መንግሥት ትልቅ ራዕይ ታየው፡፡ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ማግስትም ራዕዩን ዕውን ለማድረግ የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን እቅድ ተግባራዊ አደረገ፡፡ በትራንስፎሜሽን ዕቅዱ አገር ሰከረ፡፡ ህዝብና መንግሥት በጊዜ የለንም መንፈስ እጅና ጓንት ሆነው ወደሥራ ገቡ፡፡
አገሪቱ በደመነፍስ በየቦታው የትልልቅ ፕሮጀክቶችን የመሰረት ድንጋይ ኮለኮለች፡፡ ከአስር ዓመት በኋላ ግን ጥቂቶቹ ብቻ ተግባራዊ ሲሆኑ ብዙዎቹ የመሰረት ድንጋይ ታቅፈው ቀሩ፡፡ አንዳንዶቹን ደግሞ አሁንም መንግሥት በቀጭን ተስፋ ተግባራዊ ለማድረግ እየሞከረ ነው፡፡ ከነዚህ ሥራዎች መካከል ትላልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሁፍ ሰሞኑን የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት ያቀረበባቸውን የዛሬማ ሜይ ዴይ እና የመገጭ የመስኖ ፕሮጀክቶችን የደመነፍስ ቁማር እንዳስሳለን፡፡
የደመነፍስ ቁማር አንድ
በኢትዮጵያ የስኳር ልማት ታሪክ ከ60 ዓመታት ውስጥ አስር ስኳር ፋብሪካዎች አልተገነቡም፡፡ በእቅዱ ግን በአንድ ጊዜ 10 ፋብሪካዎች ለመገንባት ተያዘ፡፡ መታቀድ ብቻ ሳይሆን የስኳር ኮርፖሬሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገባ፡፡ አዲስ የተቋቋመው ኮርፖሬሽን ያላቅሙ በርካታ ፋብሪካዎችን መሥራት ጀመረ፡፡ የመንግሥት ውሳኔ በሚልም የግድቦቹ ሥራ ከአገሪቱ ህግና አሰራር ውጭ ህገወጥ በሆነ መንገድ ለተቋራጭ ተሰጠ፡፡ ደመነፍሳዊው ቁማርም ‹‹ሀ›› ተብሎ ተጀመረ፡፡ በዚህ መልክ ከተወጠኑ በርካታ ፕሮጀክቶች መካከል የዛሬማ ሜይዴይ የመስኖ ግድብ ግንባታ አንዱ ነው፡፡
የዛሬማ ሜይዴይ ግደብ የተጀመረው እአአ በጥቅምት 2011 ነበር፡፡ ግንባታውን ስኳር ኮርፖሬሽን መፈጸም ስላልቻለ ከ2016 ጀምሮ በውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር እየተገነባ ነው፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ስለፕሮጀክቱ አፈጻጸም የክዋኔ ኦዲት አድርጓል፡፡ የክዋኔ ኦዲት ግኝቱም፤ ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ በፊት የቅድመ አዋጭነት ጥናት አለመካሄዱን አመላክቷል፡፡ ወደ ሥራ ከተገነባ በኋላም የተሰራው የአዋጭነት ጥናት በገልለተኛ ባለሙያዎች ተገምግሞ አልጸደቀም፡፡ ቀድሞውኑ የተሟላ ዲዛይን ያልነበረውና የአካባቢ ጥበቃ ግምገማ ያልተካሄደበት መሆኑን በማንሳትም የፕሮጀክቱ ግንባታ ለአገሪቱ አዋጭ መሆን አለመሆኑ ሳይጠና የህዝብ ሀብት በደመነፍስ መፍሰሱን አረጋግጧል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትም፤ ፕሮጀክቱን ከስኳር ኮርፖሬሽን ተረክቦ በባለቤትነት እያሠራ ላለው የውሃ መስኖና አሌክትሪክ ሚኒስቴር ስለምን የአዋጭነት ጥናት ሳይካሄድ ወደ ግንባታ ተገባ? ግንባታው ከተጀመረ በኋላስ የተጠናው ጥናት ለምን በገልለተኛ አካል ተገምግሞና ጸድቆ ወደ ሥራ አልተገባም? አዋጭነቱ ሳይረጋገጥ የህዝብ ገንዘብ ማፍሰስ ተገቢነት አለው ወይ? ሲሉ በክዋኔ ኦዲቱ ላይ ተመስርተው ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
