ኢህአዴግ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ብርቱም ደካማም ጎኖች ነበሩት፡፡ አሉትም፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው ሀገሪቱን በለውጥና በዕድገት ምዕራፍ ላይ ያረማመደ ፓርቲ መሆኑም አይካድም፡፡ ውስጠ ድርጅት ትግል ጥንትም ነበር፤ዛሬም አለ ነገም ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ሆኖም ግን በእርስ በርስ ሽኩቻና የመበቃቀል ስሜት የሀገሪቱን መጥፋትና መመሰቃቀል ለሚመኙ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ልቅ የሆነ በር መክፈት አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡ ኢህአዴግ ሆይ አለህ እንዴ ?
ሕግና ሥርዓት ካልተከበረ የሀገርና የሕዝብ ሰላም ከሌለ የመንግሥትነት ፋይዳው ምንድነው ለሚለው ጥያቄም የኢህአዴግ ጉባዔ መልስ በመስጠት ታላቅ ሀገራዊ አደራውን መወጣት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ምንም ሆነ ምንም በህግና በሥርዓት ስትመራ የኖረች ረጅም የመንግሥትነት ታሪክ ያላት ቀደምትና ጥንታዊ ሀገር ናት፡፡ ይሁንና እንደዚህ ዘመን ዓይነት የዘረኝነት ልክፍትና ደዌ በሽታ ውስጥ የተዘፈቀችበት ጊዜ በታሪኳ ውስጥ ያለ አይመስልም፡፡ ከዚህ አደገኛ ቀለበት ውስጥ ለመውጣት የኢህአዴግ ጉባዔ ወሳኝ አቋም መያዝ ይጠበቅበታል፡፡
ዛሬ ላይ የመጣውን ለውጥ ያመጣው የሕዝብ ትግልና በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የለውጥ ኃይል ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መመረጥና ከኢህአዴግ ውስጥ ጎልቶ መውጣት የዚሁ ትግል ውጤት ነው፡፡በአለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የቱንም ያህል የፍትህ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮች ስር ሰደው የቆዩ ቢሆንም በራሱ በገዢው ፓርቲ ውስጥም ሆነ በሕዝቡ በኩል የገዘፉ መራራ ትግሎች ተካሂደዋል፡፡ ሥርዓቱ በሙሰኞች ተቀፍድዶ በመያዙ አመጣለሁ ያለውን የለውጥ እርምጃ ማምጣት ተስኖት ቆይቷል፡፡
በዓይን የሚታየውን ለውጥ የሚክዱ ሞልተው ቢተርፉም በሀገራችን የተካሄዱት ሰፊ የመሰረተ ልማት፣የመንገድ፣ የግድቦች፣ የፋብሪካዎች ፣ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታዎች፣ የኮንዶ ሚኒየም ቤቶችና የከተሞች ማደግና መስፋፋት፣ የባቡር መስመር ዝርጋታው፣ የሆስፒታሎችና የክሊኒኮች ፣ የገጠር ልማትና የመሳሰሉት መስፋፋትና ማደግ ሁሉ የተገኘው በነዚሁ የኢህአዴግ 27 የአመራር ዘመናት ውስጥ ነው፡፡
በሀገሪቱም በአብዛኛዎቹ ዓመታት የተረጋጋ ሰላም የነበረ ከመሆኑ በላይ የመስፋፋት አዝማሚያ ይዞ የነበረው የአልሻባብ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን መናኸሪያና የቀውስ አውድማ አደርጋለሁ ብሎ አስቦ የተንቀሳቀሰበት ሁኔታም ወደ እኛ ሳይሻገር የተገታው ሠራዊታችን ታላቅ መስዋዕትነት በመክፈል ሊመክተው ስለቻለ ነው፡፡ኢህአዴግ ጥልቀት ያለው ተሀድሶ ለማድረግ የገባውን ቃል ጠብቋል፡፡
