አንድ ይፈርዳል፤ አንድም ይነዳል፤
ውሎዬና አዳሬ ከቤቴ ውስጥ ከሆነ የመጻሕፍት መደርደሪያዬን ሳልጎበኝ የዋልኩበትን ዕለት አላስታውስም። ለምን እንደሆነ ባይገባኝም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ፈጥኜ ዓይኔን የምወረውረው፣ መጻሕፍትን ለመግዛትም ምርጫዬ የማደርገው በአመራር ጥበብና በግለ ታሪክ መስክ በተጻፉ መጻሕፍት ዙሪያ ከሆነ ሰነባብቷል። ለራዕያቸው ኖረው በክብር የተሰናበቱ የበርካታ የሙያ ዘርፍ አርአያ ሰብ (Role Model) ጀግኖች ታሪክ በእጅጉ ይማርከኝ ጀምሯል። አልፎ አልፎ ግን የመጻሕፍቱን ገጾች ገልጬ በንባቤ ስቆዝም በትካዜ የሚንጡኝ በርካታ ሃሳቦች ሲወሩኝ ይታወቀኛል።
ታሪክ ያከበራቸው ቀደምት ጀግኖቻችን ብርቱ፣ ብልሃተኛ፣ እምዬ ወዘተ. እየተባሉ ታሪካቸው ሲሞካሽ ልክ እንደ ተረት ገፀ ባህርያት “እውን በሕይወት ኖረው ነበርን?” እያልኩ እጠራጠራለሁ። ከመጻሕፍት ገጾች ወጣ ብዬም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዙሪያ ገብ “ዓለሜን ስቃኝ” ምነው ታሪካችን እንደሚያሞካሻቸው እንደነዚያ መሰል ጀግኖች፤ ቢቻልም የበለጡ፤ በዛሬው በእኔ ጀንበር ሀገሬ አላበቅል አለች እያልኩ እጠይቃለሁ።
ይህን መሰሉ የስሜት መዋዠቅና መንተክተክ ባጠቃኝ አንድ ዕለት የሞነጫጨርኩትን አጭር ግጥም ከራሴው መጽሐፍ በመዋስ የብዕሬን የዕለት ዳረጎት ለአንባብያን ማዕድ ለማቅረብ በመወሰን “ነገም ሌላ ቀን ነው” እያልኩ በረቡዕ ቋሚ አምዴ ላይ ስለማቀርበው ተከታዩ ጽሑፍ ከመንጎሌ ጋር እመካከራለሁ።
«በተራሮቼ ልክ እጁን የዘረጋ፣
እስኪ አንድ ሰው ስጡኝ፤ እኔን የተጠጋ።
አድማሴ የማይርቀው፤ ሜዳዬ ያልታከተው፣
አንድ ሰው ጠቁሙኝ፤ ርሃቤ እሚርበው፣
ስሜቴ እሚጥመው።
በዓላማው ጽኑ፤ አዕምሮውም ግዙፍ፣
ዘመን ተሻጋሪ፤ ዕቅድ ሥራው ህሉፍ፣
እስቲ አንድ ሰው ስጡኝ፤ ራዕዩ የሚያከንፍ።
ግጥሙ የሚቃትተው “የመሪ ያለህ!” ጩኸት እያሰማ ነው። የጅምላ መሪነትን ሳይሆን አንድ ባለ ራዕይ መሪ ፍለጋ። ይህን መሰሉን ጩኸት ዛሬያችን የፈጠረው ፋሽን አይደለም። በየዘመናቱ መሰል የለሆሳስ ጩኸቶች ተደምጥዋል። እኛ ከቀደምት ባለራዕይ መሪ ፈላጊ ጯኺዎች የምንለየው የመጯጯሂያ መድረኮቻችን ስለተመቻቹልን ብቻ ነው። ቢያሻን በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ቢያሻን በመጻፍትና በየእምነት ተቋሞቻችን፣ ቢያሻን በየጎጣችንና በየፖለቲካ መድረኮቻችን “ባለ ራዕይ መሪ ሆይ ወዴት አለህ?!” እያልን ለማንቧረቅ ሁኔታው ተመቻችቶልናል።
ግን ለምን ለአንድ ሰው ፍለጋ እንጮኻለን?
