ኢትዮጵያዊነት የባህል ድርብር ብነት፣ የመከባበር ተምሳሌት፣ የውህደትና የአብሮ መኖር ውጤት ነው። ማህበረሰባዊ እሴቶቻችን የእርስ በእርስ መከባበራችንን የሚያጎሉ የአብሮ መኖር ትስስራችንን የሚያደምቁ ትልቅ ሀብቶቻችን ናቸው።
አገሪቱ በተፈጥሮ ውበቷ፣ በታሪክ፣ በቅርስ በበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ፣ በቱሪዝም ሀብቶቿ የምትታወቅ ናት። ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቷም አንዱ እና ዋነኛ መገለጫዋ ነው። ባህል ሲባል በመሠረቱ እጅግ ክቡር ነው፤ የአንድ ኅብረተሰብ ባህል በራሱ የኅብረተሰቡ እንክብካቤ መጠበቅ መዳበር መሻሻልና የላቀ ዕድገት ማሳየት እንዳለበት ይታመናል።
አንድ ኅብረተሰብ እራሱን የሚያስተዳድርበት ባህላዊ ሥርዓቶችና ደንቦች ተቀብሎ በእነዚህ መተዳደሪያ ደንቦች ይመራል። ይገለገላል። እንዲህ ያሉ የባህል ባለቤቶች ታዲያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ጊዜውን ባገናዘበ መልኩ እንዴት እንዲህ ያሉ ወርቃማ እሴቶቻችንን እንጠብቃለን? እንከውናለን? ብለን ስናስብ አስተዋይ ሰው በመሆን ይሆናል ምላሹ።
የማህበራዊ ክዋኔዎችም ቢሆኑ እንዲሁ ጊዜን ያገናዘቡ ሊሆኑ ይገባል። እንደሚታወቀው በማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ እና ቦታ ከሚሰጣቸው ሁነቶች መካከል ለቅሶ እና ሠርግ ዋነኞቹ ናቸው፤ የተለያዩ ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት የአካላዊ እና የመንፈሳዊ ውህደት መገለጫ የሆነው ጋብቻ በኅብረተሰቡ ብሎም በጎጆ ወጪዎች ዘንድ መሠረታዊ ትርጉም ያለው እና የለውጥ ማሳያ ጭምር ነው።
ይህ በብዙዎች ዘንድ በወጣትነት የሚከወን ማህበራዊ ሥርዓት ከቦታ ቦታ፣ ከባህል ባህል ከአገር አገር ይለያያል። ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ በአመዛኙ ሠርግ የሚደረገው በወርሃ ሚያዝያ ከወሩም የፋሲካ በዓልን ተከትሎ ነው።
ታዲያ በዚህ ሳምንት በተለይ በዛሬዋ ዕለት በዳግማዊ ትንሳኤ ከዓመት አሊያም ከወራት በፊት ቀን ተቆርጦለት፣ ለድግስ የሚያስፈልጉ ነገሮች ተሟልተው በሕይወት አንዴ የሚደረገውን የሠርግ ሥርዓት ለመከወን ወሯ እንደገባ እርጉዝ ቀን ሲቆጥር የኖረ ሰው አያሌ ነው። ነገር ግን ይህ የተለፋለትን፣ የተደከመለትንና በጉጉት የሚጠበቀውን ሠርግ እንደወትሮ መከወን እንዳይቻል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ጋሬጣ ሆኗል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ እና የፎክሎር ባለሙያው የሆኑት አቶ ኤሊያስ ወላንሳ እንደሚሉት በአብዛኛው ሠርጎች በተለይ ወደ ገጠሩ የሚደረጉት ብዙ መነካካት መገፋፋት … በአጠቃላይ በጣም የቀረበ አካላዊ ንክኪ ባለበት ሁኔታ ነው። ይህ ማለት ግን በከተማ ከሚካሄደው የሠርግ ሥርዓት ጋር ሲነጻጸር እንጂ በከተማው እንደ ገጠሩም ባይሆን አካላዊ ንክኪ አለ።
