹህና ጽዱ አዲስ አበባችን መልካም የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ተመኘሁ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 8/2011
ፍሬህይወት አወቀ