ምክንያቱም በብዙኃን ሕይወት ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ጽንሱን የሚሸከመው አንድ ሰው ስለሆነ ነው። ብዙኃንም በየውሎ አምሽቷቸው ለውጥ ማምጣታቸው ባይካድም ብዙኃኑን የሚያስተባብር የአንድ ሰው መገኘት ግን የግድ ይሏል። ያ አንድ ሰው ብዙኃኑን ማስከተል የሚችለው የራዕይ አቅሙ ከፍ ያለ እንደሆነ ብቻ ነው። እርግጥ ነው የራዕዩ አቅም ለበጎነትም ይሁን ለጥፋት ጉልበት እንደሚኖረው አይካድም።
በብሩህ የራዕይ አቅማቸው፣ በአመራር ችሎታ ቸው፣ በብርሃናማ ህልማቸውና በባህርያቸው ተመስግ ነው፤ ቤተሰብን፣ አነስተኛ ቡድንን፣ ተቋማትን፣ ቤተእምነቶችን፣ ግዙፍ ኮርፖሬሽኖችንና ሀገርን መርተው በውጤታማነታቸው የተጨበጨበላቸው በርካታ ተምሳሌ ቶችን ዓለማችን ማፍራቷ ይታወቃል።
በአንጻሩም የመሪነትን መንበረ ሥልጣን ተቆናጠው በጨበጡት በትረ ሹመት ተመሪው ሕዝብና ጀማ በጩኸትና በእዮታ “ስለ ፍትሕ” እየሞገታቸው አስተዳደራቸውን ሲቃወም ቁብ ባለመስጠት በብረት በትር ቀጥቅጬ ካልገዛሁ እያሉ ሲፎገሉ በተባበረ የብሶተኞች ጉልበት ተሽቀንጥረው የተወረወሩ አምባገነኖችም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ለዚህም ነው “የመሪ ያለህ!” ጩኸት በዘመናት ውስጥ ሳይቋረጥ ዛሬም ድረስ እያስተጋባ ያለው።
«ሀገር ቤታችንን እንቃኝ!»
በግሌ እንደ ማንኛውም የዚህች ሀገር ዜጋ ከሁለት ዓመታት ወዲህ “የመሪ ያለህ” ጩኸቴ ገርገብ ብሎ መስከኑን የምመሰክረው በእውነትና ከልቤ ነው። ቢያንስ ሀገሬ የሕዝብ ጠረን የሚያመነጭና በወገን ፍቅር “የተነከረ” ፊትአውራሪ መሪ አግኝታለች ብዬ ማመን ከጀመርኩ ውዬ አድሬያለሁ። ፊትአውራሪውን ተከትለው የሚጓዙ ጥቂት ደቀመዛሙርትም እየተስተዋሉ ነው። የሀገሬ ዕጣ ፈንታ በጫንቃቸው ላይ ያረፈውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን (ዶ/ር) ሕዝቡ በእልልታና በሆታ የተቀበላቸው፣ ሣር ቅጠሉ ያረገደላቸውና የዓለም ማሕበረሰብ ነዎር ብሎ ከወንበሩ የተነሳላቸው በወረት ተማርኮና በጭፍን አፍቅሮተ ሰብ አብዶም አይደለም። በራዕያቸው ምጥቀት፣ በጅማሯቸው ርቅቀት (Excel¬lence) ተማረኮ እንጂ።
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ጸሐፊ ዓይኑ ተገልጦ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን እንደ ብዙኃኑ ዜጎች ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥት መስኮት የተዋወቃቸው በሕዝብ ተወካዮች መንበር ፊት ቆመው የበዓለ ሲመታቸውን ንግግር ባንቆረቆሩበት ዕለት ነበር። ከዚያ በፊት ስለ ሰውዬው ብዙ አልሰማም፤ ብዙም አላነበበም። ከብዙኃኑ ተሰውረው እንዴት እንደኖሩ የሚገርም ነው። “ልታይ ልታይ” ብለው በአደባባይ ተገልጠው ባይወጡም ልክ እንደ ባለሙያ እመቤት በየተመደቡበት የኃላፊነት ወንበር ዙሪያ መዓዛው የሚያውድ የፍቅርና የውጤታማነት ብርጉድ እያጠኑ በዙሪያቸው ያሉትን ሲማርኩ የኖሩት ለረጂም ጊዜያት ስለመሆኑም ምስክሮች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ነው።