አቶ ኤሊያስ በገጠሩ ጥናት ባደረጉበት ቦታ የሠርጉ ሥርዓት ከዋዜማ ጀምሮ የሙሽራው ጓደኞች ሙሽራውና ሚዜው በአቻ ዕድሜ ላይ ያሉ ዘመድና ወዳጆቹ ተሰብስበው ወደ ሙሽሪት ቤተሰብ ቤት በመሄድ ሙሽራዋን ይዘው ይመጣሉ። ሠርገኞቹ ወደ ሙሽሪት ቤት በሚደርሱበትና ሙሽሪትን ካልወሰድን በሚሉበት ወቅት ከሙሽሪት ጓደኞችና የሰፈሯ ወጣቶች በበሰበሰ እንቁላል፣ በኩበት የመደብደብ ፈተና ይደርስባቸዋል። በዚህ ወቅት የመነካካቱ የመቀራረቡ ነገር በጣም ያይላል፤ በዚህ ሁኔታ አይደለም አሁን እየፈራነው ያለነው የኮሮና በሽታ ቀርቶ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች እንኳ በቀላሉ የሚተላለፉበት ቅርበት ነው።
ሌላኛው በሠርግ ወቅት የሚታሰበው የአመጋገብ ሥርዓት ነው፤ አጃቢዎቹ በሙሽሪት ቤተሰቦች ቤት የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ይቀርብላቸዋል። ታዲያ የቀረበው ምግብ የሚበላው በጋራ በአንድ ማዕድ ነው። ይሄ በየትኛውም ቦታ እና ብሔረሰብ የሚካሄደው የሠርግ ሥነሥርዓት ተቀራራቢ ነው።
እነዚህ ባህላዊ የሠርግ ክዋኔዎች በራሳቸው ችግር የሌለባቸው ናቸው የሚሉት ባለሙያው በዓለም ብሎም በአገሪቱ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ እንዲህ ያሉትን ማህበራዊ መስተጋብሮች ለጊዜው ገታ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
አቶ ኤሊያስ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የሚገኙ የትኛውም ብሔርብሔረሰብ የራሱ የሆነ የደረጀ መረጃን መቀበያ፣ ችግር ሲያጋጥም እርምጃ መውሰጃ መንገድ አለው። ይህንን መንገድ በመከተል ማህበረሰቡን በማስተማር እና የበሽታውን አስከፊነት በመንገር ችግሩን መከላከል ይቻላል። ካልሆነ ግን ማህበረሰቡ ባህሉ፣ ወጉ እና ልማዱ የተቀማ ስለሚመስለው እነዚህን ባህላዊ ተግባራት አታድርግ ቢባል አሻፈረኝ ሊል ይችላል ብለዋል።