የዛሬማ ሜይዴይ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አሚን ሸምሱ፤ ከአባላቱ ለቀረበው ጥያቄ፤ ፕሮጀክቱ የተጀመረው በስኳር ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተረከበው 40 በመቶ ከደረሰ በኋላ ነው፡፡ የአዋጭነት ጥናት መደረግ የነበረበት ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ በፊት ነው፡፡ በመሆኑም የአዋጭነት ጥናት ለምን እንዳልተደረገ ማብራሪያ መስጠት ያለበት ኮርፖሬሽኑ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ የአዋጭነት፣ የአካባቢና የማህበረሰብ ጥበቃ ጥናት ሪፖርት ‹‹ስጠን›› ብንል እንኳ አልሰጠንም፡፡ በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ከደሙ ንጹህ ነን፤ ማብራሪያ ልንጠየቅ አይገባም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የሚኒስቴሩ ኃላፊነት ፕሮጀክቱን ተረክቦ ማስጨረስ ነው፡፡ ይህን ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው በማለትም ማብራሪያ መስጠት እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ግን አስተባባሪውን በማቋረጥ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፕሮጀክቱን ከኮርፖሬሽኑ የተረከበው ስኬቱንና ጉድለቱን በሙሉ ነው፡፡ የፕሮጀክቱን ጠንካራ ጎን ለማስቀጠልና ደካማውን ለማስተካከል ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሙሉ በሙሉ መረጃዎችን የመቀበል ግዴታ አለበት፡፡ ቀደም ሲል በፕሮጀክቱ የነበሩትን ጥፋቶች በማረም፤ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ካሉ በመጠየቅ ጭምር ፕሮጀክቱን በሚመለከት ለሚነሳ ማንኛውም ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፤ ሲሉ የአስተባባሪው ምላሽ ትክክል አለመሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
አቶ አሚንም ‹‹ልንጠየቅ አይገባም›› የሚለውን ሀሳብ ማስተካከል አለባቸው፡፡ የፕሮጀክት ኃላፊ ሆነው፤ የህዝብ ገንዘብ እየባከነ ከተጠያቂነት አይዳንም በማለት አካሄዱ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡ ዛሬ የተገናኘነው የስኳር ኮርፖሬሽንን ኃጢያት ለመዘርዘር አይደለም ሲሉም ምላሹን ማስተካከል እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ኃላፊ፤ ፕሮጀክቱን 40 በመቶ ላይ ተረክበን አሁን ላይ 90 በመቶ አድርሰናል፡፡ ምክር ቤቱ እውነቱን ከፈለገ ሀቁ ይህ ነው፡፡ ባልሰራነው ነገር ልንጠየቅ አይገባም፡፡ መጠየቅ ካለብን ሥራውን ከጀመርን በኋላ ነው፡፡ በአረካከቡ ላይ ያለውን ሁኔታ ግን የበላይ ኃላፊዎች ምላሽ ሊሰጡበት ይችላሉ፤ በማለት ጥያቄውን ለውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አብርሃ አዱኛ ወርው ረውታል፡፡
ሚኒስቴር ዴኤታውም፤ ሚኒስቴሩ ከተረከበ በኋላ ተጠያቂነቱ የእነሱ መሆኑን በማመን ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቱ አጣዳፊ ነው ተብሎ ዲዛይኑን፣ የአዋጭነት ጥናቱንና የማህበረሰብ ጥበቃ ግምገማውንና ቀደም ሲል መሠራት የሚገባቸውን ተግባራት ጎን ለጎን ለማከናወን ታስቦ ሥራው ተጀምሯል፡፡ ሥራው ከተጀመረ በኋላም ኮርፖሬሽኑ የአቅም ውስንነት ስለነበረበት መፈጸም አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ ሚኒስቴሩ እንዲያጠናቅቀው ፕሮጀክቱ መዛወሩን አብራርተዋል፡፡ የኦዲት ግኝቱም ትክክል መሆኑን በማመን በቀጣይ የአዋጭነት፣ የአካባቢ ተዕፅኖ ግምገማና የማህበረሰብ ጥናት ሳይደረግ እንደማይጀመር በማንሳት መንግሥት ይህን ትልቅ ፕሮጀክት ያለጥናት፣ ያለዲዛይን፣ ያለማህበረሰብ ጥናት በደመነፍስ በማስጀመሩ በፕሮጀክቱ ላይ ትልቅ ኪሳራ መሆኑንም አምነዋል፡፡
የደመነፍስ ቁማር ሁለት