ከአንድም ሁለት ጊዜ ጥልቀታዊ ተሀድሶው የመከነ ቢሆንም ድርጅቱ እንደገና በውስጡ ባደረገው ትግል የለውጡን ሂደት ማስቀጠል በመቻሉ ብዙ ያልተጠበቁ ለውጦች መጥተዋል፡፡ እስረኞች ተፈተዋል፤ በውጭ የነበሩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሀገር ወስጥ ገብተው መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በውጭ የነበሩ ሚዲያዎችም ገብተዋል፡፡ ያልበሰለ ሚዛናዊነት የጎደለው፣በእብደትና በስሜታዊነት፣ በጥላቻ ተሞልቶ ጥላቻን እየረጨ፣በገንዘብ አትራፊነት ስሜት የሚንቀሳቀስ ሚዲያም ዛሬም እሳት ከመለኮስ ተግባሩ ያልታቀበ ቢሆንም ከቀድሞው ሰፋ ያለ ዕድል አግኝቶ እየሰራ ይገኛል፡፡
ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንዲሉ ሁሌም ጥላቻና ተቃውሞን ብቻ የሚረጨው ሚዲያ አሁንም ሀገራዊ ፈተና መሆኑን ቀጥሏል፡፡ መልካሙን መልካም፣መጥፎውን መጥፎ የሚል ሚዛናዊነት የለውም፡፡ በአጉል የአርበኝነት ስካር እየናወዙ የሚሰሩትንና የሚጨብጡትን ስተዋል፡፡ ህዝብን ለጥፋት እያጎሹት ባዶ ፕሮፓጋንዳ እየጋቱትም ይገኛሉ፡፡ በለውጡ ሰሞን የነበረው ሀገራዊ እምነት የተረጋጋ ሀገራዊ ሰላም ይፈጠራል የሚል ነበር፡፡ በሰላም ወደ ሀገራችሁ ግቡ የተባሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በሰላም ገብተናል ቢሉም የበቀል ጥማታቸው አገርሽቶ በስውር ጦር እያሰለጠኑ ለውጊያ ብቁ የማድረግ ሥራዎችን ሲሰሩም ታይተዋል፡፡
ዛሬ በሁሉም ክልሎች ማለት በሚቻል መልኩ ሕግና ሥርዓት አይከበርም ወይንም ጥያቄ ውስጥ ወድቋል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የሚያሳየን ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ስሙ ቢኖርም በተግባር ድርጅታዊ ቁመናውን አሰራሩን አጥቷል ማለት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በውል ሊረዱት የሚገባው ነገር ቢኖር ወደ ስልጣን ያመጣቸው ድርጅት ከሌለና ከፈረሰ እሳቸውም የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲ የለም ማለት ነው፡፡ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በጋራ መክረው ዘክረው ተራርመው የተሻለ ሥራ ይሰራሉ ተብሎ ሲገመት ዛሬ ላይ በገሀድ የሚታየው ድርጅቱ ለመስጠም እንደምትንደረደር መርከብ የቁልቁለት ጉዞውን መጀመሩ ነው፡፡ ለመሆኑ ኢህአዴግ አለሁ የሚለው የት ላይ ነው ያለው?
የድርጅቶቹ አባላት በሀገራዊ ጉዳይ የማይወ ያዩበት፣ የማይነጋገሩበት፣ሃሳባቸውን የማይሰ ጡበት፣ ከሕዝብ ጋር ወርደው የማይመክሩበት፣ የህዝብን ሃሳብ እንደ ፖለቲካ ድርጅት በማያዳም ጡበት ሁኔታ የፖለቲካ ድርጅት ናቸው ብሎ መደምደሙ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ሕዝባዊነትን ማረጋገጥም ያዳግታቸዋል፡፡ ዛሬ ዛሬ ኢህአዴግ ድርጅታዊ ጥንካሬና አንድነቱ እንዲሁም የነበረው ብርታትና ጥንካሬው ተሸርሽሮ በነፋስ ላይ የቆመ ድርጅት መስሎ የሚታይበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ኧረ ለመሆኑ ኢህአዴግ አለ እንዴ ?