ዓይናቸው በጎውን ለማየት፣ ጆሯቸው መልካሙን ለመስማት እንደታወረውና እንደተደፈነው፤ “ጠብ ያለሽ በዳቦ እየሸተታቸው ጦርህን ካልወለወልክ” እያሉ እንደሚጎተጉቷቸው እንደ አንዳንድ ተቃዋሚዎቻቸው ሳይሆን ሰውዬው “ጦርነት የሚፈሩ ጀግና” እንደሆኑ ደጋግመው ሲናገሩ ካደመጥኩበት ዕለት ጀምሬ በእጅጉ አክብሬያቸዋለሁ።
በቤተሰብ፣ በቡድን፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በፖለቲካ፣ በሀገርም ይሁን በአህጉር ደረጃ ታላላቅ የተሰኙ መሪዎች ከሚጋሯቸው በርካታ በጎ ባህርያት መካከል ከአግባብ ውጭ የሆነ ጦርነት መፍራታቸው በተቀዳሚነት ይጠቀስላቸዋል። የጦርነት ዒላማ የሚያነጣጥረው በሰው ልጆች ላይ ነው። ውጤቱም እልቂትና ውድመት ነው። ጦርነት እስትንፋስን መንጠቅ፣ አካልንና ንብረትን ማውደም ብቻ ሳይሆን ህሊናንና ስብዕናንም የሚያቆስለው ክፉኛ ነው። ግድ ካልሆነበት በስተቀር አክብሮትና አድናቆት የሚዥጎደጎድለት ታላቅ የሚሰኝ መሪ የጦርነትን ዘር ዘርቶ ሞትን ለማዝመር የማይፈልገው ዘገር መነቅነቁን ፈርቶ፣ ዱታ ነኝ ብሎ ለማቅራራትም ልቡ ዝሎበት አይደለም።
እንደ ጥንታዊው የግሪክ ፈላስፋ እንደ አርስጣጥሊስ “ጦርነት እንኳ የመፈጠሩ ነገር ግድ ቢሆን ጦርነቱ መካሄድ ያለበት ለሰላም መገኘት ሲባል መሆን ይኖርበታል” የሚል ጽኑ አመለካከት ስላለውም ነው። የፈላስፋው ዘመነ ጓድ ሲሴሮም “ሰላምን ሳታመነታ አስፈላጊውን ዋጋ ከፍለህም ቢሆን ግዛው!” በማለት የጓደኛውን የአርስጣጥሊስን ሃሳብ አግዝፎለታል።
የሆነውስ ሆኖ ታላቅ የሚባል መሪ የሚሸሸው ጦርነት ምን ዓይነቱን ነው? ጦርነት ሁሉ የጠብመንጃ ቃታ እየተሳበ አረር የሚዘንብበት የሞት ጨዋታና ልፊያ ብቻ አይደለም። በእብሪት፣ በጀብደኝነትና በአምባገነንነት ከአንደበት የሚፈተልኩ ሚሳይሎችን በማምዘግዘግም ከመደበኛ ጦርነት ባልተናነሰ ጥፋት ብዙዎችን መረፍረፍ ይቻላል። ጦርነትን የሚፈራ መሪ ከተቀናቃኞቹ ጋር በምላሱ እሩምታ ቀድሞ የማይፋለመውና እሰጥ አገባውን የማይወደው ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ ስለሚረዳና ከጦርነት ይልቅ አቅምን በሥራ መፈተኑ ይበልጥ እንደሚያዋጣ ስለገባው ነው።
