
የፌዴራል ዋና ኦዲተር በየዓመቱ ሁሉንም የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ኦዲት ያደርጋል፡፡ በየዓመቱም ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ግኝቶችን ይፋ ያደርጋል፣ እያደረገም ነው፡፡ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ሃብት መባከኑን በኦዲት ሪፖርቱ ያቀርባል፡፡ የአገር ሀብት የብክነት ሪፖርት ዓመት በመጣ ቁጥር ይደጋገማል፡፡
ዋና ኦዲተሩ የአስፈጻሚ ተቋማትን ገመና በአደባባይ ይፋ ያደርጋል፡፡ አስፈጻሚው የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ መሳይ ብዙ የማይረቡ ምክንያቶችን ይደረድራል፡፡ በማሳረጊያው እንደሚያስተካክልም ቃል ይገባል፡፡ ግን ዓመት በመጣ ቁጥር ያለፈው ሳይስተካከል ሌላ ችግር ፈጥሮ ይገኛል፡፡ ዋና ኦዲተሩም ያለፈው ሳይሽር አዲስና የባስ የኦዲት ጉድለት ይዞ ይቀርባል፡፡ የፓርላማውን ውሎ የተከታተሉ ዜጎች ቆሽታቸውን አሳርረው ከንፈራቸውን ይመጥጣሉ፡፡ መፍትሄ ግን ማግኘት አልተቻለም፡፡
የኦዲት ሪፖርቱ የሚቀርብለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከቃላት ማስጠንቀቂያና ምክር ያለፈ ከደረሰው ጥፋት ተስተካካይ እርምጃ ወስዶ ወይም አስወስዶ፣ አሊያም ይወሰድ ብሎ አያውቅም፡፡ ዓመት በመጣ፣ ስብሰባ በተካሄደና ሪፖርት በቀረበ ቁጥር ከመለመንና ከመለማመጥ፣ በዛ ካለም ከማስፈራራት ያለፈ የመንግሥት ገንዘብ አጉዳዮቹንና የሕዝብ አደራ በሎችን አንዴም ጠይቆም ሆነ አስጠይቆ አያውቅም፡፡ በዚህም ምክንያት፤ ምክር ቤቱ አስገድዶ የሚያስፈጽም ስልጣን ያለው አካል ሳይሆን የምክር አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መስሏል፡፡ እናም ለወደፊቱ «አስተካክሉ» ይላል፡፡ ምክር ይሰጣል፡፡ አስፈጻሚዎች «እናስተካክላለን» ይላሉ፡፡ በቀጣዩም ያው ነው፡፡ ምክር ቤቱ ‹‹የ… አስተዛዛኝ›› ዓይነት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ይህ ሁኔታ እስከመቼ እንደሚቀጥል የሚያውቁት ሪፖርት አቅራቢዎቹና ሪፖርት አድማጮቹ ብቻ ናቸው፡፡ የሕዝብ ተወካዮችነትን ሥም ይዞ ለሕዝብ አደራና ለመንግሥት ሀብት ጥብቅና የማይቆም እንደራሴ የሚገኘው ምናልባትም በዚች አገር ብቻ ይሆናል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ሳይቀር ደብዛቸው መጥፋቱና ጭርሱኑ ሳይገነቡ መቅረታቸው የተረጋገጡ በርካታ የኮንዶሚኒየም ሕንጻዎች ጉዳይ ሁሉንም ወገኖች ያገር መተረቻ አድርጓቸው ማለፉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በወቅቱ የቋሚ ኮሚቴው አባላት በርካታ ህንጻዎች መጥፋታቸውን እንዳረጋገጡና እናንተስ ይህንን ታውቃላችሁ ወይ? ያሏቸው ኃላፊዎች ለጉዳዩ እንኳን አዲስ እንደነበሩ፤ ከመስሪያ ቤታቸው፤ ከዋና ኦዲተርና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኮሚቴ አዋቅረው እንደሚያጣሩ ሲናገሩ አንዳችም ዓይነት ድንጋጤ በፊታቸው ላይ አለመታየቱ በወቅቱ በተላለፈው የቴሌቪዥን ዜና እወጃ ብዙዎች ታዝበዋል፡፡ መታዘብ ብቻ አይደለም ተቆጭተዋል፡፡ አስፈጻሚዎች ለዚህ ድፍረታቸውም ይመስላል ከተግሳፅ ይልቅ የትምህርት ዕድል ተሸለሙ ይባላል፡፡ ይህ እንደ አገር አስተዛዛቢ ነው፡፡