ከወረዳ፣ ክፍለከተማ፣ ከተማ አስተዳደር፣ ክልሎች ሁሉ ያለው ድርጅታዊ መዋቅሩ በአዲስ መልክ ተለውጦና በለውጡ መንፈስ ተቃኝቶ የሚሰራበት ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ በዚህ መልኩ ኢህአዴግ አለ ብሎ ለማለት አያስደፍርም፡፡ አለ እንዴ አላችሁ እንዴ ኢህአዴጎች ? ጅርቱ እንዲል ሀጫሉ፡፡
የኢህአዴግ መኖር የሚሰማው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአልፎ አገደም ድርጅቴ ሲሉ ብቻ ነው፡፡ እንደ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅት ኢህአዴግ አለ ብሎ የሚያምን ዜጋ በአሁኑ ሰዓት የለም፡፡ የሥርዓት ለውጥ የተደረገ ያህል ሁሉም ከሕግና ከሥርዓት ውጪ ሲፈነጭ ሥርዓተ አልበኝነት ነፍስ ዘርቶ እግር አውጥቶ ሲራመድ፣ በክልሎች የዜጎች መፈናቀል፣ ግድያውና ዘረፋው መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ ዛሬም በቀጠለበት ሁኔታ ውስጥ ኢህአዴግ ሆይ እንደው በእውነት አለህ ወይ ብሎ ሕዝቡ ቢጠይቅ አይፈረድበትም፡፡ ማፍረስ ከፈለጋችሁም በሥርዓቱ አፍርሱት፡፡ አለን ካላችሁም በሥርዓቱ ሥሩ፡፡ ጥፋት እያመጣና ሀገሪቱን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየመራት ያለው የእናንተ መዝረክረክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፈጠረቻችሁ እንጂ አልፈጠራችኋትም፡፡ ከእናንተም በፊት ነበረች፡፡ ከእናንተም በኋላ ትኖራለች፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም ሀገር ላይ ውስጠ ፓርቲ ትግል ይካሄዳል፡፡ መሪዎች ይለወጣሉ፡፡አሰራር ይቀየራል፡፡ የለውጥ ኃይሎችም የጀመሩትን ለውጥ ያስቀጥላሉ፡፡ እንደእኛ ቅጥ ያጣ ግን የለም፡፡በዴሞክራሲ ስም እየተነገደ ፤ሀገር ከቀን ወደ ቀን ወደ በከፋ ሁኔታ እየተረማመደች ያለችበት ዜጎች መሽቶ ሲነጋ ምን ያጋጥመናል ደግሞስ ምን ይፈጠራል እያሉ የሚባንኑባት ሀገር እንድትሆን ልቅነትና ሥርዓተ አልበኝነትን በሌለ ዴሞክራሲ ስም እያበረታታ ያለው ራሱ ኢህአዴግ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ኢህአዴግ ሆይ ኧረ ለመሆኑ አለህ ወይ፤ እንዴት ከረምክ ቢባል ምንም አይደንቅም፡፡
በእኔ እምነት ከተጀመረው ለውጥ በኋላም ራሱን አጠናክሮ መቀጠል ነበረበት፡፡አሊያም በኦፊሴል ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት ፈርሷል ብላችሁ አውጁ፡፡ ሕዝቡም እርሙን ያውጣ፡፡ ማንም እየተነሳ የሚፈነጭባት፣ ሰው በአደባባይ ያለወንጀሉ የሚሰቀልባት፣ ሽማግሌዎችና አዛውንቶች ቀልበው ባሳደጉት ጎረምሳ በአጠና የሚወገሩባት፣ የመንደር ወመኔና ወጠምሻ የሚያገሳባት፣ ሰላማዊ ዜጎች በፍርሀት እየራዱ አንገታቸውን የሚደፉባት እርግማን የወረሰች ሀገር ግን አታድርጓት፡፡ ከሰራችሁ ተባብራችሁ ተማክራችሁ፣ ተከባብራችሁ፣ ተደማምጣችሁ ስሩ፡፡ ይህችን ታላቅና ውብ ሀገር ከገባችበት ቀውስ ተባብራችሁ አውጧት፡፡ ይህ ማድረግ ካልቻላችሁ አለን ብትሉም የላችሁም፡፡
ኢህአዴግ ከስህተቱ ታርሞ ከሁሉም ድርጅቶች ውስጥ በሙስናና ሥነምግባር ጉድለት እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተገኙትን በሙሉ በሥርዓት ለሕግ አቅርቦ ጉዞውን ለመቀጠል በጋራ መስራት ቀዳሚ ኃላፊነቱ መሆን ነበረበት፡፡ ኢህአዴግ አደረጃጀቴን ለውጬ እሰራለሁ ካለም መብቱ ነው፡፡ ዛሬ ጥላቻና ቂም በቀል ነግሷል፡፡ የጥፋት ሰይፎች በየቦታው ተስለዋል፡፡ ሕግና ሥርዓት ተጥሷል፡፡ ጽንፍ የወጣ ዘረኝነት ጽንፍ የወጣ ጎጠኝነት ነፍስ ዘርቶ በአደባባይ እየተወራጨ ይገኛል፡፡ በሀገር ውስጥ በውጭ ኃይሎች እየተረዳ ራሱን ለሕዝብ የቆመ ነጻ አውጪ አድርጎ በመሳል ባሕር ማዶና በሀገር ውስጥ ያለውም መንግሥትን ጡጦ የሚጠባ ሕጻን ይመስል ይሄን አድርግ ይሄን አታድርግ እያለ በራሱ አጀንዳ እጁን ይዘው ሊጎትት ሲሞክር ይታያል፡፡
