ክፍል አንድ
በሕግ የተፈቀዱ ድርጊቶች
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
በመርህ ደረጃ አንድ ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት ላደረገው ወንጀል አላፊ ነው – ይከሰስበታል ይቀጣ በታል።
ያም ሆኖ ግን ምንም እንኳን የፈጸመው ድርጊት በሕግ የሚያስቀጣ ቢሆንም ሕጉ ራሱ ባስቀመጣቸው ምክንያቶች ከመከሰስና ከመቀጣት ነጻ ሊሆን ይችላል። እነዚህም በሕግ የተፈቀዱ አድራጎቶች፤ የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ ሁኔታዎች ናቸው።
እነዚህ ሁኔታዎች አንድም በወንጀል ከመከሰስና ከመቀጣት ነጻ የሚያስደርጉ ናቸው።በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ ወንጀል ፈጽሟል በሚል የተከሰሰ ሰው እነዚህን ምክንያቶች በማንሳት ክርክሩን የሚያቀርብባቸው መከላከያዎች ናቸው።
እነዚህ ምክንያቶች እንደየአገራቱ የሕግ ሥርዓት የተለያየ እንድምታ አላቸው።ተቀባይነታቸውም እንዲሁ ይለያያል። ፈረንሳይን የመሰሉ አገራት እነዚህን ሁኔታዎች የማያስቀጡ (Justifications) እና ይቅርታ የሚያሰጡ (Excuses) ምክንያቶች በማለት ለሁለት ከፍለው በወንጀል ሕጋቸው ውስጥ ደንግገዋቸው እናነባለን።
በዚሁ መሰረት በሕግ የተፈቀዱ ድርጊቶች፣ ሕጋዊ መከላከል፣ አስገዳጅ ሁኔታ እና የተበዳዩ ፈቃደኝነት የሚሉት ምክንያቶች የማያስቀጡ ሁኔታዎች ተብለው ተመድበዋል።በሌላ በኩል ይቅርታ በሚያሰጡ ምክንያቶች ዘውግ ስር ቅጣትን የሚያቀልሉ ጠቅላላና ልዩ ሁኔታዎች ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ማንም ሰው የሚያስቀጣ ወንጀል ፈጽሞ እያለ ነገር ግን ከተጠያቂነት የሚድንባቸውን እነዚህን ምክንያቶች በአንድ በኩል በሕግ የተፈቀዱ አድራጎቶች በማለት ዘርዝሯቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የማያስቀጡ ድርጊቶችንና ይቅርታ የሚያሰጡ ሁኔታዎችን በአንድ ቋት ውስጥ በማድረግ ዝርዝራቸውን አስቀምጧል።
የወንጀል ሕጉ ለሶስቱም ምክንያቶች ትርጓሜ አላስቀመጠላቸውም።ያም ሆኖ በተለያዩ ጸሐፍት ከተሰናዱ ስንክሳሮች ትንታኔ በመነሳት ትርጓሜቸውን ማስቀመጥ ይቻላል።በዚሁ መሰረት በሕግ የተፈቀዱ ድርጊቶች የሚባሉት አድራጊያቸው ሰው ለማድረግ በሕግ ፈቃድ የተሰጠው ሲሆን ነው።
በእነዚህ ድርጊቶች ሕጉ ለማድረግ ፈቃድ ከመስጠት አልፎ በአንዳንድ ሁኔታዎች ከሕግ ተጻራሪ በሆነ መልኩ እንዲፈጽሙም ግዳጅ ሊያስቀምጥ ይችላል።ለምሳሌ ሰውን መግድል የሚያስቀጣ ቢሆንም በግዳጅ ላይ ያለ ወታደር ግን ጠላትን መትቶ እንዲጥል ይገደዳል። ይህ ድርጊቱ ታዲያ በሕግ የተፈቀደ በመሆኑ በወንጀል አያስጠይቅም።
በሕግ ከተፈቀዱ አድራጎቶች በተጨማሪ አንድ ሰው ወንጀል ፈጽሞ እያለ ከመከሰስና ከመቀጣት ነጻ የሚሆንባቸው ምክንያቶች (ቢከሰስ መከራከሪያዎቹ) የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ ሁኔታዎች ናቸው።
ሕጋችን እነዚህን ሁለት ሁኔታዎች እንደ ተመሳሳይ ምክንያት በመቁጠር “እና” በሚለው አያያዥ በመጠቀም በአንድ ቋት ውስጥ ነው ያካተታቸው።
ያም ሆኖ የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ ሁኔታዎች ምንም እንኳን በሕጉ እንደ አንድ ምክንያት ተወስደው የተቀመጡ ቢሆንም በጽንሰ-ሐሳብ ደረጃ የተለያዩ ናቸው።