የዋና ኦዲተር የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ያረጋገጠው ሌላው ደመነፍሳዊ ቁማር ፕሮጀክቱ የመንግሥትን የግዥ መመሪያ ጥሶ ያለጨረታ በቃለ ጉባዔ ብቻ ለስቱዲዮ ጋሊ ኢንጂነሪንግ በአማካሪነት እና ለሱር ኮንስትራክሽን ግድቡን በተቋራጭነት በቀጥታ ሰጥቷል፡፡ የአገሪቱን የግዥ ህግ በመጣስ ያለጨረታ ፕሮጀክቱን ከመስጠት ባለፈ፤ ለፕሮጀክቱ ግንባታ ብር 4 ቢሊዮን 179 ሚሊዮን 655 ሺህ 504 ዋጋ ውል ቢገቡም፤ ተጨማሪ 10 ቢሊዮን 352 ሚሊዮን 938 ሺህ 599 ብር ፤ ወይም በውል ከተገባው በላይ የ347 በመቶ ጭማሪ ተደርጎ በድምሩ በብር 14 ቢሊዮን 532 ሚሊዮን 594 ሺህ 103 የፕሮጀክቱ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የኦዲት ሪፖርቱ አረጋግጧል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ ሁለቱ ድርጅቶች የመንግሥት ድርጅቶች አይደሉም፡፡ የአገሪቱ የግዥ ህግ ተጥሶ ያለጨረታ ፕሮጀክቱ ለምን ተሰጣቸው? ይህ በየትም ዓለም ታይቶ የማይታወቅ የገንዘብ ልዩነት እንዴት መጣ? ህግን ባልተከተለ የግዥ ጨረታ የተመረጡ ተቋራጭ እንደመሆናቸውስ የገንዘቡ ልዩነት ምን ያህል ህጋዊ ነው? ሲሉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ኃላፊዎች ጠይቀዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አብርሃ፤ የፕሮጀክቱ ሥራ ህግና ሥርዓትን ተከትሎ አልሄደም፡፡ በአስቸኳይ ለመሥራት በሚል በፖለቲካ ውሳኔ የግዥ ሥርዓትን ሳይጠብቅ ነው የተከናወነው፤ ፕሮጀክቱ ሲካሄድም የክልሎችን አቅም መገንባትን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ በመሆኑም ፕሮጀክቱን እንዲገነባ የታሰበው የትግራይ ክልል የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፤ አቅም ስለሌለው ክልሉ ፕሮጀክቱ ለሱር ኮንስትራክሽን ይሰጥልኝ በማለቱ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በስሜት በመጀመሩ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ አልነበረም፡፡ በትክክል መሬት ላይ ሲወረድ ግን ሥራው የተገለጸውን ጊዜም ሆነ ገንዘብ እንደሚፈጅ በማንሳት የገንዘቡ ልዩነት ተገቢነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሚኒስቴሩን ምላሽ ተከተሎ ባለድርሻ አካላት ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ ከሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የመጡት አቶ አዳነ፤ በፌዴራል መንግሥት በጀት የክልል መንግሥት ማዘዝ አይችልም፡፡ የክልሉ መንግሥት ለሱር ኮንስትራክሽን ይሰጠኝ ስላለ ህግ ተጥሶ በመስኖ ግንባታ ልምድ ለሌለው ለሱር ስለምን ተሰጠው? የፕላን ኮሚሽኑ አቶ በረከት ፍስሃጽዮን በበኩላቸው፤ ሙሉ መረጃ ሳይኖራችሁ እየገነባችሁ ያላችሁት ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ይሰጣል የተባለውን ጥቅም ይሰጣል ወይ? ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይጠናቀቃል የተባለበትም ጊዜ አልፏል፡፡ ለተቋራጮቹ የከፈላችሁት የአገሪቱን ህግ ጥሳችሁ ነው፡፡ ሌሎቹን በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ተቋራጮች የሚያቀጭጭ ነው፡፡ ከዚህ በስተጀርባ ያለው ነገር ምንድን ነው? ሲሉ ለኃላፊዎቹ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
