‹‹ከትልቅ ወይም ከትንሽ ቢሆን መወለድ ሙያ አይደለም፤ ራስን ለታላቅ ታሪክ መውለድ ግን ሙያ ነው›› ይላል፤ በአራዳው ጊዮርጊስ አደባባይ በታላቅ ግርማ ሞገስ የቆመ ሐውልት ግርጌ የተቀመጠው ዘመን አይሽሬ ጥቅስ። ሐውልቱ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሲሆን፤ የከተማዋ ግርማ ሆኖ ዘመናትን አስቆጥሯል ።
የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐውልትን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥራቸው በርከት ያሉ ሐውልቶች በተለያዩ ዋና ዋና አደባባዮች ተተክለው ይገኛሉ። እነዚህ ሐውልቶች የአገሪቱን ብሎም የከተማዋን ታሪክ በማውሳት ረገድ ማስታወሻነታቸውና የድል ምልክትነታቸው ከፍ ያለ ነው።
በአራዳው ጊዮርጊስ አደባባይ የሚገኘው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ፈረስ ላይ ተቆናጠው የሚሳየው ይህ ሐውልት፤ የተሰራው በልጃቸው ንግስት ዘውዲቱ ጊዜ እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ይጠቅሳሉ። ንግስቲቱ ሐውልቱን ያሠሩት የአባታቸው የአፄ ምኒልክ ማስታወሻ እንዲሆን በማሰብ ነው። ሐውልቱ ሁለት ነገሮችን ያመላክታል፤
እነርሱም ፀረ ቅኝ ግዛት ትግል እና የስልጣኔ ራእይ ናቸው። ሐውልቱ የተሰራው ከመዳብ ነው፤ የተቀረጸው ደግሞ በጀርመናዊው አርክቴክት ሃርትል ስፒንግለር ሲሆን፣ የተቀረፀው ጀርመን አገር እንደሆነ ይነገራል።
ሐውልቱ ከጀርመን አገር ተሠርቶ ከመጣ በኋላ የሚቆምበት ቦታ በዝግጅት ላይ እያለ ንግሥት ዘውዲቱ በድንገት መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም. ማረፋቸውን ታሪክ ያወሳል። ነገር ግን የተጀመረውን ሥራ የንግሥቲቱን አልጋ የወረሱት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እንዲጠናቀቅ በማድረግ፤ በንግሥናቸው በዓል ዋዜማ ጥቅምት 22 ቀን 1923 ዓ.ም. በታላቅ ክብር በንጉሠ ነገሥቱ መገለጡም ይነገራል።
አፄ ምኒልክ፣ በሐውልቱ ላይ የሚታዩት ካባ ለብሰውና በእጃቸው ደግሞ ጣምራ ጦር ይዘው ነው። ይጋልቡበት በነበረው በፈረሳቸው በ ‹አባ ዳኘው› ላይ ተቀምጠው ሲሆን፤ የሐውልቱም ቁመት ከፍ ያለ ነው። ‹አባ ዳኘው› በመባል የሚታወቀው ይኸው ፈረስ የሚታየው ፊቱን ወደ ሰሜን አቅጣጫ መልሶ፣ በኋላ እግሮቹ ቆሞ እና የፊት እግሮቹን ወደላይ አንስቶ ነው ። ፊቱን ወደ ሰሜን አቅጣጫ የመመለሱ ጉዳይ ጦርነት የተካሄደባት ቦታ አድዋ መሆኑን ለማስታወስ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
የአድዋ ጦርነት በመጨረሻው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በወራሪው የጣሊያን መንግስትና በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር መሃከል የተካሄደ ጦርነት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አሸናፊነትም በድል
መጠናቀቁ የኢትዮጵያውያን ብሎም የአፍሪካውያን ኩራት ሆኖ ዛሬ ድረስ መዝለቁ እውን ነው።
ሐውልቱ፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በብዙ ዘርፍ ለአገር ትልልቅ ተግባራትን ያከናወኑ ንጉሥ በመሆናቸው ታላቅ ስራቸውን ለማንጸባረቅ የተቀረፀ እንደሆነ ይታወቃል። ጣሊያኖች ሐውልቱን አፍርሰውት የነበረ ቢሆንም፤ ከነፃነት በኋላ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐውልት ከተቀበረበት ቦታ ወጥቶ እንደገና ታድሶና ተጠግኖ ቀድሞ በነበረበት ቦታ ሚያዝያ 27 ቀን 1934 ዓ.ም. እንዲቆም መደረጉን ከታሪክ መረዳት ይቻላል። ጽሑፉን ያጠናቀርነው ከሌሎችና ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ካገኘነው መረጃዎች ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20/2012
አስቴር ኤልያስ