የማያስቀጡ አድራጎቶች የሚባሉት በባህሪያቸው ወንጀል ቢሆኑም ቅሉ፤ አድራጊዎቹ ግን በሕሊናቸው ወንጀል የማድረግ አሳብ ቋጥረው ሆነ ብለው ያደረጓቸው አይደሉም።
ይልቁንም የተፈጥሮ ወይም ሰው-ሰራሽ አደጋ በራሳቸው ወይም በሌላ ሰው ላይ በመጋረጡ ምክንያት
ያንን ለመከላከልና ለማስቀረት ሲሉ የሚያደረጓቸው ተገቢነት ያላቸው ድርጊቶች (Justifiable Acts) ናቸው።አስገዳጅ ሁኔታና ሕጋዊ መከላከል በዚህ ሥር ይመደባሉ።
በሌላ በኩል ይቅርታ የሚያሰጡ ሁኔታዎች (Ex¬cusable Acts) የሚባሉት ደግሞ በመከላከያነት የሚያነሷቸው ሰዎች ከሌሎች ወንጀል አድራጊዎች ጋር በመሆን በወንጀሉ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው ሆነው ነገር ግን በዕድሜያቸው፣ በጾታቸው ወይም በአዕምሯቸው ደካማነት ፍጹም ተገደው ወንጀል አድርገው ከተገኙ አልያም ትዕዛዝ ተቀባይ ሆነው በመገደድ ወንጀል ሰርተው ቢገኙ የሚያነሷቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡
በዚህ ጽሁፍ በሕግ የተፈቀዱ ድርጊቶችን በዝርዝር ለመዳሰስ የምንሞክር ሲሆን፤ የማያስቀጡና ይቅርታ የሚያሰጡ ሁኔታዎችን ደግሞ በቀጣይ ጽሁፋችን እናስቃኛችኋለን።
የሕዝብና የመንግስት አገልግሎት
የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 68 እና 69 በሕግ የተፈቀዱ የሚባሉትን ዘርዝረዋል።የመጀመሪያው በሕዝብ አገልግሎት ሥራ ወይም በመንግስት ወይም በወታደር ሥራ አፈጻጸም የተከናወኑ አድራጎቶችን ይመለከታል።
ሕጉ “የሕዝብ አገልግሎት ሥራ” ምንድን ነው በሚል የተገለጸው ምንን ለማመልከት እንደሆነ ባለማሳየቱ ግልጽነት ይጎድለዋል።በዚህ መነሻ የትኞቹ አድራጎቶች ናቸው የሕዝብ አገልግሎት ሥራ የሚሆኑት የሚለውን በቀላሉ ለመመለስ አስቸጋሪ ይሆናል።
ያም ሆኖ በድንጋጌው ውስጥ “የመንግስት ሥራ” በሚል ከተገለጸው ጋር በማነጻጸር ስንመለከተው የሕዝብ አገልግሎት ሥራ የሚለው ከመንግስት ሥራ ውጭ የሚገኝ የትኛውም ሰው ወንጀል ቢያደርግ ሊያነሳው የሚችለው መከራከሪያ መሆኑን መረዳት እንችላለን።
ለምሳሌ አንድ ሰው እጅ ከፍንጅ ወንጀል የፈጸመን ሰው አስሯል ወይም ፖሊስ በሚያስርበት ጊዜ በማሰር ሂደቱ ላይ ትብብር አድርጓል እንበል።ይህ ሰው ታዲያ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 585 መሰረት ሰውን ይዞ በማስቀመጥ ወንጀል ቢከሰስ ለሕዝብ ሰላምና ደህንነት ሲል በፈጸመው በዚህ ድርጊቱ ሊከሰስና ሊቀጣ አይገባውም ማለት ነው።
ይሁንና ይህ መከራከሪያ የራሱ የሆነ ገደብ አለው።በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሰረት ማንኛውም ሰው ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ የእጅ ከፍንጅ ወንጀል የተፈጸመ እንደሆነ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወንጀል ሰሪውን ለመያዝ ይችላል።
እናም ከዚህ የምንረዳው የእጅ ከፍንጅ ወንጀል የፈጸመን ሰው ያሰረ ሰው ሁሉ ሰውን በመያዝ ወንጀል ቢከሰስ ከተጠያቂነት ይድናል ማለት እንዳልሆነ ነው።ይልቁንም ኮሶስት ወር በታች በሆነ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል የፈጸመን ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያሰረ ሰው ይህንን መከላከያ ሊያቀርብ አይቻለውም።