ዶክተር አብርሃ፤ የክልሎችን አቅም ለመገንባት ታሳቢ ተደርጎ ከመሆኑ ውጪ ተጨማሪ ሀሳብ ለማንሳት አልቻሉም፡፡ በልምድ ደረጃ የሥራ ተቋራጩ ሥራው ከቁፋሮ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ልምዱ ተቀራራቢ ነው፡፡ ሙሉ መረጃ አለመያዝ ከኮርፖሬሽን ጋር በመናበብ መረጃውን የማሟላት ሥራ ይሰራል፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ ከ90 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ ሥራው እየተጠናቀቀ ባለበት ወቅት ላይ በባለሙያዎች ‹‹ሚዲል ሊቪል አውትሌት›› የግድ እንደሚያስፈልግ በመረጋገጡ ይህ መሥራት ስላለበት ነው፡፡ ይህ ግድቡ ተቦርቡሮ እንደተሰራ ውሃ መያዝ ይጀምራል፡፡ ተጨማሪው ገንዘብ ከአገሪቱ ህግ ውጭ የሚለው ትክክል ነው፡፡
ከዚህ በኋላ እንደዚህ አይነት እንዳይደገም ልምድ መውሰድ ብቻ እንደሚገባ በማንሳትም ያለፈውን በመንግሥትና በህዝብ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የተሠራውን ቁማር በዝምታ ያልፉታል፡፡
የደመነፍስ ቁማር ሦስት
በዋና ኦዲተር የቀረበው ሌላው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት የመገጭን የመስኖ ግድብ ይመለከታል፡፡ በዚህም፤ ግድቡ የአዋጭነት ጥናት እንዳልተሰራለት፤ ዲዛይን ቢኖረውም በገለልተኛ አካል አለመገምገሙና በተደጋጋሚ ዲዛይን እንዲቀያየር መደረጉ፤ በ 2 ቢሊዮን 451 ሚሊዮን 923 ሺህ 789 ብር ለመሥራት ውል ቢታሰረም ዋጋው ወደ 5 ቢሊዮን 667 ሚሊዮን130 ሺህ 760 ብር ማደጉ፤ ይህም ከተያዘለት በጀት 53 በመቶ የውል ማሻሻያ የገንዘብ ጭማሪ መደረጉ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም፤ ተቋራጩም ሆነ አማካሪው በውሉ መሰረት እየሠሩ አለመሆናቸውን ይህም በሚያቀርቡት የተለያየ ሪፖርት መረጋገጡን፤ ሚኒስቴሩም ፕሮጀክቱን የሚከታተል የባለሙያዎች ቡድን ያለመመደቡ፤ የፕሮጀክቱ የውሃ መስመር ዝርጋታና የመስኖ እርሻ ዝግጅት የተቀናጀ የጋራ እቅድ አለመኖሩና በቅንጅት አለመሠራቱ፤ እንዲሁም ለካሳ ክፍያ መሟላት የሚገባው የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ሳይሟላ ክፍያ መፈጸሙ በኦዲቱ ተረጋግጧል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የፕሮጀክቱን አስፈላጊ ደረጃዎች መተግበር ለምን አልፈለገም? በውል በተገባው ጊዜ፣ ጥራትና ትክክለኛ ዋጋ ተገንብቶ የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲጠቅም ሚኒስቴሩ ምን ያህል ፍላጎት አለው? ካለውስ ለምን አቃተው? በተያዘለት የውል ጊዜ ባለመገንባቱ የመንግሥትና የህዝብን ጥቅም ያሳጡ አካላት ተጠያቂ ተደርገዋልን? ካልተጠየቁ ለምን? አሁንስ ምን እየተሠራ ነው? መሥሪያ ቤቱ በቢሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ሀብት የሚያወጣውን ሥራ ለምን ተከታትሎ አላሠራም? በመሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ሥራው መሠራቱ ሳይረጋገጥ ለምን ክፍያ ተፈጸመ? ይህን የፈጸሙ ሰዎች ተጠያቂ ተደርገዋል ወይ? የተቀናጀ እቅድ ዘርግቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስለምን በጋራ መሥራት አቃተው? የመሬት ይዞታ መኖሩን ሳያረጋገጥ ለምን ክፍያ ፈጸመ? ክፍያውስ ለባለመብቶቹ መድረሱን አረጋግጧል ወይ? ሲሉ የክዋኔ ኦዲቱን መነሻ ያደረጉ በርካታ ጥያቄዎች ሰንዝረዋል፡፡