ከመሠረታዊው የማሕበረሰብ አስኳል ከቤተሰብ ተነስተን ጉዳዩን በዝርዝር መመልከት ይቻላል። የመልካም ቤተሰብ መልካም መሪ ቤተሰቡ የጦርነት አውድማ እንዲሆን አይፈልግም። ባል በሚስቱ ላይ፣ ሚስት በባሏ ላይ ቤቱን የጦርነት ቀጣና በማድረግ አረር ሲያስወነጫጭፉ ልጆች የነገር ሚሳኤሉን ቀለህ እንዲያቀብሉ አይፈቅዱም። ታላላቅ የቤተሰብ መሪዎች፤ ታላላቅ የማሕበረሰብ መሪዎችን ይፈጥራሉ መባሉም ስለዚሁ ነው። ታላላቅ መሪዎች ታላላቅ ጦርነቶችን ብቻም ሳይሆን ታናናሽ የግጭት ብልጭታዎችንም ሊሸሹ ይገባል። ሽሽታቸው ማሸነፍ ስለማይችሉ ሳይሆን የማሸነፍና የመሸነፍ ውጤቱ የሚያስከትለው ጉዳት ከሩቁ ስለሚሸታቸው ብቻ ነው። የሰውየው አንዱ ባህርይም ይሄ ነው።
ባለ ራዕይ መሪዎች ጦርነትን የሚፈሩት የድል በለስ አይቀናኝም በሚል በአዕምሯቸው ንግር ስለሚልፈሰፈሱም አይደለም፤ የአንድም ንፁህ ደም ለእብሪተኞች የግብር መዋጮ እንዳይገበር በመስጋት እንጂ። የጦርነት ድግስ ሞትና ውድመት መሆኑን በሚገባ ስለሚረዱት “ይዋጣልን!” እያሉ ጠብመንጃቸውን እየወለወሉ አያቅራሩም። እንደ ጎልያድም የታላቅነታቸውን ኃይል ለማሳየት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በሕዝብ ፊት እየቆሙ አይደነፉም። ባለ ራዕይ መሪዎች የጎልያድን ፉከራ በአንዲት የዳዊት ጠጠር ዝም ማሰኘት እንደሚችሉ ቢረዱም ፈጥነው ከኮሮጇቸው ውስጥ ጠጠር ለማፈሰ ግን አይጣደፉም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን “ጀግና!” አሰኝቶ በሕዝባቸው ፊት ያስከበራቸው፣ “የሰላም ሰው!” አሰኝቶ ዓለም እንዲያጨበጭበላቸው ምክንያት የሆነው ይሄው የጦርነት ጠል እምነታቸው ነው። እንጂማ ስብእናቸው የታሸው በጦር ሜዳም አይደል። ወጣትነታቸው የተፈተነውስ በአረር ፉጨት መካከልም አይደል። የጦርነትን ስሙን ብቻም ሳይሆን ጦርነትን ራሱን ያውቁታል። ግን ለሰላም ሲሉ ለጦርነት ደጋግመው ፊት ሲነሱ ተስተውለዋል። በዚህም ምክንያት ዓለም “የዘመናችን የሰላም ሰው” በማለት “የዘንባባ አክሊልና” ኒሻን አጎናጽፏቸዋል።
አንዳንድ ተፃራሪዎቻቸው በሰንጋ ፈረስ ላይ ተኮፍሰው፣ ኮልት ሽጉጣቸውን በቀኝ ሽንጣቸው፣ የመግረፊያ ጅራፋቸውን በግራ ጎናቸው ታጥቀው መንጋቸውን እንደሚያመሳቅሉት እንደ አሜሪካዊያኑ የቴክሳስ እረኞች (Cowboys) ሕዝቡን እያተራመሱ እያዩ እንኳን ያሉበት ቦታ ድረስ በመገኘት እያቀፉ የሚስሟቸው እብሪታቸውን ማብረድ ተስኗቸው አይመስለኝም። በወጣትነት ዕድሜያቸው የታጠቁት ወታደራዊ ሞራልም ስለቀጠነባቸው አይደለም። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከብት የማያስተኛ ክፉ እረኛ በክፉ የበሬ ቀንድ ተወግቶ እንደሚሰናበት ጭምር በሚገባ ስለተረዱት ነው።
ጸሐፊው ስለ ጠቅላዩ እውነቱን የሚመሰክረው የፖለቲካቸው ምርኮኛ ሆኖ ስለገበረ ሳይሆን የስብእናቸውና የተግባራቸው አድናቂ ስለሆነ ብቻ ነው። ህሊናውንና ብዕሩንም ያጀገነው ለይምሰል ሳይሆን እውነቱ ስለገባው ነው። የአስተሳሰባቸው ምጥቀትና የራዕያቸው ጥልቀት ዓለምን እያስደመመ እያስተዋልን እኛ ባለሀገሮቹ በምን ይሉኝ ይሉኝታ እየተሽኮረመምን አንደበታችንንና ብዕራችንን ዝም ብናሰኝ ጥሉ የሚሆነው ከታሪክና ከህሊና ጋር ነው።