ከሶስት ወር በታችና በላይ በሆነ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል በሚል ሕጉ ገደብ ያስቀመጠበት ምክንያት ከሶስት ወር በላይ እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች ጉዳታቸው ከፍተኛ በመሆኑና ወንጀል ሰሪዎቹም በአንጻራዊነት በቁጥጥር ስር ሳይውሉ ቢያመልጡ ለሕዝብ ደህንነት ሥጋት ስለሚሆኑ ማንም ሰው እንዲይዛቸው ፈቃድ መስጠቱ ተገቢ መሆኑን ከግምት በማስገባት ነው።
ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ከሶስት ወር የማያንስ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ወንጀልን እጅ ከፍንጅ ሲፈጽም ያየውን ወንጀል ሰሪ በሚይዝበት ወቅት ያ ወንጀል ሰሪ አልያዝም ብሎት በኃይል ባልተከላከለበት ወይም ለማምለጥ ባልሞከረበት ሁኔታ የኃይል ርምጃ ቢወሰድበት በዚህ ድርጊቱ ቢከሰስ መቀጣቱ አይቀሬ ነው።
የሕዝብ አገልግሎት ሥራ ከሚባለው በተጨማሪ የመንግስት ወይም የወታደር ሥራ አድራጎቶችም በሕግ የተፈቀዱ በመሆናቸው ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ለመሆን ያግዛሉ።
የመንግስት ወይም የወታደር ሥራ አድራጎቶች የሚባሉት በመንግስት ሰራተኞች ወይም በወታደሮች የተፈጸሙ በመሆናቸው ለመረዳት ግልጽ ናቸው።
በዚሁ መሰረት ፖሊስ ቢያስር ቢበረብር፤ ዓቃቤ ሕግ ቢከስስ ቢከራከር፤ ዳኛ ፈርዶ ወደ ማረሚያ ቤት ቢልክ፤ የማረሚያ ቤት ፖሊስ በሞት ፍርደኛ ላይ የተሰጠ ውሳኔን ቢፈጽም፤ ወታደር በጦር ሜዳ ጠላት መትቶ ቢጥል መከሰስ መቀጣት አይገባቸውም።ይሁንና ድርጊታቸው በሕግ ከተፈቀደው ውጭ ከሆነ ግን እንደሚጠየቁ ልብ ይሏል።
የማረም ወይም ዲሲፕሊን የመውሰድ ኃላፊነት
በሕግ የተፈቀደ ሁለተኛው አድራጎት የማረም ወይም ዲሲፕሊን የመውሰድ ኃላፊነትን በመወጣት ሂደት የተሰሩ ተግባራትን ይመለከታል። እናም ድርጊቶቹ ምንም እንኳን የሚያስቀጡ ቢሆኑም ሊያስከስሱና ሊያስቀጡ አይገባም፡፡
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ቀድመው የሚጠቀሱት ወላጆች፣ አሳዳጊዎች፣ የልጆች ባለአደራ ጠባቂዎች ወይም መምህራን ናቸው።እነዚህ አካላት ልጆችን በማረም፣ በማነጽ፣ በበጎ አስተሳሰብ በመቅረጽ፣ በመንከባከብና በማስተማር ለፍሬ የማብቃት ኃላፊነት አለባቸው።
ይህን ባለማድረጋቸው ታዲያ ልጆች በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢያደርሱ ከውል ውጭ የሆነ ሀላፊነት ይመጣባቸዋል፤ ይከሰሳሉ ካሳ ይከፍላሉ።ምክንያቱም ግብረ-ገብነትን በልጆቹ አዕምሮ ውስጥ አለመቅ ረጻቸውን ስለሚያንጸባርቅ ለሚያደርሱት ጉዳት አላፊ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው፡፡
እንዲህ ከሆነ ልጆችን ማረም ግዴታቸው ነው ማለት ነው።ማረም ሲባል ደግሞ የሕጻናቱን
የአካል ደህንነት የሚጋፋ እንደሚሆን እሙን ነው። ከፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2039/ሐ ገጸ-ንባብ በግልጽም ባይሆን በገደምዳሜው እንደምንረዳው ወላጆች፣ አሳዳጊዎች፣ የልጆች ባለአደራ ጠባቂዎች ወይም መምህራን ልጆችን በሰውነታቸው ላይ ተገቢ የሆነ አቀጣጥ ፈጽመው የማረም መብት አላቸው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የወንጀል ሕጉ ለአካለ መጠን ያላደረሱ ልጆችን መምታት በእስራት እንደሚያስቀጣ የደነገገ ቢሆንም፤ ወላጆችና የተጠቀሱት ሌሎች ሰዎች ለልጆች መልካም አስተዳደግ የሚወስዱትና ሕግን የማይቃረን የዲሲፕሊን ርምጃ እንደማያስቀጣ በግልጽ አስቀምጧል።