የመገጭ መስኖ ፐሮጀክት አስተባባሪ እንግዳሰው ዘሪሁን፤ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የአዋጭነት ጥናትና የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ቀድሞ ያልተካሄደው ፕሮጀክቱ ትልቅ ከመሆኑ አንጻር እየተሠራ ለማካሄድ ታስቦ እንደሆነና ውል ከተገባ በኋላ የተፈጠረው የዋጋ ልዩነትም እንደተባለው ከፍተኛ ባይሆንም ሥራው ሁሉ ተጠናቅቆና ታውቆ ባለመጀመሩ የመጣ ልዩነት ነው፤ ይህም ከመጀመሪያው ፕሮጀክቱ ሲሰጥ የተፈጠረ ችግር ነው፤ ብለዋል፡፡ አያይዘውም፤ ግንባታውን ሲያካሄድ የነበረው የቀድሞው የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ለተወሰነ ጊዜ እንዲያስተዳድረው ተብሎ ይህ ባለመሆኑ ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ የዋጋ ልዩነቱ ሲፈጠር ግን በሚኒስቴሩ ብቻ ስለማይወሰን በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ጭምር ተፈቅዶ የተከፈለ በመሆኑ ገንዘቡ አላግባብ አልባከነም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በግንባታው ሥራ ላይ ለምን ቁጥጥር አይደረግም በሚል ለተነሳው ጥያቄም አስተባባሪው ሲመልሱ፤ በግንባታው ሂደት ቁጥጥር እንደሚደረግና ሳይሠራም የተከፈለ ገንዘብ እንደሌለ አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም፤ የመስኖ ዝግጅትና የመስመር ዝርጋታ አለመጀመሩን አምነው፤ ያልተጀመረውም ለገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር የበጀት ጥያቄ ቀርቦ ውድቅ በመደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር አብርሃ በበኩላቸው፤ የመገጭ ፕሮጀክት ግንባታ የሚካሄደው በመንግሥት ድርጅት በመሆኑ ግንባታውን የጀመሩት መንግሥት ባስቀመጠላቸው ዋጋ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ድርጅቶቹን ሊያሳድጋቸው ስለማያችልና የተቋቋሙበትን ዓላማ ስለማያሳኩ እንደግል ድርጅት በገበያ ዋጋ እንዲወዳደሩ መንግሥት ወስኗል፡፡ በዚህም መሰረት የአሁኑ ክፍያ መጀመሪያ ከተገባው ውል ከፍተኛ ጭማሪ ለማሳየቱ ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከመስኖ በተጨማሪ የጎንደር ከተማን የመጠጥ ውሃ ሥራ የያዘ በመሆኑ ግድቡ ሳይጠናቀቅ ቢሠራ ጥቅም እንደሌለው፤ ሆኖም ከገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በጀት ሲፈቀድ ከግድቡ መጠናቀቅ ጎን ለጎን የመጠጥ ውሃውን ሥራ ለማከናወን መስማማታቸውን ያነሳሉ፡፡ በሪፖርቱ ላልተከናወነ ሥራ ተከፍሏል ሲባል ለተነሳው ጥያቄም፤ ክፍያ በትዕዛዝ ስለሚፈጸም አንዳንድ ቦታዎች ላይ ክፍተት ቢኖርም ሳይረጋገጥ ግን የተከፈለ የለም፡፡ ካሳን በሚመለከት የአማራ ክልል ከመደበኛ ሥራው ደርቦ ስለሚሠራው መዘግየት ቢኖርም በሁሉም አካባቢ ለባለመብቶቹ ገንዘቡ መከፈሉን ያረጋግጣሉ፡፡
ቁጥጥርን በተመለከተም፤ በየወሩ ስብሰባ በማካሄድ በጊዜ፣ በገንዘብና በአፈጻጸም ፕሮክጀቱ ይገመገማል፡፡ ችግሩ ግን ተቋማዊ ስለሆነ በአስተዳደራዊም ሆነ በህግ በሚኒስቴሩ እርምጃ የተወሰደበት ሰው የለም፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ትልቁ ችግር የቁጥጥር አለመኖርና በጋራ ያለመሥራት ሳይሆን የገንዘብ ነው፡፡ በዚህም ለሁለቱ ፕሮጀክቶች ያልከፈልነው ከ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሚኒስትር ዴኤታው ምላሽ አልረኩም፡፡ ይልቁንም፤ ከአገሪቱ ህግና አሰራር ውጪ የተፈጸሙ በርካታ ጉዳዮችን የተቋም ችግር ነው ብሎ ማለፍ መንግሥት ሌቦችን ተጠያቂ ለማድረግ የጀመረውን ሥራ ለመደገፍ አለመዘጋጀታቸውን አመላካች መሆኑን አንስተዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በክዋኔ ኦዲቱ የተገኙ ጉድለቶችን አለማመኑንም በትልቅ ህጸፅነት አንስተዋል፡፡
የደመነፍስ ቁማር አራት