ሌላኛው የፎክሎር ባለሙያው ተካልኝ ብርሃኑ በሸካ ብሔረሰብ ላይ በሰራው ጥናት እንደተመለከተው ጋብቻ በሸካዎች የሚሰጠው ቦታ ከፍ ያለ ነው፤ ሸካ በወርሃ ሚያዝያ ድል ተደርጎ ሠርግ ከሚደረግባቸው ማህበረሰቦች አንዱ ነው። በብሔረሰቡ የፋሲካን ባህል ተንተርሶ የጋብቻ ባህል ለማድረግ ዕቅድ ያቅዳል። ብሔረሰቡ የተለያዩ የጋብቻ ዓይነቶች እንዳሉም ባለሙያው ያትታሉ። ከእነዚህም መካከል «ማኮ» የወንዱ ቤተሰብ አይተው ለልጃቸው የፈቀዷትን ልጅ ማንኛውንም ባህላዊ ሥርዓት አልፈው የልጃቸው ሚስት እንድትሆን የሚያደርጉበትን ባህላዊ የጋብቻ ሥርዓት የሚመለከት ነው። ይህም ይሆን ዘንድ የልጁ ቤተሰቦች በአካባቢው ተቀባይነት ያላቸውን ሦስት ሽማግሌዎች መርጠው በመላክ አስፈላጊው ማጣራት እና ሥነ-ሥርዓት ታልፎ የሚፈፀም የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ነው። በዚህ ሂደት የሴቷ ወገኖች ልጃቸውን ለትዳር የፈለገውን ወጣት እና ቤተሰቦች ማንነት፣ በጎሳ ወይም በሌላ በማንኛውም ዓይነት መንገድ የደም ትስስር አለመኖሩን በማጣራት ከተደጋጋሚ ደጅ ማስጠናት በኋላ የሚፈፀም የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ነው።
«ኤችዮ» ይህ የጋብቻ ዓይነት በሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነት የሚፈፀም ነው። አንድ ወንድ የወደዳትን ሴት አብዛኛውን ጊዜ ጎረቤቷ ከሆነች ጓደኛዋ ጋር በመሆን ከሚኖሩበት ቦታ በመሰወር ከፍቅረኛዋ ጋር ቀድመው ወደተነጋገሩበት አካባቢ በመኮብለል ለተወሰነ ጊዜ ተሰውረው ከቆዩ በኋላ በወንድ ወገን ቤተሰቦች አመቻችነት ለሴቷ ወገን ቤተሰቦች ሽማግሌ ተልኮ እርቅ በመፈፀም ጥሎሽ ከብት እና ሠርግ መደገሻ በመስጠት በመልስ ሥነ-ሥርዓት የሚፈፀም የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት ነው።
«ሾሶ» ጠለፋ ማለት ሲሆን በሸካቾ ብሔረሰብ ዘንድ በሁለት ዓይነት መልኩ የሚፈፀም ነው። አንደኛው «ጋፖ» ሲሆን አንድ ወንድ ላጫት ሴት ቤተሰቦች የሚከፍለው ጥሎሽ በማጣቱ ሳቢያ እጮኛውን በወቅቱ ሳያገባት ይቆይና በአንድ አሳቻ ወቅት ቤተሰቦቿ በአካባቢው ያለመኖራቸውን አረጋግጦ እጮኛውን ወደቤቱ በማስገባት ትዳር የሚመሰረትበትን ሂደት የሚመለከት ነው። ወንዱ ሴቷን ይዞ በሚጓዝበት ወቅት የአካባቢው ሰዎች ወይም ዘመዶቿ ደርሰው ሊያስጥሉ ቢሞክሩ «በፈጠራችሁ ማንም እንዳይነካኝ፣ የገዛ እጮኛዬን ነው እየወሰድኩ ያለሁት» በማለት ይማፀናል፤ በመሆኑም በማህበረሰቡ ባህል መሠረት ማንም ሰው ተማፅዕኖውን ጥሶ ሰውየውን መንካት የተወገዘ በመሆኑ እጮኛውን በሰላም ይዞ ወደ ቤቱ ይገባል።
ከዚህ በኋላ ሽማግሌዎች ተመርጠው ወደ ልጅቷ ቤተሰቦች ይላኩና ቅሬታው ተፈቶ ተጋቢዎቹ በሰላም እንዲኖሩ ይደረጋል። በሸካዎች ባህል ጋብቻ በዚህ ዓይነት መልኩ እንዲፈፀም መፈቀዱ አንድ ሰው በአቅም ማነስ የተነሳ የሚፈልጋትን ሳያገባ እንዳይቀር ከሚል አመለካከት የመነጨ ሲሆን አሁን አሁን ግን ሰዎች «ጥሎሽ የሚከፍለው ገንዘብ አጣ» መባልን ስለማይፈልጉ በዚህ መልክ የሚፈፀም ጋብቻ እየቀረ መጥቷል።