ለምሳሌ፤ ከአሁን ቀደም እንደገዙን መሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በባህል ልብሳቸው ሽክ ብለው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሀሴት ማድረጋቸውን ለማሳየት፤ የሕዝብ ሚዲያ ጋብዘው እንቁልልጮሽ በማለት መብል መጠጣቸውን፣ ዊስኪና ቁርጣቸውን እያሳዩ አላስጎመጁንም። የማንበላውን የኬክ ድፎ ጠረጴዛቸው ላይ ደርድረው “እንኳን አደረሳችሁ!” በማለትም አልተሳለቁብንም። ይልቁንስ የምናያቸው በየዓውደ ዓመቱ ማለዳ ተነስተው ከክብርት ባለቤታቸው ጋር በድሆች ጎጆ ውስጥ እየተገኙ ፍቅርን ሲያካፍሉ ነው። ግፉዓንንና ምስኪኖችን እያቀፉ እንባ ሲያብሱ አይተንም ፈዘናል። ማዕዳቸውን ማጋራት ብቻም ሳይሆን ሙሉውን “ሞሶባቸውን” እንዳለ ለጉስቁል ወገናቸው ሲለግሱም አስተውለናል።
ስለዚህም ወደናቸዋል፣ አክብረናቸዋል፣ እንዲመሩንም ቀኝ እጃችንን በፍቅር ሰጥተናቸዋል። በነጋ በጠባ የሚያቅዷቸው ታላላቅ ዕቅዶች እንዲሰምሩላቸውም እንደ የእምነታችን በፈጣሪ ፊት ቃትተንላቸዋል። “አንድ ሰው እንደሚፈርድ፣ አንድ እንጨትም እንደሚነድ” በእርሳቸውና በቤተሰባቸው ሕይወት ውስጥ ተገልጦ ተመልክተናል። የእርሳቸውን ፈለግ ተከትለው ጎምቱ ሹማምንቶቻችንም ከደሃው ሕዝብ ጋር በዓልን ሲያከብሩ ተመልከተን ተገርመናል። “ቀላዋጭ” ሚዲያዎቻችን እንደተለመደው በየባለሥልጣናቱ ቤት እየዞሩ “በዓልን ከቤተሰብዎ ጋር እንዴት እያከበሩ ነው?” ከሚል ትዝብት እንዲላቀቁ ጠቅላዩ ያስተማሩት በንግግር ሳይሆን በተግባር ጭምር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን መሰል “ዝቅታ” እያስተማሩ ያሉት የፌዘኞችን የአንደበት ጦርነት ተቋቁመው፣ የእርባና ቢስ “ተቀናቃኞቻቸውን” ኡኡታና እሪታ በመናቅ ጭምር እንደሆነ በተግባራቸው እያስመሰከሩ ነው። ስለዚህም “ባለ ራዕይ አይሙት” ብለን እንዲህ ተቀኝተንላቸዋል።
ባለ ራዕይ ይኑር አይሙት አያንቅፈው፣
እግዚአብሔር ለእኛ ነው ራዕይ ሲሰጠው።
እንዲያተርፍበት ነው መክሊቱን የሰጠው፣
ባለ ራዕይ አይሙት ሞቱን አናፍጥነው።
ሊወጣ ሲነሳ ወጥመድ አናብዛበት፣
እንቅፋቱ ይወገድ ቁስል አንሁንበት።
ተግባሩን ውደዱ እናንተም ጠንክሩ፣
ማሸነፍ በተግባር በርትታችሁ ሥሩ።
የወጣን ለማጥፋት፤
ገመድ አትግመዱ፣ ጉድጓድ አትቆፍሩ።
(ፀዳለ ሞገስ “እውነተኛ ዳኛ” 1998 ዓ.ም)። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 / 2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.co