አዎ አሜሪካ ተቀምጦ ያማረ ሸሚዝና ከረባት አድርጎ ወንበር ላይ እየተንቆራጠጡ አሥሩን ሲወሻክቱ መዋልና ማደር እጅግ በጣም ቀላሉ ነገር ነው፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ የየእለቱን ፈተና በመጋፈጥ ሀገር እንዳትፈርስና እንዳትበተን መስራት ደግሞ እጅግ ከባዱ ሥራ ነው፡፡ በመከላከያው ላይ የማያባራ ዘመቻ ተከፍቷል፡፡ መከላከያው ሀገር በጠበቀና ሰላምን ባስከበረ ሊከበር ነበር የሚገባው፡፡ በአጠቃላይ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት እንደ የጋራ ፓርቲ አለ ማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
ሁሉም ያልተረዳውና ያልተገነዘበው እውነት ለስልጣን ጥም ከሚደረገው መክለፍለፍ ባሻገር ይሄ ድርጅት ሀገር መርቶ ሀገር አስተዳድሮ ለውጥና ልማትንም አምጥቶ ከነድክምቱ ሰላምዋን ጠብቆ ኖሯል፡፡ ኢህአዴግ እንደ አንድ ግዙፍ ድርጅትና ፓርቲ መፍረሱ ደስታ የሚሰጣቸው ቢኖሩም ሀገሪቷ ተመልሳ ወደ አንድ መስመር ለመምጣት ታላቅ ቀውስና ፈተና ውስጥ እንደምትወድቅም መረሳት የለበትም፡፡
የመበቃቀል ፖለቲካ ነፍስ ዘርቶ እያየነው ነው፡፡ ሃያና ሰላሳ ዓመት ቀርቶ ከዛም በላይ ቢቆዩ ምንም መፍጠር የማይችሉ ሙት ፓርቲዎችን ሰብስቦ ሀገርን መታደግ አይቻልም፡፡ ስማቸው የገዘፈው በሚዲያ እንጂ በተግባር ጭርሱንም የሌሉ ናቸው፡፡ ግማሹ የውጭ ኃይሎች ተላላኪና ቅጥረኛ ነው፡፡ ኢህአዴግ ሆይ እንደ ፖለቲካ ድርጅት አለህ ወይ ኧረ እንዴት ከርመሀል ቢባል ምንም አይገርምም፡፡
አብዛኛው ሕዝብ በቅዠት ፖለቲካ ውስጥ ተጥዶ ውሎ ያድራል፡፡ ሥራ የለም፡፡ ሀገራዊው ኢኮኖሚው በፍጥነት እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡ ሁሉም ፖለቲካ ቀለቡ ቁርስና ምሳው እራቱ ሆኖአል፡፡ የሚያወራ እንጂ የሚሰራ እየጠፋ ነው፡፡ እንዲህ ሁነን የትም አንደርስም፡፡ ኑሮ ወድነቱ ከሕዝቡ አቅም በላይ እየወጣ ነው፡፡ የገበያ ዋጋ እጥፍ ጨምሯል፡፡ የገበያ ሥርዓተአልበኝነት ሆን ተብሎ እየፈጠረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ኢህአዴግ የሰራቸው በርካታ ሀገራዊ ትሩፋቶችም አሉት፡፡ ዛሬ ሁሉም ጎራ በክህደት ተውጧል፡፡ የተሰሩትን በጎ ነገሮች ሁሉ የመካድ የማጥላላት ትርክት ሰፍኗል፡፡ አንዲት በጎ ነገር ለሀገሩ ያላደረገ ያልሰራ አስተዋጽኦ ያላደረገ ሁሉ በአርበኝነት ስም ተመጻዳቂ ሆኖአል፡፡ ወሬና አሉባልታ እየተቀቀለና እየተገነፋባት ያደገችና የለማች ሀገር የለችም፡፡ አትኖርምም፡፡
እንደ ሀገር የሚጠብቀን ሁለት ነገር ነው፡፡ ወይ ተያይዞ መጥፋት ወይም ተያይዞ መልማትና ማደግ ነው፡፡ ሌላ ሦስተኛ መንገድ የለም፡፡ እውነተኛው ሀገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ይሄው ነው፡፡ ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይጠብቅ፡፡ ለልጆችዋም ፍቅርና መግባባት መደማመጥን ያድል፡፡ ከጥፋም ያድናት !! ኢህአዴግም ጠንክሮ በመውጣት አይዟችሁ እረ አለሁ ለማለት ያብቃው!
አዲስ ዘመን ጥር8/2011
መሐመድ አማን