ሌላኛው በጠለፋ የሚፈፀም የጋብቻ ዓይነት «ሾቶ» ነው። ይህ የጋብቻ ዓይነት አንድ ወንድ የወደዳትን ሴት ጓደኞቹን አስተባብሮ ጠልፎ የሚያገባበትን ሂደት የሚመለከት ነው። በሸካቾዎች ዘንድ የጠለፋ ጋብቻ ሰፋ ያለ ውዝግብ እና ጭቅጭቅን በሴቷ እና በወንዱ ቤተሰቦች መካከል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ጠላፊውን ከፍ ላለ ቅጣት የሚዳርግ በመሆኑ አብዛኞቹ የማህበረሰቡ አባላት ጋብቻቸው በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፍ አይፈቅዱም።
«ፉሶ» የማባበል ጋብቻ ማለት ሲሆን አንድ ወንድ የወደዳትን ሴት እሷን በሚቀርቡ አካላት አማካኝነት የሚያገባበትን ሂደት የሚመለከት ነው። ልጅቷን የሚቀርቡ ተብለው የተመረጡት አካላት በተደጋጋሚ ስለልጁ መልካም ገፅታዎች በተለያየ መንገድ በመንገር የልጅቷ ቀልብ ልጁ ላይ እንዲያርፍ ካደረጉ በኋላ ሊያገባት ከሚፈልጋት ልጅ ጋር በቀጠሮ ያስተዋውቋታል። በዚህ መልክ የተጀመረው ቅርርብ ለጋብቻ እንዲበቃ ይሆናል።
«የቾ» አንድ ሰው የሟች ወንድሙን ወይም ዘመዱን ሚስት በውርስ የሚያገባበትን ሂደት የሚመለከት ነው። ይህ ጋብቻ ዋነኛ ዓላማው የሟች ልጆች በባዕዳን እጅ ወድቀው መጎሳቆል እንዳይደርስባቸው እና የሟች ሀብት እና ንብረት ባክኖ እንዳይቀር በሚል እንደሆነ ይገልፃሉ። በባህሉ መሠረት ሟች ወንድም ኖሮት ሌላ ጋብቻ ያለው ቢሆን እንኳን በተጨማሪነት የሟች ወንድሙን ሚስት እንዲያገባ ይገደዳል።
«ሸፖ» ምንም ዓይነት የደም ትስስር የሌላቸው ሁለት ጓደኛሞች ያላቸውን መቀራረብ ይበልጥ በጋብቻ ማጠንከር ሲፈልጉ ልጅህን ለልጄ በተባባሉት መሠረት የሚፈፀመውን የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት የሚመለከት ነው።
«ኢሞ» የስጦታ ጋብቻ ማለት ሲሆን ይህ የጋብቻ ዓይነት ቀደም ሲል ከተጠቀሰው የጋብቻ ሥርዓት ጋር የሚመሳሰልባቸው ነጥቦች ቢኖሩትም ይህኛው የጋብቻ ዓይነት በአንደኛው አካል ፍቃድ ላይ ብቻ ተመስርቶ የሚጀመር ነው። አንድ ሰው በምግባሩ አሊያም በሌላ ማንኛውም ምክንያት ከሌላኛው ሰው ጋር መዛመድ በሚፈልግበት ወቅት «ልጄን ለልጁ» ሰጥቻለሁ ሲል ለአካባቢው ሽማግሌዎች ይገልፃል። ይህን የሰሙት ሽማግሌዎችም ቃል ለተገባለት ልጅ አባት ስለሁኔታው በማስረዳት በሂደት ጋብቻው እንዲፈፀም የሚደረግበት ሂደት ነው።