እንዲህ ዓይነቱ የአስፈጻሚዎች ጥፋት ጊዜ እየጠበቀ በተናጠል ይቅረብ እንጂ የገንዘብ ጉድለቱና የሀብት ምዝበራው በሁሉም ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ተደርጓል፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ግን የምክር ቤቱ አባላት ለሁሉም ሪፖርቶች የሚሰጡት «በቀጣይ ይስተካከል» የሚለው ምክር ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ በአሁኑ ወቅት የጠፋው፤ የባከነውና የተመዘበረው የህዝብና መንግሥት ሀብት በርካታ ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ያጠፋው ያልተቀጣበት አጥፊውና መዝባሪው ግን በመጠንም በዓይነትም የጨመረበት ክስተት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ሀይ ባዩና ተቆጭው አካል አሁንም ጥርስ አልባ ነው፡፡ ግን እስከመቼ?
የምክር ቤቱ የሁልጊዜ የ«አስተካክሉ» የምክር አገልግሎት ሲታይ ደግሞ ፓርላማው በአስፈጻሚው ቁጥጥር ስር መሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ በእርግጥ አስፈጻሚው በፓርላማው ሥራና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ እንደሚገባ ከሰሞኑ የአባላቱ ንስሀ መሰል የሚዲያ መግለጫ መረዳት አያዳግትም፡፡ የዚህ ሰሞኑ የዋና ኦዲተር የሁለት ግድቦች የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት፤ አስፈጻሚዎች ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽና ከሁሉም በላይ ራሱ ምክር ቤቱ ያወጣውና ያጸደቀው የግዥ ህግ ተጥሶ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ የውል ማሻሻያ አላግባብ ለግል የግንባታ ድርጅቶች ለምን ተከፈለ ሲባሉ «ክፍያው አግባብነት ያለው ነው» ሲሉ መመለሳቸውና አባላቱም «ከዚህ በኋላ እንደዚህ ዓይነት እንዳይደገም ልምድ መውሰድ ያስፈልጋል» በማለት ያለፉበት ሁኔታ አገሪቱ አንዳችም ተቆርቋሪ እንደሌላት አመላካች ነው፡፡
ይህም በመሆኑ መንግሥት ሚሊኒየሙ እንደባተ የሰነቀው ራዕይ እና የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲል የተለመው ዕቅድ አብዛኞቹ ሕልም ብቻ ሆነው እንደቀሩ ይታያል፡፡ የአገሪቱ ሀብትም በአስፈጻሚው አቅራቢነት በምክር ቤቱ ወሳኝነት የይሉኝታ ቢሶች መቆመሪያና ኪስ ማደለቢያ ሆኗል፡፡ እዚህ ላይ ግን ሊቆም ይገባዋል፡፡ ዘራፊዎችም ሀይ ሊባሉ፤ ባጠፉት ልክ ህግ ፊት ቀርበው ሊጠየቁም የግድ ነው፡፡ ምክር ቤቱም አደራ በል መሆኑ መቆም አለበት፡፡ የአገር ሀብት ሲዘረፍና የመንግሥት ካዝና ኦና ሲቀር እያየ «ለወደፊቱ እንዳይደገማችሁ» በማለት የሚያልፍ ከሆነ ለዕድሜ ልክ ትዝብት ነው የሚዳረገው፤እናም ምክር ቤቱ በቀሩት ጥቂት ወራት እድሜው አጥፊን ለፍርድ አቅርቦ ያሳየን ዘንድ እንጠብቃለን፡
አዲስ ዘመን ጥር 8/2011