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሁለቱ ፕሮጀክቶች መቼና በምን ያህል ገንዘብ ተጠናቅቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት ይሰጣሉ? ምን ያህል የህብረተሰቡን ችግር ይፈታሉ? ከሌብነት ምን ያህል የጸዱ ናቸው? ሲሉም ለሚኒስቴሩ ጥያቄ አንስተዋል፡፡
ዶክተር አብርሃ፤ ሁለቱም ፕሮጀክቶች በትክክል በዚህን ጊዜ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ለህዝብ ቃል መግባት እንደማይቻል አንስተው፤ የመገጩን ፕሮጀክት በሚቀጥለው ዓመት ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል፡፡ የዛሬማ ሜይዴይ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቋል፡፡ ሆኖም፤ የሚዲል ሌቭል ማስተንፈሻ ግንባታ ከሌለው ውሃ መሙላት እንደማይችል በመረጋገጡ ዲዛይን በመሥራት ግድቡ ተቦርቡሮ ማስተንፈሻ ከተሠራ በኋላ ወደ ሥራ መግባት ይችላል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ግድቡ ተጠናቀቀ ማለት የቦይና ሌሎች መፋሰሻዎች ካልተጠናቀቁ አገልግሎት አይሰጥም፡፡ ግድቡ እስከሚሞላም ጊዜ ይወስዳል፤ በመሆኑም መቼ አገልግሎት እንደሚሰጥ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አልቻሉም ብለዋል፡፡
መሥሪያ ቤቱ ለዛሬማ ሜይዴይ ግድብን ለሌሎች ሥራዎች ያወጣው ገንዘብ በድምሩ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ አሁንም በምን ያህል ገንዘብ እንደሚጠናቀቅ በግልጽ ማስቀመጥ አልቻሉም፡፡ የመገጭ ግድብም በቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎች በመኖራቸው ወጪው ሊጨምር እንደሚችል ከማመላከት ውጪ ምን ያህል እንደሚፈጅ አልተናገሩም፡፡
ፕሮጀክቶቹ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ሲገቡ ህዝቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ብልሹ አሰራሮችን ለማስተካከል መፍትሄ አስቀምጠናል ብለዋል፡፡ ተቋሙ ከሌብነት ነጻ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ቶሎ ቶሎ ማለቱና ወደሥራ መግባቱ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ሁሉም ነገር ሳይጠናቀቅ ሥራ አንጀምርም ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ግን፤ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ኃላፊዎች ለነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ትኩረት አልሰጣችሁም፤ ኦዲቱን እንኳን የጋራ አድርጋችሁ አልመጣችሁም፡፡ ከዓመታት በፊት ተጠናቅቀው አገልግሎት ይሰጣሉ የተባሉ ፕሮጀክቶች ዛሬም መቼና በምን ያህል ገንዘብ እንደሚጠናቀቁ አታውቁም ሲሉ ተችተዋቸዋል፡፡
አባላቱ ያለጨረታና በህገ ወጥ መንገድ የተሰጡ ፕሮጀክቶች መቼ እንደሚጠናቀቁም ዛሬም አይታወቅም፡፡ በመገጭ ፕሮጀክት አካባቢ በባህላዊ መንገድ የሚያመርተውን ገበሬ እንዳያመርት ፕሮጀክቱ አግዶታል፡፡ መንግሥት ለህዝብ ቃል የገባውን እየፈጸመ አይደለም፡፡ እናም፤ ‹‹ቢያንስ እኛ አይለፍልን፤ ለልጆቻችን እንዴት የከፋ እዳ እናስተላልፋለን?›› ሲሉም ፕሮጀክቶቹ እንዲጠናቀቁ ተማጽነዋል፡፡
በቀረበው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ውይይት ማገባደጃ ላይ የዋና ኦዲተር የሥራ ኃላፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በዚህም፤ ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ፤ የሁለቱ ፕሮጀክቶች ኦዲት እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ የዲዛይን፣ የጥናትና የአፈጻጸም ችግር መኖሩን አረጋግጠናል፡፡ ሚኒስቴሩ የክዋኔ ኦዲቱን አይቶ እያስተካከለ አይደለም፡፡ የማስተካከያ ዕቅዳቸውንም በ15 ቀናት ውስጥ መላክ ሲገባቸው አልላኩም፡፡ የፕሮጀክቱ ወጪ ከ4 ቢሊዮን ወደ 20 ቢሊዮን ብር ሲያድግ ብክነት አይኖርም ማለት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ሚኒስቴሩን ከዚህ በኋላ እንከሳለን ብለዋል፡፡
ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶም፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የፕሮጀክት እቅድ የለውም፤ የገንዘብ ሚኒስቴር የፕሮጀክት መመሪያዎች የተገኘው በተገቢው ቢሮ ሳይሆን በሌላ ሰው እጅ ነው፡፡ ለሥራው ያለው መደብ 50 ቢሆንም ሥራው የሚካሄደው በ21 ሰው ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ጥናት በገለልተኛ አካል አልተካሄደም፡፡ ዲዛይኑም ሳይጸድቅ ነው ወደሥራ የተገባው፡፡ የሱር ኮንስትራክሽን የግዥ ህጉን የጣስ ነው፡፡ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አልተካሄደም፡፡ በመሆኑም የመንግሥትና የአገር ሀብት እየባከነ ከሥርዓት ውጪ እየፈሰስ ነው፡፡ አላግባብ ለሚባክነው ሀብትም ተጠያቂ የለም ሲሉ የፕሮጀክቶቹ አካሄድ እንዲስተካከል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የምክር ቤቱ የደመነፍስ ውሳኔ ቁማር አምስት
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚውን የመቆጣጠር ሥልጣን በህግ ተሰጥቶታል፡፡ በወጣው የግዥ ህግ መስረት መፈጸሙን ይቆጣጠራል፡፡ አስፈጻሚውም ምክር ቤቱ ባወጣው ህግ መሰረት መፈጸም ይገባዋል፡፡ ነገር ግን፤ የዛሬማ ሜይዴይ ግድብ ከህግ ውጪ ያለጨረታ ለተቋራጭ ሲሰጥ ተቆጣጥሮ ማስቆም አልቻለም፡፡ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ሥራ ከመጀመሩ በፊት የአዋጭነት ጥናት፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ፤ እንዲሁም የተሟላ ዲዛይን ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መግባት እንዳለበት በህግ ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ይህ ሳይሆን ፕሮጀክቱ እንዲጀመር ምክር ቤቱ በጀት አጽድቋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ የግዥ ህግ አንድ ተቋራጭ ከገባው ውል ከ25 እስከ 30 በመቶ ብቻ የክፍያ ጭማሪ እንደሚያድግ ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም፤ ለሁለቱ ፕሮጀክቶች ከተገባላቸው ውል በላይ የ347 እና የ53 በመቶ ጭማሪ ሲደረግ ምክር ቤቱ አስፈጻሚው የሚሰጠውን ትዕዛዝ ከመፈጸም ውጪ ማስቆም አልቻለም፡፡
በአጠቃላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ላይ መወጣት ያለበትን ኃላፊነት በጊዜው አልተወጣም፡፡ አስፈጻሚው እንዲተገብራቸው ያወጣቸው ህጎች ሲጣሱም ማስከበር አልቻለም፡፡ የህዝብ ገንዘብም በትክክል ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ሊያረጋግጥ በሚችል ሥርዓት ማሳለፍ አልቻለም፡፡ እናም፤ በፕሮጀክቶቹ ላይ የታየው ክፍተት ምክር ቤቱ በህዝብ የተሰጠውን ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ስግብግቦች በህዝብ ሀብት ላይ ሲቆምሩ በደመነፍስ ይወስን እንደነበር ያመለክታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር8/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