በአጠቃላይ በሸካቾ ብሔረሰብ ባህል መሠረት ቀደም ሲል የተጠቀሱት የጋብቻ ዓይነቶች በዋናነት ሊፈፀሙ የሚችሉት ተጋቢዎች የአንድ ጎሳ አባል ያልሆኑ እንደሆነ ብቻ ነው፤ ዛሬም ድረስ ማንኛውም የብሔረሰቡ አባል ከጎሳው አባል እንዲያገባ አይፈቀድለትም። ምክንያቱም የአንድ ጎሳ አባል ማለት የአንድ እናት እና አባት ልጆች ተደርገው የሚቆጠሩ በመሆናቸው ነው።
የተወገዙት የጋብቻ የትስስር መንገዶች እንዳሉ ሆኖ ከሠርጉ መነሻ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ያለው ጤናማ የሚባለው የጋብቻ ትስስር መፍጠሪያ መንገድ ከንክኪ እና ከማህበራዊ ቅርበት የሚከወኑ ናቸው። ይህንን በማስመልከት አሁን ባለንበት ወቅት በተፈጠረው ወረርሽኝ ምክንያት እንዲህ ያሉ የማህበራዊ ትስስርን ለጊዜው ማቆም እንዴት ይቻላል ኅብረተሰቡስ ምን ማድረግ አለበት የሚለውን ጥያቄ በመያዝ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ እና ሶሻል ወርክ መምህር የሆኑት መምህር ኢሳያስ ውብሸት ዘንድ አመራን መምህሩ እንደሚሉት ሰው በተፈጥሮ ለብቻ የሚባለው ነገር የማይስማማው ማህበራዊ ሕይወትን ሙጥኝ ያለ እንደሆነ ይናገራሉ።
በተለይ በኢትዮጵያ የማህበራዊ መስተጋብሩ ከፍ ያለ ነው። በማህበራዊ ሕይወት ላይ ኖሮውን የመሰረተ ሰው የምንለው ፍጥረት ወደ ብቸኛ ግለኛ ሕይወት ውስጥ ግባ ማለት እጅጉን ከባድ ነው። አገሪቱ ግን እንዲህ ያሉ ፈታኝ ጊዜያት መውጫ መንገዶች ያላት የደረጀ ባህል አላት። የባህላዊ መድሐኒት፣ የሥነፈለክ … የመሳሰሉ ባለቤት ናት። ባህላዊ የሆነ የማህበራዊ ሳይንስ ስልትን ተከትሎ የመጣውን ወረርሽኝ የምትመክትበት ዕውቀትም ባለቤት ናት።
ስለዚህም ይላሉ ልክ እንደ አፋሩ ዳጉ ያሉ የመረጃ መለወጫ ስልቶችን፣ በየማህበረሰቡ ያሉ ኢመደበኛ አደረጃጀቶችን ማለትም እንደ ዕድር፣ ዕቁብ ወንፈል፣ ደቦ… በመጠቀም ሠርግም ጨምሮ ማህበረሰቡ የትኛውንም ማህበራዊ ክዋኔዎችን ለጊዜው ገታ አድርጎ ወረርሽኙን በመከላከል እንዲያተኩር ማድረግ ይቻላል።
እንደ መምህር ኢሳያስ ገለጻ ማህበረሰቡ ለአባቶች ሃሳብ እና ሥልጣን የሚገዛ፣ ለሃሳባቸው ደግሞ የማይገዛ ከሆነ ቅጣት የሚጣልበት ሲሆን ቅጣቱም ከኅብረተሰቡ እስከመገለል ይደርሳል። ማንኛውም ግለሰብ በማህበር፣ በመረዳዳት ውስጥ የኖረ ስለሆነ ከማህበረሰብ መገለል አይፈልግም፤ ስለዚህም ይላሉ መምህር ኢሳያስ የአባቶች ሥልጣን በመጠቀም ወረርሽኙ በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዳይስፋፋ እንደ ሠርግ ካሉ አካላዊ መቀራረብን ከሚፈጥሩ ማህበራዊ ክዋኔዎች እንዲርቁ ማዘዝ፣ ማስጠንቀቅና ማስተማር እንደሚቻል ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18/2012
አብርሃም ተወልደ