በመሆኑም በእነዚህ ሰዎች የሚወሰደው የማረም ወይም የዲሲፕሊን ርምጃ ምንም እንኳን ድርጊቱ ወንጀል ቢሆንም በሕግ የተፈቀደ ድርጊት ስለሆነ የሚያስከስስም የሚያስቀጣም አይደለም።
የግል መብትን ሥራ ላይ ማዋል
በሕግ የተፈቀደ ሶስተኛው ምክንያት የግል መብትን ሥራ ላይ ለማዋል የተፈጸሙ ድርጊቶች ናቸው። እነዚህም ከሕግ ወሰን እስካላለፉ ድረስ ወንጀል ቢሆኑም አያስቀጡም።
ከፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1148 እንደምንገነዘበው የንብረት ባለይዞታ የሆነ ሰው ይዞታውን ለመንጠቅ ወይም ሁከት ለማንሳት የሚደረግ ማንኛውንም ኃይል በመከላከል መመለስ ይችላል።የተወሰደበትን፣ ተወስዶ የተደበቀበትን ወይም ሲወሰድበት የደረሰበትን ንብረትም በጉልበት የማስመለስ መብት አለው።
በሕጉ ቁጥር 2076/2 መሰረት ደግሞ አንድ እንስሳ ከእሱ ዋጋ በላይ በሆነ ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ እያለ እንስሳውን የገደለው ሰው በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷልና በወንጀል ተከሶ መቀጣት አለበት አይባልም።
በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ታዲያ ጉዳት ቢደርስም እንኳ የንብረት መብቱን ያስከበረውን ሰው በወንጀል መቅጣት አይቻልም፤ ድርጊቱ በሕግ የተፈቀደ ነውና።
የሙያ ግዴታን መወጣት
በሕግ የተፈቀደ ሶስተኛው አድራጎት የሙያ ግዴታን ለመወጣት የተፈጸመ ድርጊት ነው።እነዚህ ድርጊቶች ከሙያው ደንብና አሰራር ውጭ እስካልሆኑና ከባድ የሙያ ጥፋት ካልተጸመ በቀር አያስቀጡም።
ለምሳሌ ቀዳጅ ሐኪም የታካሚውን አካል ቀዶ ቢሰፋ፤ ጠበቃ ስለደንበኛው ሆኖ ዝሙትን ምክንያት በማድረግ የፍቺ አቤቱታ ለፍርድ ቤት ቢያቀርብ፤ መካኒክ መኪና ለመስራት አካሏን በሙሉ ፈታትቶ ቢበታትነው አይጠየቅበትም።
አንድ ሰው በወንጀል ሲከሰስ የሙያ ግዴታን ለመወጣት የተፈጸመ ድርጊት ነው የሚል መከራከሪያ ለማቅረብ እንዲችል ሁለቱን መለኪያዎች በጣምራ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት።
የሙያ ደንብና አሰራር የሚባለው የተጻፈ የተደጎሰ ሊሆን ይችላል።አልያም በልማድ የዳበረና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ አሰራር ይሆናል።በሕሊና ሚዛን ላይም ሲቀመጥ ቅቡልነት ባለው አመክንዮ የተደገፈ እውነታም ይሆናል።ለምሳሌ ሐኪም በሕክምና መሳሪያ እንጂ በሽንኩርት ቢላዋ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አይችልም።
በሌላ በኩል የሙያ ግዴታን ለመወጣት የተፈጸመ ድርጊት ነው የሚለውን መከራከሪያ ለማቅረብ ከሙያ ደንብና አሰራር ውጭ አለመሆን እንደተጠበቀ ሆኖ ከባድ የሙያ ጥፋት ያልተፈጸመበት አድራጎት መሆኑንም ማስረዳት ያስፈልጋል።
ለማሳያነት ሐኪሙ ተገቢውን የሙያ ደንብና አሰራር ጠብቆ በብርቱ ጥንቃቄ ታካሚውን ቀዶ አክሞ ከሰፋው በኋላ መቅደጃ መሳሪያውን ወይም መርፌውን በሆዱ ውስጥ ረስቶት ታካሚው በዚሁ መነሻ ቢሞት ሐኪሙ በቸልተኝነት ሰውን በመግደል ወንጀል ከመጠየቅ አይድንም።
ይቀጥላል
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2012
በገብረክርስቶስ